ኢህአዴግ አድርባይነትን ከማጥፋት ራሱን ማጥፋት ይቀለዋል

በዳዊት ሰለሞን

ዘጠነኛውን የኢህአዴግ ጉባዔ ተከትሎ ጎላና ረገጥ ባለ ድምጸት ሲነገሩ ካደመጥናቸው ቃላቶች መካከል አድርባይነት በእኔ እምነት ግምባር ቀደሙ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ ከዚህ ጉባዔ ቀደም ብሎ ህወሓት በመቀሌ ባደረገው ጉባኤ አድርባይነት የድርጅቱ ትልቅ ስጋት መሆኑ ስምምነት ተይዞበት ነበር፡፡ ምሬትና ቁጭት በሚነበብበት ስሜት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ‹‹አድርባይነትን መታገል እንደሚገባን አቋም ወስደናል፡፡ ድርጅቱን የሚያገለግሉ ሰዎች ስለ ሚያገኙት ደሞዝ ብቻ ማገልገል የለባቸውም፡፡›› በማለት አድርባይነትን መዋጋት አስፈላጊ ስለ መሆኑ አብራርተዋል፡፡
መቼም ኢህአዴግ ዘመቻ ይወዳል፡፡ የሚያደርጋቸውን ጠቅላላ ጉባኤዎች ተከትሎ በከፍተኛ ሹማምንቶቹ አማካኝነት የዘመቻ አጀንዳዎችን ይቀርጻል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ አድርባይነትን እዋጋለሁ ብሎናል፡፡ የጉባኤው ተሳታፊዎችና እታች ያሉት ካድሬዎች ስለ አዲሱ የዘመቻ መፈክር እንጂ ስለ በፊቶቹ ብዙም ግድ ያላቸው አይመስሉም፡፡ ከዚህ በመነሳትም የአምናውና የአቻምናው ዘመቻ ምን ለውጥ እንዳመጣና በምን ደረጃ እንደሚገኝ የሚጠይቅ የለም፡፡ “ኪራይ ሰብሳቢነት”፣ “ሙስና”፣”ድህነት” ለመዋጋት ቆርጫለሁ በማለት ከዚህ ቀደም ዲስኩር ያሰማን ገዢው ፓርቲ ኪራይ ሰብሳቢዎችን፣ሙሰኞችን ከፊት ይልቅ በብዛት ማፍራት ችሏል፡ ፡ አሁን ደግሞ ሌላ አጀንዳ ተነስቷል ስሙም አድርባይነትን መዋጋት ተሰኝቷል፡፡
አድርባይነት መገለጫው ብዙ ቢሆንም ለመኖርና የግል ጥቅምን ለማሟላት ሲባል ያላመኑበትንና የማይከተሉትን የፖለቲካ አስተሳሰብ፣አቋምና መስመር የተቀበሉ በማስመሰል ሌሎችን መሸንገል ነው፡፡ ጥቅም ይገኝበታል ለተባለ ነገር ሁሉ ህሊናን በመሸጥ ለሆድ ማደር አድርባይነት ነው፡፡ አድርባይነትን በሀይማኖት መስመር ውስጥ በማስገባት ብንመነዝረው በውስጡ የምናገኛቸው ሰዎች ራሳቸውን ከጳጳሱ በላይ ክርስቲያኑ በማድረግ የሚወስዱ ናቸው፡፡
ኢህአዴግ ከ21 ዓመታት የስልጣን ላይ ቆይታው በኋላ ቀጣዮ አጀንዳው አድርባይነትን መዋጋት ስለመሆኑ ነግሮናል፡፡ አድርባይ የተሰኙት
ደግሞ በድርጅቱ ውስጥ የሚገኙ አባላቶቹ ናቸው፡፡ ወ/ሮ አዜብም ሆኑ ድርጅቱ እነዚህን አድርባዮች በምን አይነት የፖለቲካ ላብራቶሪ መንጥረው ሊያወጧቸው እንደሚችሉ ዝርዝር መግለጫ ባይሰጡም ድርጅቱ በአድርባዮች የተወረረ ስለ መሆኑ የቀደምትና የአሁን ታሪኩን በመንተራስ መናገር ይቻላል፡ ፡ በምርጫ 1997 ኢህአዴግ ሙሉ ለሙሉ በአዲስ አበባና በዋና ዋና ከተሞች በዝረራ መሸነፉን ተከትሎ እስከታች እስከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ ባደረገው ግምገማ የቀበሌ አመራሮች ጭምር ድምጻቸውን በወቅቱ ከፍተኛውን ድምጽ ላገኘው ለቅንጅት መስጠታቸውን አረጋግጧል፡፡
ሚያዚያ 28 እና 29 በአዲስ አበባ በተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ የተሳተፉ ብዛት ያላቸው ወጣቶች ለገዢው ፓርቲ ቀደም ብሎ በተደረገ የድጋፍ ሰልፍ መሳተፋቸውን የሚያሳይ በነጻ የታደላቸውን ቲ-ሸርት በማጥለቅ ‹‹ትናንት ለ ቲሸርት ዛሬ ለአንድነት›› በማለት በሁለቱ ቀናት ለሰልፍ የወጡበትን ምክንያት ማብራራታቸው አይዘነጋም፡፡ እዚህ ጋር መሰረታዊ ጥያቄ መነሳት ይገባዋል፡፡ ቲሸርት
በመስጠት ሰልፍ እንዲወጡ ያደረገው ማን ነው ሰዎችን በኢኮኖሚ ችግራቸው እየገባ መደለያ እያቀረበ ህሊናቸውን እየጣሉ እንዲከተሉት ያደረገ ድርጅት ዛሬ ድንገት ተነስቶ አድርባይነትን እዋጋለሁ ቢል ማን ያምነዋል?
የዴሞክራሲ እጦትና የአድር ባይነት ቁርኝት
ኢህአዴግ እከተለዋለሁ የሚለው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፍልስፍና መመሪያዎች ከላይ ወደታች ስለሚወርዱ የበታች ሹማምንትም የሚወርድላቸውን መመሪያ ሳይከልሱና ሳይበርዙ እንዲያወርዱ ያዛል፡፡ እናም የአብዮታዊ ዴሞክራሲ
ጭንቅላት
ሊበራል፣
ሰብሳቢነት፣
…. ሲሉ የበታቾቻቸውም ምንም እንኳ ኒዮ ሊበራል ወይም ኪራይ ሰብሳቢነት የሚባሉ ፅንሰ ሀሳቦች ትርጉም ባይገባቸውም እነዚህኑ ቃላቶች በተነገሩበት የድምጽ ቶን መድገማቸው አይቀሬ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በፓርቲው ውስጥ የራሳቸውን ሃሳብ የሚያንሸራሽሩበት መድረክ ባለመኖሩና ይህንን ለማድረግ ከሞከሩም ምን እንደሚደርስባቸው ስለሚገነዘቡ የህሊና ጥያቄና ሙግትን በማፈን መስለው ያድራሉ፡፡
ኢህአዴግ ለውስጥ ዴሞክራሲ ባዕድ መሆኑን ለመገንዘብ ሩቅ ሳንሄድ በአባላቶቹ የተሞላውን ፓርላማ መመልከት ይበቃል፡፡ ፓርላማው ከአንድ ድርጅት ቁመት በላይ አገርን የሚመለከቱ አጀንዳዎች የሚነሱበትና ህጎች የሚጸድቁበት መድረክ ቢሆንም የመቀመጫ ወንበሮችን ያገኙ የተከበሩ ተወካዮች አንዱ ካድሬ የተናገረውን ‹‹እከሌ እንደተናገረው›› ከማለት ውጪ የተለየ ነገር ሲናገሩ ተደምጠው አያውቁም፡፡ ይህም ድርጅቱ አድርባይነትን ተሸክሞ ለመቆየቱ አይነተኛ ማረጋገጫ ነው፡፡ ኢህአዴግ አድርባይነትን መዋጋት ድርጅቱን በገዛ ራሱ እንዲጠፋ የሚያደርገው በመሆኑ ‹‹ አድር ባይነትን እዋጋለሁ›› ማለቱ ከዲስኩር አይዘልም፡፡
በነገራችን ላይ ኢህአዴግ አድርባዮችን ከምር የሚዋጋ ከሆነ የፎረሞች፣ የሊጎች፣ የሴቶች ማህበራት፣ የአርቲስቶች ማህበርና ሌሎችም ምን ሊውጣቸው ነው? መልሱ ናፈቀኝ፡፡

fnotenetsanet

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: