የብሮድካስት ባለሥልጣን ለአዲስ ታይምስ መጽሔት አሳታሚ የሙያ ብቃት ከለከለ

•    መጽሔቱ ከሕትመት ውጭ ሆኗል

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የአዲስ ታይምስ አሳታሚ ለሆነው አዱ ሕትመትና ማስታወቂያ ኩባንያ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ አልሰጥም አለ፡፡

አዱ ሕትመትና ማስታወቂያ ከብሮድካስት ባለሥልጣን የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሠርተፊኬት ባለማግኘቱ ከሕትመት ውጭ ሆኗል፡፡

ባለሥልጣኑ የሙያ ብቃት ላለመስጠት ሦስት ምክንያቶችን አስቀምጧል፡፡ የመጀመርያው በአሳታሚው ድርጅት የአክሲዮን ድርሻ ለውጥ ሲደረግ፣ በ15 ቀን ውስጥ የመዝጋቢው አካል እንዲያውቅ መደረግ ነበረበት ብሎ፣ ይህ ተግባራዊ እንዲደረግ የመገናኛ ብዙኅንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ በግልጽ መደንገጉን አስታውቋል፡፡ 

ነገር ግን አዱ ሕትመት በድርጅቱ ውስጥ የአክሲዮን ድርሻ የነበራቸው ሰዎች የአክሲዮን ድርሻ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ለውጥ ሲያደርጉ ለውጡን ባለሥልጣኑ ሳያውቅ ሕትመቱ ቀጥሏል፡፡ እንዲሁም የአድራሻ ለውጥ ሲደረግ ባለሥልጣኑ እንዲያውቅ አልተደረገም የሚል ነው፡፡

ሁለተኛው ምክንያት ማንኛውም በየጊዜው የሚወጣ ሕትመት ታትሞ በወጣ በ24 ሰዓት ጊዜ ውስጥ የሕትመቱን ሁለት ቅጅ በነፃ ለብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ መስጠት እንዳለበት መደንገጉን፣ ነገር ግን አዱ ሕትመትና ማስታወቂያ ለበርካታ ጊዜያት የሕትመቱን ቅጅ ለኤጀንሲው አላስገባም የሚል ነው፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው ምክንያት በመገናኛ ብዙኅንና የመረጃ ነፃነት አዋጅም ሆነ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ መስፈርት ማንኛውም የመገናኛ ብዙኅን ድርጅት ባለቤት ሥራውን ማንቀሳቀስ ያለበት በራሱ የፋይናንስ ምንጭ ነው፡፡ ነገር ግን የአዱ ሕትመትና ማስታወቂያ ሥራ በራሱ ውስጥ የአክሲዮን ድርሻ ባላቸው አካላት ብቻ ፋይናንስ መንቀሳቀስ ሲገባው፣ ድርጅቱ ከባለቤቶቹ ውጭ ባሉ ሰዎች ፋይናንስ እየተደረገ የሚንቀሳቀስ ነው የሚል ነው፡፡

‹‹ሕግ በመጣሱ ነው የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሠርተፊኬት ያልተሰጠው፤›› ሲሉ የብሮድካስት ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ልዑል ገብሩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አዱ ሕትመትና ማስታወቂያ ድርጅት መስፈርቶችን አሟልቶ ነበር መቅረብ የነበረበት የሚሉት አቶ ልዑል፣ አሟልቶ ባለመቅረቡ ግን የብቃት ማረጋገጫ ሠርተፊኬት ተከልክሏል ይላሉ፡፡

የአዲስ ታይምስ አሳታሚ የሆነው አዱ ሕትመት ይህንን አባባል በፍፁም አይቀበለውም፡፡ አክሲዮን በመግዛት የአዱ ሕትመትና ማስታወቂያ ድርጅት ባለቤት ሆኛለሁ የሚለው የቀድሞ ፍትሕ ጋዜጣ አሳታሚ የብሮድካስት ባለሥልጣንን ውሳኔ አጥብቆ ይቃወማል፡፡

የአዱ ሕትመትና ማስታወቂያ ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ የአክሲዮን ዝውውር መደረጉን የውልና ማስረጃ ጽሕፈት ቤት ያረጋገጠበት ሰነደ አለ፡፡ ይህ ሰነድም ለባለሥልጣኑ ገብቷል፡፡

ለሁለተኛው ክስም ጋዜጠኛ ተመስገን ምላሽ ሲሰጥ፣ ለብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ ሁለት ኮፒ እንደሚገባ ሕጉ ያስገድዳል፡፡ የእሱ ድርጅት ግን አምስት ኮፒ እንደሚያስገባና ለዚህም ደረሰኝ እንዳላቸው አስረድቷል፡፡

ለሦስተኛው ምክንያት ጋዜጠኛ ተመስገን በሰጠው ምላሽ፣ የእሱ ድርጅት በአገሪቱ 35 ሺሕ ኮፒ መጽሔት በየ15 ቀኑ አሳትሞ ያከፋፍላል፡፡ ከዚህ ሽያጭ በርካታ ገቢ ስለሚገኝ መጽሔቱ የሚታተምበት የገንዘብ ምንጭ ገልጽ ነው፡፡ ‹‹ሆን ተብሎ ለመዝጋት ታስቦ ነው፤›› በማለት ጋዜጠኛ ተመስገን በተወሰደው ዕርምጃ ምሬቱን ገልጿል፡፡

ምናልባት አዱ ሕትመትና ማስታወቂያ የተባሉትን ነጥቦች አስተካክሎ ቢመጣ የእርስዎ ባለሥልጣን ምላሽ ምን ይሆናል ተብሎ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ልዑል ሲመልሱ ‹‹ወደፊት የሚታይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አዲስ ታይምስን ባለፉት አራት ወራት ለሕትመት ያበቃው ዝግጅት ክፍል፣ ቀደም ሲል ፍትሕ ጋዜጣን ያሳትም እንደነበር ይታወቃል፡፡ ፍትሕ ጋዜጣ በአሁኑ ጊዜ ከሕትመት ውጭ ነው፡፡

ethiopian reporter

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: