የመቀሌ ከተማ የመጠጥ ውኃ ችግር ነዋሪዎችን አሳስቧል

• ግድብ ለመገንባት የሚያስፈልገው 3.5 ቢሊዮን ብር ከክልሉ አቅም በላይ ነው ተባለ

በዳዊት ከበደ፣ ከመቀሌ

የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ዋና ከተማ የሆነችው መቀሌ በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ከሚገኙ የክልል ከተሞች መካከል አንዷ ብትሆንም፣ የመጠጥ ውኃ ችግር መፍትሔ ካልተበጀለት ነዋሪዎች ለከፍተኛ ችግር እንደሚጋለጡ አሳሰቡ፡፡

በከተማዋ የነዋሪው ሕዝብ ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚገኝ ሲሆን፣ ከአምስት ዓመት በኋላ አንድ ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት ተገልጿል፡፡ በአሁኑ ወቅት 300 ሺሕ ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡ በከተማዋ ላለፉት አሥርት ዓመታት ዘላቂ መፍትሔ ያልተገኘለት ከፍተኛ የመጠጥ ውኃ እጥረት ያለ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስም ችግሩ አልተቀረፈም፡፡ በተለይም በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች በአማካይ ለሁለት ሳምንት የመጠጥ ውኃ እንደማያገኙ ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡ ይህ ችግር ከከተማዋ መስተዳድር ጀምሮ እስከ ክልሉ ምክር ቤት በየጊዜው የመወያያ አጀንዳ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ግን ዘላቂ መፍትሔ አልተገኘለትም፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች ተወካዮች የመቀሌ ከተማን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወክሉት አምባሳደር ዶ/ር አዲስ ዓለም ባሌማ በተገኙበት በመቀሌ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ተገኝተው የችግሩን አሳሳቢነት በምሬት መግለጻቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የክልሉ መንግሥት በየጊዜው ለችግሩ ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እየተንቀሳቀስኩ ነው ቢልም፣ አሁንም እየተባባሰ ከመሄዱ ውጪ የተገኘ ለውጥ የለም ሲሉም ነዋሪዎች በምሬት ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎችም በከተማዋ በአሁኑ ጊዜ እየተካሄዱ ያሉ የበርካታ መኖርያ ቤቶችና ትላልቅ ሕንፃዎች ግንባታዎች የውኃ እጥረቱ ካልተፈታ ከአንድ ዓመት በኋላ ሊቆሙ ይችላሉ ሲሉ ሥጋታቸው ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የመቀሌ ከተማ ከንቲባ አቶ ንጉሠ ገብረ መንግሥት የችግሩ አሳሳቢነት ከፍተኛ መሆኑን እንደሚገነዘቡ ገልጸው፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ግድብ ለመሥራት ጥናት ሲካሄድ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ መንግሥት የመጠጥ ውኃ እጥረቱን በጊዜያዊነት ለመፍታት በየጊዜው ለተጨማሪ የውኃ ጉድጓዶች ከፍተኛ በጀት በመመደብ ሲያስቆፍር መቆየቱን አስረድተው፣ በአሁኑ ወቅት ግን የውኃ መጠናቸው እየቀነሰ መምጣቱ ተናግረዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ግድብ መገንባት እንደሚያስፈልግ በጥናት መረጋገጡን አስረድተው፣ ለግድቡ ግንባታም 3.5 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ወጪው ከከተማው መስተዳድርም ሆነ ከክልሉ መንግሥት አቅም በላይ መሆኑን የተናገሩት ከንቲባው፣ ግንባታውን ለማካሄድ የሚያስችል ገንዘብ ለማግኘትም ከሚመለከታቸው የክልልና የፌደራል መንግሥት አካላት ጋር ውይይት እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በውይይቱ የከተማዋ የሕዝብ ቁጥር ከአምስት ዓመት በኋላ አንድ ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት የተገለጸ ሲሆን፣ አሁን ያለው የመጠጥ ውኃ እጥረት ከአሁኑ ትኩረት ተሰጥቶት ካልተፈታ ችግሩ የከፋ እንደሚሆን ተወካዮቹ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የመቀሌ ከተማ ዕድገት ከሌሎች የክልለ ዋና ከተሞች ጋር ሲነፃፀር በተለይም በመሠረተ ልማት ግንባታው አጥጋቢ አይደለም የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ ለዚህ ዋነኛው ማነቆ እየሆነ ያለው ደግሞ እስካሁን ዘላቂ መፍትሔ ያልተገኘለት የመጠጥ ውኃ እጥረት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በተወሰነ የከተማዋ አካባቢዎች ሥርጭቱ የተሻለ ቢሆንም፣ በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች ግን ነዋሪዎች ውኃ የሚያገኙት ሌሊት በመሆኑ እንቅልፍ አጥተን ለማጠራቀም እየተገደድን ነው ብለዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የመቀሌ ከተማ የመጠጥ ውኃ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጊደና አበበ፣ መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት 150 ሚሊዮን ብር ወጪ በማውጣት ዘጠኝ ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶች ማስቆፈሩን፣ 200 ኪሎ ሜትር አዳዲስ የውኃ መስመሮች መዘርጋቱንና የውኃ ሽፋኑም ከነበረበት 41 በመቶ ወደ 80 በመቶ ማደጉን ተናግረዋል፡፡ የመጠጥ ውኃ መስመር የተዘረጋላቸው የመኖርያ ቤቶች ቁጥርም ከ17 ሺሕ ወደ 33 ሺሕ ማደጉን ገልጸው፣ ይህ ማለት ግን ሁሉም ማግኘት የሚገባቸውን የመጠጥ ውኃ ያገኛሉ ማለት አይደለም ብለዋል፡፡ በከተማዋ በአሁኑ ጊዜ ካለው አጠቃላይ ዕድገት ጋር ሲነፃፀር አቅርቦቱና ፍላጎቱ እንደማይጣጣም የተናገሩት ኃላፊው፣ ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የሕዝብ ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱና የመጠጥ ውኃ ጉድጓዶቹም ይዘታቸው እየቀነሰ መሄዱን አብራርተዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ችግሩን በዘለቄታ ለመፍታት የገጸ ምድር አማራጭ ማለትም ግድብ ለመገንባት ጥናት አካሂዶ በሒደት ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ የጥናቱን ዝርዝር መረጃ ለመናገር ግን ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡

Ethiopian Reporter

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: