በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በውኃና ኤሌክትሪክ መቋረጥ ግራ ተጋብተዋል

•    ‹‹መብራቱንስ በኩራዝ እንታገሳለን ውኃውን በምን?›› ነዋሪዎች
•    ‹‹ከአቅም በላይ ችግር ካልገጠመ በስተቀር የኃይል መቆራረጥ ቀንሷል››  የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን 

የውኃና የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ ይሻሻላል በሚል በትዕግስት ቢጠባበቁም፣ እየባሰበት እንደመጣና መፍትሔ በማጣታቸው ግራ መጋባታቸውን በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እየገለጹ ነው፡፡

ውኃና ኤሌክትሪክ ከዓመት እስከ ዓመት ተቋርጦባቸው እንደማያውቅ ሲነገርላቸው የነበሩ በተለይ በቤተ መንግሥት አቅራቢያ ያሉ ነዋሪዎች ሳይቀሩ፣ ውኃ በሳምንት ሦስትና አራት ቀናት እንደማያገኙ፣ ኤሌክትሪክ ደግሞ በሳምንት ውስጥ በቀን ሁለትና ሦስት ጊዜ በመጥፋት ንብረቶቻቸው ጭምር እየተቃጠሉባቸውና አንዳንዴም በፍርኃት ሳያበሩ እንደሚያመሹ ገልጸዋል፡፡

በሞባይል ስልክ እየተነጋገሩ ሲቋረጥ የተለመደ ችግር በመሆኑ፣ ከመማረር አልፈው የሚያነጋግሩትን ሰው ‹‹ቁም ነገሩን ብቻ ንገረኝ›› ማለት መጀመራቸውን የገለጹት ወ/ሮ በለጡ ማንደፍሮ የተባሉ ነዋሪ፣ የውኃና የኤሌክትሪክ ችግርን ግን መቋቋም እንዳቃታቸው ገልጸዋል፡፡ 

በተለይ የውኃ ችግርን መቋቋም እንደተሳናቸው የሚናገሩት ወ/ሮ በለጡ፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት አንዱ መንደር ቢጠፋ ከሌላው መንደር ወይም ቦኖ ውኃ ይገዙና የዕለት ችግራቸውን ይወጡ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን አሁን ግን በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኙ አካባቢዎች ሁሉ ስለሚጠፋ የሚያደርጉት ግራ እንደገባቸው ተናግረዋል፡፡ የሕፃናትን ጥም ለማስታገስ የታሸገ ውኃ ለመግዛት ሲሞክሩ አምስት ብር የሚሸጥ ግማሽ ሊትር እሽግ ውኃ ስምንት ብር ክፈሉ እንደተባሉ የተናገሩት ወ/ሮ በለጡ፣ ነጋዴው ከሰው ያልተፈጠረ ይመስል አጋጣሚን ተጠቅሞ ለመክበር የሚያደርገው መሯሯጥ እንዳሳዘናቸው ይናገራሉ፡፡ ኤሌክትሪክ ቢቋረጥ በእንጨትና ከሰል ማብሰል እንደሚቻልና በኩራዝ ማምሸት ጊዜያዊ መፍትሔ እንደሚሰጥ የገለጹት ወይዘሮዋ፣ ‹‹የውኃን ችግር ምን ያስታግሰው?›› በማለትም ይጠይቃሉ፡፡

እንደ ወ/ሮ በለጡ ሁሉ በአብዛኛዎቹ ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች የውኃና የኤሌክትሪክ በየጊዜው መጥፋት ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን ገልጸው፣ የሚመለከተውን የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ቅርንጫፍና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዲስትሪክት ጽሕፈት ቤቶችን ሲያነጋግሩ፣ እንኳን መፍትሔ ሊሰጧቸው ቀርቶ ሊያነጋግሯቸው ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የሚመለከተው የመንግሥት አካል አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡

ነዋሪዎቹ እያነሱት ያለውን ችግር በሚመለከት ማብራሪያ እንዲሰጡን የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋለም ባዩን አነጋግረናቸው እሳቸው ወደ ስብሰባ እንደሚገቡ ገልጸው፣ አቶ ፈቃዱ የተባሉ የመሥርያ ቤቱ ባልደረባ እንደሚያነጋግሩን ቢነግሩንም፣ አቶ ፈቃዱን አግኝተን ለማነጋገር አልቻልንም፡፡ አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የባለሥልጣኑ ባልደረባ እንደገለጹልን ውኃ የሚቋረጠው እጥረት ኖሮ ሳይሆን፣ ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ ነው፡፡ የውኃ ፓምፖች የሚንቀሳቀሱት በኤሌክትሪክ ኃይል በመሆኑ፣ ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ ውኃም ይቋረጣል፡፡ ችግሩ የባለሥልጣኑ ሳይሆን ከኮርፖሬሽኑ ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ባለሥልጣኑ የአዲስ አበባ ከተማ ውኃ የማዳረስ አቅሙ ከ93 በመቶ በላይ መድረሱን መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የውኃ እጥረት ችግር የሚፈጠረው ከኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ጋር በተያያዘ መሆኑንና በተደጋጋሚ እየተቋረጠ በነዋሪዎች ንብረት ላይ ችግር መፍጠሩን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡን የኮርፖሬሽኑን የድስትሪቢዩሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ብርሃነን አነጋግረናቸዋል፡፡

‹‹ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ካልገጠመ በስተቀር በተለይ ከሐምሌ ወር 2004 ዓ.ም. እስከ የካቲት ወር 2005 ዓ.ም. ድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፤›› በማለት ምላሽ የሰጡት አቶ መስፍን፣ ኃይል የሚቋረጠው በፕሮግራም ለተለያዩ ጥገና ሥራዎች፣ ለመንገድ ግንባታና ለመሳሰሉት በመገናኛ ብዙኅን ተነግሮ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሌላው ኃይል የሚቋረጠው በተፈጥሮ አደጋና ትላልቅ ግንባታዎች በሚካሄዱባቸው አካባቢዎች የተለያዩ መሣሪያዎች ወድቀው መስመር ላይ ችግር ሲከሰት ብቻ መሆኑንም አቶ መስፍን አውስተዋል፡፡ ከዋናው ማሰራጫም ቴክኒካዊ ችግሮች ሲያጋጥሙ የኃይል ማቋረጥ እንደሚገጥም አልሸሸጉም፡፡

ከውኃ ጋር በተያያዘ ስለተነሳላቸው ጥያቄ እስካሁን ተባብረው እንደሚሠሩና ውጠታማ መሆናቸውን ገልጸው፣ ችግር የለም ሊባል እንደማይቻል ያንንም ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ ጠንክረው በጋራ እየሠሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ከኢትዮ ቴሌኮምም ጋር ተመሳሳይ ተግባር እየፈጸሙ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ሁሉም መሥርያ ቤቶች ኅብረተሰቡን ለማገልገል እስከተሰለፉ ድረስ አንዱ በአንዱ ላይ ምክንያት ማቅረብ ተገቢ አለመሆኑን የገለጹት አቶ መስፍን፣ ቀደም ብለው እንደገለጹት ከአቅም በላይ የሆነ ጊዜያዊ ችግር ሊፈጠር ስለሚችል፣ ውኃም ሆነ ቴሌኮም ጊዜያዊ መፍትሔ መስጫ ጄኔሬተር ገዝተው ማዘጋጀት እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

Ethiopia Reporter

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: