አሜሪካ በአፍሪካ ወታደራዊ የበላይነቷን ልታረጋግጥ ነው!

ፕሮግራሙን ለማስፈጸም 35 አገሮች ተመርጠዋል

africom 1

አዲስ በተያዘው የአውጳውያን ዓመት አሜሪካ በአፍሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ የበላይነትን ሊያረጋግጥላት የሚችል ፕሮግራም ነድፋለች፡፡ ከሦስት ሳምንታት በፊት ይፋ የሆነውን ፕሮግራም ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ ላይ የተነደፈውን ዕቅድ የሚያስፈጽሙ 35 የአፍሪካ አገሮችም ተመርጠዋል፡፡

ምንም እንኳን ዜናው ይፋ ከሆነ የቆየ ቢሆንም የአሜሪካንን የመከላከያ ሚኒስቴር (ፔንታጎን) እንዲመሩ የታሰቡት ሪፓብሊካኑ ቸክ ሔግል ቀዳሚ ተወዳዳሪ መሆናቸው እስከሚገለጽ ድረስ የብዙዎችን ቀልብ አልሳበም ነበር፡፡ የአሜሪካንን ጦር ሠራዊት በየአገሩ በማዝመት ጉዳይ ላይ ጽኑ የተቃውሞ አስተሳሰብ የሚከተሉት ሔግል እንዲህ ዓይነቱን ፕሮግራም ለማስፈጸም ገጣሚ ሚኒስትር እንደሚሆኑ በሰፊው እየተነገረ ነው፡፡

የመከላከያ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ይፋ እንዳደረገው በአፍሪካ በየጊዜው እያገረሸ የሄደውን የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ ለመቆጣጠርና ሌሎች በክፍለ አህጉሩ የሚነሱ ቀውሶችን ለመከላከል የሚል ዕቅድ የወጣለት ፕሮግራም በያዝነው የአውሮጳውያን ዓመት ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ይህ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው ፕሮግራም የሚያተኩረው ጦርነት ወይም ሁከት በተፈጠረ ጊዜ የአሜሪካንን ወታደሮች በየቦታው ከመላክ ይልቅ አፍሪካውያንን ለራሳቸው ችግር ወታደራዊ ዕርምጃ ለመውሰድ እንዲችሉ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ እንዲያስችል የአሜሪካ ወታደራዊ መኮንኖች ለአፍሪካውያኑ የተለያየ ወታደራዊ ሥልጠና ለመስጠት ወደዚያው ያመራሉ፡፡

መቀመጫውን በካንሳስ ጠቅላይ ግዛት የራይሌ ምሽግ ባደረገው በ1ኛው የእግረኛ ዲቪዚዮን ሥር የሚገኘው ሁለተኛው ብርጌድ (ወይም በልዩ ስሙ ጩቤ ብርጌድ) የሚውጣጡ አሰልጣኝ መኮንኖች በሊቢያ፣ ሱዳን፣ አልጄሪያና ኒጀር የሚገኙ የአልቃይዳ ደጋፊዎችን ዋና ዒላማ በማድረግ በቅድሚያ እንደሚንቀሳቀሱ ፎክስ ኒውስ ዘግቧል፡፡ ከአልሸባብ ሚሊሻዎች ጋር ጦር የገጠሙትን ኬኒያና ዑጋንዳንም እንደሚያግዙ ጨምሮ ተገልጾዋል፡፡

ይኸው በቡድን እየተደራጀ ሥልጠና የሚሰጠው የወታደራዊ መኮንኖች ስብስብ በአንዳንድ ቦታዎች በጥቂት መኮንኖች ብቻ በሌሎች አገሮች ደግሞ በመቶዎች በመሆን ሥልጠናውን እንደሚሰጡ ታውቋል፡፡ መኮንኖቹ ሥልጠናውን ለመስጠት በሚቆዩበት ጊዜያት ሁሉ የባህል፣ የአካባቢ፣ የቋንቋ፣ ወዘተ ችግር እንዳይገጥማቸው የሚላኩበትን አገር በተመለከተ የአጭር ጊዜ ሥልጠና እየተሰጣቸው ይገኛል፡፡ አላላካቸውም ጥቂት በጥቂት ይሆናል፡፡

በፕሮግራሙ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ጄኔራል ሬይመንድ ዖዲዪርኖ አሜሪካ ከዚህ በፊት የነበራትንና አሁን በአዲሱ ፕሮገራም የሚኖራትን ሚና ሲገልጹ “ከዚህ በፊት ስንከተል የነበረው ስትፈልጉን ጥሩን ዓይነት ነበር፡፡ አሁን ግን ከዚያ ባለፈ መልኩ” እንደሚሆንና ከዚህ በፊት ከነበረው አሠራር በስፋት የተለየ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ የአፍሪካን የዕዝ ማዕከል (አፍሪኮም) እንዲመሩ የታጩት ጄኔራል ዴቪድ ሮድሪጌዝ በበኩላቸው ሲናገሩ “እኛ እዚያ የምንሄደው የእኛ አሠራር እንዴት እንደሆነ ልናሳያቸው አይደለም፤ የራሳቸው አሠራር እንዴት ተግባራዊ መሆን እንደሚችል ለማስተማር ነው፡፡ የጦር ሠራዊታቸው አሁን ያለበትን ሁኔታ ከተመለከትን በኋላ የት ደረጃ ላይ መድረስ እንዳለበት እናሠለጥናቸዋልን፤ እናዘጋጃቸዋለን” ብለዋል፡፡

ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር፣ ሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ ወዘተ ብርቅ በሆነባት አፍሪካ ይህ ዓይነቱ የአሜሪካ ወታደራዊ ድጋፍ በአምባገነኖች የተሞላውን አህጉር የበለጠ ጨለማና ተስፋ ቢስ እንደሚያደርገው የአፍሪካ ጉዳይ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ለአብዛኛዎቹ አምባገነን መሪዎች ህዝባቸውን ለመርገጥና በሥልጣን ለመቆየት የአሜሪካ ወዳጅ መሆን እንዲሁም ይህንን ዓይነት በቀዳሚነት የአሜሪካንን ጥቅም የሚያስጠብቅ ወታደራዊ የበላይነት በአገራቸው እንዲካሄድ መፍቀድ ቀላሉ መንገድ እንደሚሆናቸው አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡

በሚያዚያ 2000ዓም የአሜሪካ መኮንኖች በኢትዮጵያ ሥልጠና ሲሰጡ::(የፎቶው ባለቤት:US Army Africa’s photostream)

ሟቹ ጠ/ሚ/ር በአገር ውስጥ የነበረውን የፖለቲካ ውጥረት ለማርገብ ሶማሊያንን በመውረር የአሜሪካ ጠንካራ ወዳጅ በመሆን በሥልጣን ለመቆየት አማራጭ እንዳደረጉት አሁን ያሉትም ሆነ ሌሎቹ አምባገነን መሪዎች ይህንኑ መስመር እንደሚከተሉ ከተለያዩ የዜና ምንጮች የሰበሰብነው የአፍሪካውያን ምሁራን አስተያየት ይጠቁማል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድም ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉትን አሸባሪዎች ሳይሆን በአገር ውስጥ የዴሞክራሲ፣ የመብት፣ ወዘተ ጥያቄ የሚያነሱ ሁሉ በአሸባሪነት እየተፈረጁ ለሥቃይ የተዳረጉበት፤ መብት ረገጣው የተስፋፋበት እና ምዕራባውያን ከዝምታ ወይም ከውግዘት ያላለፈ ጠንካራ እርምጃ ሊወስዱ የማይፈልጉበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል፡፡

የአፍሪካንን ጉዳይ በቅርብ በሚከታተሉ ዘንድ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ይኸው የአሜሪካ ወታደራዊ የበላይነት በይፋ ከተነገረው አሸባሪዎችን የማጥቃትና የመቆጣጠር ዋና ዓላማ ሌላ ዕቅድ አለው የሚል የመከራከሪያ ነጥብ ቀርቦበታል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከአፍሪካ አምባገነን መሪዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት በማድረግ አፍሪካን እየተቆጣጠረች የመጣችውን የቻይናን እንቅስቃሴ በቅርብ ሆኖ ለመከታተል እንዲያመች ነው የሚል ጠንከር ያለ አስተያየት በእነዚሁ  ወገኖች ተሰጥቶበታል፡፡ ከአሜሪካ ጋር በወታደራዊ ስምምነት በመተባበር ወይም ከቻይና ጋር በኢኮኖሚ በመተሳሰር በየትኛውም መልኩ ቢሆን የአፍሪካ አምባገነኖች የአገዛዝ ዘመናቸውን የሚያረዝሙበት ምቹ አማራጭ ማግኘታቸው ጨምሮ ተገልጾዋል፡፡

ፕሮግራሙን በተመለከተ ከአፍሪኮም እስካሁን ወደ መቶ የሚጠጉ የምደባ ጥያቄዎች መቅረቡን የተናገረው የዜና ዘገባ ዝግጁ የሆኑትና ሥልጠናቸውን ያጠናቀቁት የመጀመሪያዎቹ ወታደራዊ መኮንኖች በጥቂት ወራት ውስጥ ወደ አፍሪካ እንደሚያቀኑና ጨምሮ አስታውቋል፡፡

(ፎቶ፡ sott.net)

goolgule

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: