33ቱ ፓርቲዎች ቀጣይ እርምጃ ምንመሆን ይገባዋል?

ነብዩ ኃይሉ

 

ህዳር 4 በወጣችው ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ላይ “ምርጫ ለለውጥ ወይስ ከአምባገነኖች ጋር ለመደነስ?” በሚል ርዕስ ሀቀኞቹ ተቃዋሚዎች ውጤቱ አስቀድሞ ወደታወቀ ምርጫ ከመግባት እንዲቆጠቡ በማሳሰብ፤ ለአንድ ምርጫ ውጤታማነት የሚያስፈልጉ መሰረታዊ የሆኑ የቅድመ ምርጫ መደላድሎች (ለመራጮች ትምህርት የሚሰጡ ጠንካራ የሲቪክ ማህበራት መኖር፣ ለውድድር የሚቀርቡት ተፎካካሪዎች የምርጫ ቅስቀሳ የሚያደርጉበትና ህዝባዊ ስብሰባዎችን የሚያደራጁባቸው ሁኔታዎች ምቹ መሆን፣ አድሏዊ ያልሆነ የመገናኛ ብዙሀን አጠቃቀም መኖር፣ ግልፅነትና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን የምርጫ አስፈፃሚ አካልና ስርአት መኖር እንዲሁም በምርጫው ላይ የሚፈጠሩ ቅሬታዎችንና አለመግባባቶችን ያለአድሎ መፍታት የሚያስችል አካልና ስርአት) እንዲፈጠሩ መንግስት ላይ ጫና ማድረግ እንደሚገባቸው ጽፌ ነበር፡፡ ከወራት በኋላ 33ቱ የአዳማ ፔቲሽን ፈራሚ ፓርቲዎች ምርጫው ለሁሉም ወገን ምቹ እንዲሆን፣ ምርጫ ቦርድና መንግስት ሊመልሷቸው ይገባሉ ያሏቸው ባለ 12 ነጥብ ጥያቄዎች ባለመመለሳቸው በምርጫው እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ጽሁፌ ደግሞ ከምርጫ መውጣት ብቻውን መፍትሔ እንዳልሆነና ፓርቲዎቹ ጥያቄዎቻቸው ተመልሰው ዳግም ምርጫ እንዲጠራ በገዢው ቡድን ላይ በተለያዩ ሰላማዊ ተቃውሞዎች ጫና ማድረግ እንደሚገባ ለመጠቆም እሞክራለሁ፡፡

እንደ ኢህአዴግ ያሉ አምባገነን መንግስታት ምርጫን የህዝብን ሉአላዊ የስልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ እንደማይጠቀሙበት የታወቀነው፡፡ በመሆኑም ስልጣናቸውን በማያሳጣቸው አግባብ ለወጉ ያክል የውሸት ምርጫ እንዲካሄድ ያደርጋሉ፡፡ ኢህአዴግም የስልጣን ሽግግር የማይደረግበት የፌዝ ምርጫ በማድረግ የሚስተካከለው የለም፡፡

በመሰረቱ 33ቱ ፓርቲዎች በፌዝ ምርጫ ላለመሳተፍ ያስተላለፉት ውሳኔ ትክክለኛ ነው፡፡ የፓርቲዎቹን ከምርጫ መውጣት ተከትሎ፣ በምርጫው እስከአሁን ከኢህአዴግ ውጪ አንድም ፓርቲ ዕጩ አለማስመዝገቡና አብዛኛው ህዝብ በግዳጅ የምርጫ ካርድ እንዲወስድ መገደዱ በዚህም ከፍተኛ ቅሬታ መፈጠሩ፣ ምርጫው ኢህአዴግ ብቻውን የሚሮጥበት እንደሆነ ያሳየበት ነው፡፡ ይህም ምርጫው ከአሁኑ ቅቡልነት(legitimacy) እያጣ ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ እጅግ ያሳሰበው ኢህአዴግ በጽ/ቤት ኃላፊውና የምርጫ ኮሚቴው ሰብሳቢ በሆኑት አቶ ሬድዋን ሁሴን በኩል አነጋጋሪ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶ ነበር፡፡ በዚህ መግለጫው በምርጫው አንሳተፍም ያሉትን 33ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከመተቸት አልፈው ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ በምርጫው ተሳተፉ አልተሳተፉ የሚጨምሩትም፤ የሚቀንሱትም ነገር የለም የሚል ኃይለቃል ሰንዝረዋል፡፡

ይህ የሰውየው ንግግር የኢህአዴግን ዕብሪት አጉልቶ ያሳየ ይመስለኛል፤ ፓርቲው ባለፉት 21 አመታት ራሱን በሀገሪቱ ጉዳይላይ አድራጊ ፈጣሪ በማድረግ በሀይል ሰይሟል፡፡ ሌሎች ፓርቲዎችም ሆኑ በሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል አካልን ፋይዳ ቢስነት በአደባባይ በዕብሪት በማናናቅ ይጠመዳል፡፡ ሆኖም ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ተጠናክረው ሲመጡ ጨዋታውን ይቀይረዋል፤ ፓርቲዎቹን በህገወጥነትና መክሰስ፣ ህዝባዊ መሰረታቸው ካስፈራው ደግሞ ወደ ድርድር መሳብ ይጀምራል፡፡

ይህ የሚያሳየን የኢህአዴግና የባለስልጣናቱ የዕብሪት መግለጫዎች የተፎካካሪዎቻቸው የማስገደድና ተፅእኖ የማሳደር አቅም ላይ የተመሰረተ መሆኑን ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቁርጠኛ ሆነው በህብረት መቆም ከቻሉ ያለጥርጥር ኢህአዴግን ማስገደድ ይችላሉ፡፡ በአዳማ የተፈጠረው የ33 ፓርቲዎች መሰባሰብ ደግሞ አንድነቱ ተጠብቆ እስከዘለቀ ድረስ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ፓርቲዎቹ ካወጧቸው መግለጫዎች መረዳት እንደሚቻለው፣ ፓርቲዎቹ ራሳቸውን ከምርጫው አግልለው መቀመጥን የመረጡ አይመስሉም፡፡ ይልቁኑም ህዝቡ በፌዝ ምርጫዎች እንዳይሳተፍ ጥሪዎችን በማስተላለፍ፣ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ለመጥራት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡

በእስካሁኑ ተሞክሮ እንደታየው ግን አምባገነኑ የኢህአዴግ ስርአት ተቃዋሚዎች እንኳን እንደዚህ አይነቱወግዙፍ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ህዝብን እንዲያወያዩ ይቅርና፣ በውቅታዊ ጉዳዮች ላይም እንዳይወያዩ አዳራሽ እንዳያገኙ መሰናክሎችን ያስቀምጣል፡፡

እነዚህን መሰናክሎች አልፎ ውጤት ላይ ለመድረስ የፓርቲዎቹ ቁርጠኝነትና ህዝቡን ለማነቃነቅ አቅም ወሳኝ ነው፡፡ 33ቱን ፓርቲዎች ከሚያስተባብሩት የኮሚቴ አባላት መረዳት እንደሚቻለው ለጥር 26 ተጠርቶ የነበረው ህዝባዊ ስብሰባ “በአዳራሽ እጦት” ተራዝሟል፡፡ ሁኔታዎች በዚህ እንዳይቀጥሉ ፓርቲዎቹ አማራጫችን ብለው የያዙት ህዝባዊውን ስብሰባዎቹን በየፓርቲዎቹ ጽ/ቤት ውስጥ ማድረግን ነው፡፡ የኢህአዴግ ፍላጎትም ይኸው ይመስለኛል፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከጽ/ቤታቸው ወጥተው ህዝብን እንዲያገኙ አይፈልግምና፡፡

የአዳራሽ ህዝባዊ ስብሰባዎች ይልቅ የአደባባይ ስብሰባዎች የተሸለ ተሳታፊ ለማሳተፍ ያስችላሉ፡፡ ይህም የሚሆነው ስብሰባውን ጉዳዬ ብሎ ከሚመጣው ታዳሚ በተጨማሪ አላፊ አግዳሚውም የስብሰባውን መልዕክት እንዲሰርሰው ማስቻሉ ነው፡፡ በመሆኑም ከትላልቅ አደባባዮች እስከ መንደር ሜዳዎች ተጠቅሞ ህዝብን በቅርበት ማግኘት በአዳራሽ ወይም በፓርቲዎች ጽ/ቤት ከሚደረጉ ስብሰባዎች ይመረጣል፡፡ ከስብሰባዎቹ አስቀድሞ የስብሰባውን አላማ የሚያስረዱ በራሪ ወረቀቶችን በስፋት መበተን፣ እንዲሁም ስብሰባዎቹን በተከታታይ በተለያዩ ቦታዎች ማድረግ መልዕክቱ ህዝቡ ዘንድ እንዲዘልቅና ጥያቄው ህዝባዊ መሰረት እንዲይዝ በማድረግ ረገድ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ፓርቲዎቹ ያቀረቧቸውን መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎች በሚመለከቷቸው መንግስታዊ አካላት አለመመለሳቸውን እንደ አንድ የተቃውሞ ማድረጊያ ነጥብ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም 12ቱ ጥያቄዎች እንዲመለሱ መንግስትን ለማስገደድ፣ ጥያቄዎቹ በሚመለከቷቸው የመንግስት መስሪያቤቶች(በምርጫ ቦርድ፣በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና በፍትህ ሚ/ር) ደጃፍ ላይ በአነስተኛ ቁጥር(በፓርቲ አመራሮችና አባላት) ተጀምሮ ወደ ህዝባዊ ተቃውሞ የሚያድግ እንቅስቃሴ ማድረግ ኢህአዴግ ከዕብሪት እንቅልፉ እንዲነቃና ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ያስገድደዋል፡፡ ይህም 33ቱን ፓርቲዎች ወደ ተፅእኖ ፈጣሪነት ያሸጋግራቸዋል፡፡

fnotenetsanet

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: