ሕዝብ እየጠበቀ ነው!!!!

Image

የኢትዮጵያ ሕዝብ መንግሥት በርካታ ጉዳዮቹን እንዲፈጽምለት ለሚያቀርባቸው ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጠው ቢፈልግም ሐዘን በማጋጠሙ፣ እስኪረጋጉ፣ ጉባዔያቸውን እስኪያካሂዱ፣ እስኪተካኩና እስኪገማገሙ እንጠብቅ እያለ በትዕግሥትና በተስፋ ቆይቷል፡፡

አሁን ግን ኢሕአዴግ ጉባዔውን አጠናቋል፡፡ የውስጥ ችግሬን ፈትሼያለሁ፣ ገምግሜያለሁ፣ ተረድቻለሁ ብሏል፡፡ ዕቅዱንም መርምሬያለሁ ብሏል፡፡ በቀጣይ የሚካሄዱ ሥራዎችን ለይቼ አውቄያለሁ ብሏል፡፡ በወጥነቱ ላይ ሕዝብ ጥያቄ እያነሳ ቢሆንም መተካካት አካሂጃለሁ ብሏል፡፡ በምን ደረጃ የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ቢችልም ሙስናንና ኪራይ ሰብሳቢነትን አውግዤያለሁ ብሏል፡፡ ሕዝብን ለማገልገልና ድህነትን ለማጥፋት ቃል እገባለሁ ብሏል፡፡

ከአሁን በኋላ ጨርቄን ቅሌን የለም፡፡ ሕዝብ ኢሕአዴግ ከሚመራው መንግሥት የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሕ፣ የሰብዓዊ መብት ክብርና ልማት እየጠበቀ ነው፡፡ በተግባር፡፡

ኢሕአዴግ የሙስናንና የኪራይ ሰብሳቢነትን ችግር ስፋትና ጥልቀት አሳንሶ ወይም ከእነእከሌ የተሻለ ነው እያለ ተረጋግቶ እንዳያየው ሊጠነቀቅ ይገባል፡፡ አሳፋሪ፣ አስፈሪና አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በሙስና ምክንያት ኢሕአዴግም መንግሥትም ተቦርብረዋል፡፡ መንግሥትንና ሕዝብን ከማገልገል ይልቅ ለግል ጥቅም፣ ለባለገንዘብ ያደሩና የተንበረከኩ ተላላኪዎችና ጉዳይ አስፈጻሚዎች በመንግሥት ውስጥ ተበራክተዋል፡፡ ተሰግስገዋል፡፡ የበላይነትም እየያዙ ናቸው፡፡ በዚህ ደረጃ መንግሥት አይቶና አምርሮ ከባድና ፈጣን ዕርምጃ እንዲወስድ ሕዝብ እየጠበቀ ነው፡፡ የተሟላ ዕርምጃ በአስቸኳይ!

ሁሉም ችግር ከሙስና ጋር ብቻ የሚያያዝ አይደለም፡፡ በቂ አቅም፣ ዕውቀትና አመለካከት አለመኖሩም ሕዝብን እየጎዳ ነው፡፡ አገርን እያዳከመ ነው፡፡ ስለሆነም ደካማውን በመቀየርና አቅም ያለው ሊሠራበት በሚችለው ወንበር ማስቀመጥ የግድ ይላል፡፡ ከባድ፣ ፈጣንና አስቸኳይ ለሆኑ ሥራዎች መንግሥት ብቁና ንቁ ሰዎችን ማስቀመጥ አለበት እያለ ሕዝብ እየጠበቀ ነው፡፡ የተሟላ ዕርምጃ በአስቸኳይ!

የኑሮ ውድነት እየከበደና እየተካበደ ነው፡፡ በደመወዝ የማይሸፈን ሕይወት እየተመራ ነው፡፡ በዚህም የኑሮ ውድነት የሚቀንስበትና የኅብረተሰቡ አቅም የሚጨምርበት ሁኔታ እንዲፈጠር ሕዝብ ከመንግሥት እየጠበቀ ነው፡፡ የተሟላና ጠንካራ ዕርምጃ በአስቸኳይ!

አንዳንዱ አሠራር አለመሻሻል ብቻ ሳይሆን በሚያሳፍር ደረጃ ወደኋላ እየተንሸራተተ ነው፡፡ በፓስፖርት አሰጣጥ ሥርዓት የኢምግሬሽን መሥሪያ ቤት በጣም የሚደነቅ ነበር፡፡ ሥርዓት ነበረው፡፡ ከጥንቃቄ ጋር ፍጥነት ነበረው፡፡ አሁን ለፓስፖርት አርባ ቀን፣ ስድሳ ቀን ጠብቁ ሲባል እንዴት ነው ነገሩ ያሰኛል፡፡ ከመሻሻል ይልቅ እንዴት ወደኋላ ይመለሳል ያሰኛል፡፡

የግሉ ፕሬስ በዋነኛነት በመንግሥት ማተሚያ ቤት የሚታተም ነው፡፡ አሁን ግን በመንግሥት ማተሚያ ቤት ጋዜጣና መጽሔት የመረጃ ማቅረቢያ መሣሪያ መሆናቸው ተረስቶ ታትመው ለሕዝብ የሚደርሱበት ቀን ገጠመኝ እየሆነ ነው፡፡ ሕዝቡ እሑድ በጠዋት ጋዜጣ ለመግዛት ወጥቶ በብዛት አጥቶ የሚመለስበት አጋጣሚ እየበዛ ነው፡፡ የእሑድ ጋዜጦች የማክሰኞ ጋዜጣ እየሆኑ ናቸው፡፡ ከመሻሻል ወደኋላ መጎተት ሲታይ መንግሥት እንዴት አይደነግጥም? ለመፍትሔ አይሯሯጥም እያለ ነው ሕዝቡ፡፡ በዚህ ዙሪያም ሕዝብ መሻሻልና መፍትሔ እየጠበቀ ነው፡፡ የተሟላ ዕርምጃ በአስቸኳይ!

የግል ቢዝነስ ዘርፉም እንደዚሁ እንዴት ነው ነገሩ የሚሰኝበት በርካታ ችግሮች እያጋጠሙት ነው፡፡ የባንክ ብድር ለማግኘት በእጅጉ እየተቸገረ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ችግር እያለ ‹‹በሽበሽ ነው›› የሚል ቀልዳቀልድ እያጀበው ነው፡፡ ከውጭ የሚመጡ ዕቃዎች ከጂቡቲ አዲስ አበባ መቼ እንደሚደርሱ አይታወቅም፡፡ በጂቡቲ ወደብና በደረቅ ወደብ ስንትና ስንት ቢሊዮን ብሮች የፈሰሱባቸው ንብረቶች ተከምረውና ባለቤታቸው ሳይታወቅ ሲቀር እንዴት ነው ወዴትስ እየተሄደ ነው እያሰኘ ነው፡፡ ኮንትራክተሮች ሕንፃና መንገድ ገንብተው አጠናቀው ከፍያቸው ግን እየዘገየ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሲታይ መንግሥት ቀረብ ብሎ ችግሩን አይቶ አስቸኳይና የተሟላ ዕርምጃ እንዲወስድ እየተወተወተ ነው፡፡ በዚህም ሕዝብ የተሟላና አስቸኳይ ዕርምጃ እየጠበቀ ነው፡፡ በተግባር!

ፍትሕ እየተጓተተና እየጠፋ ነው፡፡ የተጀመረ ጉዳይ መቼ ተጀምሮ መቼ እንደሚያልቅ አይታወቅም፡፡ ዓመታት ይፈጃል፡፡ በተዋረድ ያሉት የፍትሕ ደረጃዎች የሚገዙት በሕግ ስለመሆኑ መተማመኛ የለም፡፡ ማስረጃና መረጃ ዋጋ ቢስ የሚሆኑበት ሁኔታ ላይ ነን፡፡ ገንዘብ፣ ግንኙነት፣ ኔትወርኪንግና የቴሌፎን ችሎት የበላይነት እየያዙ ናቸው፡፡ ተስፋ መቁረጥ እያስከተለ ነው፡፡ መንግሥት በአስቸኳይና በልዩ ትኩረት ፍርድ ቤቶችን ያስተካክል፣ ያዋቅር፣ ያጠናክር፡፡ ሕዝብ እየጠበቀ ነው፡፡ በአስቸኳይ! በተሟላ ተግባር!

ሕዝብ ብዙ ነገሮችን እየታዘበ ነው፡፡ ይህችን አገር እየመራት ያለው ማን ነው? የሚል ጥያቄም እያነሳ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ለምን ጠንካራና የኮራ አይሆንም? የሚል ጥያቄ የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ እየሆነ ነው፡፡ ስድስት መቶ ብር አልከፈላችሁም ተብለው ዜጎች ሲከሰሱና ሲታሰሩ፣ ስድስት መቶ ሚሊዮን ብር ያልከፈሉ ግን እንኳን ሊከሰሱና ሊጠየቁ ጭራሽ ሲሰገድላቸውና ልዩ ፕሮቶኮል ሲዘጋጅላቸው ሕዝብ እየታዘበ ነው፡፡ ሚኒስትሮችና ኮሚሽነሮች ተሸማቅቀው ተቀምጠው ባለገንዘብ ሲፈነጭ ሕዝብ እየታዘበ ነው፡፡ ይህችን አገር እያሽከረከራት ያለው ማነው? እያለ ነው፡፡ ባለሥልጣናት ለምን ከአሽከርነትና ከተላላኪነት አይላቀቁም? እያለ ነው፡፡ ለምን አይፀዱም? ለምን ኮራ አይሉም? እያለ ነው፡፡

ለዚህም ኃይለኛ ፈጣን፣ ቆራጥና ፅዱ ዕርምጃ ሕዝብ እየጠበቀ ነው፡፡ የተሟላ! በአስቸኳይ! በተግባር!

አሁን ኢሕአዴግ ጉባዔውን ጨርሶ ወደ ቀጣይ ተግባሩ እየገባ ነው፡፡ መልካሙን እንመኛለን የአገር ጉዳይ ነውና፡፡ ግን ለሕዝብ በአስቸኳይ ፈጣንና አኩሪ መልስ ይሰጥ፡፡
ሕዝብ እየጠበቀ ነውና!

Ethiopian Reporter

 

 

Advertisements

One thought on “ሕዝብ እየጠበቀ ነው!!!!

  1. daneil.zeleke April 3, 2013 at 12:49 am Reply

    the only good thing as far as we know that,people of ethiopians they know what they want and they know what they need.so basical change is the only way to bring new vision.olso freedom must be our priority.What is freedom of expression? Without the freedom to offend, it ceases to exisit,

    Like

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: