ሰላሳ ሦስቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተቃውሞ ሕዝባዊ ስብሰባ ጠሩ

ሰላሳ ሦስቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተቃውሞ ሕዝባዊ ስብሰባ ጠሩ

‹‹ከምርጫ ሒደት ውጭ አይደለንም ማንም ሊያደርገንም አይችልም››  የፓርቲዎቹ ጊዜያዊ ኮሚቴ

በመጪው ሚያዝያ ወር የአዲስ አበባ አስተዳደርና የአካባቢ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገር እንፈልጋለን በሚል ለምርጫ ቦርድ፣

ለገዢው ፓርቲና ለመንግሥት ጥያቄያቸውን አቅርበው ተቀባይነት ተነፍገናል ያሉ 33 ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተቃውሞ ሕዝባዊ ስብሰባ ጠሩ፡፡

የሰላሳ ሦስቱ ፔቲሽን ፈራሚ ፓርቲዎች ጊዜያዊ ኮሚቴ ትናንት በሰማያዊ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት፣ ‹‹ጥያቄያችን ‹በጆሮ ዳባ ልበስ› ሊታለፍ አይችልም፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ገዢው ፓርቲ ተገደው እንዲሰሙ የማድረግ ሕዝባዊ ትግል ይቀጥላል፤›› በማለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነበር ፓርቲዎቹ አሁንም ከምርጫ ራሳቸውን አለማግለላቸው ያሳወቁት፡፡

ከመጪው ምርጫ ራሳቸውን እንደሚያገልሉ ሲጠበቁ የነበሩት እነዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚሁ መግለጫቸው የጋራ አቋማቸውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት፣ ‹‹ጥያቄያችን ከመነሻው በምርጫ የመሳተፍ ወይም ያለመሳተፍ ጉዳይ አልነበረም፤ ዛሬም አይደለም፤›› በማለት ውሳኔያቸውን ለማሳወቅ እንደ መነሻ ተጠቅመዋል፡፡ ቀደም ሲል ምርጫ ቦርድ በመጪው ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማወያየት በአዳማ በጠራው ስብሰባ ከተገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል 41 የሚሆኑት መጀመርያ በአገሪቱ የምርጫ ሜዳ፣ የሚዲያ አጠቃቀምና የሕግ የበላይነት ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ቦርዱንና ኢሕአዴግን ጠይቀው እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ ሰላሳ ሦስቱ አንድ የጋራ ኮሚቴ በማቋቋም ፔቲሽን ተፈራርመው ለምርጫ ቦርድ 18 ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ የፓርቲዎቹ ጥያቄ ‹‹አንድም በማስረጃ አልተደገፈም፣ ወቅታዊም አይደለም፤›› በሚል ውድቅ አድርጎባቸዋል፡፡ ‹‹ምርጫ ቦርድ የኢሕአዴግ አስፈጻሚ ሆኗል›› በሚል በገለልተኝነቱ ላይ አሉን ያሉዋቸውን የተለያዩ ማስረጃዎች በማቅረብ እየሞገቱ ከሰነበቱ በኋላ፣ ራሳቸውን ከምርጫ ማግለላቸውን ያሳውቃሉ ተብሎ ሲጠበቅ ነው ትናንት፣ ‹‹ከምርጫው ሒደት ውጭ አይደለንም›› በማለት በገዢው ፓርቲና በምርጫ ቦርድ ላይ የተቃውሞ ሕዝባዊ ስብሰባ ለመጥራት መወሰናቸውን ያሳወቁት፡፡

‹‹በጥያቄያችን የተነሱ መሠረታዊ ጉዳዮች ባልተሟሉበት እንደ ፓርቲ ስለውድድር፣ እንደ ዜጋ ስለ መራጭነት ምዝገባ መነጋገር ለገዢው ፓርቲ የምርጫ ሴራ ይሁንታ መስጠት ነው፤›› ይላል መግለጫቸው፡፡ ወቀሳቸው በምርጫ ቦርድና በኢሕአዴግ ላይ ተቀላቅሎ የቀረበ መሆኑን፣ ማን ላይ ማነጣጠር እንደሚፈልጉ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የኮሚቴው አባላት፣ ‹‹ተቀላቅለው እያሉ እኛ ማንንና ማንን ቀላቀልን? ምርጫ ቦርድ የራሱ ሳንባ የለውም፡፡ በኢሕአዴግ በሚነፋው አርቴፊሻል ሳንባ ነው የሚተነፍሰው፤›› በማለት አሁንም ጥያቄያቸው ምርጫ ቦርድ የኢሕአዴግ ጉዳይ አስፈጻሚ ከመሆን ተላቆ ገለልተኝነቱ እስኪረጋገጥ ድረስ ሕዝባዊ ትግል እናቀጣጥላለን ብለዋል፡፡ ‹‹ለምርጫው አስገቢም አስወጪም የለም፤›› በማለት፡፡ እንደ ዋነኛ የምርጫ ባለድርሻ በሒደቱ ላይ ያነሱት ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ መራጩ ሕዝብ ከጎናቸው እንዲሠለፍ ጠይቀዋል፡፡ የሥልጣን መሸጋገርያ ብቸኛ መንገዳችን የሚሉት የምርጫ ሒደቱ ተስተካክሎ እስኪያገኙት መብታቸውን በትግል ለማስከበር መወሰናቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹ጥያቄያችን ባልተመለሰበት ስለምርጫ ተሳትፎ ማሰብ ተጨፈኑ ላሞኛችሁን መቀበል ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ጥያቄያችንን እነርሱ ወደፈለጉት ደረጃ ማውረድና ማሳነስ ነው፡፡ ስለዚህ ይዘን ለተነሳነው ጥያቄ ምርጫ ቦርድም ሆነ ገዢው ፓርቲ ወይም መንግሥት እስከ ዛሬ ድረስ ጆሯቸውን ቢደፍኑም፣ ዛሬም ጊዜ እንዳላቸው በማስረዳት ተገደው እንዲሰሙ ለማድረግ ሕዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር የተባበረና የተቀናጀ ትግላችንን እንቀጥላለን፤›› ብለዋል በመግለጫቸው፡፡

መራጩ ሕዝብና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከጎናቸው እንዲቆም በመጠየቅ፣ ጎን ለጎን ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ፣ በትብብር ለመሥራት የሚያስችል የጋራ የመግባቢያ ሰነድ ለማፅደቅና ከሕዝቡ ጋር ተከታታይ የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት በመርሐ ግብራቸው ላይ ማስፈራቸውን አስረድተዋል፡፡

16,January 2013

Ethiopian Reporter

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: