መንግሥት የዘንድሮን በጀት ጉድለት ለመሸፈን ከአገር ውስጥ ሊበደር ነው

–    ብድሩ ብር በማተም የሚገኝ አይሆንም ተብሏል “የአገሪቱ ባንኮች የማበደር አቅም በመናመኑ መንግሥት ብር እንዲያትም ሊገደድ ይችላል” የኢኮኖሚ ባለሙያዎች

የአገሪቱ ኢኮኖሚንና የዜጎችን ኑሮ እየተፈታተነ የሚገኘውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር መንግሥት ከአገር ውስጥ መበደር አቁሞ የነበረ ቢሆንም፣

የዘንድሮን 26.8 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ለመሸፈን ሲባል ግን ከአገር ውስጥ እንደሚበደር አስታወቀ፡፡ ባለሙያዎች ግን የአገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀዛቀዙ ከአገር ውስጥ ምንጮች ብድር ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ፣ መንግሥት ብር ማተም ውስጥ ሊገባ ይችላል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ፡፡የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሐጂ ኢብሳ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ የዚህን ዓመት የበጀት ጉድለት ለመሸፈን መንግሥት ከአገር ውስጥ እንደሚበደር ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ብድሩ ከብሔራዊ ባንክ (ብር በማተም) የሚገኝ ሳይሆን፣ በኢኮኖሚው ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ከሚገኘው ገንዘብ ነው ለመበደር የታቀደው ብለዋል፡፡ 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የ2005 ዓ.ም. የፌደራል መንግሥት በጀት 137.8 ቢሊዮን ብር መሆኑ ይታወሳል፡፡ ይህንን በጀት ለመሸፈን ከታክስና የተለያዩ ገቢዎች 111.03 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን፣ ቀሪው 26.8 ቢሊዮን ብር ግን በበጀት ጉድለትነት ተይዞ በተለያዩ አማራጮች ለመሸፈን መታቀዱን ያስረዳል፡፡ ከእነዚህም መካከል 7.9 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን ከውጭ አገሮች ከሚገኝ የፕሮጀክት ብድር፣ 5.03 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን በዓለም ባንክ በኩል ለመሠረታዊ አገልግሎቶች ከለላ ከሚገኝ ብድር፣ እንዲሁም 169.7 ሚሊዮን የሚሆነውን ብር በእዳ ስረዛ ከሚገኝ ለመሸፈን መታቀዱን ይተነትናል፡፡ 

በመሆኑም ከላይ የተዘረዘሩት አማራጮች ከአጠቃላይ የበጀት ጉድለቱ 13.2 ቢሊዮን ብር ያህሉን የሚሸፍኑ ሲሆን፣ ቀሪውን 13.6 ቢሊዮን ብር ግን ከአገር ውስጥ ብድር ለመሸፈን መታቀዱን ያብራራል፡፡ 

አቶ ሐጂ የሚገልጹትም መንግሥት የገንዘብ ፖሊሲውን የማስፈጸም ኃላፊነት በጣለበት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በኩል የበጀት ጉድለቱን ለመሸፈን ከአገር ውስጥ እንደሚበደር ነው፡፡ መንግሥት ከውጭ መንግሥታት በብድርና በእዳ ስረዛ ለማግኘት ያቀደውን ያህል ገንዘብ አለማግኘቱን መረጃዎች የሚጠቀሙ ሲሆን፣ ይህም ማለት ከአገር ውስጥ ብድር ለመሸፈን የታቀደውን የገንዘብ መጠን ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

መንግሥት ከአገር ውስጥ ምን ያህል ሊበደር እንደሚችል የተጠየቁት አቶ ሐጂ፣ “አሁን ላይ ሆነን መንግሥት ምን ያህል ሊበደር ይችላል የሚለውን መገመት አዳጋች ነው፤” ብለዋል፡፡ ነገር ግን ከብሔራዊ ባንክ የመበደር ዕቅድ በጭራሽ አለመኖሩን፣ ብድሩን በኢኮኖሚው ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ ከሚገኝ ገንዘብ ለመሸፈን መታቀዱንና እየተረጋጋ የመጣውን የዋጋ ንረት በማይጎዳ ሁኔታ እንደሚፈጸም አስረድተዋል፡፡ 

በኢኮኖሚ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ከሚገኝ ገንዘብ ማለት ከሌሎች የመንግሥት አበዳሪ ባንኮች እንደ ንግድ ባንክና ልማት ባንክ እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ ተንታኞች የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከመቀዛቀዝ ባለፈ ችግር ውስጥ ስላለ የባንኮች የማበደር አቅም የሳሳ መሆኑን ያሳያል ይላሉ፡፡ ስለዚህ መንግሥት ብር የማተም ግዳጅ ውስጥ ሊገባ ይችላል ሲሉ ፍርኃታቸውን ይገልጻሉ፡፡ 

አሁን የሚስተዋለው ዝቅተኛ የዋጋ ግሽበት ምጣኔ መንግሥት እንደሚለው በወሰዳቸው የበጀትና የገንዘብ ፖሊሲ ዕርምጃዎች የተገኘ አይደለም የሚሉት ባለሙያዎቹ፣ የኢኮኖሚው መቀዛቀዝ የወለደው ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ተፈላጊው የባንክ ብድር ባለመገኘቱ በባንኮች የማበደር አቅም መሳሳት የተነሳ መሆኑን፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረት መከሰት የመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶችና የግሉ ዘርፍ መካከለኛ ፕሮጀክቶች የመቆም አዝማሚያ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል ሲሉ ባለሙያዎቹ ይከራከራሉ፡፡ 

ይህም የአገሪቱ ኢኮኖሚን በማቀዝቀዙና የዜጎችን የመግዛት አቅም በመፈታተኑ ነው የዋጋ ግሽበቱ ያቆለቆለው በማለት ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከአገር ውስጥ ብድር ማግኘት የማይታሰብ ነው በማለት ይገልጻሉ፡፡ ይህንን ማድረግ ቢቻል ኖሮ የግል ባለሀብቱ የጀመራቸውን ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ የብድርና የውጭ ምንዛሪ ወረፋ ውስጥ አይገባም በማለት በአፅንኦት ይከራከራሉ፡፡ 

አቶ ሐጂ ግን የዋጋ ግሽበቱ አምና በታኅሳስ ወር ከነበረው 35.9 በመቶ ባለፈው ታኅሳስ ወር ወደ ደረሰበት የ12.9 በመቶ ሊያሽቆለቁል የቻለው መንግሥት በወሰዳቸው የገንዘብና የበጀት ፖሊሲዎች፣ እንዲሁም ከውጭ እያስገባ በሚያቀርባቸው የመሠረታዊ ሸቀጦች አቅርቦትና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች ቅንጅት ውጤት መሆኑን ይናገራሉ፡፡

Ethiopian Reporter

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: