ዕውን ኢትዮጵያን የሚመሯት ኢትዮጵያውያን ናቸው?

የኢትዮጵያ ክብር ተቆርቋሪ የግል ተነሳሽ ኮሚቴና ባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር በመሆን ያዘጋጁት ሰላማዊ ሰልፍ አላማ ለፋሺስቱና ለጦር ወንጀለኛው ግራዚያኒ በጣሊያን ሀገር የተገነባውን መናፈሻ ስፍራና ሀውልት ለመቃወም ነው፡፡ ይህ ግለሰብ ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ ታሪክ አይዘነጋውም፡፡

ግራዚያኒ በመርዝ ጋዝ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ጨፍጭፏል፤ ከየካቲት 12 ጀምሮ ለቀናት በዘለቀው የበቀል ጭፍጨፋም በአካፋ ሳይቀር በአዲስ አበባና በአካባቢዋ ያሉ ኢትዮጵያውያንን በግፍ ጨፍጭፏል፡፡ ግራዚያኒ በወቅቱ በሰጠው ትዕዛዝ የፋሺስት ወታደሮች ህይወት ያለውን ተንቀሳቃሽ ፍጥረትን ሁሉ ገድለዋል፡፡ ይህ እሩቅ በማይባል ጊዜ የተፈፀመ ድርጊት ነው፡፡
የኢህአዴግ ባለስልጣናት ለእንዲህ አይነቱ ጨፍጫፊ የተገነባን ሀውልት ለመቃወም በወጡ ዜጎች ላይ የወሰዱት የእስር ተግባር እውን ኢትዮጵያን የሚመሯት ኢትዮጵያውያን ናቸው? አስብሎናል፡፡ ኢህአዴግ በስልጣን ዘመኑ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ በተደጋጋሚ ጥፋት ፈፅሟል፡፡ ሀገራችንን የባህር በር ማሳጣትን ጨምሮ ሀገራዊ ስሜትን አንኳሶ ጠባብ የብሔር ስሜት እንዲንሰራፋ አድርጓል፣ ታሪክን ለስልጣኑ መደላድል ሲል በራሱ መንገድ የሚያዘጋጀው የኢህአዴግ መንግስት ኢትዮጵያን ጠፍጥፎ እንደሰራት ሁሉ ደርግን ለመጣል ካደረገው ትግል ውጪ ያለውን የአርበኞች ተጋድሎ እውቅና ሲሰጥ አይታይም፡፡
መንግስት ለፋሽስቱ ሩዶልፍ ግራዚያኒ የተገነባውን ሀውልት በመቃወም የወሰደው እርምጃ አለመኖሩ ሳያንስ ግራዚያኒን ለማውገዝ የወጡ ዜጎችን በመደብደብና በማንገላታት ማሰሩ አሳፍሮናል፡፡ ለዜጎቻቸው እና ለሚመሯት ሀገር ክብር የማይሰጡ ይልቁንም የጦር ወንጀለኛና ፋሺስትን ለመቃወም የወጣን ዜጋ ማሰርራቸው የኢህአዴግ ባለስልጣናት ወገንተኝነታቸው ለዜጎቻቸው ነው ወይስ ለፋሺስት? የሚል ዘግናኝ ጥያቄ እንድንሰነዝር ያስገድደናል፡፡
በሰልፉ ላይ የተገኙት ሀገር ወዳድ ዜጎች በማን አለብኝነት ሲታሰሩ ድባደባ ተፈፅሞባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የታሳሪዎቹን የኢሜይልና የማህበራዊ ገፅ የይለፍ ቃል (password) በግዳጅ የሚቀበሉ የደህንነት ሀይሎች ተልከውባቸዋል፡፡ ይህን ቅጥ ያጣ አንባገነናዊ ድርጊት የፈፀመው ወይም እንዲፈፀም ትዕዛዝ የሰጠው አካል ማንነት ተጣርቶ የማስተካከያ እርምጃ ሊወሰድ ይገባዋል፡፡ በየምክንያቱ ዜጎችን ማሰር የለመደው አንባገነኑ የኢህአዴግ መንግስት ምን ያክል ኢትዮጵያዊነትን እየተዋጋ እንዳለም የሚያሳይ ድርጊት ነው፡፡ መሰረቱ ዜጎች በማንኛውም ጉዳይ ላይ የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ ሰልፍ ማድረግ እንደሚችሉ ህገመንግስቱ ደንግጓል፡፡ ይህን መብት ዜጎች እንዳይጠቀሙ ያፈነው መንግስት፣ ኢህአዴግን የሚደግፉ አልያም በራሱ ከተጠሩ ሰልፎች ውጪ ዜጎች እንዳይሳተፉ በአሰራር ከልክሏል፡፡ ይህ የመብት ረገጣ ከመሆኑም በላይ በዜጎች መካከል 1ኛ ደረጃና 2ኛ ደረጃ ዜግነትን ያስቀመጠ ነው፡፡
የኢህአዴግን ባናውቅም፣ እኛ ኢትዮጵያውያን በቅኝ ገዢዎች የተዋረደ ስነልቦና የለንም፡፡ ሆኖም የግል ጥቅማቸውን ለማደላደል ሲሉ ለቅኝ ገዢ ጠላቶቻችን ያደሩ ባንዳዎች እንደነበሩ ታሪክ በጥቁር መዝገቡ ሸክፎታል፡፡ ይህን አሳፋሪ ተግባር በጣሊያን ወረራ ወቅት የፈፀሙ ኢትዮጵያውያን ለልጅ ልጆቻቸው የሚያስተላልፉት አንገት ቀና የሚያደርግ ታሪክ አይኖርም፡፡
በዚህም ዘመን ተመሳሳይ ክህደት የሚፈፅሙ አካላት መኖራቸው አይጠረጠርም፡፡
የኢህአዴግ መንግስት በይፋ ለጦር ወንጀለኛውና ለፋሺሽቱ ሩዶልፍ ግራዚያኒ የተሰራውን ሀውልት በይፋ ካለማውገዝ ባለፈ ለተቃውሞ የወጡትን ኢትዮጵያውያን በግፍ የማሰሩን ምክንያት ስንመረምር አንድ መራራ እውነት እንረዳለን፤ ይኸውም ጣሊያን ለኢህአዴግ መንግስት ዋንኛዋ ለጋሽ ሀገር መሆኗ ነው፡፡ ይህ የኢህአዴግ መንግስት ተግባር በስልጣን ዘመኑ በኢትዮጵያዊነት ላይ ከፈፀማቸው ክህደቶች እኩል በታሪክ ጥቁር መዝገብ የሚቀመጥ ይሆናል፡፡

Image

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: