አማርኛ ተናጋሪዎች ከደቡብ ክልል በድጋሜ እንዲለቁ ተደረገ

መጋቢት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- ፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ እንደገለጠው፣ ቀደም ሲል በቤንች ማጂ ዞን በጉራፈርዳ ወረዳ የተፈናቀሉ ከ20 ሺ ያላነሱ አርሶደሮች የገቡበት ሳይታወቅ፣ አሁን ደግሞ በዚሁ ዞን በሚኒት ወልድያ ወረዳ በተለይም ዘንባብና አርፋጅ ቀበሌ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ከ350 በላይ የአማርኛ ተናጋሪዎች ተፈናቅለው በወረዳው አካባቢ በሚገኝ ጫካ ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ።
ተፈናቃዮቹ ከመኖሪያ አካባቢያቸው 61 ከብቶችና ግምቱ ያልታወቀ እህል ተዘርፈው አካባቢያቸውን ጥለው ለመውጣት የተገደዱት ሲሆን ተሸሽገው ባሉበት ጫካ ለከፍተኛ ርሃብና ውሃ ጥም መዳረጋቸውንም ጋዜጣው ዘግቧል።
ከተፈናቃዮች መካከልም 4 ሰዎች በግፍ መገደላቸውንና የወረዳው አስተዳደር አካላት “እናጣራለን” ከማለት ውጭ ምንም መልስ ባለመስጠታቸው ጉዳዩ እየባሰ በመሄዱ ንብረቶቻቸው ተዘርፈው በአሁን ወቅት ለዓመታት የኖሩበትን አካባቢ ጥለው በጫካ መጠለልን መርጠዋል።
በአሁን ወቅት ከወረዳው ፖሊሶች ውጭ የአስተዳደሩ አካላት በግፍ መፈናቀላችንን በተመለከተ ያላቸውን ውሳኔ እንዲያሣውቁን ብንጠይቅም ምላሽ የሰጠን ባለመኖሩ አሁንም ለከፍተኛ ችግር በመጋለጣችን የሚመለከተው የመንግስት አካል ምላሽ እንዲሰጠን እንፈልጋለን ማለታቸውን ጋዜጣው ተፈናቃዮችን በዋቢነት ጠቅሶ ዘግቧል።
የደቡብ ክልላዊ መንግስት የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት አቶ ሁሴን “በአሁን ወቅት በክልሉ ምንም ዓይነት የአማርኛ ተናጋሪ ዜጎችን ማፈናቀል ስራ አልተካሄደም፤ የተላለፈ መመሪያም የለም፤ እንደውም በተለያየ ምክንያት ከተለያየ ቦታ ወደ ክልሉ የመጡትን እንኳ እየተንከባከብን ነው” ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።
ቀደም ሲል በዚሁ ክልል የተፈናቀሉ አብዛኞቹ ዜጎች የሰፈሩበት ቦታ እስካሁን አልታወቀም። የተወሰኑ ተፈናቃዮች በከተሞች በልመና ላይ መሰመራታቸውን ለማወቅ ቢቻልም፣ ቁጥራቸው ከ20 ሺ የማያንሱ ተፈናቃዮች የሰፈሩበትም ቦታም ይሁን የደህንነታቸው ሁኔታ አልታወቀም።
በቅርቡ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ የተፈናቀሉ ከ5 ሺ በላይ አማርኛ ተናጋሪዎች ፣ ህገወጥ በሆነ እና ሰብአዊ ክብራቸውን በሚነካ መልኩ ለረጅም አመታት ከኖሩበት ቀያቸው እንዲወጡ መደረጉ፣ በደቡብ፣ በሶማሊ፣ በኦሮምያ እና በሌሎች ክልሎች ከተፈጸሙት ተመሳሳይ ድርጊቶች ጋር ተዛምዶ ብዙዎች፣ የአማራን ህዝብ ኢላማ የሚያደርገው የህወሀት የቆየ ፖሊሲ ውጤት ነው በማለት አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ሳያስገድዳቸው አልቀረም።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ የተፈጸመው ኢሰብአዊ ድርጊት ከአገር ውስጥ አልፎ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ተቃውሞዎችን እያዘጋጁ ነው። በጀርመን አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ፣ ለአንድ ወር የሚቆይ የፊርማ ማሰባሰብ ስራ እየሰሩ ሲሆን፣ ተመሳሳይ ፊርማ የማሰባሰብ ስራም በኢንተርኔት እየተደረገ ነው።፡
በስዊድን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የመንግስትን ፖሊሲ በመቃወም በስቶክሆልንም ከአራት ቀናት በሁዋላ ሚያዚያ 4 ወይም ኤፕሪል 12 የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚያደርጉ አስተባባሪዎቹ ለኢሳት ገልጸዋል።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: