ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ… ከዛም እኔም ደስ ይበለኝ

 

 

 

ወዳጄ እንዴት ሰነበቱልኝ፤ ዛሬ አስቸኳይ ጉዳይ ገጠመኝና የደቡብ ልጆች በኬኒያ የሚለውን ጨዋታ ሳልቀጥልልዎ ልቀር ነው። በምትኩ የቀድሞው የደቡብ ክልል ፕረዘዳንት የአሁኑ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለሆኑት አቶ ሃይለማሪያም አንድ ደብዳቤ አዘጋጅቻለሁ… እማኝ ይሆኑኛል አብረዋቸው ያንብቡልኝ!

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ሃይለማሪያም ደሳለኝ፤

በመጀመሪያ ሰላም ልበልዎ መሰለኝ፤ እንዴት አሉልኝ! ቀጥሎም ልጠይቅዎ መሰለኝ፤ ያንን ሃይማኖተኝነትዎን ተዉት ወይስ እንዳለ ነው? ባለፈው ግዜ በፓርላማው “እግዜር ኢትዮጵያን ይባርክ” ሲባል ከፓርላማ አባላቱ ጋር ሆነው ከት ብለው ሲስቁ አይቼዎታለሁ…? ወይስ አላየዎትም? የሆነው ይሁንና፤ ቢያንስ ግን የፓርላማ አባላቱን በምግባራቸው ሲገስፁ ባለማየቴ ነው ሃይማኖተኝነቱን ትተውት ይሆን…? ብዬ መጠራጠሬ፤ ግድየለም አለተዉትም በሚለው ታሳቢ አድርጌ ልቀጥል፤

እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረስዎ! እንዲሁም በየሱስ ስም ቀልብዎን አሰባስበው ያንቡብልኝ፤

ያኔ የስልጣኑ በር ላይ ቆመው የሀገሪቱ ጠቅላይ የመሆን አለመሆንዎ ነገር እንደ አጓጊ ትያትር ልብ ሰቀላ ላይ ሳለ፤ ከተለያዩ ቦታዎች እርስዎ ቀጣዩ ጠቅላይ የመሆን እድል እንዳልዎት ፍንጭ በሰማን ቁጥር፤ ነግሰው በፍንጭትዎ ፈገግ ሲሉልን እየታየን “ወፌ ቆመች ባልወደቀች…” እያልን ደጋፊዎ ሆነን የቆየን እጅግ በርካቶች ነን።

ለዚህ በርካታ ምክንያቶች አሉን፤ ከምክንያቶቻችን ውስጥም፤ ታጋዮቹ ደማቸው ቶሎ ቶሎ ግንፍል እያለ ፓርላማ ውስጥ ቁጣቸው አሰልችቶን ነበርና ቢያንስ እኒህ የሀይማኖት ሰው ሰከን ብለው ሲናገሩ እንሰማቸው ይሆናል። የሚለው አንዱ ነበር። ሌለውስ…? ሌላው ደግሞ አሁንም ከዕምነትዎ አንፃር መዋሸት እንደነውር ይቆጠራልና እንደቀድሞዎቹ… የምናውቀውን ሀቅ ሲዋሹን አናይም ከሚል ተስፋም ነበር። ሌላስ…? ሌላማ እንግዲህ እርስዎም እንደቀድሞዎቹ “ፈሪሳውያን” በርባን ይፈታ ክርስቶስ ይሰቀል የሚሉ አይደሉምና ንፁሀንን ለሞትና ለእስር አይንዎ እያየ አሳልፈው አይሰጡም በሚል ተስፋም ነበር።

ከነበር በኋላ፤

በዛንም ቀን አነሆ እርስዎ የተከበሩት፤ አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በተቀበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ምትክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ። መጀመሪያ ደስ አለን ቀጥሎም ደስታችን ከምን የተነሳ ነበር…? ብለን ጠየቅን።

ቆይማ ደረቅ አደረኩብዎ መሰል… ትንሽ ዋዛ እንጨምርበት፤ ለመሳቅ ይዘጋጁ በእርስዎ ላይ የተቀለደች አንዲት ቀልድ ናት፤ አዲስ መስመር ይውረዱና ያገኟታል። (በቅንፍም አይዝዎት አዲስ መስመር ይውረዱ ነው ያልኩዎ ከስልጣንዎ ይውረዱ አላልኩም።)

በአንዱ ቀን አሉ ከሶስቱ ልጆችዎ አንዷ ኩርፍ ብላ ሳሎን ተቀምጣ አገኟት፤ ታድያ እርሶ ሆዬ በአባት አይንዎ እያዩ እና አናቷን ዳበስ ዳበስ እያደረጉ “ምን ሆነሻል ልጄ!?” ሲሉ ጠየቋት። እርሷም ለንቦጯን ጣል አድርጋ የፈተና ውጤቷ ጥሩ እንዳልሆነ ነገረችዎ፤ ይሄኔ እርስዎ ሆዬ “አይዞሽ ያገኘሽው የስራሽን ውጤት ስለሆነ አትከፊ” አሏት፤ እርሷ ግን “የሚያናድደውኮ እሱ ነው!” አለችዎ። ለካስ ልጅዎ ፈተናዋን የወደቀችው ከሰው ኮርጃ ሰርታ ኖሯል። ይሄኔ እርስዎ ሆዬ ሊመክሩ… መቼም ምክር ቀላል ነውና፤ “ልጄ የሰው ነገርማ መኮረጅ አይገባም…” ብለው ገና  ሲጀምሩላት ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የእርስዎ ንግግር ሲጀምር እኩል ሆነ፤ “መረጃ አለን ማስረጃ ግን የለንም…” ብለው ልክ እንደ ሟቹ ሲናገሩ ተሰማ፤ ይቺን ንግግር አቶ መለስ ፈጠሯት፤ ከዛ ሰው ለሰው ድራማ ኮረጃት፤ ከዛ ደግሞ እርስዎ ኮረጇት… ልጅዎ ይሄንን ሁሉ አየች ሳቀችም። ከዛ ስለኩረጃ አስከፊነት እንዴት ይምከሯት…!

ቀልዷ አላሳቀችዎትም መሰል። አዎ ዋናው ቁምነገሯ ማሳቁ ላይ ሳይሆን በኩረጃዎ ቤተሰብዎም መሳቀቁን ለመጠቆም ነው።

እናልዎ ስንት ተስፋ ያደረግንብዎ ሰውዬ ከውሃ አጠጣጥዎ ጀምሮ እስከ ኩስትሪያዎ እና ቁጣዎ ድረስ ቁርጥ ያለፉትን ሆነው ቁጭ! እኛም፤ ለመሆኑ ቪዲዮውን ስንት ግዜ ቢያዩት ነው!? ብለን ተደነቅን፤ ተደንቀንም ፃፍን፤

በነገራችን ላይ በዚህ የፓርላማ ውሎዎ ላይ ከብቸኛው ተቃዋሚ ክቡር አቶ ግርማ ሰይፉ ስለ ማተሚያ ቤት ተጠይቀው የመለሱት መልስ አስደምሞኛል። እዝችው ላይ ነገርን ነገር ያንሳውና “በሀገሪቱ ውስጥ ያሉት ማተሚያ ቤቶች 34 ይመስሉኝ ነበር ለካስ ከሁለት መቶ በላይ ማተሚያ ቤቶች አሉ…” ብለው ገና መልስዎ ሲጀምሩ ድሮውንም ስለሚመሯት ሀገር ያልዎት ዕውቀት አናሳ መሆኑን “አስፎገሩ” ለዚህም ነው ይህንን ንግግርዎን ኢቲቪ ማታ ድጋሚ ሲያቀርበው በሳንሱር መቀሱ ቆርጦ ያወጣው።

ለነገሩ እርስዎ ስለሀገርዎ ጉዳይ ባዳ እንደሆኑ ካወቅን ቆየን፤ ምነው እንኳ ባለፈው ጊዜ ከአልጀዚራ ቴሌቪዥን ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ “ኤርትራ የሚወስደኝ ባገኝ ሄጄ ከአቶ ኢሳያስ ጋር እታረቅ ነበር” ብለው ሲሉ፣ ጋዜጠኛይቱ፤ “ታድያ የዚህ የዚህ እግር ኳስ ቡድናችሁ ሰሞኑን ኤርትራ ሄዶ እንዳይጫወት ለምን ከለከላችሁ?” ብላ ብትጠይቅዎ “ይሄንን ገና ካንቺ ሰማሁ” ብለው ብንሰማ እኛ ለርስዎ ተሸማቀን፣ ተሸማቀን ሸማቂ መሆን አልነበር እንዴ የተመኘነው…!?

የኔ ነገር፤ የጀመርኩትን ወሬ ሳልቋጭ ሌላ ጨዋታ ውስጥ ዶልኩዎ አይደል፤ ይቅርታ ያድርጉልኝ፤ እኔስ ከአንዱ ጨዋታ ወደሌላ ጨዋታ ነው የዶልኩዎ አንዳንዶች አሉ ከችግር ወደ ችግር የሚዶሉ፤ እነርሱን ነው መገሰፅ! ታድያ ስም አልጠቀስኩም…

እናልዎ ታድያ “ማተሚያ ቤቶችን የኢህአዴግ ካድሬ ደውሎ በፍፁም አያስፈራራም” ብለው አፍዎን ሞልተው ሲናገሩ ብሰማ እኔ አፍሬ አፌን ያዝኩልዎ…

ይሄ መልስዎ ከምን ጋር ይመሳሰላል መሰልዎ አንዳንድ እናቶች አሉ ልጆቻቸውን የተንከባከቡ መስሏቸው ለባሰ ጥፋት የሚያጋልጧቸው። እንዲህ አይነት እናቶች ስለ ልጃቸው ጥፋት ስሞታ ቢመጣላቸውም “የኔ ልጅ በፍፁም እንዲህ አያደርግም” ይላሉ። ይሄ አይነቱ ምላሽ ልጆቹን የባሰ አጥፊ እነዲሆኑ ነው የሚያደርጋቸው። እንዲህ አይነት እናትና ልጆች በየሰፈሩ አሉ፤ እርስዎም ሰፈር አይጠፉም። (የድሮ ሰፈርዎ ማለቴ ነው)

ታድያ እርስዎም እዲህ እንዳሉት እናቶች “የኔ ካድሬ በፍፁም እንዲህ አያደርግም ይሉልኛል” እኔ አለሁ አይደል እንዴ ያልሞትኩ እማኝ፤

በአንድ ወቅት አንድ መፅሀፍ ላሳትም ፈልጌ ላንቻ አካባቢ ያለ አንድ ማተሚያ ቤት ሄጄ ነበር። ቀብድ ከከፈልኩት በኋላ መፅሐፌን ማተም ሊጀምር ሲል ሽፋኑን ተመለከተው። በሽፋኑ ላይ የአራት ሰዎች ፎቶግራፍ ይታያል። የዳኛ ብርቱካን ሚዴቅሳ፣ የዶክተር ብርሃኑ ነጋ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና የምንም አቶ ልደቱ አያሌው ፎቶግራፍ ነበረበት።

እና አታሚዬ እነዚህን ፎቶግራፎች ብቻ ተመልክቶ የሰጠሁትን አስራ ምናምን ሺህ ብር ቀብድ መለሰልኝ፤ ከዛም፤ “እኔ በእሳት አልጫወትም ሰዎቹ አስጠንቅቀውኛል ውሰድልኝ” አለኝ። “በእሳት አልጫወትም” ያለው እናንተን መሆኑ ነው። በወቅቱ መንግስታችን ፀሐይ እንጂ እሳት እንዴት ይባላል ብዬ ቅር ብሎኝ ነበር። አሁን ግን እርስዎም ደጋግመው ሲናገሩ እንደሰማሁት፤ ማንኛውም ሰዉ መንግስትን አንድ ጥያቄ ሲጠይቅ “ይሄ በእሳት መጫወት ነው” ሲሉ ብሰማ እውነትም መንግስቴ እሳት ነውና እውነትም ይፋጃልና! ስል ዕውቀቴን አዳብሬያለሁ።

የሆነው ሆኖ አቶ ሃይለማሪያም ተስፋ የጣልንብዎትን ያህል ተስፋ እያስቆረጡን ነው።

ዛሬ ይሄንን ደብዳቤ እንድፅፍልዎ ያስገደደኝ ዋናው ምክንያት፤ ሰሞኑን በፌስ ቡክ ላይ አጭር መልዕክት ሰድጄልዎ ምንም ምላሽ በማጣቴ እስቲ ደግሞ ዘርዘር አድርጌ ልንገራቸው ብዬ ነው።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር፤

አሁን በቅርቡ ሁለት ህፃናት ልጆች በታጠቁ የፖሊስ ሀይሎች ተገድለዋል። ይሄ የምነግርዎት ታሪክ ጋዛ ውስጥ በሮኬት ጥቃት የሆነውን አይደለም። እኛው ሀገር ኢትዮጵያችን ውስጥ ነው። ሮኬት በሆኑ ፖሊሶችዎ የተደረገ እንጂ፤

አንዷ ጡት ጠብታ ያልጨተረሰች ህፃን በእናቷ ጀርባ እንደታዘለች አዲሳባ ውስጥ “ቤታችን ፈረሰ” ብለው ለመንግስት አቤት ሲሉ በፖሊስ ዱላ ተመታ መገደሏን ሰምተን ሀዘኑ ከልባችን ሳይወጣ፤ ሌላው የሰባት አመት ህፃን ደግሞ በሀረር ከተማ ያለምንም ሰሚ አንድ አመቱን የደፈነው የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ተቃውሞ ላይ በአጋጣሚ በመገኘቱ ተገደለ። ምናልባት ይህንን አልሰሙ ይሆናል።

በሀገሪቱ ውስጥ ስንት ማተሚያ ቤት እንዳለ የማያውቁ ሰውዬ፣ የሀገርዎ ብሄራዊ ቡድን ኤርትራ ሄዶ እንዳይጫወት መከልከሉን ከውጪ ጋዜጠኛ የሚሰሙ ሰውዬ፣ ይሄንን ጉዳይ እስካሁን አልሰማሁም ነበር፤ ቢሉኝ አይገርመኝም። አሁን ግን ይስሙኝ…

ባለፈው ግዜ በፌስ ቡክ ገፄ ላይ እንዳልኩዎ ይህ አይነቱ ጭካኔ የሄሮዶስ ወታደሮች ብቻ ናቸው ያደረጉት።

ወቅቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ይወለዳል እርሱም የአለም ሁሉ ንጉስ ይሆናል ተብሎ ትንቢት የተነገረበት ወቅት ነበር። ታድያ ሄሮዶስ በዚች ምድር ላይማ እኔ እያለሁ ማንም አይነግሳትም ብሎ በዛን ወቅት የተወለዱ ህፃናትን በሙሉ አስጨፈጨፈ። ቁጥራቸውም ሶስት ሺህ ይደርስ ነበር።

በነገራችን ላይ በሀረር ከተማ ለተገደለው ህፃን አስከሬን ለመውሰድ እናቲቱ ሶስት ሺህ ብር ክፈይ ተብላለች አሉ።

እናም ራሄል ስለ ልጆቿ አለቀሰች ልቅሶዋም በሰማይ ተሰማ!

ይላል እያነበቡ ያደጉት መፅሐፍ።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሆይ በየሱስ ስም፤ ዛሬ ነገ ሳይሉ ይህ አይነቱን ጥቃት ያስቁሙ። እንዲሁም ይህንን የፈፀሙ ሰዎች ቅጣታቸው ሲፈፀም ያሳዩን ይህንን ማስፈፀም ከተሳንዎ ፍፃሜዎ ቢሆን ይሻልዎታል።

አክባሪዎ!

14,January 2013

Abetokichaw.

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: