ኢህአዴግ እንደ ድርጅት አንድ ሆኖ መውጣት ተስኖታል ተባለ

የካቲት ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የውስጥ ሽኩቻ መበራከት የተነሳ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት አንድ ሆኖ መውጣት እንደተሳነው የሚያመለክቱ መረጃዎች እየወጡ ነው።

በህወሀት ውስጥ ሁለት ቡድኖች ድርጅቱን ለመቆጣጠር እንቅስቃሴ መጀመራቸው ከተዘገባ ከወራት በሁዋላ ችግሩ ከመቃለል ይልቅ እየጨመረ መምጣቱን አንድ የቀድሞ የህወሀት ነባር ታጋይ ለኢሳት ዘጋቢ ገልጸዋል።

ነባር ታጋዩ፤ በአቶ ስብሀት ነጋ በኩል ባሉ ሰዎች ወደ ድርጅቱ እንዲመለሱ ጥሪ ቀርቦላቸው እንደነበር ጠቅሰው፤  እርሳቸው ግን አሻፈረኝ ማለታቸውን ገልጸዋል።

 በድርጅቱ ውስጥ የሚታየው ክፍተት ለአደባባይ ባይበቃም፣ ህዝቡ የሚያየውና  እየተነጋገረበት ያለ ጉዳይ መሆኑን ነባር ታጋዩ ገልጸዋል።

በኦህዴድ በኩል ከአቶ መለስ ዜናዊ ሞት በሁዋላ የታየው ክፍተትም እየሰፋ እንጅ እየጠበበ ሲሄድ አለመታየቱ ነው የተገለጸው።

ከአንድ ወር በፊት የጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት በድርጅቱ ውስጥ የሚታየው ሙስና እና ጎሳዊነት እንደጨመረና ድርጅቱንም አደጋ ላይ እንደጣለ አንዳንድ የምክር ቤቱ ተወካዮች ቢናገሩም፣ ምክር ቤቱ በስፋት እንዳይወያይበት መደረጉን በወቅቱ መዘገባችን ይታወሳል።

 በተለይም በከፍተኛ ህመም የሚሰቃዩትን ፕሬዚዳንቱን አቶ አለማየሁ አቶምሳን ለመተካት ቢፈለግም፣ በእርሳቸውና በአፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ ደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ሌላ ፕሬዚዳንት ለመሾም ሳይቻል በመቅረቱ አቶ አለማየሁ  በስልጣን  ላይ እንዲቆዩ ተደርጓል።

በኦህአዴድ ስራ አስፈጻሚዎች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ተባብሶ በዞን ደረጃ ያሉ ስራ አስፈጻሚዎች ሳይቀሩ እንደተከፋፈሉና አጠቃላይ ድርጅቱ ወደ ሞት እያመራ እንደሆነ መዘገባችን አይዘነጋም።

ሪፖርተር  ዛሬ ባወጣው ዘገባ ደግሞ ኦህዴድ የካቲት 20 ቀን 2005 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔውን ለማድረግ የተሰበሰበ ቢሆንም ፤ያልተጠበቁ አጀንዳዎች በመቅረባቸው ፤ ለኢሕአዴግ በሚቀርበው የሁለት ዓመታት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ብቻ በመወያየት ጉባዔውን ለሚቀጥለው ሳምንት አስተላልፎአል።

የ ኦህዴድ አባላት፤ ድርጅታቸው የተለያዩ ችግሮች ስላሉበት ጉዳዩ  በአጀንዳ ተይዞ ውይይት እንዲደረግበት ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ፣ የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ሰብሳቢዎች በድጋሚ ሌላ ስብሰባ እንደሚደረግና በዚያ ስብሰባ ላይ <<አሉ>> የተባሉ ችግሮችን በማንሳት መወያየትና መፍታት እንደሚቻል ቢናገሩም፣ ስምምነት ላይ አልተደረሰም ብሎአል- ጋዜጣው።

አባለቱ፤ ችግሩ የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ደጋግመው በመግለጽ ራሱን የቻለ አጀንዳ ተይዞለት ውይይት እንዲደረግበት ቢጠይቁም፣ እንዲሁም የተወሰኑ አባላት ድርጅቱ በሁለት ዓመታት ውስጥ ባከናወናቸው ሪፖርት ውስጥ የተነሳው ጥያቄ ተካቶ አንድ ላይ እንዲታይ ሐሳብ ቢያቀርቡም ፤ስምምነት ላይ ስላልተደረሰ ነው ጉባዔው እንዲተላለፍ የተደረገው።

ሥራ አስፈጻሚው፤ ለኢሕአዴግ በሚያቀርበው የሁለት ዓመታት ሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ሲወያይ በዋናነት ያነሳቸው ችግሮች፣ በድርጅቱ ውስጥ የአመራር ችግር መኖሩን፣ እንደ ድርጅቱ ሳይሆን በግል የመጠቃቀም ሁኔታ መባባሱን፣ ለሥልጣን መሯሯጥ መስተዋሉን፣ ድርጅት ሳይመክርበት የፍርድ ቤት ሹማምንት ከኃላፊነት እንደሚነሱ መደረጋቸውን እና የግለሰቦች አምባገነንነት መንገሱን  የሚመለከቱ ናቸው።

አባላቱ በችግሮቹ ዙሪያ ከተወያዩ በኋላ፣  የተፈፀሙት ድርጊቶች ተገቢ እንዳልሆኑ መተማመናቸውን ጋዜጣው አክሎ ዘግቧል።

ከዚህም ባሻገር የኦህዴድ ስራ አስፈጻሚ አባል የነበሩት አቶ ጁነዲን ሳዶ ከድርጅት ተባረው አገር ጥለው መጥፋታቸው እንዲሁም በድርጅቱ ውስጥ በርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮች መንግስት የሚከተለውን ፖሊሲ መቃወም መጀመራቸው በኦህዴድ ብቻ ሳይሆን በኢህአዴግም ውስጥ ትልቅ ራስ ምታት ፈጥሯል ተብሏል።

ለኢሳት ቅርበት ያላቸው የኢህአዴግ  ሰዎች እንደገለጡት፣ በርካታ የኢህአዴግ በተለይም የኦህዴድ አባላት ሙስሊም ኢትዮጵያውያን የጀመሩትን እንቅስቃሴ ከመደገፍ አልፈው በተለያዩ መንገዶች አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው።

በኢህአዴግ ውስጥ የሚታየው ልዩነት ያሳሰበው ሪፖርተር  ጋዜጣ ዛሬ በርእሰ አንቀጹ ድርጅቱ በመጪው ጉባኤ አንድ ሆኖ በመውጣት ለአገሪቱ የተጠናከረ አመራር እንዲሰጥ ተማጽኗል።  

ጋዜጣው ” ሁኔታዎች እየከበዱና እየተካበዱ ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም በአገር ደረጃም የኢኮኖሚው ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡ ምንም እንኳ አሁንም በኢትዮጵያ ከፍተኛ ዕድገት ለማስመዝገብ የሚያስችል አመቺ ሁኔታ ቢኖርም፤የውጭ ምንዛሪ እጥረትን፣ ግሽበትንና የኑሮ ውድነት ችግሮችን ለመፍታት እንዲሁም፤ ለተጀመሩና ለታቀዱ ዓበይት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ በቂ ገንዘብ አግኝቶ መተግበር ትልቅ ፈተና ነው” ብሏል።

  የመልካም አስተዳደር መጥፋት፣ የአቤቱታ ብዛትና የሰሚ እጦት እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱንም አልሸሸገም።

ጋዜጣው አያይዞም፦ ” መጪው የኢህአዴግ ጉባኤ ጠንካራ ኢሕአዴግና ጠንካራ መንግሥት ፈጥሮ፤ ጠንካራ መፍትሔ በመስጠት እንደ አንድ ኩሩ ሕዝብ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንቀጥል ማድረግ  ይጠበቅበታል ፣ህዝብም ጠንካራ ኢሕአዴግ ከጉባዔው እውን እንዲሆን ይጠብቃል” ብሎአል።

በሌላ በኩል ደግሞ በአገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች የኢህአዴግን መዳከም በመጠቀም ወደ አንድነት ጎዳና በማምራት ለለውጥ መስራት እንዳለባቸው ከተለያዩ ወገኖች ጥሪ እየቀረበ ነው።

 በቅርቡ በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች በተካሄደ የኢሳት ገቢ ማሰባሰብ ዝግጅት ላይ የተገኙ ኢትዮጵያውያን፤ ኢሳት ሁሉንም ተቃዋሚዎች በአንድ ጉባኤ በመጥራት አብረው እንዲሰሩ ግፊት እንዲያደርግ ተማጽነዋል። 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: