ኑሮ እየተባባሰ ነው! መፍትሔውስ?

d9ce752361d454057c245a6d830e76f3_L

ኑሮ እየከበደ ነው፡፡ ገቢና ወጪ አልጣጣም እያለ ነው፡፡ ኑሮ እየከበደና እየተወደደ እየመጣ ለመሆኑ ልዩ ጥናትና ምርምር አያስፈልገውም፡፡

ግልጽና ግልጽ ሆኖ በየቀኑ በአደባባይ ኅብረተሰብን እየኮረኮመ ያለ ነውና፡፡ ምን እየኮረኮመ እንዲያውም እየደበደበና እየቀጠቀጠ እንጂ፡፡

ስለቅንጦት ዕቃ አይደለም እያወራን ያለነው፡፡ እጅግ በጣም መሠረታዊና አስፈላጊ ስለሆኑ ዕቃዎችና ሸቀጦች እንጂ፡፡ ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ስኳር፣ ልብስ፣ ትራንስፖርት፣ የጽሕፈት መሣሪያ፣ ወዘተ፡፡

የመንግሥት ሠራተኞችም ሆኑ የግል ድርጅት ሠራተኞች የሚያገኙት ደመወዝና ገበያው እየጠየቀው ያለው የገንዘብ መጠን በእጅጉ እየተራራቀ ነው፡፡ በቅጡ መመገብ፣ መልበስ፣ መጓጓዝ፣ መማርና መኖር አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ ኑሮ እየከበደ ነው፡፡

ይህ ችግር አስቸኳይ መፍትሔ ያስፈልገዋል፡፡
ከመፍትሔዎቹ አንዱ መነጋገርና መመካከር ነው፡፡ መንግሥት ወደ ሕዝብ ቀረብ ብሎ ስለአጠቃላዩ የኑሮ ሁኔታ መነጋገር አለበት፡፡ የሕዝቡን ሁኔታና ስሜት በትክክል መገንዘብ አለበት፡፡ ኑሮ እንደተወደደ መንግሥት አያውቅም ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን በሪፖርት በተዋረድ ማግኘትና በቀጥታ ከሕዝብ ጋር ተገናኝቶ ችግሩን ማወቅ ከፍተኛ ልዩነት አለው፡፡

እያነሳን ያለነው ተራ የዋጋ ጭማሪን አይደለም፡፡ የቢዝነስ መቀዛቀዝም እየተስተዋለ ነው፡፡ የባንክ ብድር ማግኘት ዕድል ቁልፍልፍ ሲል፣ ኤልሲ የመክፈት ዕድል እየጠበበ ሲመጣ የሥራ ዕድልንም ያጠባል፡፡ እንቅስቃሴን በመቀነስ ገቢና ክፍያም እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ በተጨባጭም አድርጓል፡፡

ስለሆነም ለኑሮ ክብደቱ መፍትሔ ለማግኘት መንግሥት በኢኮኖሚውና በቢዝነስ እንቅስቃሴው ላይ ምን ዕርምጃ ልውሰድ ብሎ ማሰብ አለበት፡፡ መንግሥት ራሱ የሚለውና የሚያምንበት፣ ነገር ግን በተገቢው ደረጃ ተግባራዊ ያልሆነ አስተሳሰብ አለ፡፡ የአገር ውስጥ ምርትን በመጨመር ከውጭ የሚገቡትን መተካትና አቅርቦትን በመጨመር በአነስተኛ ዋጋ ማግኘት መቻል የሚል ነው፡፡ ጥሩ በተግባር ግን ተፈላጊው ምርት ከውስጥ አድጎና አቅርቦት ጨምሮ ዋጋ ሲቀንስና የኑሮ ክብደት ሲሻሻል አይታይም፡፡ ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም የሚል መልስ ሊሰጠን ይችላል፡፡ በአንድ ቀን ባትገነባም ግንባታዋ ግን ይቀላጠፍ እያልን ነን ያለነው፡፡

ምግባረ ብልሹነት፣ ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር መጥፋትና የመሳሰሉት የኑሮ ክብደቱን ይበልጥ እያከበዱት ይገኛሉ፡፡ በኅብረተሰቡ ላይ አላስፈላጊ ወጪ እየጫነ፣ አላስፈላጊ ውጣ ውረድና ማንገላታት እየጨመረ ያለው የቢሮክራሲው አቅም ውሱንነትም ነው፡፡ በኪሳራ ላይ ኪሳራ እያስከተለ የሚጓዝ ቢሮክራሲ ነው ያለው፡፡

ለኑሮ ውድነቱና መካበዱ መንግሥት ብቻ አይደለም ተጠያቂው፡፡ በውጭና በአገር ውስጥ ጥረው ግረው ኑሯቸውን ለማሻሻል ባጠራቀሙት ገንዘብ ቤት በመግዛት የተደላደለ እንኖራለን ብለው ተስፋ ሲያደርጉ፣ ተስፋቸው በአንዳንድ የሪል ስቴት ባለቤቶች በኖ የቀረና ያጠራቀሙትን ገንዘብ የተዘረፉ ወገኖችም አሉ፡፡

መኪና ገዝተን ኑሯችንን እናሻሽላለን ብለው አስበው ወይ ከገንዘባቸው ወይ ከመኪናቸው ሳይሆኑ የቀሩ ወገኖችም አሉ፡፡ ታማኝና ጥሩ ባለ ሪል ስቴቶችና መኪና ገጣጥመው የሚያስረክቡ ባለሀብቶች አሉ፡፡ ምሥጋና ይድረሳቸው፡፡ አጭበርባሪዎችና ወሮበሎች መኖራቸውና የዜጎችን ኑሮ እያካበዱና እያበላሹ እንዳሉም አሌ የማይባል ነው፡፡

ከድህነት እንላቀቅ ብለናል፡፡ ኑሯችንን ወደ መካከለኛ ደረጃ እናሸጋግር ብለናል፡፡ በቀን ሦስቴ እንብላም ብለናል፡፡ ተግባር ላይ የሚውል ምኞት አይደለም፡፡ ግን ደግሞ ስለተነገረና መግለጫ ስለተሰጠበት ብቻ የሚሳካ ራዕይና ዕቅድ አይደለም፡፡ ዋጋ ይጠይቃል፡፡

ምን የሚሉት ዋጋ?
ፖሊሲ ማስተካከል አንዱ ዋጋ ነው፡፡ አሁን ያለውን ሁኔታ የሚለውጡና የሚያሻሽሉ አዳዲስ ‹‹አበረታች›› ፖሊሲዎች ሊነደፉ ይገባል፡፡ ኅብረተሰቡ ወደ ሥራ እየገባ ኑሮውን የሚያሻሽልበትና ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ሥራዎችና ኢንቨስትመንቶች ሊበረታቱ ይገባል፡፡ ሥራ እንዲፈጠር፣ ገቢ እንዲጨምር፡፡

የመልካም አስተዳደር ዕጦትንና ሙስናን የማስወገድ ከፍተኛ፣ ፈጣንና ቁርጠኛ ዕርምጃ ያስፈልጋል፡፡ መግለጫ ሳይሆን ተግባር፡፡

የውጭ ኢንቨስትመንት ሊበረታታ ይገባል፡፡ ነገር ግን ሀቀኛ ኢንቨስትመንት እንጂ ፌዘኛ ኢንቨስትመንት አያስፈልገንም፡፡ ሕይወት ለዋጭ ኢንቨስትመንት እንጂ አላጋጭ ኢንቨስትመንት በቃን፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ ኑሮ እየተካበደ ነው፡፡ ችግሩን መፍታት ይቻላል፡፡ ኑሮ እንዲሻሻል የመንግሥት፣ የሕዝብና የግሉ ዘርፍ የጋራ ምክክርና ርብርብ ያስፈልጋል፡፡

Ethiopian Reporter

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: