‹‹በሕዝብ የተመረጥኩ ነኝ›› ብሎ የሚያምን መንግሥት ‹‹ሕዝብ አለቃዬ ነው›› ብሎ ማመንም አለበት

457eb5238cd7f28655abc78f62a70278_L

ሕገ መንግሥታችን ሥልጣን የሚይዝ መንግሥት በሕዝብ ድምፅ ብልጫ የተመረጠ መሆን አለበት ይላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉድለት አለው እንዲህ መሰል ችግር ነበረው ቢባልም፣ በተግባር ምርጫ የሚካሄድበት አገርና ሕዝብ ሆነናል፡፡

ምርጫ በማካሄድ መንግሥትን ሥልጣን ላይ ማስቀመጥ ማለትና ለገዥው ፓርቲ ሕዝባዊ ድምፅ ሰጥቶ በአመራር ላይ ማስቀመጥ ማለት ግን በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ኃላፊነት የማኖር ተግባር ነው፡፡ ኃላፊነቱም ሕዝብን በግዴታም በውዴታም የማገልገል ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ሕዝብ መንግሥትን የሚመርጠው፣ አመራርን የሚመርጠው፣ አስተዳደርን የሚመርጠው ‹‹አገልግለኝ›› ብሎ ነው፡፡

ስለሆነም በሕዝብ ተመርጦ ሥልጣን ላይ የተቀመጥኩ መንግሥት ነኝ የሚል ገዥ ፓርቲ አለቃዬ የመረጠኝ ሕዝብ ነው በማለት ማመን አለበት፡፡ በሕዝብ መመረጥ መብቴ ነው የሚል ገዥ ፓርቲ ሕዝብን ማገልገል ግዴታዬ ነው ብሎም ማመን አለበት፡፡ ሕገ መንግሥታችንም ያስገድደዋል፡፡

ሕዝብ አለቃዬ ነው፣ ሕዝብን ማገልገል ግዴታዬ ነው ብሎ የሚያምን መንግሥት ደግሞ የሕዝብን ጥያቄ ይመልሳል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲ ራሱን መጠየቅ፣ መፈተሽና መገምገም ያለበት በእውነት የሕዝብን ጥያቄ እየመለስኩ ነው ወይ? ብሎ ነው፡፡

ሕዝብ መልካም አስተዳደር እንዲኖር እየጠየቀ ነው፡፡ ሕዝብ እንደ አለቃ መንግሥትን ሥልጣን ላይ ያስቀመጥኩህ መልካም አስተዳደር እንድታመጣልኝ ነው፡፡ የት አለ መልካም አስተዳደሩ እያለ ነው፡፡

ኢሕአዴግ ደፈር ብሎ አዎን ሕዝብ ሆይ የሚገባኝን መልካም አስተዳደር ስላልሰጠሁህ ይቅርታ እጠይቃለሁ፤ አሁን ግን አሟላለሁ ማለት አለበት፡፡ የት አቤት እንደሚባል እየጠፋ ነው፡፡ መልስ ሰጪ እየታጣ ነው፡፡ እንባ ሲፈስ እንጂ ሲታበስ አይታይም፡፡ መልካም አስተዳደርን እውን አድርግ የሚለውን የሕዝብ ትዕዛዝ መንግሥት እንደታዘዘው እየፈጸመው አይደለም፡፡ መመረጥን እንደ ‹‹መርህ›› የሚወስድ መንግሥት ሕዝብን ማገልገል ግን ‹‹ገጠመኝ›› እያደረገ ነው፡፡

ሕዝብ ከሙስና የፀዳ አገልጋዩን ሠራተኛና ሹም ይፈልጋል፡፡ ሲመርጥም ይህን አገኛለሁ ብሎ ነው፡፡ ከሙስና የፀዳችሁ ሁኑ፣ ከሙስና ፀድታችሁ እኔን አገልግሉ የሚል ትዕዛዝ ነበር ያስተላለፈው፡፡ ለዚህ ትዕዛዝ ግን ‹‹ጥሪ አይቀበልም›› ምላሽ እየተሰጠ ነው፡፡

በሕዝብ ተመርጠው ሹመት ላይ የተቀመጡት ኃላፊዎች ትዕዛዙን ጥሰው ለግላቸው ጥቅማ ጥቅም እየተገዙና እየተረባረቡ ናቸው፡፡ የአገር ሀብት እያባከኑ ናቸው፡፡ ራሳቸውን ከሕዝብ በላይ እያደረጉ ናቸው፡፡ ተገዥነታቸው ለሕዝብና ለሕገ መንግሥት መሆኑ ቀርቶ ለገንዘብ፣ ለንብረትና ለጥቅማ ጥቅም ሆኗል፡፡

ሕዝብ ኑሮ ተወዷል፣ ሸክሙ ከብዶኛል፣ አሻሽሉት የሚል ትዕዛዝ ለመረጣቸው ኃላፊዎችና ላስቀመጠው መንግሥት እያስተላለፈ ነው፡፡ መንግሥት ግን ይህን የአለቃ ትዕዛዝ እያዳመጠና እየመለሰ አይደለም፡፡ መፍትሔ እየሰጠበት አይደለም፡፡

ሕዝብ ኑሮው እንዲሻሻል ባዘዘ ቁጥር መንግሥት ወዲያው ኑሮን ያሻሽላል ማለት አይደለም፡፡ ጊዜ ይፈጃል ሒደት አለው፡፡ ነገር ግን ትኩረት ሰጥቶ ርብርብና እንቅስቃሴ መጀመርና እንዴት እናሳካው ብሎ ከሕዝብ ጋር ሆኖ በፍጥነት መጀመር አለበት፡፡ ይኼ ጥረት አልተጀመረም፡፡ የሕዝብ አለቃነትና የመንግሥት ታዛዥነት በተግባር እየታየ አይደለም፡፡ ሕዝብ የመንግሥት ኃላፊዎች ኮራ፣ ጠንከር ያሉ፣ ብቁና ታታሪ እንዲሆኑ ይፈልጋል፡፡ ያዛል፡፡ ራሳቸው ኮርተው አገርን የሚያኮሩና የአገርን ክብር እንዲያስጠብቁ ይፈልጋል፡፡ ግን ይህንን የሕዝብ ትዕዛዝ መንግሥት በተሟላ መንገድ እያከበረውና እየተገበረው አይደለም፡፡ የሚልፈሰፈሱ፣ ለባለሀብት አሽከርና ተላላኪ የሆኑ፣ አገርንና ሕዝብን ከሚያኮሩ ይልቅ የሚያሸማቅቁና የሚያሳፍሩ ‹‹ክብር አልባ›› ኃላፊዎችም እየተስተዋሉ ናቸው፡፡ በሚያስገርም፣ በሚያሳፍርና በሚያናድድ ሁኔታ፡፡

ሕዝብ መንግሥትን እያዘዘ ያለውና መንግሥትም ሕዝብ አለቃዬ ነው ብሎ ማመን ያለበት፣ ጉዳይ ብዙ መልኮችና ገጽታዎች ስላሉት ነው፡፡ ሕዝብ ስለአገሬ ግልጽ፣ ወቅታዊ፣ ሀቀኛና ሚዛናዊ መረጃና መግለጫ እፈልጋለሁ እያለ ነው፡፡ እያዘዘ ነው፡፡ ነገር ግን በሕገ መንግሥቱና በሕጉ መሠረት ከመጓዝ ይልቅ መንግሥት የራሱን መገናኛ ብዙኀን በማጠናከር ላይ ብቻ ስላተኮረ የሞኖፖሊነት ባህርይ እያሳየ ነው፡፡ የሕዝብ ትዕዛዝ እየተከበረ አይደለም፡፡ የሕዝብን አለቃነት መንግሥት እያመነበት አይደለም፡፡ በሕጉ መሠረት ቴሌቪዥንም ለግሉ ዘርፍ ፈቅዶ፣ የግል ፕሬስንም አጠናክሮ ጎን ለጎን የተለያዩ ሐሳቦች የሚንሸራሸሩበትና የመረጃ ፍሰት የሚጠናከርበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ ታዛዥ ጠፋ እንጂ አለቃው ሕዝብ እያዘዘ ነው፡፡

ያለፈውን ድክመት መንግሥት በሚገባ ፈትሾና መርምሮ ለወደፊቱ ይህ ስህተትና ጉድለት እንዳይደገም ይጠንቀቅ፡፡ ሰሞኑን ምርጫ ይካሄዳል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላም ዋናው ምርጫ አለ፡፡

ለዚህ ምርጫ ኢሕአዴግ ሲዘጋጅና አሁንም በምርጫ አሸንፌ ገዥ ፓርቲና መንግሥታዊ ኃይል ሁኜ እቀጥላለሁ የሚል ከሆነ፣ ደግመን ደጋግመን የሕዝብን ፍላጎትና እምነት እንዲያስታውስ እንወተውታለን፡፡ የሕዝብ ፍላጎትና እምነትም ቀላልና ግልጽ ነው፡፡

‹‹በሕዝብ የተመረጥኩ ነኝ›› ብሎ የሚያምን መንግሥት ‹‹ሕዝብ አለቃዬ ነው›› ብሎም ይመን!!

Ethiopian Reporter

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: