የማለዳ ወግ . . .ዛሬም ኮንትራት ሰራተኞቻችን አበሳና የሚመሰገነው ያልለመድነው የዲፕሎማቶች ትብብር !

by Nebiyu Sirak (Notes) on Wednesday, December 5, 2012 at 1:09am

መሽቷል . . .ሰአቴ ከምሽቱ 3፡ 15 ይላል ! ከወደ ጅዳ ቆንስል የቅርብ ርቀት ካንድ ወዳጀ ጋር ለመገናነት ቀጠሮ ይዘን ነበርና የቀጠሮ ሰአቴ እስኪደርስ ወደ ኮሚኒቲው ካፍቴሪያ ጎራ አልኩ፡፡ . . . አካባቢው ጭር

ብሏል፡፡ ወደ ግቢው ዘልቄ ሰገባ ከወደ ቀኝ በኩል ካለው የኮሚኒቲ ጽህፈት ቤት አናት ከተደረደሩትን የልማት ማህበራትን ጽህፈት ቤቶች መካከል 32ኛው የብአዴን ክበረ የሚከበርበትን ቀንና የድግሱም መግቢያ በነጻ መሆኑን የሚገልጸው ትልቅ ማስታወቂያ ተንዥርግጎ ይታያል፡፡ ረመድ ረመድ እያልኩ ወደ ሻሂ ቤቱ ጎራ በማለት የቋመጥኩትን ማኪያቶ ፉት ልል ወደ ካፍቴሪያው በር ልገባ ስል አንዲት በፐላሲቲክ ፊስታል እቃ ከፊት ለፊትዋ ያስቀመጠች እህት ተመለከትኩ፡፡ አንገቷን ሰብራ የተመለከትኳት እህት ሁኔታ ከሰላምታ አልፌ በዚህ ምሺት እዚህ ምን እንዳመጣት እጠይቃት ዘንድ አንዳች ነገር ተሰማኝና ጠጋ ቡእ ጠየቅኳት . . . የኮንትራት ሰራተኛ ናት ! ከአሰሪዋ ጋር ተጣልታ በቪዛ ያስመጣቻት እህት ወደ እንባሲ ሂጅና እዚያው መብትሺን ያስከብሩልሽ ተብላ የተላከች እህት እንደሆነች ገለጸችልኝ ፡፡. . . ለማረጋጋት ሞክሬ ወደ ሻሂ ቤቱ ይዣት ገባሁ ፡፡ ጠረጴዛ ከበው ካገኘኋቸው ወንድሞቸ ጋር አብራን ተቀምጣ ወደ ዚህ አገር ስለመታችበትና ስለ ስራና አጠቃልይ ሁኔታው አወጋችን፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ይህችው እህት ከፊቷ ላይ መጎሳቆል ባይታይባትም ፍርሃት ፤ ድንጋጤና አለመረጋጋግት ይታይባታል ! ” ደግሞ ከመጠለያና ከቆስንሉ እያታለሉ እየወሰዱ ይደፍራሉ ስለሚባሉና ለአረብ ይደልላሉ ስለሚባሉት ” አስፋሪ ወንድሞቻችን ፈርታ ይሆን አልኩና ራሴን ጠየቅኩ ፡፡ መልስ የለኝም ፡፡ በቆስንል መስሪያ ቤቱ የውሃ ጉድጓድ እጅና እግሯ ታስሮ ሞታ ከተገኘች ወዲህ ማንኛውም ተፈናቃይ በቆስሉ እንዳያስይጠጋ ትዕዛዝ በመተላለፉ ችግሮች እየገዘፉ ሲሄዱ አይቻለሁ ሰምቻለሁ፡፡ ከሁለት ወር በፊት በሃገሬ ቆንስል ባላ መጠጊያ ፈልጋ የመጣች ተፈናቃይ የቆስንሉ ጸጥታ አስከባሪዎች ከግቢው ማደር እንደማትችል ገለጹላት፡፡ እህት ተበሳጨች ራሷን ሳተች፡፡ ከግቢው ሲያስወጧትም ከቅርብ ርቀት ባለ አንድ ዛፍ ቆጥ ሰርታ ሶስት ቀናት ሳትበላና ሳትይጠጣ ብትቆይም ያለችበት ታውቆ ለነፍሳቸው ያደሩ ሊረዷት ፈልገው ሲጠጓትና ከዛፉ እንድትወርድ ሲማጸኗት ከዛፉ ላይ ዘላ በመውደቅ ራሷን የገደለች እህት ታሪክ አውቃለሁ፡፡ ይህ የቅርብ ቀን ትዝታ እያመመኝ የዚህችኛዋን እህት ጉዳይ ዝም ብየ ማለፍ ከብዶኛል ፡፡ እናም ሌላው ቢቀር የዛሬን መጠለያ አግኝተንላታል፡፡ ይህንንም ለቆስንስል ሸሪፍ አሳወቄ ወደ ማልቀረው ቀጠሮየ እርሷ ደግሞ ወደ ቤት የሚወስዳትን ወንድሜን ጠራሁት . . . የዚህችን እህት ጉዳት በመከታተል ላይ እያለሁ አንድ ወንድም ከካፍቴሪያው በር በኩል እየተጣደፈ መጥቶ

” ይቅርታ ነቢዩ ሲራክ ማለት አንተ ነህ ?” አለኝ ፡፡ አዎ አልኩት ፤ “እባክህን ላነጋግርህ እፈልጋለሁ ?” ሲል በትህትና ጠየቀኝ ከካፍቴሪያው ተያይዘን ወጣን ፡፡ወንድሜ ያጋጠመውን ሁሉ አስረድቶ ወዳጫወተኝ እህት ወሰደኝ ፡፡ ከቆስንሉ በር ቆልመም ብላ የተቀመጠችው እህት ተጎድታለች ፡፡. . . ሰውነቷ ደክሟል ፤ ፊቷ በልዟል፤ ደነገጥኩ ! እኔና ይህው ጠቋሚ ወንድም ደጋግመን የጠየቅናትን የስም የአድራሻና የመሳሰሉት ጥያቄዎች የምትመልስልን ፍጹም በደከመና በተቆራረጠ ድምጽ ነው ! መናገር ተስኗታል. . . ውሃዋን በግድ ትጠጣለች ! ከአፏ የሚቀመስ ምግብ አለማድረጓ እንደጎዳት የገመተው ወንድም ምግብ ብትበላ ትንሽ ነቃ እደምትል አማክሮኝ ወደ ካፍቴርያው ውስደን ምግብ እንድንገዛላት ተስማማን፡፡ . . . ከጎንና ጎኗ ደጋግፈን ብናስነሳትም መራመድ ተስኗታል፡፡ የተቀመጠችበት ቦታ ርሷል . . .እህቴ ራሷን ቆጣጠር አለመቻልዋን ለመረዳት ብዙ መሄድ አልነበረብኝም ! የደቀቀው ገላዋ ቅለት፤ የተጎዳው ሰውነቷና የፊቷ ግርጣት ሳያንስ በበለዘው ፊቷ እንደመቁሰል ካለው የፊት ቆዳዋ የሚወታው ፈሳሽ ዘልቆ ዘልቆ ይጎዳል፡፡ . . . ከስቃይ ላይ ስቃይ . . . የሚያም የሚያንገበግን የውስጥ ንዴት፤ ብሽቀትና የማንነት ርክሰት ጸጸት ጎዳን !. . . ግን ምንም ማድረግ አይቻለንም ! እንደምንም ብለን ከጥቂት ሰአታት በፊት እንዳትገባ ከተከለከለችበት የጅዳ ቆንስልና የኮሚኒቲ ካፍቴሪያ ቅጽር ወስደን አስቀመጥናት፡፡ ራሷን መቆጣጠር የማትችለውን ይህችን አሳዛኝ እህት የተመለከተ እኛ ሳንለው ጎዳቷ ዘልቆየተሰማው አንድ የካፍቴርያው የምግብ ቤት ሰራተኛ ውሃና ምግብ እየተጣደፈ አመጣላት ! ውሃውን ግብ አድርጋ ጠጣችው ፣ ምግቡንም በሥሥት እንዳቅሟ ቆረስ እያደረገች መጎራረስ ጀመረች ! ይህን ሁሉ ሲሆን ክላሽኮፑን በደረቱ ያንጠለጠለ ቡራቡሬ የፈጥኖ ደራሽ ኮማንዶ ልብስ የለበሰ ሳውዲ ጎልማሳ እየሆነ ያለውን ከሽምት ጀምሮ ተመልክቷልና አንገቱን ሰብሮ በሃዘን የኛን ነገር ይመለከታል፡፡ ይህ የሳውዲ መንግስት የኢንባሲዎች ልዩ ጠባቂ ኮማንጎ የቻልን የራሳችን እህት ስንደግፍ ተመልክቶ ከማመስገን ከመመረቅ ሳይቆጠብ ምግብ የሰጣትን ወንድም ጠርቶ የምግቡን ዋጋ እንደሚከፍል ሲገላገል በመታዘቤ ሰብዕናው ነፍሴን በሃሴት ኡደት ትመላለስ ዘንድ ምክንያት ሆነ፡፡ በዚያው ቅጽበት ስብሰባ ላይ የነበሩ ፖለቲከኞቻችን ከበን እህታችን ለመርዳት ስንረባረብ ካዩት መካከል የኢሃዲግን አጋር ድርጂት ብአዴንን እዚህ አገር የተቀላቀውለው ከፍተኛ ሃላፊ ወጣት ወንድም የሆነውን እያየ እርር ድብን አለ ፡፡ ሚጢጢ ስልኩን እየነካከም ወደ ተለያዩ ሃላፊዎች በመደወል ይህች ግፉእ እህት እርዳታ የምታገኝበትን መንገድ ለማፈላለግ ሲሞክር ተመልክቻለሁ፡፡ በአንጻሩ ለኢሃዴግ ወደ ወንድር መምጣት አነጣጥረው ተኩሰውና መድፍ አገላብጠው እዚህ እንዳደረሱት በመግለጽ ኢሃዴግ በደማቸው እንዳለ የሚነግሩን የኢሃዴግ/ ብአዴን ከፍተኛ መሪ፤ ጦር ሜዳ ሄደው ባይዋጉም ትግሬነታቸው የኢሃዴግ መስራች አውራ ፓርቲ ተሰሚነት ያላቸው የህዎሃትን አባላት ወንድሞቸ ብዙዎቻችን ጨንቆን እያዩ እንዳላዩ ሆነው ጥለውን ሲሄዱ መታዘቤ ነፍሴን አስጨነቃት ! በእኛ ፖለቲከኞች ሳዝን በሳውዲው ወታደር በሰብአዊነት የፈጸመውን በውስጤ እያስደሰተኝ በግጭት መካከል ራሴን ወሽቄ ቆዘምኩ ! ካስደሰተኝ ያሳዘነኝ አስከፍቶች ልቤ በሃዘን ደማ. . . ከሁሉም በላይ የፖለቲካ ድርጂት ከፍተኛ ሃላፊዎች ስልጣናቸውን ተጠቅመው ቢያንስ ለአንድ ቀን ሌሊት ማደሪያ ለማፈላግ ቢሞክሩ ደስ ባለኝ ነበር ፡፡ ግን አልሆነም ! ብቻ ፊታችን ላይ ከንፈራቸውን መጥጠው ” ከነገሩ ጦም እደሩ” አይነት ያዘኑ የተሰማቸውን ያህል ተንጎራደውብን ሲያበቁ እንደ ድንገት ውልቅ ውልቅ እያሉ መንጎዳቸው ጎዳኝ ! “ኢትዮጵያ ፤ ህዝብ ፤ ብሄር ብሄረሰብና ማናምን የሚባለው ሁሉ ፉከራ ምንድነው ? የሚወደስ ፤ የሚፎከር፤ የሚደለቅ ፤የሚከበረው ህዝብ ነው ? ወይስ መሬቱ ? ” ስል ጥያቄ አንስቸ ራሴን በጥያቄ አፋጠጥኩት “ፖለቲከኞች ፖለቲካቸው ለማን ነው ? ” ስል ደግሜ ራሴ አጠየቅኩ . . . መልስ ግን የለኝም ! እዚያው ቆሜ በፖለቲካው ምህዳር ዙሪያ ያገባኛል የምለውን በአረብ ሃገር የምንገኝ ስደተኞችን ጉዳይ አሰላሰልኩና አምና እና ዘንድሮ ክቡር አቶ ሃይለ ማርያም ደሳለኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባለስልጣን ሳሉ የሆነው ታወሰኝና ላፍታ አስታወስኩት . . .

ክቡር አቶ ሃይለ ማርያም ደሳለኝ አምናና ዘንድሮ . . .

ሰኔ ባባተ ማግስት ወደ ሳውዲ አረቢያን ለአጭር ቀናት ጉብኝት የመጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር ሃይለ ማርያም ደሳለኝ 30.000 ሰላሳ ሺህ የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን የሳውዲ መንግስት በኮንትራት ስራተኛን ወደ ሳውዲ ለማስገባት እንደጠየቀና የሰራተኛ አቅርቦቱን ለማሳካት አስፈላጊ ውን እርምጃ እንደሚወሰድ ለአረብ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀው ነበር፡፡ http://www.saudigazette.com.sa/index.cfm?method=home.regcon&contentID=20110613102928 ክቡር ሚኒስትሩ በዚሁ መግለጫ ቸው ሰራተኞች ከመላካቸው አስቀድሞ ተገቢ ስልጠና እንደሚሰጣቸው የተናገሩ ቢሆንም ሰኔ ሳይጠባ ከሚያዝያና ግንቦት ጀምሮ የኮንትራት ሰራተኞች ወደ ሳውዲ መግባት መጀመራቸው መረጃወች ይጠቁማሉ፡፡ መግባታችው እርግጠኛ ከመሆን አልፎ በስራ ኮንትራት የገቡት ወጣት ልጃገረዶች በተለያዩ የሳውዲ ዋና ዋና ከተሞች በጅዳ፤ በሪያድና በደማም እንዳረፉ በላኪ ኤጀንሲዎች ቅንጅት ጉድለት አሰሪዎቻቸው በጊዜ ሊወስዷቸው ባለመቻላቸው ለቀናት እስከ ሳምንታት በማቆያ እስር ቤት የተንገላቱ እህቶችን አግኝቸ ስሞታቸውን አድምጫለሁ፤ አስደምጫለሁ ! አሰሪዎቻቸውን ያገኙ አንዳንዶችም ከአሰሪዎቻቸው ጋር በተፈጠረ አለመግባባት የቀናቸው አቤት ለማለት ጅዳ ቆንስል መስሪያ ቤት መጥተው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ በምግብ አቅርቦት ጉድለት፤በስራ ብዛትና በቋንቋ አለመግባባት ችግር ደርሶባቸው ወደ ኢንባሲና ቆንስል መስሪያ ቤቶች ለአቤቱታ የቀረቡትን ጨምሮ፤አየር መንገድ እንደገቡ አድራሻቸውን አግኝቸ ያነጋገርኳቸውና ከብዙ ትግል በኋላ አሰሪዎቻቸውን ያገኙ አንዳንድ እህቶች ከአሰሪዎቻቸው ጋር ወደ ትናንሽ ከተሞች ከደረሱ በድብቅ እየደወሉ ያለባቸውን መጠነ ሰፊ ችግር በምሬት ገልጸልኛል ! እንባቸውን እያዘነቡ የሚይዙት የሚጨብጡት አጥተው የምችለውን ሁሉ እንዳደርግ ተማጽነውኛል ! ይህ ከአንድ አመት ተኩል በፊት ነው . . .

የሰራተኞችን ውል ከሳውዲ መንግስት ጋር የተዋዋሉት የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የዛሬ የሃገሪቱ የበላይ ጠቅላይ ሚኒስትር መሪ ሆነዋል . . .እናም በዛሬው ከምሸቱ የዜና እወጃ በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ እየሰጡ ነው . . .የሰራተኞችን ውል ከሳውዲ መንግስት ጋር የተዋዋሉት የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የዛሬ የሃገሪቱ የበላይ ጠቅላይ ሚኒስትር መሪ ሆነዋል . . . እናም በዛሬው ከምሸቱ የዜና እወጃ በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ እየሰጡ ነው . . . ይህው መግለጫ በኮሚኒቲው አዳራሽ ሲተላለፍ ነበርና የደረስኩት አንድ ልቤው ወደ ከአጠገቤ እየሆነ ስላለው በሌላኛው ልቤ የኢቲቪው ጋዜጠኛ የአሸብር ጌትነት ጥያቄና የጠቅላይ ሚኒስት ሃይለ ማሪያም ደሳለኝን ቃለ ምልልስ በጨረፍታ መከታተል ይዣለሁ፡፡ የልማት ጋዜጠኛው አሸብር ጌትነት በአደጋ ላይ ስላለው ከግማሽ ሚሊዮን አብዛኛው ግፉአን እህቶቻችን አጠቃላይ የመብት ጥበቃና ይዘት መጠየቅ አለመቻሉ ድፍረት ያጣበትን ጣጣ አውጥቸው አወረድኩት፡፡ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የጋዜጠኝነት ሚና ከማሳዘን አልፎ አሳፈረኝ ! ሃገር ቤት ያሉ የመንግስት ጋዜጠኞች ዲሞክራሲ በተከፈተው በር ህጋዊነት ተላብሰው የሚወጡትን እንጂ ዲሞክራሲ ያመጣውን የመብት ጥበቃ ጉዳይ የሚያይ አይን ቢያጡ እማኞች እንደአሸን ፈልተው ሳለ የመንግስት ቀረቤታ ያላችው መገናኛ ብዙሓን አይዳሧቸውም፡፡ በግፍ እየወጡ ስላሉት ዜጎች ሁኔታ ጠይቀው መረጃ ይሰጡን ዘንድ ብንመኝም አልሆነም፡፡ ዜጎች በአየር መንገዳችን በኩል አካላቸው ጎድሎ ፤ በውስጥ ደዌ ተቀስፈው ፤ አብደውና አስከሬናቸው ወደ ሃገር ቤት የሚገባበት ሁኔታ ከአምናና ካች አምናው የዘንድሮው መጠኑ ከፍ ያለ መሆኑ እየታየ ትኩረት ነፍገውታል !

ላፍታ ያህል የተመለከትኩትን የጋዜጠኛውንና የጠቅላይ ሚኒስትራችን ቃለ ምልልስ እዚያው እይለሁ አውጥቸ አወረድኩት . . . ጋዜጠኛው ህጋዊ ሆነው የወጡት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ስለሚቆጠሩ እህቶቻችን ጉዳይ በአደጋ ከቶን እያለ የህገ ወጥ ዝውውርን ጉዳይ ውሽልሽል አድርጎ ጠየቃቸው . . . ሚኒስትሩም በደላላዎችን ላይ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ ነው በማለት የጀመሩትን መልስ ለሰራተኞች በቂ ዋስትና ወደ ማስይሰጡ ሃገራት ሰራተኞች እንደማይላኩ መደረጉን ግልጽ ሳያደርጉ ገልጹት፡፡ ጠቅላያችን መንግስት ልዩ የዲፕሎማዊያዊ ጥረት እያደረገ እንደሆነም አትተዋል፡፡ በመጨረሻም በሰራተኞች ዙሪያ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ የሚመራ ቡድን ሰፊ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በጀ ! አቶ ደመቀ መኮንን መመደባቸውን ገለጽውልናል፡፡ አቶ ደመቀን እኛን እኛም አቶ ደመቀን እናውቃቸዋለን ! የአማራ ክልል ከፍተኛ ሃላፊ እያሉ ጂዳ መጥተው የውስጥ በደላችን ተመልክተው ሰምተዋልም በዚያች አዳራሽ ሰብስበውን ከተናገሩት ግን አንዱም የሰመረ ቃል አሁን ድረስ አላየንም !ሹመት ያዳብር ብለን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመው የእኛን ጉዳይ ይከታተላሉ መባሉ ባይከፋም እንደ ከዚህ ቀደሙ ቃላቸውን ካላጠፉ መልካም ነው ፡፡

የሚመሰገነው ያልለመድነው የዲፕሎማቶች ትብብር . .

ከሞቱ አሟሟቱ እንዲሉ የዚህች እህታችን ሁኔታ አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቶን በቆምኩበት ሁሉንም አውጥቸ አወረድኩ ፡፡ ማትረፍ የማይቻሉትን ማትረፍ ባይቻል ሊደንቅ አይገባም ፡፡ አሟሟታቸውንና ማንነታቸውን ለቤተሰብ የማስታወቁ ግዴታ ግን የግድ ይላል፡፡ ይህ የማይሆንበት ኩነት ሲያደክመን ኖሯልና መንገዱ ሁሉ ግራ ያጋባል፡፡ ” ታመመች ፤ ሞተች ኢትዮጵያዊ ነት ትቀበር !” ነው ! በቃ ! ይህች ሰው ማን ናት ? እንዴት ሞተች ተብሎ መልስ ማግኘት ሳንችል ወደ መቃብር የወረዱትን ቁጥር እሱ አንድ አምላክ ያውቀዋል ! . . . ወደ ሳውዲ የሚላኩልን ዲፕሎማቶች አቅም ያንሳቸዋል ባይባልም በዲፕሎማሲው ዘርፍ የሚጎላቸው የስራ ልምድና የመብት ጥበቃው እየጎዳው መቸገራችን የነበረ ያለና እንዳይቀጥል የምንፈራው ውሎ አዳራችን ሆኗል፡፡ የደከመች የተጎዳች በኮንትራት ሰራ እንደመጣች የገለጸችልን እህት የካፍቴሪያ መዘጊያ ሰአት ደርሶ እንዳስገባናት ከግቢ እንድትዎጣ የጸጥታ አስከባሪው ወንድም ሲማጸነን በግቢው ማንም እንዳያድር የተላለፈውን መመሪያ እያስታወሰ ነበር፡፡ ወንድማችን ከስራው ማፈናቀል አልፈለግንምና ደግፈን እንዳስገባናት ደግፈን ከቆንስሉ በር አስቆጣናት ! በቃ መመሪያ ፤ ህግ ነው ተባልን ! . . . ምሽቱ ነጉዶ እኩለ ሌሊት ሲቃረብ የቀረነው ጥቂት ወንድሞች ብቻ ነበርን ! እናም ወደ ቆንስል መስሪያ ቤት ሃላፊዎችና ወደ ሚመለከታቸው ሃላፊዎች ያደርገነው ያልተቋረጠ ግንኙነት የሰመረ ነበር፡፡ መኖሩ በስም እንጅ በአካል የሌለው የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ የቅርብ ቀን ተቀጣሪ ወንድም ጉዳዩን ባስረዳንው ቅስበት እየፈላች የምታስቸግረውን መኪና በብልሃት እየነዳ መድረሱን የገለጸልኝ ከቀጠሮየ ደርሸ ጉዳዩን ልከታተል ደግሜ ወደ ቆንስሉ በር ጎራ ስል ነበር ፡፡ እናም ከቆስንሉ በር ምግቧን ከጉልበቷ ላይ ያደረገችው እህት መብላቱን ትታ እንቅልፍ ያዳፋት ይዟል፡፡ አንገቷም ወደ ደረቁ የስሚንቶ ግድግዳ እያስደገፈች አረፍ ለማድረግ ስትታገል አንገቷ መልሶ እጥፍ እያለ ትነቃለች. . . ይህንን ስቃይ ማየት ከሁሉም በላይ ከበደኝና አህመድን የሳውዲውን ጠባቂና የኮሚኒቲውን የሰጥታ አስከባሪ ካሉበት ትቸ ወደ ቤቴ አመራሁ ! . . . ብዙም ሳይቆይ በእኔ እግር ጠቋሚ ወንድም ” የዚህችን ልጅ መጨረሻ ሳላይ ወደ በቴ አልገባም !” በሚል ተመልሶ መምጣቱን ስማሁ ! ጉዳዩን እየተከታተለ እንደሚነግረኝ ወንድም ከሌሊቱ 8፡00 በኋላ አዲስ የመጡትን የቆንስል መስሪያ ቤቱ ዲፕሎማት ጨምሮ አቶ ሸሪፍና ሌሎች ሰራተኞች በቦታው በመገኘት አንቡላንስ በመጥራት ያደረጉት ጥረት ቢሰናከልም አከታትለው በወሰዱት ጠበቅ ያለ ንግግርና የመብት ማስጠበቅ እርምጃ ጥለዋት የሄዱት የቀይ ጨረቃ ማህበር አንቡላንስ ሰራተኞች መልሰው በመምጣት ይህችን እህት ወደ ህክምና ማድረሳቸው በአይኑ የተመለከተ ወንድሜ በደስታ ሲገልጽልኝ እንዲህ ነበር ያለኝ ” ባልለመድነው የዲፕሎማቶች ትብብር ዛሬ ገና ኮራሁ ! ” ነበር ያለኝ . . . እኔም ኩራት ተሰማኝ ተስፋ ! . . . ይህች እህት መትረፏን ባናውቅም ፤ በዚያች ምሽት ያንጎላቸችውን እንቅልፍ ወደ የምትጨርስባትን ትራስ አግኝታ ማደሯ ብቻ በሃዘን የተሰበረ ልቤን ስናት ሰጠው . . . ማታ በአደራ አስተግቻት ያደርኳትን እህት ወደ ቆንስል መስሪያ ቤቱ እንደደረስኩ ደግሞ ወደ ቆስንሉ ግቢ እንዳይገባ የታገደ ወንድም እንዳለ ሰማሁ ፡፡ ሄጀ ፎቶ አነሳሁት ፡፡ የቆንስሉ ፎቶ አንሽም ከበር ላይ ለተዘረረው ወንድም ፎቶ ሲያነሳው ደረስኩና ለምን ጉዳይ ፈልጎት ነው ስል ጠየቅኩ ” አይ እሱማ የመተላለፊያ ደብዳቤ (ሊሴ ፓሴ) ለማዘጋጀት ነው ” ሲል አንድ አስታማሚው ገለጸልኝ ! የማያጠግበውን መልስ ከሃላፊዎቹ አውቀዋለሁና ” ይህን ወንድም ከውጭ መጥቶ ፎቶ ከማንሳት ከቆንስሉ ቢሮ ቢቀር ከግቢው ተጠልሎ ጉዳዩን ለምን አይከታተልም ? ” ብየ ታዛዡን ፎቶ አንሽውን ወንድም መጠየቅ አልፈለግኩም ! በባህር የመጣው ወንድም የሚያውቀው አለ . . . ስሙ ይታወቃል ! ግን የሱም ታሪክ ብዙ ያስብላል. . . ጊዜው ይሮጣል . . . እኔም እግር ጥሎኝ ላፍታ የታዘብኩት የማለዳ ወግ ቸር ያሰማን ቸር ያሳየን ብየ በተስፋ ወጌን ልቋጭ ! !

ቸር ያሰማን

ነቢዩ ሲራክ

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: