የአፍሪካ መዲና-አዲስ አበባ የውሀ እና የመብራት ያለህ እያለች ነው

መጋቢት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የውኃና የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ ይሻሻላል በሚል በትዕግስት ቢጠባበቁም፣ እየባሰበት እንደመጣና መፍትሔ በማጣታቸው ግራ መጋባታቸውን በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መግለፃቸውን ሪፖርተር ዘገበ።

እንደ ጋዜጣው ዘገባ ውኃና ኤሌክትሪክ ከዓመት እስከ ዓመት ተቋርጦባቸው እንደማያውቅ ሲነገርላቸው የነበሩ በተለይ በቤተ መንግሥት አቅራቢያ ያሉ ነዋሪዎች ሳይቀሩ  አሁን ውኃ  እያገኑ ያሉት በሳምንት ለሦስትና አራት ቀናት ብቻ ነው።

ኤሌክትሪክም  በሳምንት ውስጥ በቀን ሁለትና ሦስት ጊዜ እየጠፋባቸው ንብረቶቻቸው ጭምር እየተቃጠሉባቸው መሆናቸውን የገለፁት ነዋሪዎቹ፤ አንዳንዴም በፍርኃት መብራት  ሳያበሩ እንደሚያመሹ ገልጸዋል፡፡

በሞባይል ስልክ እየተነጋገሩ ሳለ መቃረጡን በተመለከተ ግን የተለመደ ችግር ስለሆነ ከመማረር ውጪ ምንም ሊያደርጉ አለመቻላቸውን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

የውኃና የኤሌክትሪክ ችግርን ግን  በመማረር ሊያሳልፉትን ሊቋቋሙት እንዳልቻሉ ነው የሚናገሩት።
በተለይ የውኃ ችግርን መቋቋም እንደተሳናቸው የሚናገሩት ወ/ሮ በለጡ የተባሉ የ አካባቢው ነዋሪ፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት አንዱ መንደር  ውሀ ቢጠፋ በሌላ መንደር  ካለ ቦኖ ውኃ ይገዙና የዕለት ችግራቸውን ይወጡ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን አሁን ግን በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኙ አካባቢዎች ሁሉ ውሀ  ስለሚጠፋ የሚያደርጉት ግራ እንደገባቸው ተናግረዋል፡፡

የሕፃናትን ጥም ለማስታገስ የታሸገ ውኃ ለመግዛት ሲሞክሩ  ለወትሮው አምስት ብር ይሸጥ የነበረው  ግማሽ ሊትር እሽግ ውኃ ስምንት ብር ገብቷል  እንደተባሉ የተናገሩት ወ/ሮ በለጡ፣ ነጋዴው ከሰው ያልተፈጠረ ይመስል አጋጣሚን ተጠቅሞ ለመክበር የሚያደርገው መሯሯጥ እንዳሳዘናቸው ይናገራሉ፡፡

ኤሌክትሪክ ቢቋረጥ በእንጨትና ከሰል ማብሰል እንደሚቻልና በኩራዝ ማምሸት ጊዜያዊ መፍትሔ እንደሚሰጥ የገለጹት ወይዘሮ በለጡ ‹‹የውኃን ችግር  ግን ምን ያስታግሰው?›› በማለትም ይጠይቃሉ፡፡

ስለጉዳዩ በጋዜጠኞች የተጠየቁት  የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋለም ባዩ ፤እርሳቸው ወደ ስብሰባ እንደሚገቡ በመጥቀስ  አቶ ፈቃዱ የተባሉ የመሥርያ ቤቱ ባልደረባ ምላሽ እንደሚሰጡ  ቢናገሩም፤አቶ ፈቃዱን  ማግኘት ሳይቻል ቀርቷል።

አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የባለሥልጣኑ ባልደረባ  ግን  ውኃ የሚቋረጠው እጥረት ኖሮ ሳይሆን፣ ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ ነው ብለዋል።

“የውኃ ፓምፖች የሚንቀሳቀሱት በኤሌክትሪክ ኃይል በመሆኑ፣ ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ ውኃም ይቋረጣል፡፡” ያሉት  የመስሪያ ቤቱ ባልደረባ፤” ችግሩ የባለሥልጣኑ ሳይሆን ከኮርፖሬሽኑ ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የውኃ እጥረት ችግር የሚፈጠረው ከኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ጋር በተያያዘ  እንደሆነ እና ከዚህም በላይ   ኤሌክትሪክ በተደጋጋሚ እየተቋረጠ የነዋሪዎችን ንብረት እያቃጠለ ስለሚገኝበት ሁኔታ   ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት  የኮርፖሬሽኑን የዲስትሪቢዩሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ብርሃነ
‹‹ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ካልገጠመ በስተቀር በተለይ ከሐምሌ ወር 2004 ዓ.ም. እስከ የካቲት ወር 2005 ዓ.ም. ድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፤››  ብለዋል።

ኃይል የሚቋረጠው በፕሮግራም ለተለያዩ ጥገና ሥራዎች፣ ለመንገድ ግንባታና ለመሳሰሉት ጉዳዮች  በመገናኛ ብዙኅን እየተነገረ ነው ያሉት አቶ  መስፍና፤
ሌላው ኃይል የሚቋረጠው በተፈጥሮ አደጋና ትላልቅ ግንባታዎች በሚካሄዱባቸው አካባቢዎች የተለያዩ መሣሪያዎች ወድቀው መስመር ላይ ችግር ሲከሰት ብቻ ነው ብለዋል። አልፎ አልፎ ከዋናው ማሰራጫም ቴክኒካዊ ችግሮች ሲያጋጥሙ የኃይል ማቋረጥ እንደሚገጥም  አቶ መስፍን አልሸሸጉም፡፡

አቶ መስፍን ችግሩ ከበፊቱ ቀንሷል ቢሉም በተጨባጭ መሬት ላይ የሚታየው ሀቅ ችግሩ እየከፋ መምጣቱን የሚያመላክት ነው።

እንደ ጋዜጣው ዘገባ ለወትሮው የችግሩ ተጠቂ ያልነበሩት መንደሮች ናቸው አሁን በውሀ እና በመብራት ችግር እየተማረሩ ያሉት።

እንደ ወ/ሮ በለጡ ሁሉ በአብዛኛዎቹ ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች የውኃና የኤሌክትሪክ በየጊዜው መጥፋት ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን ገልጸው፣ የሚመለከተውን የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ቅርንጫፍና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዲስትሪክት ጽሕፈት ቤቶችን ሲያነጋግሩ፣ እንኳን መፍትሔ ሊሰጧቸው ቀርቶ ሊያነጋግሯቸው ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከ ኢትዮጵያ አልፋ የ አፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ የቧንቧ ውሀ፣የ ኤሌክትሪክ እና የስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነችው በአፄ ምኒልክ ጊዜ ቢሆንም እስካሁን ድረስ የተጠቀሱትን አገልግሎቶች ማሟላት አለመቻሏ ብዙዎችን ያስገረመ ሆኗል።

ለኢሳት የሚደርሱት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በሰቆጣ፣ መቀሌ፣ እና በተለያዩ የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ የውሀ እጥረት ተከስቷል።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: