ድሀ ከሆኑ አይቀርስ – ልክ እንደ አቶ መለስ

azeb-mesfin-corruption(ኤፍሬም እሸቴ – http://www.adebabay.com)፦

ሰሞኑን በተካሔደው የኢሕአዴግ ጉባዔ ላይ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር የአቶ መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ያደረጉትና በኢቲቪ የዜና ዕወጃ ላይ የቀረበው ንግግራቸው የማኅበራዊ ድረ ገጾች የመወያያም የመሳሳቂያም የመሳለቂያም ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ነበር። “#SomeoneTellAzebMesfin” በሚል “ሐሽ ታግ/ #Hashtag” (ቅምር-ቃል ልበለው?) በትዊተር ላይ ኢትዮጵያውያን የግል ሐሳባቸውን ሲሰጡበት የቆዩት የወይዘሮዋ ንግግር ያተኮረው በአቶ መለስ ደሞዝና ድህነት ላይ ነበር።

ያልሰማ ካለ ንግግራቸውን ቀልበጭ አድርጎ ለማቅረብ፦ “ለቤተሰቤ፣ ለግሌ ሳይል የሞተ፣ አራት ሺህ ይሁን ስድስት ሺህ ብር የወር ደሞዝ በፔይሮል የሚከፈል ብቸኛ የአገር መሪ መለስ ብቻ ነበር። የኢሕአዴግ መዋጮ ተቆርጦ በሚተርፈው ገንዘብ እንተዳደርበታለን” ወይም ተዳድረናል የሚል ነው። ወይዘሮዋ ስለ ድህነታቸው ሲናገሩ ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው አይደለም። ከዚህ ቀድሞም ተመሳሳይ ሐሳብ ሲናገሩ የሚያሳይ ቪዲዮ በየኢንተርኔቱ ላይ ተለጥፎ ተመልክቻለኹ። ለኢትዮጵያውያን ሐሳብ መነሻ የሆነው እንግዲህ በእኔ አባባል “እኛ ድሆች ነን” የሚለው አነጋገራቸው ነው።

አቶ መለስ ራሳቸው ከሁለት ዓመት በፊት አዲስ አበባ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ደሞዛቸው 6400 ብር (360 ዶላር አካባቢ) እንደሆነ ተናግረው ነበር። በርግጥ አቶ መለስ ድሃ ነበሩ ወይስ አልነበሩም ብሎ መከራከር ጉንጭ ማልፋት ካልሆነ በስተቀር ድሃ እንዳልነበሩ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው እውነታ ነው። ምናልባት ድሃ መሆን ማለት የተለየ ትርጉም ካልተሰጠው በስተቀር።

እንዲያውም አንድ የትዊተር ፀሐፊ የወ/ሮ አዜብን አባባል ከ18ኛው መቶ ክ/ዘመን የፈረንሳይ ልዕልት ቀበጥ አባባል ጋር አመሳስሎባቸዋል። ሜሬ አንቶውኔት (Marie Antoinette) የተሰኘችው ይህች ልዕልት በድህነት ይማቅቅ የነበረው የፈረንሳይ ሕዝብ “የሚበላው ዳቦ አጣ” ስትባል “ለምን ኬክ አይበላም” እንዳለች ይነገራል። የድህነት መመዘኛዋ የሚበላ በማጣትና ባለማጣት ላይ ሳይሆን በምርጫ እና በማማረጥ ላይ ነው። የወ/ሮ አዜብም ንግግር ይህንን ስላቅ እንድናስታውስ ግድ ብሎናል።

እውነቱን ለመናገር ድህነት እንዲህ ከሆነ፣ ድሃ መሆን እንደ አቶ መለስ ነበር። በቤተ መንግሥት እየኖሩ፣ አገር ምድሩን እያዘዙ እየናዘዙ፣ በስንትና ስንት ብረት አንጋች እየታጀቡ፣ መሬት እንዳይነካቸው በቀይ ምንጣፍ እየሄዱ፣ ጠዋት የበሉትን ማታ ሳይደግሙ፣ ልጆቻቸውን በእንግሊዝ ት/ቤት ብሎም በውጪ አገር እያስተማሩ፣ ምድራችን ያፈራችውን ምርጥ ልብስ እየለበሱ፣ ጠዋት ማት በቴሌቪዥን እየታዩ … ድህነት እንዲህ ነው።

ወይዘሮ አዜብም ድሆች ሆንን፣ ማቀቅን፣ በ6ሺህ ብር ደሞዝ ኖርን ሲሉ የሌላውም ሕዝብ ድህነት ልክ እንደርሳቸው የሆነ ከመሰላቸው ነው ችግር የሚገጥመን። ሌላው ሕዝብ በርግጥም በኑሮ ውድነትና በድህነት እየማቀቀ ነው። ነገር ግን ድህነቱ እርሳቸው ካለባቸው ድህነት ይለያል።

ሌላው ሕዝብ ከወር ወር በልቶ የሚደርስበትን ቀለብ መግዣ እያጣ፣ ለልጆቹ ልብስ፣ ለራሱ ነጠላ መግዣ እየተቸገረ፣ ከሰውነት ጎዳና ወጥቶ፣ በቀን ሦስት ጊዜ መብላት ስለማይችል በቀን አንድ ጊዜ (አንዳንዱም በፈረቃ) እየቀመሰ ነው የሚኖረው። በርግጥ ባለቤታቸው አቶ መለስ ስልጣን ላይ እንደወጡ ሕልማቸው (ራዕያቸው) ምን እንደሆነ ሲጠየቁ “የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀን ሦስት ጊዜ ሲበላ ማየት ነው” እንዳሉት አልሆነም። ይባስ ብሎ ድሮ የነበረችውንም አጥቷል።

ያለፈ ሥርዓት ናፋቂ እንዳይሉኝ እንጂ ባለፉት ጊዜያት “ጤፍ ተወደደ” ሲባል የሚገባን “ጤፍ የማይበሉ ሕዝቦች ጤፍ መብላት በመጀመራቸው” ሳይሆን በርግጥም የእህል ችግር ስለነበር ነው። ጤፍ ባይበላ ስንዴውና ገብሱ፣ ሲቸግርም የፉርኖ ዱቄት እንጀራ አይጠፋም። ጎመንንና ቆሎን የመሳሰሉም ቢሆኑ ያጣ የነጣውም ቢሆን የማያጣቸው ነገሮች ነበሩ። የአሁኑ ድህነት ግን ቤት ዘግቶ የሚያስለቅስ፣ ወደ አደባባይ ወጥቶ ለመለመን የሚያስቸግር የእግር ውስጥ እሳት ነው።

በፌስቡክ አጫጭር ጽሑፎቿ የማውቃት ሕይወት እምሻው የተባለች አንዲት ፌስቡከኛ/ጦማሪት ከሰሞኑ ታክሲ ላይ የገጠማትን አንድ ገጠመኝ አንጀት በሚበላ አካኋን አስፍራው አንብቤያለኹ። ገጠመኟ ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር ስለሚሔድ ልጥቀሰው። ነገሩ ሥራ ስለረፈደባት አንዲት የመንግሥት ሠራተኛ የሚያትት ነው። ልጅቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተመረቀች፣ በኤክስፐርትነት ተቀጥራ የምትሠራ፣ ደሞዟ ከምንም ከምንም ተቆራርጦ 865 ብር እጇ ላይ እንደሚገባ ትጠቅሳለች። እንደርሷ ዓይነት ብዙ ሰዎችን እንደምታውቅ ትነግረናለች – ሕይወት። አንጀት የሚበላው ነገር ደግሞ እንዲህ ይላል፦

“እጄ ላይ የሚገባው ደሞዝ 865 ብር ነው፡፡ ፡፡ የቤት ኪራዬ 300፡፡ ለዛውም ከከተማ የትናየት፡፡ አስፋልት ለመድረስ 30 ደቂቃ በእግሬ ኳትኜ፡፡ ክፍለ ሃገር ላሉት እናትና አባቴ ካለዚያ መኖር ስለማይችሉ በወር 150 ብር እልካለሁ፡፡ የሚተርፈኝ 400 ምናምን ብር፡፡ መብላት አለብኝ፡፡ መልበስ አለብኝ፡፡ ትራንስፖርቱ እንደምታይው ነው፡፡ በታክሲ መሄድ ከተውኩማ ቆይቼ ነበር …። ሰሞኑን ግን ብዙ ግዜ ስላረፈድኩ አውቶብስ ለመጠበቅ ፈራሁ፡፡ ከሁለት ዓመት ወዲህ ምግብ እንኳን በሥርዓቱ መብላት አልችልም፡፡ አይገርምሽም…? ምግብ መብላት አልችልም! ከዩኒቨርስቲ በዲግሪ ተመርቄ ሌላው ቢቀር መራብ አለብኝ?!” ድህነት እንዲህ ነው – ወ/ሮ አዜብ።

ድሮ የምናውቀው ድህነት ሥራ የሌለውን፣ ምንም ገቢ የማያገኘውን፣ ጉልበትና ዕውቀት ያጣውን የሚያጠቃ የአገር በሽታ ነበር። የዘመናችን ድህነት ግን ሰው ሥራ ኖረው አልኖረው፣ ዕውቀት ኖረው አልኖረው፣ ዲግሪ ተሸከመ አልተሸከም፣ ኮሌጅ በጠሰ አልበጠሰ የማይለቅ ነው። ኮሌጅ መግባትና መማር፣ ሥራ መያዝ በድሮው ጊዜ ራስን ለቻለ ኑሮ አስተማማኝ ነበር። ዛሬ ጊዜ ግን ከቤተሰብ አንድ ሰው ብቻ ሠርቶ ሳይሆን ባልም ሚስትም ደህና ገንዘብ እያገኙ የኑሮን ቀንበር ለመሸከም የሚንገታገቱበት ዘመን ላይ ነን። ድህነት ማለት ይኼ ነው ወ/ሮ አዜብ።

ምናልባት ይህንን ጽሑፍ የሚያነብ አንዳንድ ቅንጡ በቃ ይኼ ሁሉ ስለ ወ/ሮ አዜብ መናገር ምን ያስፈልጋል፣ እርሳቸው የተናገሩት ሦስት ደቂቃ፣ እናንተ የምታላዝኑት 30 ሰዓት ሊል ይችላል። እኔ ግን በርሳቸው አባባል ውስጥ የፓርቲያቸውን አካሔድ፣ አቋም፣ መሪ ተብለው ሥልጣኑን የተቆናጠጡት ሰዎች ከሕዝቡ የቀን ተቀን ኑሮ ምን ያህል የራቁ ሰዎች እንደሆኑ የምረዳበት ስለሆነ ብዙ ብዙ ሊባልበት እንደሚገባ ነው የሚሰማኝ። አገራችን “ለምን ኬክ አይበሉም” የሚሉ የቅርብ ጊዜ ቀዳማይት እመቤት ነው ያሏት ማለት ነው።

ምናልባትም ወ/ሮ አዜብን በተመለከተ ውይይቱ መቀጠል ያለበት የአዲስ አበባ ቀጣይ ከንቲባ ሊሆኑ እንደሚችሉ ከግምት በላይ እርግጠኝነት በመስፈኑም ነው። እንደ ፓርቲው አሠራር የፈለገውን ሐሳብ በሕዝብ አስተያት ምክንያት የሚለውጥ እንዳለመሆኑ አዜብም ከንቲባነታቸው ሳይታለም የተፈታ ይመስላል። ድህነትን በዚህ ደረጃ የሚመለከት ሰው እንዴት የድሀው ሕዝብ ከንቲባ ሊሆን ይችላል? ከንቲባዎች የግድ ድሆች መሆን የለባቸውም። ነገር ግን ድህነትን እና ሀብታምነትን የሚለዩ መሆን ግን ይጠበቅባቸዋል። ሕዝባቸውን ካላወቁት ምኑን ሊያስተዳድሩት ይችላሉ?

ወደ ሕዝብ ባለመቅረብና በቤተ መንግሥት ቤተ መንግሥታዊ ኑሮን በመኖር መለስን የሚስተካከላቸው አልነበረም። በሞታቸው ጊዜ ከየቪዲዮ ካዝናው እየወጣ ለማስተባበል እንደተሞከረው አልነበረም። የቦሌ መንገዶች ይመሰክራሉ። አካላቸው ከሕዝቡ እንደመራቁ ስለ ሕዝቡ እና ስለ ድህነቱ ያላቸው አስተያየት እንደሚስታቸው እንዳልነበረ ግን ቢያንስ ከንግግራቸው እንረዳለን።

ከኢሕአዲጎቹ ወደ ሕዝቡ በመቅረብ አቶ አርከብ የተሻሉ እንደነበሩ ብዙዎች ይናገራሉ። ወደ ሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ለመዝለቅ የደፈሩ ነበሩ። ሕዝቡም ለዚህ ቀረቤታ የአክብሮት ምላሹን ሰጥቷቸዋል። ፓርቲው ወደ ሕዝቡ መቅረብ ከፈለገ እንዲህ ዓይነት ሰዎችን ወይም እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸውን መጠቀሙ ይበጀው ነበር። ከንቲባነትን ከአርከበ ወደ አዜብ ማውረድ ግን በሕዝብ ዕንባ መቀለድ ነው። ምናልባትም ለዚህ ዓይነቱ መራራ ቀልድ ፓርቲውም ዋጋ የሚከፍልበት ይመስለኛል።

ድሆች ባትሆኑም ድህነታችንን ብትረዱልን እንዴት ግሩም ነበር።

ይቆየን – ያቆየን

(ይህ ጽሑፍ አዲስ አበባ በሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው።)

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: