ዞምቢዎቹ እየመጡ ነው!

394711_184013551696255_1365830121_n
(ተመስገን ደሳለኝ)

ሐምሌ 11 ቀን ዓ.ም. በታተመችው በ‹‹አዲስ ነገር›› ጋዜጣ ወዳጄ መስፍን ነጋሽ ‹‹ዞምቢዎቹ›› በሚል ርዕስ ዛሬም ድረስ ከህሊናዬ ያልጠፋ ድንቅ ጽሁፍ አስነብቦን ነበር (የዚህ ፅሁፍ ሃሳብም ከዚሁ የተናጠቀ ነው)፡፡ ይኸ ከሆነ ድፍን ሶስት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት ብቻ ቀርቶታል፡፡ ‹‹አዲስ ነገር››ም ወደ ታሪክነት ከተቀየረች ሁለት ዓመት አልፏታል፡፡ ለምን? …ዞምቢዎቹ ድል ስለነሷት፤ እንዴት? ማንም ዞምቢዎቹን ድል አድርጎ ስለማያውቅ፡፡ ዞምቢ ምንድር ነው? ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ እንዲህ ገልጿቸዋል፡-
‹‹አፈታሪክም ሆነ ታሪክ እንደሚለው ዞምቢዎች የሙታንን መንፈስ በሚጠሩ ‹የሃይማኖት› ሰዎች ከመቃብራቸው ይጠራሉ፡፡ ዞምቢዎች ነፍስ የላቸውም፤ የሚንቀሳቀስ አካል እንጂ፡፡ እናም እግራቸውን እየጎተቱ፣ የተቦደሰ አካላቸውን እንደያዙ ጤነኞቹን ሕያዋን ያሳድዳሉ››
…ግና! ተወዳጇ ጋዜጣ የዞምቢዎቹ ሰለባ ከመሆን አላመለጠችም፡፡ ዞምቢዎቹ በጋዜጣዋ አዘጋጆች ላይ የሀሰት ክስ ፈብርከው በመወንጀል ለስደት ዳረጓቸው፡፡ በዚህ የክፋት ስራ ብቻም አላቆሙም፤ ቀጥለውም ‹‹አዲስ ነገር ጋዜጣ የተዘጋው ከስሮ ነው›› ሲሉ ቅንጣት ታህል ሀፍረት አልነበራቸውም፡፡ ዞምቢዎች እንዲህ ናቸውና፡፡
ዞምቢዎች መጀመሪያውንም የሚገለጡት በሞተ ልብ፣ በበሰበሰ ህሊና፣ በቆሸሸ ስብዕና በመሆኑ መልካም ነገር አይታያቸውም፤ አይስማማቸውም፡፡ ፍሬ ሲይዝ ካዩ ከስሩ ይነቅሉታል፡፡ የፊታውራሪ ተ/ሀዋርያት ተ/ማርያም ግጥም የዞምቢዎቹን ዓላማ ለመግለፅ ጉልበት አለው፡-
‹‹አንድ ነገር ሲያምር ያየሁት እንደሆን
እሱን ካላጠፋሁ እንቅልፍ አይወስደኝም!›› ከቶ ምንም ቢሆን
ዓላማቸው ሁሉንም ዞምቢ ማድርግ ነው፤ ህሊናን ወደ ሙት (በድንነት) መቀየር፡፡ ለዚህም ነው ያለው ብቸኛ አማራጭ ከዞምቢዎቹ መሸሽ የሆነው፤ ማምለጥ፤ መጥፋት-ዞምቢዎቹ ወደማይደርሱበት ሩቅ ስፍራ፡፡ …መስፍን ነጋሽም ሆነ ባልደረቦቹ ሀገራቸውን ዳግም የማይረግጡበት ምክንያት ይህ ነው፤ ሌላ አይደለም፡፡
ዛሬ ዞምቢዎቹ በጣም እጅጉ በዝተዋል፡፡ ጥቃታቸውም ረቂቅ ሆኗል፡፡ ስልጣን ወይም ገንዘብ እስካስገኘላቸው ድረስ ህሊና፣ እውነት የሚባል ነገር ለዞምቢዎች ቦታ የለውም፡፡ የህይወት መርሀቸውም በሀሰት ወንጅል፣ በሀሰት ፍረድ፣ በሀሰት ስም አጥፋ፣ አቆሽሽ፣ ከእውነት ራቅ፣ ውሸት ከአንተ አትራቅ፣ ንፁሀንን ጥላ፣ የክፋት ስራህ ምድራዊ ጥቅምን እስካሳፈሰህ ድረስ፣ ትርፍ እስካስገኘልህ ድረስ፣ ኑሮህን እስከለወጠልህ ድረስ፣ ገበያውን እስካደራልህ ድረስ …ሰው ባያየኝ፣ አምላክ ያየኛል ብለህ አትጨነቅ፤ የአማልክትን ስም እየጠራህ አታልል፣ አጭበርብር፣ ሀብትን አከማች የሚል ነው፡፡
ዞምቢዎቹ ጥቅማቸውን ሲያሳድዱ ክፋትን ለመፈፀም የማይፈሩት በሰማይ ያለውን አምላካቸውን ብቻ አይደለም፤ ቤተሰብ፣ ጓደኛ፣ ጐረቤትንም ነው፡፡ ይታዘቡኝ ይሆን? ይጠየፉኝ ይሆን? ብለው አይሳቀቁም፡፡ አካላቸው ባማረና በንፁህ ልብስ መሸፈኑ ዞምቢነታቸውን የሚጋርድ ስለሚመስላቸው በአደባባይ ሲውሉ አይሸማቀቁም፡፡ ስለራሳቸው ብዙ በማውራት ህያው ለመምሰል ይሞክራሉ፡፡ ጠልፈው የጣሉትን ማህበረሰብ፣ ነክሰው ያቆሰሉትን ህዝብ… እያገለገሉት እንደሆነ በአሰልቺና ደረቅ ወሬያቸው ይነግሩታል፡፡ ዞምቢዎቹ በግንባራቸው ላይ የተቸከቸከውን የግፉአን እንባ በአይናችሁ እያያችሁ፣ የሚነግሯችሁን ‹‹ቅድስና›› እንድታምኑ፣ የሚፅፉላችሁን ‹‹እውነት›› እንድትቀበሉ እየደሰኮሩ ያሰለቿችኋል፡፡ መስፍን ነጋሽ ‹‹በየቀኑ በተግባራቸው የሚበሰብሱት ዞምቢዎች፣ በየቀኑ በተግባራቸው የሚለመልሙ ሰዎችን ለማየት አይፈቅዱም፤ ስለዚህም ያሳድዷቸዋል›› ሲል ዞምቢዎቹ ወደ አዲስ ነገር እየቀረቡ እንደነበረ አስቀድሞ ነግሮናል፡፡ ዞምቢዎች እውነትን እንዲረዱም ሆነ ወደ ህሊናቸው እንዲመለሱ ማድረግ አይቻልም፤ ህሊናቸው በስብሷል- ሊለመልም በማይችልበት ደረጃ፡፡
በፍትህ ‹‹ካባ›› የተሸፈኑ ዞምቢዎች ስርዓቱ እስካዘዛቸው ድረስ በሀሰት ለመወንጀልም ሆነ ለመፍረድ ቅንጣት ታህል አያመነቱም፡፡ ለዞምቢዎቹ ስነ-ምግባር ፋይዳ የለውም፤ የሀሰት ፍርድ ሰጥተው ህፃናት ልጆች ጎዳና ቢወጡ፣ አረጋዊያን ያለ ጧሪ ቀባሪ ቢቀሩ፣ ትዳር
ቢናጋ፣ ማህበራዊ ስርዓት ቢፈራርስ… ደንታ አይሰጣቸውም፡፡ በዞምቢዎች ዓለም ሳዲስት (በሌላው መከራና ስቃይ የሚፈነድቅ) መሆን አዋቂነት ነው፤ ስኬት ነው፤ ማሸነፍ ነው፡፡
ካለፉት ሰላሳና አርባ አመታት ወዲህ በየትኛውም የሀገሪቱ ጓዳ ጎድጓዳ ዞምቢዎችን ማየት አዲስ አይደለም፡፡ የሀገር ጉዳይ እና መልካም ስራ ለዞምቢዎች አይጥማቸውም፡፡ ዞምቢ ለመሆን ባለመፍቀዳችሁ ያሳድዷችኋል፡፡ ለህዝብ የሚጠቅም አጀንዳ ይዛችሁ በውጣ ውረድ
ብትንገላቱ ዞምቢዎቹ ግድ አይሰጣቸውም፤ አላማቸው ሁሉንም ዞምቢ ማድረግ ብቻ ነውና የማይለጥፉባችሁ የሀሰት ውንጀላ፣ የማያወሩባችሁ አሉባልታ የለም፤ ስብዕናችሁን ለማዋረድ፣ ዕውነቶቻችሁን ለማልኮስኮስ ሲሉ የፈጠሩባችሁን ወሬ ያወሩባችኋል፤ ያስወሩባችኋል፣ ሁላችሁም ወደዞምቢነት እስክትቀየሩ ድረስ፡፡ የዞምቢ ትውልድ እስኪመጣ ድረስ፡፡
ዞምቢዎች ሞገስ ባገኙበት መንግስት የማያምኑበትን ሃሳብ መቃወም ክልክል ነው፤ መናገር አይቻልም፤ መተቸት ወንጀል ነው፤ መስማት ብቻ፡፡ ህልማቸው በድን ማህበረሰብ መፍጠር ነውና ትውልዱን ከዞምቢነት መንፈስ ለመከላከል የሚታትሩትን በጭራሽ በመንገዳቸው እንዲቆሙ አይሹም፡፡ ያሸማቅቋቸዋል፣ ያጣጥሏቸዋል፣ ያስፈራሯቸዋል፣ ይፈርጇቸዋል… በመጨረሻም በሀሰት ከስሰው ወደጨለማ ይወረውሯቸዋል፡፡ …አንድ ነገር ሲያምር ያዩ እንደሆነ …እንቅልፍ አይወስዳቸውም፡፡
ዞምቢዎች በብሔር የተገደቡ አይደሉም፡፡ ሁሉም ብሔር ውስጥ አሉና፡፡ ሀይማኖት የላቸውም፤ ሁሉም ሃይማኖት ውስጥ አሉና፡፡ የተለየ የፖለቲካ አመለካከት የላቸውም፤ ሁሉም ፓርቲዎች (ገዢውም ተቃዋሚውም) ውስጥ አሉና፡፡ ዞምቢዎች ከትልቁ መንግስታዊ ስልጣን እስከ መንደር አስተዳደሪ ድረስ አሉ፡፡ በሞያም ተለይተው አይመደቡም፤ በየትኛውም የሙያ ዘርፍ ብትሰማሩ ተጠራርተው ይመጣሉ …እግራቸውን እየጎተቱ፣ የተቦደሰ አካላቸውን እንደያዙ ጤነኞቹን ሕያዋን ለማሳደድ፡፡
ዞምቢዎቹ ምርጫ ያጭበረብራሉ፤ እንዲጭበረበርም ያደርጋሉ፡፡ ስልጣንና ጥቅም የሰጣቸውን ሁሉ ያገለግላሉ፣ ህያዋንን እየበከሉ፤ በቁም እየገደሉ፤ ስጋን እያረከሱ፣ ነፍስን እያሳደፉ፡፡ ዞምቢዎች ፈጣሪ፣ ህሊና እና እውነት የሚባሉ የሰው ልጅ የቆመባቸውን መሰረቶች አያውቋቸውም፤ ቢያውቋቸውም ደንታ አይሰጣቸውም፡፡ ዞምቢዎቹ ህግ መጣስ እንደማይፈሩ፣ እምነት ማጉደል እንደማያስጨንቃቸው፣ መዋሸት ጀብድ እንደሚመስላቸው ሁሉ መጪው ትውልድ የሚባል ሀገር ተረካቢ እንዳለ ለአፍታም ቢሆን ትዝ አይላቸውም፡፡ ቀጣዩን ትውልድ ማሰብ ከዞምቢነት መውጣት ነው፡፡ እነርሱ ደግሞ የዞምቢነት ማንነቶቻቸው ውስጥ ደስታን አግኝተዋልና ከዚህ የረከሰ ድሎታቸው የሚቀሰቅሳቸው ‹‹የሚቀጥለው ትውልድስ?›› መሳይ ሃሳቦችንም ሆነ አሰላሳዮችን ከፊታቸው ያርቃሉ፡፡
በመከላከያ ውስጥ ያሉ ዞምቢዎች በስነ ምግባር የታነፁ የሠራዊቱን አባላት አሳደው ወደ ዞምቢነት ይቀይራሉ፤ በደህንነት ተቋሙ ውስጥም ሁሉም አባል ታማኝነቱ ለስርዓቱ ብቻ እንዲሆን ያስገድዱታል፡፡ ‹‹ህግ አስከባሪ ፖሊስ ነን›› የሚሉ ዞምቢዎችም ህገ-መንግስቱንና ህጎችን
ማክበር፣ የህግ የበላይነትን መጠበቅ እና ህዝብን ማገልገል ህያው ስለሚያደርጋቸው ይጠሉታል፡፡ ከመካከላቸው ይህን ለማድረግ የሚጥሩትንም አሳደው ወደ ዞምቢነት ይቀይሯቸዋል፡፡
በእያንዳንዱ መንግስታዊ ተቋማት ውስጥ ዞምቢዎቹ ሁሉንም ኃላፊነት ተቆጣጥረውታል፡፡ የስራ ዕድገትንም ሆነ የትምህርት ዕድልን ዞምቢ መሆን ያልፈቀደ ሰራተኛ ሁሉ ታታሪና ምስጉን ቢሆንም አያገኛትም፡፡ ዞምቢዎቹ የስራ ሰዓታቸውን ከቢሮ ቢሮ ወሬ ሲያመላልሱ፣ አሉባልታን ሲያደሩ፣ ሲያሙ፣ ሲወነጅሉ፣ ሲያስወነጅሉ፣ ሲያራክሱ፣ ሲያቆሽሹ ይጨርሱታል፡፡ ኪነ-ጥበብም ለዞምቢዎቹ በምርኮነት ካደረ ሰንብቷል፡፡ ልሂቃኖቻችንም ዞምባዊነትን ተለማምደው ከጨረሱ ዘመን አልፏል፡፡ ከምሁራዊ በድንነታቸው የሚያነቃቸውንም አግልለዋል፡፡
‹‹የሚዲያ ፍቃድ መስጠትና መንሳት የኔ ነው›› የሚለውን መስሪያ ቤት የሚያሽከረክሩት ዞምቢዎች፣ በሌሎች ተቋማት ከሚገኙ ዞምቢዎች የበለጠ ዞምቢ መሆናቸውን ለማሳየት የማይፈበርኩት ወንጀል፣ የማያሴሩት ሴራ፣ የማይንዱት ማህበራዊ እሴት የለም፡፡ ሲዋሹ፣ ሲወነጅሉ፣ ሲፈቅዱ፣ ሲያፍኑ፣ አገርና ህዝብ የሚበድሉ አይመስላቸውም፤ ቤተሰብ፣ ጎረቤት፣ ጓደኛ… ይታዘበኝ ይሆን? ልጆቼ ቢጠይቁኝስ ምን እመልሳለሁ? የሚል ስጋት የለባቸውም፤ ሙት ህሊና የተሸከሙ ናቸውና፡፡
በመንግስትም ሆነ በግል ሚዲያ ውስጥ ዞምቢዎች አሉ፡፡ ግና በግልፅ ‹‹የስርዓቱ ደጋፊ ነኝ›› በሚሉትም ሆነ ‹‹ነፃ›› እንደሆኑ ለማስረዳት በሚያደነቁሩን ዞምቢዎች መካከል የአካሄድ ካልሆነ በቀር የዓላማ ልዩነት የለም፡፡ ሁለቱም ለስርዓቱ የሚጎረብጥና ነፃነቱን የማያስነካ ሚዲያ ከተመለከቱ ወደዞምቢነት ለመቀየር ያሳድዱታል፤ ድምፅ ለሌላቸው ድምፅ የሚሆን ሚዲያንም ይረባረቡበታል-ወደ ዞምቢነት ለመቀየር፡፡ ዞምቢ ማድረጉ ካልተሳካላቸውም ‹‹ስቀሎ፣ ስቀሎ…›› እያሉ ወደቀራኒዮ ያጣድፉታል፡፡
የስርዓቱ ደጋፊ በመሆናቸው የሚኩራሩም ሆነ በ‹‹ነፃ ሚዲያ›› ስም የሚያምታቱ ጥቂት መጽሔቶች እና ጋዜጦች ‹‹ፍቃድ ሰጪ››ው መስሪያ ቤት የሰጣቸውን ተልዕኮ ለማሳካት …እግራቸውን እየጎተቱ፣ የተቦደሰ አካላቸውን እንደያዙ ጤነኞቹን ሕያዋን ያሳድዳሉ፤ በጥርሳቸው ነክሰው አድምተው በብስባሽ መንፈሳቸው ለመበከል በአደባባይ ሲንቀሳቀሱ ፈጣሪንም፣ ህዝብንም አይፈሩም፡፡
ዞምቢዎቹ ሲያጠቁ ተደራጅተው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ‹‹ፍትህ ጋዜጣ››ን ሲያፍኑ መጀመሪያ እነአዲስ ዘመንና አይጋ-ፎረምን የመሳሰሉ ሚዲያዎች አዘጋጆቹን ‹‹አሸባሪዎች››፣ ‹‹የአልሸባብ ወኪሎች›› በማለት ወንጅለው መንገዱን ጠረጉ፤ ቀጥሎም ፍትህ ሚኒስቴር በደብዳቤ ታትሞ ያለቀ (ክፍያ የተፈፀመበት) ህትመት አገደ፤ ተከተለና ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ለማተም ፍቃደኛ እንዳይሆን ተደረገ፡፡ በዚህ መንገድም ጋዜጣዋን አፈኑ፡፡ ዞምቢዎች እንዲህ ናቸው፣ በየትኛውም ጠርዝ መቆማቸው ሳያግዳቸው የነገሱባቸውን ተቋማት ወደ በድንነት ቀይረው ለአላማቸው ይተባበራሉ፡፡ ‹‹ህያው›› በሙሉ ተወግዶ ዞምቢ ብቻ እስኪቀር አያርፉም፡፡ ‹‹አዲስ ታይምስ››ም በተመሳሳይ መልኩ ነበር-የዞምቢዎች ሰለባ የሆነችው፡፡ ‹‹ልዕልና››ንም የማጥፋቱ ዘመቻው ተጀምሯል፡፡ ሂደቱ ተመሳሳይ
ነው፣ ልዩነቱ በዚህኛው ዘመቻ በ‹‹ግል›› ስም የሚንቀሳቀሱ ዞምቢዎችም ተሰላፊ መሆናቸው ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ዞምቢዎች ጋዜጣዋን ‹‹የኢህአዴግ ናት›› ሲሉ በመፅሄታቸው ላይ ይፅፉና፣ መንግስት የሚወስደው እርምጃ ከነፃ ፕሬስ አፈና ጋር እንደማይገናኝ ለማሳመን ይሞክራሉ፡፡ ይህንን ተከትሎም እንደተለመደው ብሮድካስት ‹‹ዝውውሩ ህገ-ወጥ ነው›› ሲል ይወነጅላል፡፡
የበሰበሰ ህሊናን እና ስጋን ባማረ ልብስ ሸፍነው አደባባይ የሚውሉ ዞምቢዎች ምን ያህል ርቀት ሄደው እንደሚዋሹ የሚያሳየው ሰሞኑን መንግስታዊው ተቋም እና በ‹‹ግል ስም›› የሚነግዱ መፅሄቶች ‹‹ልዕልና››ን ለማፈን በተቀናጀ መልኩ እያደረጉ ያለው ሙከራ ነው፡፡ ድርጊታቸው ሀሰት፣ ክፋት፣ ጭካኔ፣ ነውረኝነት የተጠናወተው መሆኑን ዞምቢዎቹ ያውቃሉ፡፡ ቢያውቁም ግን ጉዳያቸው አይደለም፡፡ ዞምቢዎች ናቸውና ሁሉንም ዞምቢ ለማድረግ ይፈጥናሉ፡፡ …እግራቸውን እየጎተቱ፣ የተቦደሰ አካላቸውን እንደያዙ ጤነኞቹን ህያውን ያሳድዳሉ፡፡ መስፍን ነጋሽ የዞምቢዎችን አካሄድ እንዲህ ሲል ገልጾታል፡-
‹‹አገር የሚባል ጉዳይ፣ ህዝብ የሚባል ፅንሰ ሀሳብ ተሳስተው እንኳን ትዝ የማይላቸው፤ አገርንና ሕዝብን ማጭበርበርን እንደጀብድ ቆጥረው በየአደባባዩ የሚኮፈሱ ዞምቢዎች በየቀኑ ይፈላሉ፡፡››
‹‹ነፃ ነን›› የሚሉት ዞምቢዎቹ ‹‹ልዕልና ጋዜጣ አጭበርባሪ ነች›› ይሉና የሀሰት ወሬዎችን በየመፅሄታቸው አትመው ያደናግራሉ፡፡ ቀጥሎ
ደግሞ ይህንን ተልዕኮ ለ‹‹ነፃ››ው ሚዲያም የሰጠው የ‹‹አኬል ዳማ›› እና የ‹‹ጃሃዳዊ ሀረካት›› ፊልምም ደራሲ ‹‹ጋዜጣዋ በህገ-ወጥ
መንገድ ነው የስም ዝውውር ያደረገችው›› ይልና ብርሃኗን ድቅድቅ ጨለማ በነገሰበት ዋሻ ውስጥ እንዳትፈነጥቅ ያደናቅፋታል፡፡
ዞምቢዎቹ በቀጣዩ ሳምንት ‹‹ልዕልና››ን ለማጥፋት የወንዝ ዳር መሀላ ፈጽመዋል፡፡ እንደእቅዳቸውም ጋዜጣዋ በሚቀጥለው ሳምንት
አትኖርም፡፡ በመጋቢት 13 ቀን ህትመቷም መንግስት ጥቂት በ‹‹ነፃ›› ሚዲያ ስም በሚንቀሳቀሱ መጽሔቶች አማካኝነት በጋዜጣውና
በአዘጋጆቹ ላይ የስም ማጥፈት ዘመቻ ሊከፍት ዝግጅቱን መጨረሱን አስቀድማ በዜና ገጿ የዘገበችው ከታማኝ ምንጮቿ ባገኘችው መረጃ ነበር፡፡
በእርግጥ ዞምቢዎቹ ህዝብ ስንኩል ስራቸውን አወቀ፣ አላወቀ አያሳስባቸውም፡፡ አሳሳቢው ጉዳይ የአገልግሎታቸው ዋጋ ብቻ ነውና ከመንከስ ያገዳቸው የለም፡፡ አስገራሚው ጉዳይ መንግስት ጋዜጣዋን ‹‹ህገ-ወጥ›› ሲል፤ በ‹‹ነፃ ሚዲያ›› ስም የሚንቀሳቀሱት ደግሞ ‹‹ልዕልና ብትዘጋ ሀዘን አይግባችሁ፤ የወያኔ ነችና›› በማለት የእግዱን አስደንጋጭነት ለማደብዘዝ የቻሉትን አድርገዋል፤ እያደረጉም ነው፡፡ ያውም ትላንት የቀድሞው ጠ/ሚንስትር መለስ ዜናዊ ህይወት ሲያልፍ ‹‹ልዩ ዕትም›› ብሎ ባወጣው ‹‹መፅሄት›› ላይ የርዕሰ አንቀፁን ስፍራ ሙሉ ጥቁር ገፅ አድርጎ በማውጣት ሀዘን ያንሰፈሰፈው መሆኑን የገለፀ ‹‹መጽሄት›› የዞምቢዎቹ ፊት አውራሪ መሆኑ ነው (ስሙን የማልጠቅሰው ‹‹የፕሬስ ውጤት›› የሚያሰኘው ነገር ስላጣሁበት እና የጋዜጣችንን አንባቢያን በማክበር ነው፤ ‹‹መፅሄት›› እያልኩ የጠራሁትም ለመግባባት እንዲያስችል ብቻ እንጂ በመጽሔት ለመባል የሚመጥን ሆኖ አይደለም)
የሆነ ሆኖ ‹‹አግደናል›› የሚለው ደብዳቤ የእቅዱን አፈጻጸም ተከትሎ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ሀገሪቷ የዞምቢዎች ነቻ፡፡ መስፍን በፅሁፉ ላይ እንደገለፀው በማይክል ጃክሰን ‹‹ትሪለር›› ዘፈን ውስጥ መቃብር ፈንቅለው የሚወጡት ዞምቢዎች የአካላቸው መጎሳቆልና የልብሳቸው በጭቃ መለወስ ከየት እንደመጡ ይናገራል፡፡ የእኛዎቹ ዞምቢዎች ግን እንደዚያ አይደሉም፡፡ ንፁህ ይለብሳሉ፣ በቤተ- እምነቶች ተገኝተው ይንበረከካሉ፣ ከቤተሰብ፣ ከጎረቤት፣ ከጓደኛና ወዳጅ ዘመድ ጋር ተቀላቅለው ስለሀገር፣ ስለእውነት፣ ስለፈጣሪ አዳኝነት፣ ስለፖለቲካ፣ ስለጋዜጠኝነት፣ ስለእውቀት፣ ስለማህበራዊ ህይወት… አሰልቺ በሆነው አንደበታቸው ሲያወሩ ትሰማላችሁ፡፡ ዞምቢ መሆናቸውን አያምኑም፡፡
…አሁን ጊዜው እየደረሰ ይመስለኛል፡፡ ዞምቢዎቹ እግራቸውን እየጎተቱ፣ የተቦደሰ አካላቸውን እንደያዙ፣ ጤነኞቹን ህያዋን ወደ ዞምቢነት ለመቀየር እየመጡ ነው፡፡ ከበር ደርሰዋልና ዳናቸውን እየሰማሁት ነው፡፡ በዚህ የፈተና አፍታ አንዳርጋቸው አሰግድ ‹‹በአጭር የተቀጨ ረጅም ጉዞ›› በሚል ርዕስ ያስነበበንን መፅሀፍ የዘጋበት አንድ ግጥም ታወሰችኝ፡፡ እናም ‹‹ሀገር እየመራን ነው›› ለሚሉት ማስነበብን ወደድኩ፡-
‹‹ክፍ ክፍ ቢሏት የማትሰማ ድመት ሚዛኑን ደፋችው ሳንለካካበት!››
በርግጥም የቀረኝ ይህ ብቻ ነበር፡፡
ኦ… አምላኬ! እባክህ… እባክህ ሀገሬን ከዞምቢ ታደጋት…

ኢትዮሚድያ
Ethiomedia.com – March 31, 2013

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: