ኢሕአዴግ አንጋፋ አመራሮቹን አሰናብቶ 9ኛ ጉባዔውን እያካሄደ ነው

519cb84dfa56f4e64bd73c0393e49890_XL•    ሕወሓት ዘጠኝ ነባር አመራሮቹን አሰናበተ
•    ብአዴን ሁለት የሥራ አስፈጻሚ አባላትን ዝቅ አድርጓል

የተወሰኑ አንጋፋ መሪዎችን በማሰናበት የታጀበው የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች የተናጠል ጉባዔ ተጠናቆ፣ የግንባሩ ዋናውና 9ኛ ጉባዔ መጋቢት 14 ቀን 2005 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ ተጀመረ፡፡

ሕወሓት ዘጠኝ ነባር ከፍተኛ አመራሮችን ሲያሰናብት፣ ደኢሕዴን አንዳችም የአመራር ለውጥ አላደረገም፡፡

የኢሕአዴግ አባል ብሔራዊ ድርጅቶች ባለፈው ሳምንት በመቐለ፣ በሐዋሳ፣ በአዳማና በባህር ዳር ሲያካሄዱት የሰነበቱት የተናጠል ጉባዔ ከተጠናቀቀ በኋላ የግንባሩ 9ኛ ጉባዔ ተሳታፊዎች ባህር ዳር ከትመዋል፡፡

11ኛ ጉባዔውን በመቐለ ከተማ ለሦስት ቀናት ሲያካሂድ የሰነበተው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በተለያዩ የክልሉ የልማትና የፖለቲካ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተወያየ ሲሆን፣ ዘጠኝ ነባር አመራሮቹን ከማዕከላዊ ኮሚቴ፣ አራት አንጋፋ አመራሮችን ደግሞ ከሥራ አስፈጻሚነት አሰናብቷል፡፡

ከድርጅቱ መሥራቾች አንዱ የሆኑት የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ስዩም መሥፍን፣ የቀድሞው የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ አርከበ ዕቁባይ፣ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርአይ አስገዶምና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት በገዛ ፈቃዳቸው ራሳቸውን አግልለዋል፡፡ በክብርም ተሸኝተዋል፡፡

‹‹የማይቀረው ሞት እስኪመጣ መጠበቅ የለንም››
እነዚህ ነባር የድርጅቱ ታጋዮችና ከከፍተኛ የድርጅቱ አመራሮች ከኃላፊነት ራሳቸውን ያገለሉበት ምክንያት የድርጅቱን የመተካካት መርህን ተግባራዊ ለማድረግና የቆየውን አመራር በአዲስ ትውልድ ለመተካት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩን አስመልክተው ንግግር ያደረጉት ተሰናባቹ አምባሳደር ስዩም መሥፍን፣ ‹‹የማይቀረው ሞት እስኪመጣ ድረስ መጠበቅ የለብንም፤ የመሪያችን መለስ ዜናዊ ሞትም ትምህርት ሊሆነን ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ሕወሓትንና መለስን የፈጠረው ሕዝቡ ነው፡፡ ስለዚህ ለዚህ ክብርና ታላቅነት ያበቃንን ሕዝብ በዚህ አጋጣሚ ላመስግነው እፈልጋለሁ፤›› ያሉ ሲሆን፣ ተተኪ አመራሮችን በተመለከተም፣ ‹‹ለዚህ ያበቁንን ሰማዕታትና የትግራይ ሕዝብን ሳትዘነጉ ሕዝባችሁን በታማኝነትና በቁርጠኝነት ማገልገል ይገባችኋል፤›› የሚል የአደራ ቃል አስተላልፈዋል፡፡

በተጨማሪም ጉባዔው የሕወሓት ነባር ታጋዮችና አመራር የነበሩትን አቶ ሕሸ ለማ፣ አቶ መሠረት ገብረ ማርያም፣ አቶ መንግሥተ አብ ገብረ ኪዳን፣ አቶ ደስታ በዛብህና አቶ ንጉሠ ገብረ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አመራርነት ያወረደ ሲሆን፣ ሦስት ሴቶችና ሦስት ምሁራን የሚገኙበት 12 አዳዲስ አመራሮችን መርጧል፡፡ አዳዲሶቹ ተመራጮች በትጥቅ ትግሉ ያልተሳተፉ ሲሆኑ፣ ከእነዚህም መካከል የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ክንደያ ገብረ ሕይወት፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አብርሃም ተከስተና ዶ/ር ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔር ይገኙበታል፡፡

የቀድሞዎቹ ታጋዮች አቶ ፀጋዬ በርሄና አቶ አባዲ ዘሙ ከሥራ አስፈጻሚነት ወርደው በማዕከላዊ ኮሚቴነት እንዲቀጥሉ የተደረገ ሲሆን፣ አቶ መለስ ዜናዊን ጨምሮ በሞት በተለዩት ምትክ ወ/ሮ ትርፉ ኪዳነ ማርያም፣ አቶ ዓለም ገብረ ዋህድና፣ አቶ ገብረ መስቀል አዳል ከነበሩበት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ከፍ ብለው በሥራ አስፈጻሚነት እንዲሠሩ ተመርጠዋል፡፡ ዘጠኙ ነባር አባላት በኢሕአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ በድምፅ ተወክለው እንዲሳተፉም ተወስኗል፡፡

አዳማ ላይ 9ኛ መደበኛ ጉባዔውን ሲያካሂድ የሰነበተው የኦሮሞ ሕዝቦች ዲሞክራሲየዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) በበኩሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔና የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አባዱላ ገመዳን፣ እንዲሁም ደግሞ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ግርማ ብሩን ከድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አሰናብቷል፡፡ ስንብቱ በብዙዎች ያልተጠበቀ ሲሆን፣ በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው እንዲቀጥሉም ተደርጓል፡፡ በምትካቸውም የፌደራል ፖሊስ ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ወርቅነህ ገበየሁና ወ/ሮ አስቴር ማሞ ተመርጠዋል፡፡

ጉባዔውን በባህር ዳር ከተማ ያካሄደው የብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የፍትሕ ሚኒስትሩን አቶ ብርሃን ኃይሉና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ካሳ ተክለ ብርሃንን ብቻ ከሥራ አስፈጻሚነት አሰናብቶ በምትካቸው ዶ/ር አምባቸው መኮንንና አቶ አህመድ አብተውን መርጧል፡፡ ዶ/ር አምባቸው ነባር የድርጅቱ አባል ሲሆኑ፣ ለዶክትሬት ትምህርት በውጭ አገር ቆይታ አድርገው በቅርቡ ወደ አገር ቤት ተመልሰው መምጣታቸው ታውቋል፡፡ አቶ ብርሃን ኃይሉና አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን በድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚነት ተካተዋል፡፡ ብአዴን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ቁጥር ከመጨመር ውጪ ምንም ዓይነት የአባላት መተካካት አላደረገም፡፡ መተካካት በብአዴን ውስጥ አለመካሄዱ አስገራሚና የመነጋገሪያ አጀንዳ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) በበኩሉ፣ በሥራ አስፈጻሚ አባላትም ሆነ በማዕከላዊ ኮሚቴ ያለአንዳች ለውጥ የነበሩትን መልሶ በመምረጥ ጉባዔውን አጠናቋል፡፡

አራቱም የኢሕአዴግ ብሔራዊ አባል ድርጅቶች በሊቀመንበራቸውንና በምክትል ሊቀመንበራቸው ላይ አንዳችም ለውጥ ሳያደርጉ የነበሩትን መልሰው መርጠዋል፡፡ ሕወሓት፣ ብአዴን፣ ኦሕዴድና ደኢሕዴን አቶ ዓባይ ወልዱን፣ አቶ ደመቀ መኮንን፣ አቶ ዓለማየሁ አቶምሳን፣ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን በሊቀመንበርነት፤ አቶ ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤልን፣ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን፣ አቶ ሙክታር ከድርንና አቶ ሽፈራው ሽጉጤን በምክትል ሊቀመንበርነት መርጠዋል፡፡

በሰንጠረዥ የተመለከቱት አባል ድርጅቶች ለኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን መርጠዋል፡፡ ብአዴን አቶ አዲሱ ለገሰን፣ አቶ ካሳ ተክለብርሃንን፣ አቶ መላኩ ፈንታን፣ ዶ/ር አምባቸው መኮንንና አቶ ጌታቸው ጀምበርን ጨምሮ 14 አባላት ያሉት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡ ኦሕዴድ አቶ ዋቅ ቤካ፣ አቶ አብዱልአዚዝ መሐመድ፣ አቶ ኑሬ ቀመር፣ አቶ ሰለሞን ቁጩ፣ አቶ በከር ሻሌና አቶ እሸቱ ደሴን ጨምሮ 15 አባላት ያሉት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መርጧል፡፡

እንዲሁም ደግሞ ደኢሕዴን በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የወከላቸውን ዘጠኝ አባላት ጨምሮ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ፣ አቶ መለሰ አለሙ፣ ወ/ሮ ሙፍራያት ካሚል፣ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ አቶ ደበበ አበራና አቶ ሳኒ ረዲን ለድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መርጧል፡፡ ሕወሓት ለኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከመረጣቸው ዘጠኝ አባላት ውጪ ለድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚነት ያካተተው ተጨማሪ አባል የለም፡፡

በተያያዘ ዜና ከሕወሓት ውጪ ሌሎች አባል ድርጅቶች ከዚህ በፊት የነበረውን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ቁጥር ከፍ ያደረጉ ሲሆን፣ ብአዴንና ደኢሕዴን ከ45 ወደ 65፣ ኦህዴድ በበኩሉ ከ65 ወደ 81 ከፍ አድርጓል፡፡ ሕወሓት እንደበፊቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ ቁጥር በ45 ተወስኖ ቀርቷል፡፡

ሦስቱ እንስቶች
በግንባሩ ታሪክ ውስጥ ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ ሦስት ሴቶች የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ተመርጠዋል፡፡ ወ/ሮ አስቴር ማሞ የመጀመርያዋ፣ ቀጥለው ደግሞ ባለፈው 8ኛ ጉባዔ አቦይ ስብሐትን ተክተው የገቡት የቀድሞ የሕወሓት ሊቀመንበር የአቶ መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ሲሆኑ፣ ዘንድሮ በሕወሓት ለኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት የተመረጡት የትግራይ ፕሬዚዳንትና በአሁኑ ወቅት የሕወሓት ሊቀመንበር የአቶ አባይ ወልዱ ባለቤት የሆኑት ወ/ሮ ትርፏ ኪዳነ ማርያም ሦስተኛ ሴት ሆነው ሥራ አስፈጻሚውን ተቀላቅለዋል፡፡

ኢሕአዴግ በዘጠነኛው ጉባዔ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን የሁለት ዓመት ተኩል አፈጻጸም የሚገመግም ሲሆን፣ እንዲሁም ለዕቅዱ ማጠናቀቂያ አቅጣጫ እንደሚያሲዝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አዳማ ላይ በ8ኛው ጉባዔ ያፀደቃቸውን ድርጅታዊ ውሳኔዎች በመገምገም በቀጣይ ሁኔታዎች ላይ ይነገጋገራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አሳሳቢ በሆነው የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ላይ ጉባዔው በስፋት ይነጋገራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም ኪራይ ሰብሳቢነት የጉባዔው አጀንዳ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በመጨረሻም የግንባሩን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር በመምረጥ ጉባዔውን ያጠናቅቃል፡፡ በዚህ ጉባዔ ላይ በአጠቃላይ 2,500 ተሳታፊዎች ይገኛሉ፡፡ (ለዚህ ዘገባ ዳዊት ከበደ ከመቐለ አስተዋጽኦ አድርጓል

ethiopian reporter

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: