ም/ጠ ሚኒስትሩ «እስክንድር ነጋን እንፍታ» አሉ

Image
አማኑኤል ዘሰላም amanuelzeselam@gmail.com

መጋቢት 27 ቀን 2005 ዓ.ም

ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ሰኞ መጋቢት 30 ቀን 2005 ዓ.ም በእነ አቶ እስክንድር ነጋ፣ አንዱዋለም አራጌና ሌሎች ባቀረቡት የይግባኝ ጥያቄ ላይ ዉሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል። በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ዙሪያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ዉስጥ ዉይይት እንደተደረገ ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ መጋቢት 18 2005 ዓ.ም ባቀረበዉ ጽሁፍ ዘግቧል። 1
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አቶ አንዳዋለም አራጌ፣ አቶ ናትናኤል መኮንን ፣ አቶ በቀለ ገርባ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ፣ አገር ውስጥ በሰላም የሚንቀሳቀሱ ኢትዮጵያዉያን ፣ ከገዢዉ ፓርቲ የተለየ አቋም በማንጸባረቃቸው ብቻ፣ በፈጠራ የሽብር ወንጀል ተከሰው በቃሊቲ በመማቀቅ ላይ ይገኛሉ።
በፍርድ ወንበር ላይ የሚቀመጡ አብዛኖቹ ዳኞች፣ የሕግ ባለሞያ ከመሆን ይልቅ ካድሬነት መሆን፣ ሕግን በማስከበር ፍትህ እንዲሰፍን ከማድረግ ይልቅ፣ የገዢው ፓርቲ ተቀጥያ በመሆን እና ሕግን እንደበትር በመጠቀም ተቃዋሚዎችን ማጥቃት የሚቀናቸው ናቸው። በድብቅ የተሰራ ወንጀልን የሚያሳይ አንድም ሰነድ ሳይኖር፣ በሽብር ተግባር የተገድሉ ዜጎች ወይንም ለሽብር ተግባር ሊዉሉ የሚችሉ እንደ ቦምብ፣ ፈንጂ የመሳሰሉ በሌሉበት ሁኔታ፣ እነ እስክንድርን ሽብርተኛ ብሎ በጭፍን የበየኑት፣ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት ተቀምጠዉ የነበሩትን፣ ዳኛ ተብዬ ካድሬዎችን እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።
አልፎ አልፎ ግን ሕሊናቸዉን የሚያዳምጡ፣ የሕግ ባለሞያዎች ኤቲክስ ኮድ ግድ የሚላቸው፣ ፈሪሃ እግዚአብሄር ያላቸው የሕግ ባለሞያዎች እንደ ብልጭታ ብቅ የሚሉበት ሁኔታ አለ። እነ ዳኛ ወልደሚካኤል መሸሻ፣ ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ የመሳሰሉቱ ላለፉት ሃያ የኢሕአዴግ ዘመናት፣ ካየናቸው እጅግ በጣም ጥቂት እዉነተኛ የሕግ ባለሞያዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። እንደ እነዚህ አይነት ዳኞች በብዛት ቢኖሩን ኖሮ አገራችን ይሄን ጊዜ የትናየት በደረሰች ነበር።
ሰሞኑን የሕግ ባለሞያዎችን የሚያኮሩ ፣ ለፍትህ መስፈን ቁርጠኝነትን ያሳዩ፣ አንድ ዳኛ አግኝተናል። አቶ አማረ አሞኝ ይባላሉ። የጠቅላይ ፍርድ ቤት መሃል ዳኛ ናቸው። የእነ እስክንድር ነጋን ጉዳይ የያዙት እርሳቸው ናቸው። ተከሳሾችም አቃቢ ሕግም ያቀረቡትን መረጃዎች፣ የከፍተኛዉ ፍርድ ቤት ዉሳኔ የያዘዉንም ሰነድ፣ በጥንቃቄ መረመሩ። አቃቢ ሕጎችን ጠርተዉ «ይህን ሰው (እስክንድር ነጋን) አሸባሪ ነው ብላችሁ ስትከሱት ያቀረባችሁት ማሰረጃ በተለያየ ጊዜ የፃፈውን ፅሆፎች፣ ቃለ-መጠይቆች እና በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ መድርክ ላይ ተናገረው ያላችሁትን ብቻ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ፅሁፉና ንግግሩ ያስከተለው አደጋ አልተገለፀም፤ ወይም ምንም አይነት አደጋ አላስከተለም ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ተከሳሹ ላይ ቅጣት ለመጣል አያስችልም፡፡ ስለዚህም ሌላ ጥፋተኝነቱን የሚያረጋግጥ ማሰራጃ ካላችሁ አቅርቡ? አሊያም በሚቀጥለው ቀጠሮ ሲቀርብ በነፃ እለቀዋለሁ» ሲሉ የነ እስክንድርን ሽብርተኛ አለመሆን ከወዲሁ አሳወቁ።
ጋዜጠኛ ተመስገን እንደዘገበዉ አቃቢ ህጎቹ ምንም ማስረጃ አልነበራቸውምና በደፈናው «ሰውየው አሸባሪ ስለሆነ ዝም ብለህ፤ ይግባኙን ውድቅ አድርግና የከፍተኛው ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አጽናበት የሚል ምላሽ ሰጡ።
የሚኒስተሮች ምክር ቤት በዚህ ጉዳይ ላይ ስብሰባ አደረገ። አቶ አማረ አሞኝ ተጠርተዉ ማብራሪያ ሰጡ። ዳኛዉ እስክንድር ነጋን «አሸባሪ ብሎ ለመፍረድ የሚያስችል በቂ ማስረጃ ስላልቀረበ በሚቀጥለው ቀጠሮ በነፃ አሰናብተዋለሁ። እንዲህ ማድረግ አትችልም የምትሉኝ ከሆነ ግን ክቡራን ሚኒስትሮች በዕለቱ በችሎት ለመሰየም ፍቃደኛ አለመሆኔን በትህትና ትረዱኛላችሁ ብዬ አስባለሁ!» በሚል እዉነታዉን ግልጽ አደረጉ»
1 http://ethiocenter.blogspot.com/2013/03/blog-post_2730.html

በመጀመሪያ የሚኒስቴሮች ምክር ቤት በፍርድ ሂደቱ ላይ ጣልቃ ገብቶ ዳኞችን ጠርቶ የማነጋገር መብት ከየት እንዳገኝ ቢነገረን ጥሩ ነበር። የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊን ጨምሮ አብዛኞቹ የኢሕአዴግ መሪዎችና ካድሬዎች እየደጋገሙ ሲነግሩን የነበረው፣ ሕግ መከበር እንደነበረበት ነዉ። እኛም እንስማማለን። ታዲያ ዳኞችን እየጠሩ ማስጠንቀቅና ማስፈራራት ያለዉን ሕገ መንግስት ቀዳዶ እንደ መጣል አይቆጠርምን ? ሕግን መናቅ አይደለምን?
በሚኒስቴሮች ምክር ቤት የተለያዩ ሃሳቦች እንደቀረቡ አቶ ተመስገን ዘግበዋል። ‹‹እኔም ከአቶ አማረ ጋር እስማማለሁ፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሰውዬ /እስክንድር/ የተነሳ ከፍተኛ አለም አቀፍ ጫና እየደረሰብን ነው፡፡ ስለዚህም ብንፈታው ተጠቃሚዎቹ እኛው ነን ብዬ አስባለሁ፡፡›› ሲሉ ስብሰባውን የመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተሩ አቶ ደመቀ መኮንን ብስለት ያለዉ አስተያየት ይሰጣሉ።
«የአለም አቀፍ ጫና ስለበዛብን እስክንድርን ብንፈታ ጫናዉ ይቀንስልናል። እኛም እንጠቀማለት» ከሚሉ «እኛን እንደ ድርጅት ጠቀመም አልጠቀመም ፣ ፍትህ መከበር አለበት። ዜጎች ወንጀል ሳይፈጽሙ መታሰር የለባቸው» የሚል፣ ከፓርቲ ይልቅ ለአገር በማሰብና በመርህ ላይ የተደገፈ አስተያየት ቢሰጡ ኖሮ፣ የበለጠ አክብራቸው ነበር።
አቶ ደምቀ ባሉት ላይ እንደሚስማሙ የገለጹት አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ሚኒስቴር «ነገር ግን እስከዛሬ አስረነው ‹ነፃ ነህ› ብለን ብንለቀው የፖለቲካ ኪሳራ ስለሚያስከትልብን፣ ከፍርዱ ላይ ቅንስናሽ አድርገን ይቅርታ ጠይቆ
እንዲወጣ ብናደርግ የተሻለ ነው» የሚል አስያየት ይሰጣሉ። እኝህ ባለስልጣን ደካማ ባለስልጣን መሆናቸውን ነው የሚያሳዩን። መልካም የሆነን ነገር ማድረግ፣ የተሰራ ስህተትን ማረም እንዴት ተደርጎ ነዉ የፖለቲካ ኪሳራ የሚያመጣዉ
ከክርስቶስ ልደት መቶ አመታት በፊት የነበሩ የሮማ ፈላስፋ ማርከስ ሲሰሮ «ማንም ሰው ስህተት ይሰራል። ነገር ግን ኢዲየት(ማሰብ የማይችል) የሆነ ሰው ብቻ ነዉ ከስህተቱ የማይታረመው» ሲሉ፣ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ጊዜ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስተር የነበሩትና አዲስ አበባ ያለ አንድ ትልቅ መንገድ በስማቸዉ የተሰየመ ዊንስተን ቸርችል ደግሞ «ሁሉም ሰው ስህተት ይሰራል። ነገር ግን ጥበበኛ ብቻ ከስህተቱ ይማራል» በማለት፣ ስህተትን ይዞ መቀጠል ሳይሆን ፣ ስህተት ማረም ተገቢ እንደሆነ ለማስረዳት የሞከሩት።
እነ እስክንድርን ማሰር ተገቢ እንዳልሆነ የተረዱ ባለስልጣናት፣ ስህተታቸውን አርመዉ፣ እስረኞችን መፍታት ይገባቸዋል እንጂ፣ የ«ምን እንባላለን« ኋላ ቀር ፖለቲካ ማራመድ የለባቸውም። ስህተትን ማረም ትልቅነት ነዉ። ስህተትን ማረም ያስከብራል። ስህተትን ማረም አንዳችም አይነት የፖለቲካ ጉዳት አያመጣም።
ሌላ ሶስተኛ ሚኒስቴር ስለ እስክንድር ነጋ ተናገሩ የተባለው አባባል ግን በጣም ከነከነኝ። «ኧረ ለመሆኑ መለስ አለም አቀፍ ጫና እንደሚያስከትል እያወቀ ለፓርቲያችን ጥቅም ብሎ የገባበትን ጉዳይ፣ ዛሬ እርሱ አልፏል ብለን ጫና የምንፈራበት ምክንያት ከየት የመጣ ነው? በቃ! መለስ አደገኛ ሰው ነው ብሎ አስሮቷል፡፡ አለቃ! እዛው ይበስብስ!» ነበር ያሉት። እንዲህ አይነት ጨቅላ የእንስሳ አስተሳሰብ ያላቸው ባለስልጣናት፣ ከዱር አራዊቶች ጋር በጫካ እንጂ በሰዎች መካከል መኖር የለባቸውም።
እኝህ ሚኒስቴር አቶ መለስን ይጠቅሳሉ። «አቶ መለስ የሰሩት ሥራ በሙሉ ትክክል ነዉ። እርሳቸው የወሰኑትን መሻር የለብንም። የርሳቸው ቃል የእግዚአብሄር ቃል ነዉ» የሚል ይዘት ያለው እጅግ በጣም ደካማ አስተሳሰብ ነዉ ያንጸባረቁት። የኢራኑ አያቶላ አሊ ሆሚኒ፣ በተቀበሩ ጊዜ፣ በሕይወታቸው አብረዋቸው የተቀበሩ ሰዎች እንደነበሩ ያነበብኩ መሰለኝ። እኝህ ሚኒስቴር ይሄን ያህል ለአቶ መለስ ፍቅር ካላቸው፣ አብረው ቢቀበሩና ሰላም ብናገኝ የተሻለ ነበር።
እነ አቶ ደምቀ፣ የጫካ ፖለቲካ በሚያራምዱ በጥቂቶች፣ ተነድተዉ፣ ሕሊናቸውን ሽጠው ድርጅታቸውና አገራቸውን የሚጎዳ ዉሳኔ አይወስኑም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። አቶ አማረ አሞኝ በወንበራቸው ተቀምጠው፣ እስክንድር ነጋ፣ አንዱዋለም አራጌ እንዲሆም ሌሎች የሕሊና እሥረኖች በሙሉ ነጻ ወጥተዉ፣ አዲስ የመቀራረብና የመቀባበል ፖለቲክ በአገራችን እንዲጀመር፣ ዜጎችን በግፋ የማሰርና የማሰቃየት ብሃል እንዲቆም ያደርጋሉ የሚል ተስፋ አለኝ።
በአገር ቤትም ሆነ በዉጭ የምንኖር ኢትዮጵያዉያን ሁሉ እግዚአብሄር በስልጣን ላይ ላሉት ማስተዋልና ጥበብ ይዘጣቸዉ ዘንድ፣ በእሥር ለሚገኙትም ብርታትና ጥንካሬ ያበዛላቸው ዘንድ፣ በተዋረደ መንፈስና በትህትና እንዲጸልዩ ጥሪ አቀርባለሁ። ሌላ ማድረግ ባንችል ለፈጣሪ አቤት ማለቱ የሚያቅተን አይመስለኝም።
EMF

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: