‹‹ውጭ አገር ካሉት ወንድሞቻችን ጋራ እርቀ ሰላም ማድረጉ አሁንም ይቀጥላል›› ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስድስተኛው ፓትርያርክ ሆነው ባለፈው ሐሙስ የተመረጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በውጭ አገር ካሉት ጳጳሳት ጋራ እርቀ ሰላም ማድረጉ አሁንም ይቀጥላል አሉ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን ለማገልገል፣ ለማስተማር፣ ፍቅርና አንድነትን ለማጠናከርም ተግተው እንደሚቀጥሉበት አስታውቀዋል፡፡ 

በጠቅላይ ቤት ክህነት አዳራሽ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም. በተደረገው የስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ከፍተኛውን 500 ድምፅ በማግኘት የተመረጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ከምርጫው ፍፃሜ በኋላ በተለይ ለሪፖርተር በሰጡት ቃለ ምልልስ አሜሪካ ከሚገኙትና ከአራተኛው ፓትርያርክ ጋር ሆነው ከተለዩት ጳጳሳት ጋር ንግግሩ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ 

‹‹ከአሁን ቀደም እርቁ ተሞክሯል፡፡ ውጭ አገር ካሉት ወንድሞቻችን ጋራ እርቀ ሰላም ለማድረግ በተደጋጋሚ ተሞክሯል፡፡ አሁንም ቢሆን ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው መሠረት ይቀጥላል፤›› ብለዋል፡፡ 

የቤተ ክርስቲያኒቱ ዓለም አቀፍ ግንኙነትም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በጀመሩት መንገድ እንደሚቀጥሉ እምነታቸውና ተስፋቸው መሆኑን የገለጹት አቡነ ማትያስ፣ ‹‹በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ይዞታ በሆነው ዴር ሡልጣን ገዳም ከግብፅ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያለውንና ከ1770 ዓ.ም. ጀምሮ ሥር የሰደደውን ችግር ለመፍታት፣ ከግብፅ ሲኖዶስ ጋር ተደርጎ የማያውቀውን ድርድር ከእነርሱ ጋር በመነጋገር መፍትሔ ለማምጣት እንጠይቃለን፤›› ብለዋል፡፡ 

ብፁዕ አቡነ ማትያስ ስድስተኛው ፓትርያርክ ሆነው መመረጣቸውን የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ካበሰሩ በኋላ ‹‹ሥራው ከባድ ቢሆንም ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከካህናትና ከምዕመናን ጋር አብረን ስለምንሠራ ሥራው የቀለለ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፤›› በማለት ንግግር ያደረጉት ተመራጩ ፓትርያርክ፣ በልዑል እግዚአብሔር ዕርዳታ የቤተ ክርስቲያኒቱን ምዕመናን ለማገልገል፣ ለማስተማርና ፍቅር አንድነትን ለመመሥረት ከምንጊዜው በበለጠ እንደሚተጉ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ የኾኑትን ሁሉ መሥራት እንደሚቀጥሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ 

‹‹ለአፍሪካና ለኢትዮጵያ መልካም እረኛ እንዲሰጥ ለመፀለይና ለመምረጥ ነው የመጣነው፤›› ያሉትን የግብፅ አምስት ሊቃነ ጳጳሳት ጨምሮ ድምፅ ከሰጡት 806 መራጮች 500 ድምፅ በማግኘት ሲመረጡ፣ ሌሎቹ አራቱ ዕጩዎች አቡነ ዮሴፍ፣ አቡነ ማቴዎስ፣ አቡነ ሕዝቅኤልና አቡነ ኤልሳዕ በቅደም ተከተል 98፣ 98፣ 70 እና 39 ድምፅ ማግኘታቸውን፣ አንድ የድምፅ መስጫ ወረቀት ባዶ በመሆኑ መጣሉን የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢው ይፋ አድርገዋል፡፡ 

በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ የኾኑት አቡነ ማትያስ ከ30 ዓመታት በላይ በውጭ አገር በመኖር ቤተ ክርስቲያኒቱን ሲያገለግሉ ኖረዋል፡፡ በ1934 ዓ.ም. በቀድሞው አጠራር በትግራይ ጠቅላይ ግዛት አጋሜ አውራጃ በስቡሕ ሳፅሲዕ ወረዳ ከአባታቸው አቶ ወልደ ጊዮርጊስ ከእናታቸው ከወይዘሮ ከለላ የተወለዱት አቡነ ማትያስ፣ የመጀመርያ መጠርያቸው አባ ተክለ ማርያም አሥራት ነበር፡፡ እንደ ወላጅ አባታቸው ሆነው የተጠሩባቸው ማዕርገ ምንኩስና የተቀበሉበት ጭኸ ገዳም አበምኔት መምህር አሥራተ ጽዮን ናቸው፡፡

ገጸ ታሪካቸው እንደሚያወሳው፣ በትግራይ ተምቤን አውራጃ በሚገኘው ጭክ ኪዳነ ምሕረት ገዳም፣ በአክሱም ቅዱስ ያሬድ መንፈሳዊ ትምህርት ቤትና የጎንደር ከፍተኛ የነገረ መለኮት ተቋም (የታላቁ ሊቅ አራት አይና ይባሉ ከነበሩትና የመጀመርያው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የዶክተርነት ማዕርግ የተሰጣቸው የአለቃ አየለ ጉባዔ ቤት) የነገረ መለኮት፣ የትርጓሜ መጻሕፍት፣ መዝገበ ቅዳሴና ቅኔ ባሕረ ሐሳብን አጠናቀው የተመረቁት አቡነ ማትያስ፣ በ1968 ዓ.ም. ሦስተኛው ፓትርያርክ ሆነው ለተመረጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አቡነ ቀሲስ (ልዩ ጸሐፊ) በመሆን ሠርተዋል፡፡ በ1971 ዓ.ም. የጵጵስና ማዕረግ ካገኙ በኋላ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ለሦስት ዓመት ካገለገሉ በኋላ ወደ አሜሪካ በመሻገር በሊቀ ጳጳስነት መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ በ1999 ዓ.ም. ዳግመኛ ወደ ኢየሩሳሌም በመመለስ ፓትርያርክ እስከሆኑበት ዕለት ድረስ አገልግለዋል፡፡ 

ከአማርኛና ከትግርኛ ቋንቋዎች በተጨማሪ እንግሊዝኛ፣ ዕብራይስጥ (ሂብሩ)፣ ግሪክና ዓረቢኛ ቋንቋዎች የሚያውቁት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በዓለ ሲመት እሑድ የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም. በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል፡፡ 

በበዓለ ሲመቱ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ጳውሎስ ዳግማዊ የህንድ ፓትርያርክና የምሥራቅ አህጉር ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ በብፁዕ አቡነ ጳኩሚስ መሪነት በምርጫው ላይ የተገኙትና ድምፅ የሰጡት የግብፅ ኦርቶዶክስ ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም የእኅት አብያተ ክርስቲያናት ሊቃነ ጳጳሳት እንደሚገኙ ከመንበረ ፓትርያርክ የውጭ ግንኙነት መምርያ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ የእሑዱን በዓለ ሲመት የኮፕቲክ ቴሌቪዥን (ሲቲቪ) በቀጥታ ሥርጭት እንደሚያስተላልፈውም ታውቋል፡፡ 

የመጀመርያውን ፓትርያርኳን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስን በ1951 ዓ.ም. የመረጠችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን፣ ባለፉት 53 ዓመታት አምስት ፓትርያርኮች ብፁዓን ወቅዱሳን አቡናት ባስልዮስ፣ ቴዎፍሎስ፣ ተክለ ሃይማኖት፣ መርቆሬዎስ  የመሯት ሲሆን፣ አምስተኛው ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ (1928-2004) በመንበሩ ላይ 20 ዓመት (1984-2004) ከቆዩ በኋላ ያረፉት ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. እንደነበረ ይታወሳል፡፡

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስድስተኛ ፓትርያርክ ሆነው በመመረጣቸው የተሰማውን ደስታ ገልጿል፡፡ 

ቤተ ክርስቲያኒቱ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር እንደከዚህ በፊቱ በመንፈሳዊና በልማት ሥራዎች በቅርበት በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን ገልጾ፣ ከዚህ በፊት የነበሩት ፓርትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመን በአገሪቱ በሃይማኖቶች መካከል የነበረውን መልካም ግንኙነትም በአዲሱ ፓትርያርክ ዘመን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሙሉ እምነቷ መሆኑን ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳስ ዘካቶሊካውያን የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ጉባዔ ፕሬዚዳንት በላኩት የደስታ መግለጫ ገልጸዋል፡፡

Ethiopian Reporter

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: