ስደት እንደ አማራጭ – ለምን?

(ከአብዱራህማን አህመዲን የቀድሞ የፓርላማ አባል)

(ይህ ጽሑፍ ጥር 8 ቀን 2005 በወጣው ሰንደቅ ጋዜጣ ላይ ታትሟል፡፡ ጋዜጣውን የማያገኙ፣ በተለይም በውጭ ሀገር ያሉ ዜጎች ሁሉ ቢያነቡት ‘ይጠቅማል፤ በአሁኑ ወቅት ‘ኢህአዴግ እየፈጸመ ያለውንም ግፍ በግልጽ ያሳያል’ በሚል መንፈስ በኢ.ኤም.ኤፍ. ድረ-ገጽ ላይ አውጥተነዋል፡፡)

ይህቺን መጣጥፍ እንዳዘጋጅ ምክንያት የሆነኝ ሦስት የማውቃቸው ሰዎች በዚህ ሰሞን ከገጠማቸው ሁኔታ በመነሳት አገር ለቆ መሰደድን እንደ አማራጭ መውሰዳቸውን መግለፃቸው ነው፡፡ ገጠመኞቼን በተከታታይ በየተራ ካስነበብኩ በኋላ የግል እይታየን አስከትላለሁ፡፡ በመጨረሻም የማጠቃለያ ሃሳብ በማቅረብ ጽሑፌን እቋጫለሁ፡፡

እትብቴ በተቀበረባትና አፈር ፈጭቼ ባደግኩባት፣ የፊደል ሰራዊትን በተማርኩባትና ለአሁኑ እኔነቴ መሰረት በሆነችኝ በቀድሞዋ የጁ አውራጃ፣ በሐብሩ ወረዳ፣ በጊራና ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ የሆነ አንድ አርሶ አደር ዘመዴን ለመጠየቅ ባለፈው ሰሞን ስልክ መታሁ፡፡ ስለ ዘመድ አዝማዱ፣ ስለ ጋብቻ ስለሞቱ፣ ስለ ከብቱ ስለአዝመራው፣ ስለ አረዳው ስለቀየው፣ ስለመንግስት ስለአካባቢው ሁኔታ በዝርዝር ለማወቅ ስፈልግ ስልክ የምደውለው ለዚህ ዘመዴ ነው፡፡ ይህ ዘመዴ መሐመድ ሐሰን ይባላል፡፡

መሐመድ በሚኖርባት ቀበሌ ብቻ ሳይሆን በወረዳዋ የተፈጸመች ወሬ አታመልጠውም፡፡ ወሬውን እንዴት እንደሚቃርመው ሁሌም ይገርመኛል፡፡ ደግሞ ምንም ነገር አይረሳም፡፡ የዛሬ አስር ዓመት ያወራውን ዛሬ ደግሞ ሲያወራው ለመሃላ አንዲት ቃል አይጨምርም፣ አይቀንስም፡፡ ውሸት አይቀላቅልም፡፡ አተራረኩም ይገርመኛል፡፡

መሐመድ ስመ-ጥር ገበሬ ነው፡፡ በአካባቢው አባባል “እብቁን የጣለ ገበሬ” ይባላል፡፡ ጨዋታውንም፣ ቀልዱንም፣ ቁምነገሩንም ያውቅበታል፡፡ ሰሞኑን ስልክ ስደውል መሐመድን አላገኘሁትም፡፡ ባለቤቱ ስልኩን አንስታ “የሉም፣ ወጣ ብለዋል” አለችኝ፡፡ ማንነቴን ገለጽኩና ሲመጣ እንዲደውልልኝ ነገርኳት፡፡ “ኧረ … ቅርብ አገር አደለም የሄዱት….. እ… በባህር ሄደዋል” አለችኝ፡፡

የሰማሁትን ማመን አቃተኝ፡፡ መሐመድ ዕድሜው በሃምሳዎቹ አጋማሽ የሚገኝ፣ ወደ አዛውንቶች ክበብ እየገባ ያለ ጎልማሳ ነው፡፡ የራሱን መሬት ብቻ ሳይሆን የሌሎችን ተከራይቶ የሚያርስ ጠንካራ ገበሬ በመሆኑ ለስደት (ያውም በባህር) የሚያደርሰው ሁኔታ እንደማይኖር አምናለሁ፡፡ በዚያ ላይ አንዷን ልጁን ወደ ዐረብ ሀገር መላኩን አውቃለሁ፡፡ ‘ታዲያ ለስደት የሚዳርግ ምን ችግር ገጠመው?’ አልኳት ባለቤቱን፡፡ ሁኔታውን እንዲህ በማለት በዝርዝር አስረዳቺኝ፡፡

“….በአካባቢያችን ዘንድሮ አዝመራው ያን ያህል አጥጋቢ ባይሆንም መቼም ደህና አግኝተን ቆዬ… በባህር የኸዱት ግን በሌላ ምህኛት ነው… በቀበሌአችን ሁሉም ሰው አንድ በአምስት ተጠርንፏል… እስዎም (መሐመድም ማለቷ ነው) የወንዶቹ ጠርናፊ ናቸው… እኔም የሴቶቹ ጠርናፊ ተብያለሁ… አዳ… በዛን ሰሞን ጀምሮ የቀበሌው ሰው ሁሉ ለሁለት ወር በየቀኑ 8 ሰዓት ልማት እንዲሰራና ከስራ በኋላ እንዲወያይ ታዘዘ…

የቀረ ሰው ዴሞ የመቶ ብር ቅጣት አለበት፡፡ በልማት ሥራው የመጣውንና የቀረውን እየመዘገበ ቀሪዎችን የሚያስቀጣ ደግሞ ጠርናፊ ነው… ሰው ደሞ በምኑም በምኑም ይቀራል… ኸቀረ ይቀጣል፡፡ አዳ… ዝም እንዳይባል ችግር ነው፣ ግምገማ አለ… ማስቀጣቱ ደግሞ አገር ጋር ሊያጣላ ሆነ… መቶ ብር ተወየት አምጥቶ ይከፍላል?… አዝመራው ስቷል… ሰው ደሞ እገሌ አስቀጣኝ እንጂ መንግስት ቀጣኝ አይል… ነገሩ አስችጋሪ ቲሆንብን… አገርም ጋር መንግስትም ጋር ከምጣላ ከዝህ ግድም ዘወር ብል ይሻላል ብለው በባህር ሄዷ!…. የዘመቻው ስራ አስቲያበቃ ወደ አዲስ አበባም ወደ ሌላም አገር የሄደ አለ… መሄጃ የሌለው ብቻ ነው የቀረ…” በማለት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጠችኝ፡፡ ይህንን በተግባር የተገለጠ ስደት፣ አንድ በሉልኝ፡፡

ባለፈው ረቡዕ ዕለት መገናኛ አካባቢ ታክሲ ለመያዝ ቆሜ ሳለ ከወደ ኋላየ ስሜ ተጠራ፡፡ ዘወር ስል አንድ የቀድሞ የፓርላማ አባል የነበሩ ሰው ናቸው የጠሩኝ፡፡ ለሁለት ዓመታት ያህል አልተያየንም፡፡ የናፍቆታችንን ያህል ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ አረፍ ብለን ሻይ እየጠጣን ጥቂት ወሬ ሰለቅን፡፡ እኚህ የቀድሞ የፓርላማ አባል በአካባቢ ጥበቃ ትምህርት የማስተርስ ዲግሪ ቢኖራቸውም ከፓርላማ ከወጡ በኋላ እስከ አሁን ድረስ ሥራ ሊያገኙ አለመቻላቸውን ገለጹልኝ፡፡ ይህም የሆነው ቀድሞ በነበራቸው የፖለቲካ አቋም ምክንያት እንደሆነ ገጠመኛቸውን እየጠቀሱ ካስረዱኝ በኋላ፣ “ዛሬም ወደዚህ የመጣሁት የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ባወጣው የሥራ ማስታወቂያ ለመወዳደር ለመመዝገብ ነው፡፡ … እንግዲህ ይህ ካልተሳካልኝ አማራጩ ስደት ነው…” አሉኝ፡፡

“ያለውን ሁኔታ እየታገሉ መኖር ነው እንጂ ከቤተሰብ ተለይቶ ስደትማ በዚህ ዕድሜ ጥሩ አይመስለኝም” አልኳቸው፡፡

“በተማርኩት ትምህርት አገሬ ላይ ሰርቼ መኖር ካልቻልኩ ኑሮዬ ከስደት በምን ይለያል?… እንዳልነግድ ወረት የለኝ…. እንግዲህ… የበይ ተመልካች ሆኜ ከምኖርና በሀገሬ ውስጥ የስደተኛ ኑሮ ከምኖር አንድያውን የለየለት የሰው ሀገር ስደት ይሻለኛል… ለኔ ሁሉም ያው ስደት ነው” አሉኝ በምሬት፡፡ ይህንን በተግባር ያልተገለጠ ስደት፣ ሁለት አትሉም?

እነዚህን ሁለት የስደት አማራጮ ከራሴ ሁኔታ ጋር እያነጻጸርኩ በማብሰልሰል ላይ ሳለሁ፣ ተንቀሳቃሽ ስልኬ አንቃጨለ፡፡ ከሃያ ሰባት ዓመታት በፊት በንግድ ስራ ኮሌጅ፣ በኋላም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አብረን ያሳለፍን ጓደኛዬ ነበር የደወለልኝ፡፡ ‘ለገና በዓል የእንኳን አደረሰህ መልእክት ልኬለት የምስጋና ምላሽ ልኮልኛል፡፡ አሁን ደግሞ ለምን ፈልጎኝ ይሆን’ አልኩና ስልኩን አነሳሁት፡፡ ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡ ከዚያም “…ምን እዚህ አገር እኮ መኖር አልተቻለም” አለኝ፡፡

ይህ ወዳጄ ላለፉት ሃያ ዓመታት ገደማ በንግድ ስራ ላይ ያሳለፈና ሃብት ያፈራ በመሆኑ “አንተ ደግሞ ምን ሆንክና ነው የምታማርረው?… ይኸ ስርዓት እንዲያውም ለአንተ ባለውለታ ነው… ከስራ ቢያባርርህም… የራስህን የንግድ ስራ ጀመርክ… ይኸው ባለሃብት ሆንክ… ባክህ ዝም ብለህ አታማር” አልኩት፡፡

“ስርዓቱ ምን ባለውለታዬ ነው…. ያኔ ንግድ ባንክ ውስጥ የነበርን ሰራተኞች የመብት ጥያቄ አነሳን… ገና ስልጣን ከመያዛቸው… ዓመት እንኳ ሳይሞላቸው… የታገሉለትን ዓላማ ዘንግተው መብታችሁን ለምን ጠየቃችሁ ብለው አባረሩን… ዳቦ በልቼ መኖር ስለነበረብኝ… አማራጭ ሳጣ ወደ እናት መርካቶ አቀናሁ… ዕድሜ ለመርካቶ ልጆች አሁን ያለሁበት ደረስኩ… ይህ ግን ስርዓቱ በፈጠረልኝ ዕድል ያገኘሁት ሳይሆን፣ ስርዓቱ ባወረደብኝ መከራ ያገኘሁት መልካም አጋጣሚ ነው…” አለኝ፡፡

“በዚያም አለ በዚህ ቁም ነገሩ ማግኘትህ ነው”

“ምን ዋጋ አለው በመከራ ያገኘሁትን ጠራርጎ ወስዶ መልሶ ወደ ድህነቴ ሊመልሰኝ ነው”

“እንዴት ምን ተፈጠረ?”

“ይኸው አሁን ገቢዎችና ጉምሩክ መስሪያ ቤት ነው ያለሁት፡፡ ሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ክፈል አሉኝ፡፡ እኔኮ ያለኝ ወረት ቢደመር ያን ያህል አይሆንም… እኔም የሂሣብ ባለሙያ ነኝ… ግን… እነሱ ስሌቱን እንዴት እንደሚያሰሉ ሊገባኝ አልቻለም… በቀን ሦስት ጊዜ ትበላላችሁ የተባለው ቃል ተረሳና እንድ ጊዜም እንዳንበላ ጉሮአችንን ማነቅ ያዙ… የሰራሁትን የምቀማና ሙልጬን የምወጣ ከሆነ እንግዲህ ምን አገር አለኝ!?… ማቄን ጨርቄን ሳልል መሰደድ ነው አማራጩ… ” አለኝ፡፡ አሁንም የስደት አማራጭ! ይህንን ደግሞ ሦስት በሉልኝ፡፡

እነዚህ ሦስት አጋጣሚዎች ናቸው እንግዲህ ይህቺን መጣጥፍ እንድጫጭር ግድ ያሉኝ፡፡ አርሶ አደሩ መሐመድ፤ የአካባቢው የፖለቲካ አመራር በፈጠረበት ጫና ከአካባቢው ህብረተሰብም ከመንግስትም ላለመጋጨት ሲል፤ ሞፈርና ቀንበሩን ሰቅሎ፣ ባለቤቱንና ልጆቹን ጥሎ፣ የሞቀ ጎጆውን ዘግቶ፣ ወዳጅ ዘመዶቹን ተለይቶ መሰደድን መረጠ፡፡ ባህር ተሻገረ፡፡ ምሁሩ በያዘው የፖለቲካ አቋም ምክንያት ተምሮ ባገኘው እውቀትና ከሃያ ዓመታት በላይ ባካበተው ልምድ በሀገሩ ሰርቶ መኖር ባለመቻሉ “በሀገሬ ውስጥ የስደተኛ ኑሮ ከምኖር… አገር ጥዬ መሰደድ ይሻለኛል” አለ፡፡ ነጋዴው፤ ካለው ካፒታል የማይመጣጠን ግብር እንዲከፍል በተፈጠረበት ጫና በመማረር ለዓመታት ያካበተውን ሀብት ለመንግስት አስረክቦ ድንበር ተሻግሮ መሰደድን ተመኘ፡፡ ከላይ ያቀረብኳቸው ሦስት አብነቶች ሦስት የህብረተሰብ ክፍሎችን ይወክላሉ የሚል ግምት አለኝ፡፡

በአሁኑ ወቅት ያለውን የአርሶ አደሩን ሁኔታ ያየን እንደሆነ በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች የራሱን ሥራ አቁሞ ለወራት የዘለቀ የልማት ሥራ በግዳጅ እንዲሰራ እየተደረገ ነው፡፡ በርግጥ ለአንድ ሀገር ልማት የሕዝብ ተሳትፎ እጅግ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ሕዝቡም ሀገሩን የማልማት የውዴታ ግዴታ እንዳለበት እገነዘባለሁ፡፡ አፈጻጸሙ ግን ሕዝቡን የሚያስመርርና ለስደት የሚዳርግ መሆን የለበትም ባይ ነኝ፡፡ ከሁሉ በፊት በልማት ሥራው ምንነትና ከልማቱ ስለሚገኘው ጥቅም ለሕዝቡ ሰፊ ግንዛቤ በማስጨበጥ ልማቱን በባለቤትነት መንፈስ እንዲያከናውን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ካለበለዚያ ከደርግ “የሥራ ዘመቻ” በምን ይለያል? በልማት ሰበብ ሕዝብን “የመንግስት ባሪያ” ማድረግ ከሕግም ከሞራልም አኳያ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ለመሆኑ ሕዝቡ ለሁለት ወራት ያሕል ነጻ አገልግሎት እንዲሰጥ የወሰነው ማን ነው? የየአካባቢው የመንግስት አካላት ወይስ ራሱ ሕዝቡ መክሮና ዘክሮ ወሰነ? እንዲያው ለነገሩ ሕዝብን በልማት ስለማነቃነቅ የተነደፈ፣ ሕዝብ የተሳተፈበት ፖሊሲ አለ? ሕዝቡ ለሁለት ወራት ጊዜ የራሱን ሥራ አቁሞ በየእለቱ የልማት ሥራ ብቻ እንዲሰራ ማድረግስ ተገቢ ነው?

ከአንዳንድ አካባቢዎች ባገኘሁት መረጃ ሕዝቡ የተማረረው በልማት ሥራው ብቻ አደለም፡፡ ጧት ከሁለት ሰዓት እስከ ስምንት ሰዓት በልማት ሥራው ከተሳተፈ በኋላ እስከ አስር ሰዓት ድረስ “ግምገማ” በሚል ምክንያት “አፈርሳታ” መቀመጡም ሕዝቡን እንዲሰላች አድርጎታል፡፡ ለዓመታት እንደታዘብኩት የኢህአዴግ ትልቁ ችግር ፊት ለፊት ያገኘውን እንቅፋትና ጋሬጣ አንስቶ መወርወሩንና ከፊቱ ገለል ማድረጉን እንጂ፤ ያ የተወረወረ ነገር ምን ላይ እንዳረፈ አለማስተዋሉና ሌላ መዘዝ አለማስከተሉን ማረጋገጥ አለመቻሉ ነው፡፡ ለዚህም ነው የኢሕአዴግ ካድሬዎች ሕዝቡን በግድም በውድም በልማት በማሳተፍ አሰርተው “የበላይ አካል” የጣለባቸውን “ኮታ” ማሟላታቸውን እንጂ ሕዝቡ ከእለት ስራው በመለየቱ የሚበላው ሊያጣ እንደሚችል ሊያስተውሉት ያልቻሉት፡፡ አርሶ አደሩ ኩርማን መሬት አርሶ በሚያገኘው ገቢ ራሱንና ቤተሰቡን መመገብ አይችልም፡፡ እናም ተጨማሪ

ገቢ ያስፈልገዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ተጨማሪ የጉልበት ሥራ መስራት አለበት፡፡ የልማት ሥራው ይህንንም ግምት ውስጥ ማስገባት አለበት፡፡

በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድ እየታየ ያለው ስደትን የሚያስመኝ ሁኔታም ቢሆን በከተሞች አካባቢ በስፋት የሚስተዋል ሐቅ ነው፡፡ በዚሁ ምክንያት በርካታ ታዋቂ ነጋዴዎች ጭምር ራሳቸውን አጥፍተዋል፡፡ “ክፈሉ” ተብለው በተነገራቸው የግብር መጠን ደንግጠውና ራሳቸውን ስተው በሽተኛ የሆኑትንማ ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ እናም በዚህ ረገድ መንግስት ያለበትን ክፍተት መፈተሽ ይገባዋል፡፡ ካለበለዚያ ግብር ከሚከፍሉት ዜጎች ቁጥር በርግገው የሚሰደዱት ሊበልጥ የሚችልበት አጋጣሚ እንደሚፈጠር መጠርጠሩ ብልህነት ነው፡፡ “ሕዝብን” ማስበርገግና በስጋት ውስጥ እንዲኖር ማድረግ ደግሞ የሚወደድ ተግባር አይመስለኝም፡፡ ደግም አደለም፡፡ ሌላ መዘዝም ሊያመጣ ይላል፡፡

እውቀትም፣ ጉልበትም፣ ልምድም ኖሯቸው በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት በሀገሪቱ ሰርተው መኖር ያቃታቸው ዜጎች ቁጥርም ጥቂት የሚሰኝ ላለመሆኑ በርካታ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እኔ ራሴ ዛሬ እንደልጅነቴ ‘አፈር እየፈጨሁ’ መኖርን የመረጥኩት የስልጣን ጥም አናታቸው ላይ ወጥቶ የሚሰሩትን ያሳጣቸው “ግልገል ካድሬዎች” እያደረጉት ያለውን ነውረኛ ነገር ማየትም መስማትም ስላስጠላኝ ነው፡፡ የኢህአዴግ “ግልገል ካድሬዎች” ኢህአዴግን የጠቀሙ እየመሰላቸው በሰራተኛ ቅጥር፣ ዕድገትና ዝውውር ረገድ በየመስሪያ ቤቱ እየተከተሉት ያለው አድሎአዊና ሕገወጥ አሰራር በቅጡ መፈተሽ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ኢህአዴግ ራሱን በራሱ እያረመ የሚሄድ ስርዓት ለመፍጠር እየተፍጨረጨረ መሆኑን አስተውያለሁ፡፡ ይሁን እንጂ፣ በዚህ ረገድ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር የማንን ጎፈሬ እንደሚያበጥር ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ለምሣሌ፤ ወደ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ወረድ ቢል በአቶ አርከበም፣ በዶ/ር ካሡም አሁን በአቶ መኩሪያ ዘመን በሰራተኛ ቅጥር፣ ዕድገትና ዝውውር ረገድ እየተሰሩ ያሉ በርካታ ግድፈቶችን ያገኛል፡፡

አምባገነኑንና አረመኔውን የደርግ ስርዓት ለማስወገድ በተደረገው የትጥቅ ትግል ሕይወታቸውን ያጡ፣ አጥንታቸውን የከሰከሱና ደማቸውን ያፈሰሱ ሰማዕታት ያሸከሙን አደራ ሁሉም ዜጎች ሰብአዊ ክብራቸው፣ የሃሳብ ነፃነታቸውና የፖለቲካ አመለካከታቸው ተጠብቆ በሀገራቸው ሰርተው መኖር እንዲችሉ እንጂ፤ አሁን አሁን “ግልገል ካድሬዎች” እንደሚያደርጉት የመንግስት መስሪያ ቤቶችን አንድ ዓይነት አመለካከት ባላቸው ሰዎች እንዲሞሉ ለማድረግ አይደለም፡፡ እንዲህ ያለው አመለካከትና አሰራር ራሱ ኢህአዴግ እንደሚለው “ኪራይ ሰብሳቢነት” ሲሆን፣ በሌላ በኩል የነዚያን ሰማዕታት አደራ መብላት መሆኑም መታወቅ አለበት፡፡

አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ሲያሸንፍ የራሱን አባላትና ደጋፊዎች ብቻ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የመሰግሰግ አሰራር በእንግሊዝኛው አጠራር “Patronage System ወይም Spoils System” ይባላል፡፡ እንዲህ ያለው አሰራር በአሜሪካን ሀገር እ.ኤ.አ ከ1812 ገደማ ጀምሮ ስራ ላይ ውሎ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይሁን እንጂ አንዱ ፓርቲ ተሸንፎ ሌላው ሲተካ የተሸናፊው ፓርቲ አባላት ተጠርገው ስለሚወጡ የሲቪል ሰርቪሱን ቀጣይነት የሚያሳጣ ሁኔታ በመፈጠሩ እ.ኤ.አ ከ1883 ጀምሮ እንዲቀር ተደርጓል፡፡ ፓርቲዎች ቢቀያየሩም የመንግስት መዋቅሩና ቢሮክራሲው የሰው ኃይሉን እንደያዘ መቀጠል ስላለበት “Patronage System” አክሳሪ መንገድ በመሆኑ ኢህአዴግ ሰማዕታት ለተሰውለት አደራ ሲል እንዲህ ያለውን አሰራር ነገ ዛሬ ሳይል ማስቀረት ይጠበቅበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ለማጠቃለል ያህል፣ አንዳንድ ትኩረት የሚሹ ነጥቦችን ልጥቀስ፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸው ሦስት ምሳሌዎች በአሁኑ ወቅት የበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ችግሮች መሆናቸው እርግጥ ነው፡፡ እናም “የጥቂቶች” ጥያቄ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ ጥያቄው “የጥቂቶች” ነው ቢባል እንኳ፤ ደርግን የደመሰሰው ኃይል በ“ጥቂቶች” የተጀመረ እንደነበር ማስተንተኑ መልካም ነው፡፡ ጥያቄው “የጥቂቶች”ም ቢሆን ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት የመንግስትን ሆደ ሰፊነትና የገዢውን ፓርቲ ታላቅነት ከማረጋገጥ ውጪ አንዳች ክፋት የለውም ባይ ነኝ፡፡

ልማት የስደት ምክንያት ሆነ የሚለውን በተመለከተ፣ መፍትሄው ሕዝቡን በሥራው ብቻ ሳይሆን በውሳኔው ላይ ማሳተፍ ነው፡፡ እኔ ባለኝ መረጃ በአንዳንድ አካባቢዎች ይሄ አልተደረገም፡፡ ሕዝቡ በልማቱ ዙሪያ በቅጡ ተወያይቶና አምኖ የወሰነው ቢሆን ኖሮ ዛሬ አሜሪካን ጊቢንና መርካቶን ያጨናነቀው ወፈ-ሰማይ ጉብልና ጎልማሳ ሁሉ ቀየውን ለቆ ባልመጣ፣ ከፊሉም ባህር አቋርጦ ከሀገር ባልተሰደደ ነበር፡፡

እስከ አሁን ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች የተሰደዱ ዜጎችን አባብሎና መክሮ መመለስ ሲገባን፣ ስደተኞችን መርቆ ከመሸኘት ባልተናነሰ የአሰራር ክፍተት የስደተኛውን ቁጥር ማበራከት የሚወደድ መንገድ ባለመሆኑ የሚመለከታቸው የመንግስትና የፓርቲ አካላት ሁሉ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡

በመጨረሻ፣ ኢህአዴግን በተመለከተ አንድ ሁሌም የሚገርመኝን ጥያቄ ላንሳ፡፡ የመንግስት መዋቅሩም ሆነ የኢህአዴግ የፓርቲው መዋቅሮች የተለያዩ ሀገራዊና አካባቢያዊ ምርጫዎች በሚካሄዱባቸው ዓመታት ለሕዝቡ መልካም መልካም ተግባራትን በማከናወን፣ የፖሊሲና የአሰራር ማሻሻያዎችን፣ እንዲሁም አስተዳደራዊ ማስተካከያዎችን ማድረግ ሲገባቸው አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያማርሩና የተቃውሞ ድምፆችን (Protest Vote) የሚያበራክቱ እርምጃዎችን የሚወስዱት ለምንድነው? በኢህአዴግ ላይ የምርጫውን ዙር የሚያከርበት እንዲህ ያለው እርምጃ አይደለም? የዙሩ መክረር ደግሞ የምርጫውን ሂደትና ውጤት የሞት ወይም የሽረት እያደረገው መሆኑ አልተስተዋለም? አበቃሁ፡፡ በሌላ ርዕስ እመለስ ይሆናል፡፡

Ethioforum

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: