የማስቲሹ ስበት ሰለባዎች

Image

የ10ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተናን ለመውሰድ ባይታደልም 10ኛ ክፍል ደርሷል፡፡ የልጅነት ሐሳቡ የነበረው ቤተሰቡን መርዳት ቢሆንም ይህ ግን አልሆነም፡፡

በቤተሰብ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት እሱን ጨምሮ ስድስት እህትና ወንድሞቹ ከቤተሰብ ተበትነዋል፡፡ እናትና አባቱም ተለያይተዋል፡፡ ከቤተሰብ ተለይቶ ጐዳና እስከወጣበት ኅዳር 2004 ዓ.ም. ድረስ ጐዳና ላይ እወጣ ይሆን ብሎ አስቦት የማያውቀው የ24 ዓመቱ ወጣት ዕጣ ፈንታው ጐዳና ሆነ፡፡ መተዳደሪያው ደግሞ የቀን ሥራ፡፡

በቦሌ አካባቢ ከሚገኝ የስልክ መስመር ማከፋፈያ ሳጥን ጀርባ ተቀምጦ ስናገኘው ዓይኑ ድብልቅልቅ ብሎ ቀልቶ ነበር፡፡ ፊቱም ጠቁሯል፡፡ በአንድ እጁ የዓይን መድኃኒት ብልቃጥ ይዞ ነበር፡፡ ማስቲሽ እንደሚስቡ ጓደኞቹ ግን ማውራት አላቃተውም፡፡ ሰውነቱንም እንደፈቀደ ማዘዝ ይችላል፡፡ ለሚጠየቀው ጥያቄ በሙሉም ሳያዛንፍ ይመልሳል፡፡ ማስቲሽ ስለመሳብ ስናነሳለትም ፈገግ በማለት ‹‹ማስቲሽ ብስብ እንዲህ ቆሜ አታይኝም፡፡ ፍዝዝ፣ ጅዝብ ነበር የምለው፡፡ ጓደኞቼ ሲስቡ ራሳቸውን አያውቁም፡፡ ብትመቻቸው አይሰሙም፡፡ ብታዋሪያቸው አይመልሱም፡፡ ጅዝብ ብለው ዓይን ዓይንሽን ነው የሚያዩት፡፡ በዛ ወቅት ስለምንም ነገር አያስቡም አያውቁም፡፡ እኔም አንዳንዴ ስቤ በሞከርኩትና ችግሬን በረሳሁት እላለሁ፤›› ነበር ያለው፡፡ 

በብሔራዊ፣ በስታዲየም፣ በፒያሳና በአንዳንድ የትራፊክ መብራቶች ባሉባቸው መሀል አዲስ አበባ ታዳጊ ሕፃናትና ወጣት ጐዳና ተዳዳሪዎች በተለይ አመሻሹ ላይ ማስቲሽ ሲስቡ ማየቱ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ቀድሞ ቤንዚን ወይም የመኪና ጭስ ይስቡ የነበሩ ታዳጊ ሕፃናት ዛሬ ላይ ስበታቸውን ወደ ማስቲሽ አድርገዋል፡፡ 

በሃይላንድ (በውኃ መያዣ ፕላስቲክ)፣ በብልቃጥ፣ በመድኃኒት ዕቃዎችና በፊስታል አድርገው የሚይዙትን ማስቲሽ (ሙጫ) ብዙውን ጊዜ አንጠልጥለውት አይታዩም፡፡ ይደብቁታል፡፡ በተለይ ፖሊስ እንዳያያቸው በእጅጌያቸው ውስጥ ይከቱታል፡፡ አመሻሹ ላይ ሲስቡትም በቡድን ሆነው በመቀባበል ነው፡፡ ማስቲሻቸውን ማንም እንዲቀማቸው አይፈልጉም፡፡ ፖሊስ ሲነጥቃቸውም ‹‹ትልቅ ዕቃ›› የጠፋባቸውን ያህል ያለቅሳሉ፤ የማያቋርጥ እንባ፡፡ 

ማስቲሽ የሳበን ልጅ ቢያዋሩት መልስ አይሰጥም፡፡ ከሌሎች ጋር አይጫወትም፡፡ አይተባበርም፡፡ መንገድ ላይም ሆነ ጥግ ያገኘበት ቁጭ ይላል፣ ዝም ብሎ ይሄዳል ወይም ይተኛል፡፡ የሚያደርገውንም ሆነ የሚደረግበትን አያውቅም፡፡ ራሱን ይረሳል፡፡ እንቅልፍ ሲጥለውም በቀላሉ አይነቃም፡፡ 

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የለገሃር አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ የሆኑት ምክትል ኮማንደር ሞቱማ ሲማ በብሔራዊ፣ በሃራምቤና በለገሃር የትራፊክ መብራቶች አካባቢ ማስቲሽ የሚስቡ ልጆች መኖራቸውንና የክልልና የአዲስ አበባም ልጆች እንደሚገኙባቸው ይናገራሉ፡፡ 

እንደ ምክትል ኮማንደር ሞቱማ፣ ማስቲሹን ይዘው ሲስቡ በፖሊስ ተይዘው የተጠየቁ ጐዳና ተዳዳሪዎች ማስቲሹን ከመርካቶና ከተለያየ ቦታ እንደሚገዙት፣ አንዱ የገዛውን ለጋራ እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ፡፡ ማስቲሹን ለመግዛት ደግሞ ገንዘብ ለምነው ወይም የሰው ኪስ ገብተው ያገኛሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ፖሊስ ከመብራት አካባቢ የማስነሳትና ጣቢያ አምጥቶ የመምከር ሥራን ያከናውናል፡፡ ሆኖም ልጆቹ መልሰው ያው ናቸው፡፡ ማስቲሽ ከሳቡ በተለይ ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ የመደንዘዝ ሁኔታ ስለሚታይባቸው የመኪና አደጋ እንዳይደርስባቸውም ፖሊስ ከየአካባቢው የማስነሳት ሥራን ያከናውናል፡፡ 

በብዛት ማስቲሽ የሚስቡት ልጆች ዕድሜያቸው ከ16 አይዘልም፡፡ የ9 እና 10 ዓመት ልጆችና ሴቶችም አሉ፡፡ ከሴቶቹ ሕፃን አቅፈው የሚዞሩም ይገኙባቸዋል፡፡ እርስ በርሳቸው እንደቤተሰብ ተያይዘው የሚኖሩበት ሁኔታም አለ፡፡ ለምን ማስቲሽ እንደሚስቡ ሲጠየቁም ሙቀት ይሰጠናል፤ የምግብ ፍላጐታችንን ይቀንሳል ይላሉ፡፡ ሆኖም ከየሆቴሉም ሆነ ከሌላ ቦታ ያገኙትን ምግብ በፊስታል ይዘው እየተመገቡ ነው ማስቲሹን የሚስቡት፡፡ 

ምክትል ኮማንደር ሞቱማ እንደሚሉት፣ ልጆቹ ማስቲሹን ከሳቡ በኋላ ልፍስፍስ ይላሉ፤ የመናገር ችሎታቸው ይቀንሳል፡፡ ፍጥነትም የላቸውም፡፡ ሰውነታቸው ቢመታ አይሰማቸውም፡፡ የሚነገራቸውን ሰምተው መልስ አይሰጡም፡፡ ዝም ብለው ማየት ብቻ ነው፡፡ ሰውነታቸው ላይ የመንቀጥቀጥና ፊታቸው ላይ የመጥቆር ገጽታ ይታያል፡፡ ማስቲሽ ከሳቡ በኋላ በሌሎች ላይ ወንጀል ለመፈጸም አቅም ባይኖራቸውም ማስቲሹን ለመግዛት ሲፈልጉ ገንዘብ ለማግኘት ጥቃት ሊፈጽሙ ይችላሉ የሚለው ግን ሥጋት ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ፣ በደቡብ እስያና ባደጉት አገሮችም ጭምር በተለይ ከወላጆቻቸው ተለይተው በጐዳና በሚኖሩ ሕፃናት ላይ እየተለመደ የመጣው ማስቲሽ የመሳብ ሱስ፣ ለካንሰርና ለአእምሮ መቃወስ ሲያይልም ለሞት ያጋልጣል፡፡ የረዥም ጊዜ ተጠቃሚ መሆን ደግሞ ተጠቃሚዎች ስለራሳቸውም ሆነ በአካባቢያቸው ስለሚከናወን ጉዳይ እንዳያውቁና እንዳያገናዝቡ ያደርጋቸዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን የናርኮቲክና የሳይኮትሮፒክ መድኃኒቶች አለአግባብ አጠቃቀም መከላከል ቁጥጥር ቡድን አስተባባሪ ወይዘሪት ብፅአት ሽመልስ እንደሚሉት፣ በጐዳና ላይ ያሉ ታዳጊ ሕፃናትና ወጣቶች ማስቲሽ ብቻ ሳይሆን ቤንዚን፣ የመኪና ጭስ፣ የግድግዳ ቀለም፣ የፀጉር ቀለም፣ የቀለም ማቅጠኛ፣ ፓርከር፣ ጥፍር ቀለም፣ የጥፍር ቀለም ማስለቀቂያ እንዲሁም ፍሉድ (የኮምፒውተር ወይም የታይፕ ጽሑፍ ስህተት ማረሚያ) ይስባሉ፡፡ 

በሥልጠና ወቅት አግኝተው ሲያናግሯቸው የሚሰጡት መልስም ከረሃብና ከብርድ ያስታግሳል የሚለውን ነው፡፡ በጽሑፉ መግቢያ ላይ ታሪኩን ያጫወተን ወጣት ግን ጐዳና ተዳዳሪ ጓደኞቹ ማስቲሽ ከመሳባቸው በፊት ምገብ በጣም እንደሚበሉ፤ ሲስቡም ሆነ ከሳቡ በኋላ የሚያልፈውን ሁሉ ምግብ እንደሚጠይቁና ማስቲሹ ረሃብን እንደሚያባብስ ነው፡፡ 

በጤና ላይ ያለውን ጉዳት በተመለከተም ማስቲሽ የሚስቡ ሕፃናትና ታዳጊዎች ለአእምሮ በሽታ ይጋለጣሉ፤ ንግግራቸው ይጐተታል፤ ለመኪና አደጋ ይጋለጣሉ፤ ዓይናቸው ይቀላል፣ እንባም ይፈሰዋል፤ የማሽተት ችሎታቸው ይቀንሳል፣ ከአፍንጫቸው የሚወጣው ፈሳሽ ይበዛል፣ የአፋቸው ሽታ ይለወጣል፤ እንዲሁም የከንፈር መቅላት፣ ማበጥና መቁሰል ይታይባቸዋል፡፡ 

Ethiopian Reporter

 

 
Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: