የደብረ ማርቆስ ህዝብ በውሃ እጥረት ተማሯል

“የኤሌክትሪክ ሃይል እጥረትና መቆራረጥ ለችግሩ መንስኤ ነው” – የመጠጥ ውሃ ፅ/ቤት “በቂ ሃይል አቅርበንላቸዋል” – መብራት ኃይል አለማየሁ አንበሴ የደብረ ማርቆስ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፍላጐትን ያለ ችግር ለ20 አመታት ያሟላል ተብሎ በ80 ሚሊዮን ብር የተገነባው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በመበላሸቱ የከተማዋ ነዋሪዎች ለውሃ እጦት መዳረጋቸውን ገለፁ፡፡ ችግሩ ለሁለት ወራት ዘልቋል። ቅሬታቸውን ለዝግጅት ክፍላችን ያቀረቡ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት፤ ከሁለት ወራት በፊት ጀምሮ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን ውሃ ፍለጋ ከሁለት እና ከሶስት ሠአታት በላይ ወደ ገጠር አካባቢዎች በመጓዝ የምንጭ ውሃ ለመጠቀም መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ ሆቴል እና ሬስቶራንት የመሣሠሉ አገልግሎት ሠጪ የንግድ ተቋማትም በእለት ተእለት ስራቸው ላይ የውሃ ችግሩ ተፅዕኖ እንዳሣረፈባቸው ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት የከተማዋን ህዝብ የውሃ ፍላጐት ለ20 አመታት ያለ ችግር ያሟላል ተብሎ በ2002 ዓ.ም በደማቅ ስነ ስርአት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለብልሽት መዳረጉ እንዳሣዘናቸው የሚገልፁት ቅሬታ አቅራቢዎች፤ በተለይ በአገልግሎት መስጫ ማዕከሉ የሚገኙትን ሞተሮች የሚያንቀሣቅሡ ሙያተኞች ላይ የብቃት ማነስ መኖሩ ለችግሩ በምክንያትነት ሊጠቀስ እንደሚችል አመልክተዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ከተማ የመጠጥ ውሃና ፍሣሽ አገልግሎት ፅ/ቤት ስራ አስከያጅ አቶ መልሣቸው ደመላሽ በበኩላቸው፤ የከተማዋ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በ2002 ዓ.ም ለ80ሺህ የከተማዋ ነዋሪዎች አገልግሎት እንዲሠጥ ታስቦ መገንባቱን በማስታወስ፤ ከታህሣሥ 26 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ በሞተር ክፍሉ ላይ በደረሠበት ጉዳት ሣቢያ ለብልሽት መዳረጉን አስታውቀዋል፡፡

ለሞተር ክፍሉ መበላሸት መንስኤ ሆኖ በባለሙያዎች የተቀመጠውም በከተማዋ የመብራት መቆራረጥ ችግር መኖሩ እና በቂ የሆነ ሞተሩን ማንቀሣቀስ የሚችል የኤሌክትሪክ ሃይል አለመኖሩ መሆኑን ሃላፊው ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል፡፡ ይህን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ አሁን ከ45 ቀናት በፊት ተገዝተው ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገቡ ከታዘዙት አዳዲስ ሞተሮች ጋር አብሮ ቮልቴጅ ሬጉሌተር የተባለ መሣሪያ ለማስገጠምና የሃይል መብዛት ማነሱን ለመቆጣጠር ፅ/ቤቱ ማቀዱን አቶ መልሣቸው አስታውቀዋል፡፡ በ1.1 ሚሊዮን ብር ወጪ ከውጭ ሃገር እንዲገዙ የታዘዙት ሞተሮችም እየተጠበቁ መሆኑን ያመለከቱት አቶ መልሣቸው፤ ከዚህ ጐን ለጐን የኤሌክትሪክ ሃይል እጥረትን ለመቅረፍ ከመብራት ሃይል ትብብር እየጠየቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

“በአጠቃላይ ሞተሮቹን ለማንቀሣቀስ 400 ቮልት የኤሌክትክ ሃይል” ያስፈልጋል ያሉት ሃላፊው፤ ከመብራት ሃይል ሲቀርብላቸው የነበረው ግን ከ380 ቮልት በታች እንደነበር ይናገራሉ፡፡ አንዳንድ ቅሬታ አቅራቢዎች የባለሙያ ብቃት ማነስ ለችግሩ መንስኤ ይሆናል ብለው ያቀረቡትን እንደማይስማሙበት የሚናገሩት አቶ መልሣቸው፤ “እኛ ብቁ ባለሙያዎች አሉን፤ የኤሌክትሪክ ኢንጅነር፣ መካኒካል ኢንጂነሮች፣ ኦፕሬተሮችም አሉን፤ እንደውም የተበላሹ ሞተሮችን መልሠው እየገጣጠሙ ያሉት የኛ ባለሙያዎች ናቸው” ብለዋል፡፡

ለጊዜው የህብረተሠቡን የውሃ ችግር ለመፍታት መስሪያ ቤታቸው የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሠድ ላይ መሆኑን ያመለከቱት የስራ ሃላፊው፤ በጊዜያዊ መፍትሄነት በፊት የከተማዋ ማህበረሠብ ሲጠቀምባቸው ከነበሩ የውሃ ጉድጓዶች በሞተር ሃይል በመታገዝ በ12 እና በ13 ቀናት አንዴ በየሠፈሩ ውሃ በፈረቃ እንዲዳረስ ማድረግ ሲሆን ይህንን የፈረቃ ስርጭት ወደ 5 ቀን ለማሣጠር ከተቃጠሉት ሞተሮች መካከል አንደኛውን መልሶ በመጠገን አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ መሆኑንና ለዘለቄታው ሞተሮቹን በሙሉ በአዲስ ለመተካት እንዳሰቡ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ መብራት ሃይል ኮርፖሬሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ምስክር ነጋሽ በበኩላቸው፤ መስሪያ ቤታቸው በ2002 ዓ.ም 10 ሚሊዮን ብር በማውጣት ለቆቦ፣ ለዳንግላ እና ለደብረ ማርቆስ የውሃ ፕሮጀክቶች የሚውል የኤሌክትሪክ ሃይል ማቅረቡን በማስታወስ፣ የሃይል እጥረት ተፈጥሯል የሚባለው ትክክል አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከ260 እስከ 400 ቮልት የሚደርስ ሃይል መስሪያ ቤታቸው ማቅረቡን የጠቆሙት አቶ ምስክር፤ ይህም በባለሙያዎች ተጠንቶ ውሃውን ለመግፋት በቂ መሆኑ እንደተረጋገጠ ጠቁመው የከተማዋ የመጠጥ ውሃ ፅ/ቤቱ “ቮልቴጅ ሬጉሌተር” ባለማስተካከላቸው ችግሩ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡ ኃላፊው አክለውም የመጠጥ ውሃ ፅ/ቤቱ ችግሩን መብራት ሃይል ላይ ማላከኩ ተገቢ አለመሆኑን አስታውቀዋል፡፡

addisadmass.

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: