ለሞተር ብስክሌቶች አዲስ ምዝገባ!

የካቲት 26 ቀን 2005 ዓ.ም. ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ፣ ከሜክሲኮ አደባባይ ወደ ቄራ በሚወስደው መንገድ ከገነት ሆቴል ወረድ ብሎ፤ ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ ደጃፍ ላይ አካባቢ ጥቂት ሰዎች ተሰባስበው ተመለከትኩ፡፡

ወደ ሳሪስ የሚወስደኝ ታክሲ እየጠበቅኩ ነበርና እግረ መንገዴን ሰዎቹ ወደተሰበሰቡበት ቦታ ጠጋ አልኩ፡፡ ከተሰባሰቡት ሰዎች ሁለቱ ፖሊሶች ናቸው፡፡ አንድ ኮስመን ያለና ዕድሜው በአርባዎቹ መጨረሻ የሚገመት ጎልማሳ፣ በፖሊሶቹ ይጐሸማል፡፡ አንደኛው ፖሊስ እጁን ይዞታል፡፡ ሌላኛው ደግሞ ኮስማናውን ሰውዬ በእጁ ጀርባ ጀርባውን እየመታ ‹‹አውጣ›› ይለዋል፡፡ ጎልማሳው ሰው ግን አንገቱን አቀርቅሮ ለፖሊሱ ጥያቄ መልስ ከመስጠት፤ ዝምታን መርጧል፡፡

የምፈልገው ታክሲ እስኪመጣ ነገሩን ለመመልከት ይበልጥ ተጠጋሁ፡፡ በቦታው ከነበሩ ጥቂት ሰዎች መካከል አንዲት ሴት ‹‹በብስጭት አፉ ውስጥ ከቶታል … አፉ ውስጥ ነው ያለው፤›› ትላለች፡፡ ነገሩ አጓጓኝ፡፡ ፖሊሶቹ ጎልማሳው ሰው አፍ ውስጥ አለ የተባለውን ነገር ለማስተፋት ጥረት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡፡ ጎልማሳው ግን ከአፉ ያወጣው ነገር አልነበረም፡፡ ጥቂት ቆይቶ ግን አንገቱን ቀና አደረገ፡፡ ይሄኔ ወይዘሮዋ ‹‹ዋጠው፣ ዋጠው…›› ብላ ጮኸች፡፡

‹‹አፉ ውስጥ ነው››፤ ‹‹ዋጠው›› የሚለው የሴትዮዋ ንግግር ዘግይተን ቦታው ላይ ለተገኘን ተመልካቾች ግራ ቢያጋባንም እንዲህ ግርግር የፈጠረው ጉዳይ ምን እንደሆነ ለማወቅ ጓጉተናል፡፡ ወይዘሮዋ የምትናገረው ሰውዬው ተከታትሎ ወርቋን እንደነጠቃት፣ መሰረቋን አውቃ ስትጮህም አፉ ውስጥ መክተቱን ነው፡፡ ፖሊሶች ሲይዙት ደግሞ ወደ ጉሮሮው እንደላከው ተናግራለች፡፡ ተፈጠረ የተባለው ድርጊት በቦታው የነበርነውን ሰዎች አስገርሟል፡፡ አስደንግጧል፡፡ የግርግሩን ምክንያት ካወቅሁ በኋላ ተፈጸመ የተባለው ድርጊት ትክክል መሆን አለመሆኑን ሳላውቅ፣ መጨረሻውንም ሳላይ ወደ ሳሪስ የሚሄድ ታክሲ መጣና ነገሩን ስንመለከት ከነበረን ሰዎች ሁለታችን ተሳፈርን፡፡

በታክሲ ውስጥ የነበሩ ተሳታፊዎች ግርግሩን ተመልክተው ኖሮ ምን ተፈጥሮ እንደሆነ ጠየቁን፡፡ አብሮኝ የተሳፈረው ሰው ተደረገ የተባለውንና የሰማውን ተናገረ፡፡ አጀብ ተባለ፡፡ ‹‹ደግሞ እንዲህ ማድረግ ተጀመረ?›› ‹‹ከዋጠው በኋላ ምን ሊያደርገው ነውና?›› የሚሉና ሌሎች ብዙ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው የተሳፋሪው መነጋገሪያ ሆነ፡፡ ስለስርቆትና ሌብነት ሁሉም የመሰለውን አስተያየት እየሰጠ፣ አንዳንዱም ገጠመኙን እያወጋ ሳሪስ ደረስን፡፡ ወርቅ ሰርቆ ውጧል የተባለው ጐልማሳ ድርጊት፣ ከስርቆት ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ወንጀሎች መልካቸውን እየቀየሩ መምጣታቸውን የሚያመለክት ነው፡፡ በዕለቱ ተፈጸመ የተባለውን ዓይነት ስርቆት ከዚህ በፊት ያለመስማቴም በነገሩ እንድገረም አድርጐኛል፡፡ ገጠመኜ እንዳለ ሆኖ ሰሞኑን የምንሰማው ሌላ የወንጀል ድርጊትም የስርቆት ዓይነቶች በአስገራሚ ሁኔታ እየተለወጡ መምጣታቸውን ያመላከተኝ ነው፡፡

ይኸውም በሞተር ብስክሌት አማካይነት እየተፈጸመ ያለው ሥርቆት ነው፡፡ የመዲናችን፣ አዲስ ዓይነት የወንጀል አፈጻጸም ዘዴ ሆኖ ብቅ ያለው ይህ የስርቆትና የነጠቃ ወንጀል፤ በጠራራ ፀሐይ የሚፈጸም መሆኑ ደግሞ የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ አገር ሰላም ብሎ የሚጓዝ መንገደኛ በእጁ ያንጠለጠለው ቦርሳ በሞተረኛ ሌቦች ተነጥቆ በቅፅበት እብስ ሲሉበት ጮኾ እንኳ ለማስያዝ አይችልም፡፡ ቦርሳዋን ያነገተች ጉብል በፍጥነት በሚከንፍ ሞተር ጋላቢ ቀማኛ ቦርሳዋን ተመንትፋለች፡፡

የእግረኛ መንገዱን ይዞ በሞባይሉ ስልክ የሚያናግረው ሰው ሳይታሰብ በክንፋሞቹ የሞተር ሳይክል ሌቦች ተቀምቶ በድንጋጤ መደንዘዙ እየተለመደ ነው፡፡ አላፊ አጋዳሚው እንደልብ በብዛት በሚንቀሳቀስበት ሥፍራ ሳይቀር እየተፈጸመ የሚታየው ንጥቂያ፣ መዘውተሩን ተከትሎ ፖሊስ አንዳንድ ዕርምጃዎችን መውሰድ ጀምሯል፡፡ ለከተማችን እንግዳ የሆነው የዚህ ዓይነቱ ሥርቆት መበራከት ተከትሎ ፖሊስ ጥቂት የማይባሉ ሞተር ብስክሌቶችን መያዙ፣ እንዲህ ባለው ድርጊት ተሳትፈዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ስለማዋሉም ተሰምቷል፡፡

በዚህ አኳኋን እየተፈጸመ ያለው ወንጀል ሥር እንዳይሰድ ለማድረግ የፖሊስ ኃላፊነት ከፍተኛ ቢሆንም ወንጀሉን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሌሎች ዕርምጃዎች መኖራቸው የግድ ይላል፡፡ በሞተር ሳይክል የሚፈጸሙ ወንጀሎች እዚህም እዚያም እንዲከሰት ወይም እንዲበራከቱ ሊያደርጉ ከቻሉት ምክንያቶች አንዱ፣ በከተማው ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሞተር ሳይክሎች ላይ የሚደረግ ሕጋዊ ቁጥጥር መላላት ሊሆን ይችላል፡፡

ባለሁለትም ሆነ ባለ ሦስት እግር ሞተር ብስክሌቶች (ባጃጅ)፣ እንደ ማንኛውም ተሽከርካሪ በቂ ቁጥጥር ስለማይደረግባቸው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲሀ እየጎላ ለመጣው ወንጀል አስተዋጽኦ ማድረጉን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ፣ በከተማው ውስጥ የምንመለከታቸው ሞተር ሳይክሎች ታርጋ ቁጥራቸውን እንኳ መለየት ማስቸገሩ አንዱ ችግር ነው፡፡ ታርጋ የሌላቸው ሞተር ሳይክሎች በጎዳና ላይ የመታየታቸውም ጉዳይ ከዚሁ ጋር ሊፈተሽ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡

ሌላው ቀርቶ ከአገልግሎት ውጭ የተደረጉ ታርጋዎችን የለጠፉ ሞተር ሳይክሎች በከተማ ውስጥ በምን አግባብ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ የሞተር ሳይክል እያከራዩ የሚጠቀሙ ሰዎች አሉ፡፡ በምን አኳኋን እንደሚያከራዩና ለምን እንደሚያከራዩ መታወቅ አለበት፡፡ ሌሎችም ድርጊቶች እየታዩ ዕርምጃ ሳይወሰድ መቅረቱ ለወንጀሉ መስፋፋት ምክንያት መሆኑ ላያከራክረን ይችላል፡፡ ስለዚህ በሞተር ሳይክል የሚካሄዱ ሥርቆቶችን ከምንጫቸው ለማድረቅ በመጀመርያ የሞተር ሳይክሎች ባለቤትነት ምዝገባ ማካሄድ ነገሩን በእንጭጩ ለመቅጨት ያስችላል፡፡

እያንዳንዱ ሞተር ሳይክል በማን ንብረትነት እንደተመዘገበ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ሞተር ሳይክሎቹ ለምን አገልግሎት እየዋሉ እንደሆነና ሞተር ሳይክሎቹን የሚያሽከረክሩ ግለሰቦች ማንነትም መጣራት ይኖርበታል፡፡ እንደማንኛውም ተሽከርካሪ በጎዳናዎች ለመንቀሳቀስ የሚያስችላቸው ዓመታዊ የተሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ እንዲይዙ ማድረግም ተገቢ ነው፡፡ ሞተር ሳይክል እያከራዩ የሚጠቀሙ ዜጐችም ቁጥጥር ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ ተከራዩም ቢሆን ለምን እንደሚከራየውና ማንነቱን በግልፅ የሚያሳይ አሠራር መዘርጋት እንዳለበት የሰሞኑ ወንጀሎች በቂ ማሳያዎች ናቸው፡፡

በተለይ ከምዝገባው ጎን ለጎን ለሞተር ሳይክሎቹ አዲስ የታርጋ ቁጥር መስጠቱ ወንጀሉን ለማስቀረት ወይም ለመቀነስ እጅግ የሚጠቅም መሆኑን በመገንዘብ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አፋጣኝ ዕርምጃዎችን ሊወስዱበት ይገባል፡፡

እንዲህ አይነቱን መሠረታዊ ዕርምጃ ተግባራዊ ከማድረግ ጎን ለጎን፣ ፖሊስ ድርጊቱን ለማቆም የሚያደርገውት ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም ሞተር ሳይክሎቹን የመቆጣጠሩን ሥራ በማጥበቅ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ሕብረተሰቡም የችግሩ ገፈት ቀማሽ ነውና መተባበር አለበት፡፡

ethiopianreporter

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: