የተቃዋሚ ድርጅቶች ሰላማዊ ትግል? ወይንስ ሰላማዊ እንቅልፍ?

ባሁኑ ወቅት ሃገራችን ኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በበለጠ ሁኔታ ውሉ የጠፋባቸው የወያኔ አመራሮች በሚያካሂዱት ድንቁርናን መሰረት ያደረገ የግፍ አገዛዝ እየታመሰችና ህዝቧም ከመጠን ያለፉ ሰቆቃና ግፎችን በዝምታ እየተቀበለ ይገኛል:: የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን በተቀራመቱበት ወቅት እንግሊዞችና ጣሊያኖች የዓገዛዝ ስርዓታቸውን ለማቆየትና ግዛታቸውን ለማስፋፋት የወረሩትን ህዝብ እርስበርሱ ማጋጨትንና መከፋፈልን ጨምሮ የተለያዩ የከፋፍለህ ግዛ ስልቶችን ይጠቀሙ እንደነበር ሁሉ ፤ የወያኔ ስርዓትም በሃገራችን ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ስልቶችን በግልፅ ህዝባችን ላይ እየጫነ እንደሆነ እናውቃለን::

ዘረኛው የወያኔ ስርዓት የተለያዩ የከፋፍለህ ግዛ ስልቶችን ከአያቶቹ ጣሊያኖች እንደወረሰ ሁሉ ከትናንሽ የማህበራዊ ስብስቦች እስከ ታላላቅ ማህበራት ፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ከሚገኙ የተማሪዎች ስብስቦች እስከ ታላላቅ የሰራተኛና የመምህራን እንዲሁም ሌሎች ማህበራት ፣ ከግለሰቦች እስከ የሰፈር እድሮች ድረስ ወርዶ ጫና በመፍጠር ህዝቡን ወደማይፈታ የእርስ በእርስ ጥላቻ ለመዝፈቅ ቀን ከሌሊት እየሰራ ይገኛል:: ከዚህም ባለፈ መልኩ የሃገሪቱን ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶችን ከምድረገፅ ለማጥፋት በወጠነው መሰሪ እቅዱ መሰረት በልማት ስም ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ሃብቷን ገዳማትን ፣ ቤተክርስቲያናትንና ፣ መስኪዶችን ጨምሮ እያፈረሰና እያጠፋ ይገኛል:: ይህ በልማት ስም የሚፈፀም የወያኔ መሰሪ እቅድ በሃገሪቱ ቅርስ የማጥፋት ዘመቻ ብቻ ሳይወሰን በአሁኑ ሰአት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ለዘመናት ከኖሩበት ቤት ፣ ንብረታቸውና ፣ ከቀዬአቸው በግፍ አፈናቅሎ የዜግነት ክብራቸውን በማዋረድ በረንዳ ላይ እንዲወድቁ እያስገደደ ይገኛል::

በኢትዮጵያ ሰላምዊ ህዝብ ላይ አሰቃቂ ወንጀሎችን እየፈፀመ የሚገኘው ዘረኛው የወያኔ ቡድን ቢሆንም በሃገራችን የሚታዩት ነባራዊ ሁኔታዎች እንደሚያመላክቱት ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችም ከተጠያቂነት የሚድኑ አይመስልም:: ይህ ነባራዊ ሁኔታ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ውጤት አልባ የሆኑበትን ምክንያት ሊያስብና እየተከተሉ ያሉትን መንገድ ሊመረምር እንዲሁም በተጠያቂነት ሊፈርጃቸው የሚችልበት ወቅት መድረሱን በግልፅ ያመላክታል:: ስለሆነም ይህ ችግር ስር ከመስደዱ በፊት የፖለቲካ ተቃዋሚ ድርጅቶች ከታሪክ ተጠያቂነት እራሳቸውን ለማዳን ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው በጥልቀት ሊሰሩበት ይገባል:: የውጤታማነት መመዘኛው በቁጥር መብዛት ቢሆን ኖሮ ከበቂ በላይ ያሉን ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያስገኙልን ድሎችና ነፃነት ጎተራችንን ሞልቶ በተረፈ ነበር:: ነገር ግን ቁምነገሩ በቁጥር መብዛት ባለመሆኑ እልቆ መሳፍንት የሆኑት ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶቻችን አንዳችም የሚጨበጥ ፋይዳ ማስገኘት ተስኗቸው ህዝብም ነፃነትን እንደናፈቀ ይሄው አመታት ተቆጥረዋል::

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደትና ህዝብ ላይ ለደረሱት አደገኛ ችግሮች ምክንያትነት ከወያኔ ቀጥሎ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉት በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን የሚሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው:: በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወያኔ ጥቅም አስከባሪ እንደሆኑ ሁሉ በህዝብ ዘንድ በጥርጣሬ አይን እስከመታየት መድረሳቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው:: እየታገሉ ያሉት ለህዝብ ሳይሆን የፖለቲካ ስልጣን ላይ ለመቀመጥ ብቻ እስኪመስል ድረስ በሃገሪቷ የወያኔ የምርጫ ወቅት በደረሰ ቁጥር ኮሽታ ሳያሰሙ ከተደበቁበት ብቅ በማለት ህዝብ በነርሱ ላይ ያለውን አመኔታ ይበልጥ ሲሸረሽሩት በተደጋጋሚ ይታያሉ::

ሰላማዊ ትግል የብዙ ሚሊዮኖች ህዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎን የሚጠይቅና ከህዝብ ውጪ ሁኖ ሰላማዊ ትግልን መተግበር ፈፅሞ እንደማይቻል ይታወቃል:: ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆነና ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶቻችን ከፍጥረታቸው ጀምሮ በሰላማዊ የትግል ስልት እንታገላለን ብለው ሲለፍፉ እንጂ አንድም ህዝብን ያሳተፈ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ታይተው አይታወቁም:: “ፅድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ” እንዲሉ የተቃዋሚ ድርጅቶች አያሌ አባሎቻቸው መሪዎቻቸውንም ጨምሮ በወያኔ የሃሰት ውንጀላ በየ እስር ቤቱ ውስጥ ታጉረው እየማቀቁ ቢሆኑም ድርጅቶቹ ህዝብን አስተባብረው ጫና በመፍጠር ለማስፈታት ያደረጉት ሙከራ የለም:: ባሁኑ ወቅት ህዝቡ “ሰላማዊ የትግል ስልት መጨረሻው ቃሊቲ ነው” የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ በመያዝና ትግሉን መቀላቀል አሰቃቂ ዋጋ የሚያስከፍል እንደሆነ አምኖ የተቀበለ ይመስላል:: በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ህዝብ ተስፋ ቆርጦና ነገር አለሙን እርግፍ አድርጎ በመተው የወያኔን ግፍ አቅሙ እስከፈቀደለት ድረስ ችሎ

ለማለፍ የወሰነ ይመስላል:: ይህ አደገኛ ሁኔታ የህዝብን ስነልቦና በማኮላሸት በሰላማዊ መንገድ የሚደረግ የህዝብ ትግል በኢትዮጵያ ፈፅሞ የማይታሰብ የቀን ቅዠት እያደረገው ይገኛል::

የወያኔ መንግስት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እያደረሳቸው የሚገኙት አስከፊ በደሎች እንኩአን ለህዝብ ለሚታገሉ የፖለቲካ ተቃዋሚ ድርጅቶች ይቅርና ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ በግልፅ የሚታዩ የቀን ተቀን ትርዒቶች ሆነዋል:: ይህ በእንዲህ እንዳለ ብዙ ጊዜ ከሚያስቆጩ ክስተቶች አንዱ እውነታው ህዝብ እየተሰቃየ፣ እየተበደለ፣እየተጨቆነ፣ ያለአግባብ ቤቱን፣ ቀዬውንና፣ ንብረቱን እየተቀማ ግፉ ስለበዛበት በተናጥል ብሶቱን በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች ሲገልፅ ቢታይም ሃይሉን አስተባብሮ ወደፊት ከመገፋት ይልቅ የህዝብ ንቅናቄዎችና ብሶቶች ተዳፍነው ሲቀሩ ይታያሉ:: ይህም አሳዛኝ ክስተት የህዝብ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንታገላለን የሚሉ የተቃዋሚ ድርጅቶች ምን እየሰሩ ነው? ፤ ህዝብን አስተባብረው ወደሚፈለገው ለውጥ መጓዝ ያልቻሉበት ምክንያት ምንድነው? የሚሉትን ሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎች በማንኛውም ለሃገር ተቆርቋሪ ዜጋ ዘንድ ማጫሩ የግድ ነው::

ስለሆነም የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የመፍትሄው ቀጥተኛ ተሳታፊ የመሆን ታሪካዊ ግዴታው መሆኑን እያሳሰብን የተቃዋሚ ድርጅቶች አመራሮች ይህንና መሰል የህዝብን ቀጥተኛ ተሳትፎ መሰረት ያደረጉ ግልፅ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀትና በመምራት የህዝብ ወገንተኝነታቸውን እንዲያረጋግጡ ስንል በአክብሮት እየጋበዝን ከላይ ለተጠቀሱት ችግሮች የጋራ መፍትሄ ለመፈለግ መነሻ የውይይት ሃሳብ ይሆኑ ዘንድ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እናቀርባለን::

  1. “ሰላማዊ የትግል ስልት መጨረሻው ቃሊቲ ነው” የሚለውንና ሌሎች መሰል የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን በመቅረፍ ትግሉን ወደተሻለ አቅጣጫ ለማሸጋገር ፣ ህዝብ በራስ መተማመንን አጎልብቶ በቁርጠኝነት ለመብቱ በጋራ እንዲቆም ፣ ብሎም ነፃነቱን ተጎናፅፎ እኩልነትንና የህዝብ የበላይነትን በኢትዮጵያ ለማረጋገጥ የትግሉ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆን እንደ ህዝብ የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት ለማስቻል ምን መደረግ አለበት? በዚህ ረገድ የተቃዋሚ ድርጅቶች አካሄድና ሚና ምን መሆን አለበት?

  2. ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ሰላማዊ ትግሉን ከጀመሩ አመታትን አስቆጥረዋል:: ነገር ግን መግለጫዎችን በማውጣት ብቻ ተወስነው ለገዢው አካል የውጪ ዲፕሎማሲያዊ ጥቅም ከማበርከት በስተቀር በተጨባጭ የሚታይ አንዳችም ውጤት አላስገኙም:: በአንፃሩ ደግሞ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በተመሳሳይ ሰላማዊ የትግል ስልት በአጭር ግዜ ውስጥ እጅግ በርካታ ወጤቶችን በተግባር አሳይተውናል:: እነኝህ ድርጅቶች ከሙስሊሙ ትግል ጋር ተመሳሳይ ስልቶችን የሚከተሉ ሆነው ሳሉ ውጤታማ ያልሆኑበት ምክንያት ምንድን ነው? ከሙስሊሙ ሰላማዊ ትግል ምን ሊማሩ ይገባቸዋል?

  3. ባሁኑ ወቅት ወያኔ በህዝብ ላይ ከሚፈፅማቸው በደሎች የተነሳ በሃገራችን የተለያዩ ክልሎች ህዝብ በተደጋጋሚ እምቢተኝነትን እየገለፀ ይገኛል:: ነገር ግን የሚያስተባብረው አካል በማጣቱ ወደፊት ሊገፋበት ሳይችል ብዙ ጊዜ ተዳፍኖ ሲቀር ይታያል:: ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ይህንን የህዝብ እምቢተኝነት አቀናጅተው ወጥ በሆነ መልኩ ከፍ ወዳለ የህዝብ ሰላማዊ ትግል እንዲሸጋገር ከማድረግ ይልቅ ዳር ቆመው ተመልካቾች የሆኑበት ምክንያት ምንድነው? በዚህ ረገድ ወደፊት ምን ማድረግ አለባቸው?

ስምንቶቹ
Email: nleethiopia@gmail.com

 
Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: