የፀረ ሙስና ኮሚሽን ባለስልጣናት ፍርሀት ውስጥ ናቸው

የካቲት ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የፌዴራል የስነምግባርና ጸረ ሙስና ኮምሽን በሐብት ማሳወቅና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 668/2002 መሰረት የመዘገበውን የባለስልጣናት ሐብት ለህዝብ የማሳወቅ ግዴታውን ተከትሎ በቅርቡ ይፋ ለማድረግ ቢያቅድም የኮምሽኑ ባለስልጣናት በፍርሃት ምክንያት ዝምታን መምረጣቸውን የኮሚሽኑ ምንጮች ጠቆሙ፡፡

ኮምሽኑን የሚመሩት የብአዴኑ አባል የቀድሞው የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ሀላፊ አቶ ዓሊ ሱሌይማን ሲሆኑ ይህው ኮምሽን ለአንድ ዓመት ያህል ክፍት የነበረውን የምክትል ኮምሽነርነት ቦታ ባለፈው ወር ማገባደጃ ላይ የደኢህዴን ከፍተኛ ካድሬና የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮምሽነር የነበሩት አቶ ወዶ አጦን እንዲይዙት ተደርጓል፡፡

በኮሚሽኑ ውስጥ በርካታ አዳዳስ ሰዎች እንዲገቡበት ቢደረግም የባለስልጣናት ሐብት ምዝገባን ይፋ የማድረጉ ጉዳይ ግን እስካሁን የሚደፍር አመራር አለመገኘቱን ምንጫችን ገልጸዋል፡፡
ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በፌዴራል ደረጃ የጠ/ሚኒስትሩ፣ የም/ጠ/ሚኒስትሩ፣ የሚኒስትሮች፣ የምኒስትር ዴታዎች ፣የዳኞች፣ የፓርላማ አባላት፣ የዳሬክተሮችና የመሳሰሉት ባለስልጣናት ሐብትና ንብረት ምዝገባ ተካሂዷል።

ኮምሽነር አሊ ከአንድ ወር በፊት በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ቀርበው ሐብታቸውን ያስመዘገቡ ባለስልጣናትን ዝርዝር ሐብት በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ ይሆናል በሚል የተናገሩ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ኮምሽኑ በምን ሁኔታ መረጃውን ይፋ እንደሚያደርግ ግራ ተጋብቶ ቁጭ ብሎአል።

ኮምሽኑ ተጠሪነቱ ለጠ/ሚኒስትሩ ቢሆንም እስካሁን ጠ/ሚኒስትሩ በዚህ ጉዳይ ላይ ቁርጥ ያለ ውሳኔ አልሰጡም፡፡ የአዋጁ ዋና ዓላማ የመንግስትን አሰራር በግልጽና በተጠያቂነት መርህ በመምራት፣የመንግስት ባለስልጣናት ከገቢያቸው በላይ ሐብትና ንብረት እንዳያፈሩ መቆጣጠር አጥፍተው ሲገኙ ለህግ ማቅረብ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በስርዓቱ ውስጥ ባለው ስር የሰደደ ሙስናና ብልሹ አሰራር አንጻር ሒደቱ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ ከጅምሩም ጥያቄ ውስጥ ገብቶ እንደነበር የሚታወስ ነው።

አብዛኞቹ ባለስልጣናት ሀብትና ንብረታቸውን በዘመዶቻቸው ስም ያስያዙ ቢሆንም፣ ኮሚሽኑ የእነዚህን ሰዎች ሀብት ተከታትሎ ከመመዝገብ ተቆጥቧል። ከሁሉም የከበደው ደግሞ በመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ የሚሰሩ የህወሀት ጄኔራሎች በስማቸው በተለያዩ ከተሞች የገነቡዋቸውን ፎቆችና ዘመናዊ ቪላዎች እንዲሁም በቤተሰቦቻቸው እና በዘመዶቻቸው ስም የየዙትን የቢዝነስ ኢምፓየር ኮሚሽኑ ለመመዝገብ አለመቻሉ ጥርስ አልባ አድርጎታል። ኢሳት የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አዛዦች በአገሪቱ ውስጥ የሚሰሩትን ዋና ዋና ዘመናዊ ህንጻዎች መቆጣጠራቸውን የጄኔራል ወዲ አሸብርን 55 ሚሊዮን ብር የሚፈጀውን በአለ አራት ፎቅ ህንጻ ፣ 30 ሚሊዮን ብር የወጣበትን የኮሎኔል ታደለን እና 45 ሚሊዮን የወጣበትን የጄኔራል ዮሀንስን ህንጻዎች እንዲሁም ብቸኛው የኦሮሞ ተወላጁ የጄ/ል ባጫ ደበሌን 12 ሚሊየን ብር የፈጀ ህንጻዎች በፎቶግራፍ አስደግፎ ማውጣቱ ይታወሳል።

ጉዳዩን በቅርበት ከሚከታተሉት ኢንጂነሮች ለኢሳት እንደገለጡት በቦሌ መድሀኒአለም ፊት ለፊት እና በቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጎን የሚሰሩት ከ4ኛ ፎቅ ጀምሮ ያሉት ህንጻዎች ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት በህወሀት ጄኔራሎች ስም፣ ወይም በቤተሰቦቻቸው የሚሰሩ ናቸው።

ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ በየአመቱ ከኢትዮጵያ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እየተዘረፈ እንደሚወጣ በተደጋጋሚ ሪፖርት ቢያደርግም ጸረ ሙስና ኮሚሽን አንድም ቃል ተናግሮ አያውቅም። የህወሀት ኩባንያዎች በመንግስት ከለላ የአገሪቱን ሀብት እንደሚዘርፉ በተደጋጋሚ ጥቆማ የደረሰው ጸረሙስና ሰምቶ እንዳልሰማ መሆንን መርጧል።

ወ/ሮ እንወይ ገ/መድህን ኮሚሽኑን አጠናክራለሁ ብለው በመነሳት በተወሰኑ ባለስልጣናት ላይ ምርመራ ከጀመሩ በሁዋላ በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ትእዛዝ ከሀላፊነት እንዲወርዱ መደረጉ ይታወሳል።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: