ህወሓትና የመሰነጣጠቅ አዝማሚያው

ዳዊት ሰለሞን

 

ትግራይን የማስገንጠል ራዕይ በመሰነቅ ዱር ቤቴ ብለው የነበሩት የህወሓት ፋኖዎች የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ ተነጥሎ መኖር እንደማይችልና ይህንንም አጀንዳቸውን ሊያስፈፅምላቸው እንደማይችል ሊገነዘቡ “የትግራይ ሪፐብሊክን” የመመስረት አጀንዳቸውን ወደ መዝገብ ቤት በመመለስ ኢህአዴግን መሠረቱ የኢህአዴድ፣ ብአዴንና የደቡብ ህዝቦችን ይወክላሉ የተባሉ ድርጅቶች (በህወሓት ይሁንታ) ከተማረኩ የደርግና የኢህአፓ ወታደሮች አማካኝነት መመስረታቸውንና ግምባሩን መፍጠራቸውን የሚናገሩ ተንታኞች በሦስቱ ድርጅቶች ውስጥ ለአመታት ህወሓት የብረት ጡንቻ እንደነበረው የተለያዩ ዋቢዎችን በመጥቀስ ይሞግታሉ፡፡
የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ግን በአንፃሩ ተጠፍጥፈው (ህወሓት የሚፈልገውን አይነት ቅርፅ) እንዲይዙ ተደርገዋል ከሚባሉት ድርጅቶች በተሻለ የተለያዩ ሃሳቦችን በማንሳት የመወያየት ያልጣማቸውን ውሳኔ የመቃወም መብት እንደነበራቸው የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡

ከህወሓት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል በዛ ያለ ቁጥር የነበራቸው ኤርትራ እንደ አገር ከታወቀች በኋላ የኢትዮጵያ የጡት ልጅ በመሆኗ ያለገደብ ተጠቃሚ መሆኗ ያበሳጫቸው ነበር፡፡ በ1993 ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የነበረው ልዩነት ገሃድ ወጥቶ ህወሓት ለሁለት ተሰነጠቀ፡፡ ለፍኖተ ነፃነት ኦን ላይን ሚዲያ ቃለ ምልልስ የሰጡት አንጋፋው የህወሓት ታጋይ አቶ ስብሃት ነጋ “ህወሓት በታሪኩ ተሰንጥቆ አያውቅም፡፡ ተፈጠረው ልዩነት ደስተኛ ያልነበሩ አባላት ድርጅቱን ለቅቀው ወጡ እንጂ መሰንጠቅ የሚባል ነገር አልተፈጠረም” ብለዋል፡፡
እነ ስዬ አብርሃን ተከትለው የወጡት የህወሓት ነባር ታጋዮች፣ ህወሓት ውስጥ በቀሩት የእነ መለስ ዜናዊ ቡድን “እንደ ከሃዲ” ሲቆጠሩ እነርሱም በተራቸው “ተንበርካኪ” በማለት አንዳቸው ሌላኛቸውን ሲያወግዙ ታይተዋል፡፡ ስዬም በሙስና ተጠርጥረው ከእነ ቤተሰቦቻቸው ዘብጥያ እንዲወርዱ ተደርገዋል፡፡ “እስከ አናቴ በስብሼ ነበር” በማለት ከስንጥቁ በኋላ አፈር ልሶ መነሳቱን የሚናገረው ኢህአዴግ በተሀድሶ መጠነኛ ለውጥ ካደረገ በኋላ መለስ እስከ ሞቱበት ጊዜ ድረስ ጤናማ ድርጅት መስሎ መጓዝ ችሎ ነበር፡፡

                                                                    የመለስ ሞት የህወሓት ለስላሳ ሞት?
መለስ የህወሓት ሊቀመንበርነትን ከስብሃት ነጋ እጅ ከተቀበሉባት ሰዓት አንስቶ ግብአተ መሬታቸው እስኪፈፀም የድርጅቱ ሁሉም ነገር ነበሩ፡፡ ቀሪዎቹ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ምን ሲሰሩ እንደከረሙ ለማንም ግልጽ ባይሆንም መለስ የህወሓት ኢህአዴግ ጭንቅላት እንደነበሩ በለቅሶው ሰሞን በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ያሉ ቱባ የኢህአዴግ አመራሮች ሲናገሩ መመልከታችን አይዘነጋም፡፡ “ከመለስ በኋላ ህወሓት በኢህአዴግ ውስጥ የነበረውን የበላይነት በማስጠበቅ ሊያስጉዘው የሚቻለው ማን ነው?” የሚል መሠረታዊ ጥያቄ አመራሮቹን ከስብሰባ ስብሰባ እየተከተለ በውጥረት እንዲከርሙ አድርጓቸዋል፡፡
“መለስም ተተኪውን ባለማዘጋጀቱ ለዚህ ክፍተት ተጠያቂ መሆን ይገባዋል፡፡” የሚሉ ድምፆች ከመደመጣቸው ባሻገር “መፍትሔው ከዚህ ቀደም የተሰናበቱ አባላቶቻችን እንዲመለሱ ማድረግ ነው፡፡” እስከ ማለት ተደርሷል፡፡ ምንም እንኳን የህወሓት ነባር ታጋዮች “አቦይ” (አባት) በማለት የሚጠሯቸው አቶ ስብሃት ነጋ ራሳቸውን ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ቀደም ብለው ያገለሉ ቢሆንም በጭንቅ ሰዓት ማዕከላዊ ኮሚቴውን “ቤታቸው” በማድረግ ከመፍትሄ አፈላላጊዎቹ ዋነኛው እንደነበሩ ምንጮቻችን ይገልፃሉ፡፡ “ህወሓትን ከጀርባ ይዘውሩታል፤” የሚባሉት አቶ ስብሃት የቀድሞዎቹ አመራሮች ወደ ድርጅቱ ይመለሱ የሚለውን ሐሳብ ማራመድ መጀመራቸው ለጉዳዩ ክብደት እንድንቸረው ያደርገናል፡፡ አቦይ ስብሃት በቅርቡ ለ “ኢቲዮ ምህዳር” ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ ከህወሓት የወጡት ሰዎች የአካሄድ እንጂ የፕሮግራም ልዩነት ከህወሓት ጋር እንደሌላቸው መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ የአቦይን “ወንድሞቻችን ይመለሱ፤” የሚል ሀሳብ በጽኑ የተቃወሙ ደግሞ በአቦይ ፀሐዬ ዙሪያ መሰለፋቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ ቡድን በቅርቡ በመቀሌ ባደረገው ስብሰባ የህወሓትን መካከለኛና ዝቅተኛ አባላት በመሰባሰብ የእነ ስብሀትን ሐሳብ ለማንኳሰስ ቢጥርም ተሰብሳቢው ሰዎቹ የተጣሉት ከእናንተ ጋር እንጂ ከእኛ ጋር ባለመሆኑ ወደ ድርጅቱ መመለስ ይኖርባቸዋል” የሚል ምላሽ ማግኘቱ ተሰምቷል፡፡ በእነ አባይ ወልዱ ይደገፋል የተባለው ቡድን ለተወሰኑ የድርጅቱ ተፅእኖ ፈጣሪ አመራሮችና አባላት በተነው በተባለው ወረቀትም ከድርጅቱ የተሰናበቱ ሰዎች በየትኛውም መንገድ ወደ “እናት” ድርጅታቸው መመለስ እንደማይገባቸው አጽንኦት በመስጠት አባላቱ “በመለስ መንገድ” ድርጅቱን ለማዳን እንዲንቀሳቀሱ ጠይቋል፡፡
የቀድሞዎቹን የህወሓት ታጋዮች ወደ ድርጅታቸው የመመለስ እንቅስቃሴ መለስ አልጋ ላይ መዋላቸው ከተነገረባት ቅጽበት አንስቶ ውስጥ ውስጡን በአቶ ስብሃት ነጋ አማካኝነት ስካሄድ እንደነበረ የሚጠቅሱ ምንጮች ይህንኑ እንቅስቃሴ ለማኮላሸት በማሰብ አንደኛው ቡድን(የእነ አቶ አባይወልዱ መሆኑ ነው) ለህዝብ ይፋ ሳይደረግ የቆየውን እነ ስዬ አብርሃ መለስ ይመራት የነበረውን ስብሰባ ረግጠው ሲወጡ የሚያሳይ ቪዲዮ በዩቲዩቡ አማካኝነት መልቀቃቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በቪዲዮው ላይ መለስ ድርጅቱን ለማዳን ቀሪዎቹ አባላት ጠንክረው እንዲሰሩ ለማፀኑ ይታያሉ፡፡
ህወሓት በመጪው የካቲት 11 የምስረታ በሚሉን ያከብራል የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤም በዚህ ወቅት ይደረጋል፡፡ አሁን የተለኮሰው የልዩነት እሳት በክብረ በአሉና በስብሰባው ወቅት ጥርስና እግር ተበጅቶለት አካል ሠርቶ ሊታይ እንደሚቻል የሚተነብዩ ብዙዎች ናቸው፡፡ እስከዛው ግን ሁሉን ነገር ምስጢር በማድረግ ማቆየት የሚፈልገው ህወሓትን የሚያፈተልኩ መረጃዎችን ከዳር ሆነን መቃረማችንን እንቀጥላለን፡፡

fnotenetsanet 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: