በሙት መንፈስ የምትመራ ብቸኛ ሀገር

ለዘመናት የነፃነት ሸማ ለብሳ የኖረች ታላቅ አገር የአያሌ ድንቅና ብርቅ ታሪክ ባለቤት የነበረችና በብልህ አመራራቸው አንቱ በተባሉ ልጆቿ ራሷም ሆነ የዜጎቿ ክብር ሳይጓደል የኖረች አገር ዛሬ ፋና ወጊ ሆኖ የሚታደጋት ዜጋዎቿን የሚያስተዳድርላት የሰው ደሀ ወይም የወላድ መካን ሆና በአለማችን ለመጀመሪያ ጊዜ በሙት መንፈስ በመመራት ብቸኛዋና ግንባር ቀደም አገር ለመሆን በቅታለች።

አቶ መለስ ዜናዊ ላለፉት ሀያ አንድ አመት ከበርሀ ጠንስሰው በመጡት ጥንስስ ሀሳብ እየታገዙ አገራችንን የባህር በር ከማሳጣት ጀምሮ የዜጎችን ሰብአዊ መብትና ክብር በመርገጥ የተወለዱበትን ብሔረሰብ ከወርቅ ተራ በመመደብ ሌላውን በማሳነስ አገር እመራለሁ ከሚል ከመጨረሻው መንግስታዊ የስልጣን ማማ ላይ ከተቀመጠ ሰው በማይጠበቅ ወፍ ዘራሽ ንግግራቸው የመሰላቸውን ሲክቡ ያልመሰላቸውን ሲያኮስሱ በዚች ምድር ላይ ብቸኛ የሁሉ ነገር አፍላቂ ከአገራችህ አልፈው የአፍሪካና የአለም ሕዝቦች ተቆርቋሪ ለመምሰል ብዙ የሐሰት ድርሳናትን የደረደሩ ከመሆናቸውም በላይ እንደተፈጠሩ ዘላለማቸውን የሚኖሩ የመሰላቸው ሞት የሚባለውን የሕይወት ማሳረጊያ የረሱ ሰው ቢሆኑም እሳቸው ሞትን ቢረሱት እሱ ግን ሳይረሳቸው ባለተራ አድርጎ ድንገት እሳቸው በተቃዋሚዎቻቸው ላይ የሚመዙትን ቀይ ካርድ አይምሬ ሞት የራሱን ቀይ ካርድ መዞባቸው በወርሃ ነሐሴ በግል ንብረትነት መዝግቦ መኖርና ማረፍ በሚገባቸው ቦታ ወስዶ እረጅሙን የጥፋት እቅዳቸውን በአንድዬ ቸርነት አምክኖልናል።


መቼም በባህላችን “ሙት አይወቀስም” ቢባልም ሰውዬው ዝምታን እያስጣሰ ሊያስወቅሳቸው የሚችል አያሌ የሞገደኛነት ባህሪ እንዳላቸው አያከራክርም። ሆኖም ዳግም ላይሰድቡንና ላያዋርዱን ተጠናቀው ላይመለሱ ሄደዋልና ባሉበት ይመቻቸው። በራሳቸውም አነጋገር መገዱን ጨርቅ ያርግላቸው።
አሁን እኔን ያሳሰበኝና አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚጋራው ተመሳሳይ ስጋት ኢትዮጵያ የምንላት ታላቅ አገርና ኢትዮጵያዊ የሚባለው ኩሩ ሕዝብ ዛሬ በማን እየተመራን እንዳለ ለይተን ለማወቅ ከማንችልበት ደረጃ ላይ እንገኛለን። አቶ መለስ እመራዋለሁ ለሚሉት ሕዝብ ሊገለፅ ባልቻለ የጤና ጠንቅ እስከወዲያኛው ቢያሸልቡም ከህልፈታቸው በኋላ መንበራቸው ላይ የመቀመጥ እድል የገጠማቸው አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የአመራር የብቃት ደረጃቸው ከሩቅና ከቅርብ ለተመለከታቸው የሚታዘንባቸው ሳይሆኑ የሚታዘንላቸው ሰው እየሆኑ መጥተዋል።
ይህንን አባባሌን ሰፋ ለማድረግ ኃይላማርያም ደሳለኝን ላስተዋላቸው እንደ ገና ዳቦ ከላይ እሳት ከታች እሳት ሆኖባቸው መብሰል ይሁን ማረር ባልታወቀ መንገድ ሲንከላወሡ ላያቸው ስልጣኑ ምነው ቢቀርባቸው ያሰኛል። ሰውዬው ዛሬ የእለት ተእለት ንግግራቸውም ይሁን እንደ ጠ/ሚኒስትርነታቸው በመገናኛ ብዙሃን የሚደረግላቸውን ቃለ መጠይቅ ሲመልሱም ሆነ መግለጫ ሲሰጡ የሟቹን ሁለንተናዊ የአነጋገር ዘይቤ ሳይቀር በኑዛዜ የተረከቡ ይመስል መናገርና መደመጥ ከጀመሩ አንድ ሁለት ወራት ማስቆጠር ችለዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ የቪኦኤ ሀላፊ የሆነው ፒተር ሃይላይን ባለፈው ወር ያቀረቡላቸው ቃለ መጠይቅና የአቶ ኃይላማርያም ሽሙጥ አዘል ምላሽ በአንክሮ ላዳመጠ አቶ መለስ በአቶ ኃይላማርያም ሆድ እቃ ውስጥ መሽገው የሚያወሩ እስኪመስል የቃላትና የአረፍተ ነገር አሰካካቸውን ላስተዋለ የአቶ መለስን ሞት ከሚጠራጠርበት ደረጃ የማይደርስበት ምክንያት ያለ አይመስለኝም።
ብዙ ወንድሞቼ “ትንሽ እድል ለኢዲሱ ጠ/ሚኒስትር ልንሰጣቸው ይገባል” በሚል መንፈስ በተለያዩ ድህረ ገፆች ላይ “ግልፅ ደብዳቤ ለጠ/ሚኒስትር ኃይላማርያም ደሳለኝ” በማለት የሰውዬውን የእምነት መሰረት የሆኑ ውድና ምርጥ
የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በማጣቀስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በጎ መንፈስ ያዘሉ ውብ ፅሁፎችን አስነብበውናል ግን የተፃፈላቸው ግለሰብ ራሳቸውን ለመሆን ገና ብዙ ይቀራቸዋል። እናም የአቶ ኃይላማርያም በራስ የመተማመንና በዚያ ደረጃ አገግሞ የመገኘት ጉዳያቸው ሲፈተሽ በጊዜ ቀጠሮ ለማስቀመጥ ብዙ አሻሚ ገፀ ባህሪያት በሰውዬው ላይ ፍንትው ብለው ይታያሉ፡፡ በአንድ በኩል መንፈሳዊነታቸው ጭልጥ ያለ የሰብሃዊ መብት ረገጣ ወደሚፈፅሙበትና ወደሚያስፈፅሙበት ቁልቁለት ሊያንደረድራቸው አልቻለም። በሌላ በኩል ከአቶ መለስ ብዙ ነገር ተምሬያለሁ የሚሉት የመለስን ድርሳን የመድገም አባዜያቸው በተለያዩ መድረኮች እንደሚሉት “የታላቁን መሪ” ትልሞ ተግባራዊ ከማድረግ ውጪ የራሳቸውን አዲስ ሀሳብ የማመንጨት ብቃታቸውን ከሙከራቸው በፊት በአራት ነጥብ ያመከኑት የሚያስመስል ንግግር ያሰማሉ ምንም እንኳ የተፈጠሩትም ከደቡብ ክልል ቢሆንና የሚያራምዱትም በዚያው ክልል ሲነሱ ይዘውት በተነሱት የፖለቲካ ድርጅት እሳቤ ቢሆንም ከፊትና ከኋላቸው በሕዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይና (ሕወአት) እና በብአዴን የበርሃ ግብረ ኋይሎች አጣብቂኝ ተይዘው “እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው” በሆነ የስልጣን ዥዋዥዌ ላይ ሲንገላቱ ሳያቸው ይብሱኑ እያዘንኩላቸው መጣሁ።
እናም የሚከተለውን የበኩሌን ሀሳብ ልሰነዝር ወደድኩ፡ ክቡር ጠ/ሚኒስትር ኃይላማርያም እባክዎ እርሶ የሚያመልኩት አምላክ ሲፈጥሮ ለርሶዎ የሚሆን ፀጋና ባህሪ ማንም ሊጋራዎት ሌላው ቀርቶ ቤተሰቦችዎ እንኳ ሊወርሱት የማይችሉት ብቸኛ የርሶነት ብቃት ስላሎዎት ሳያመነቱ ወደ ራስዎ የአስተሳሰብ አድማስ ይመለሱ፣ እርሶ የሚለብሱት ልብስ በራሶ ልክ እንጂ በሌላ ሰው የተሰፋ ስለማይሆን አገርን ባፈረሰ ብሔረሰብን ከብሔረሰብ ባጋጨ የመጥፎ ሐሳብ ባለቤት በሆነ እኩይና ሙት መንፈስ ወረስኩ ወይም የመለስን ራእይ አስፈፅማለሁ ከሚለው የተሳሳተና የፌዝ መንገድ ተመልሰው የአገራችንንና የሕዝባችንን የሰቆቃ ዘመን በማሳጠር ከሁሉም የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በመነጋገር ወደ ብሄራዊ እርቅ እንዲያመሩና በሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች እንደባለድርሻ የሚሳተፉበትን እድል የመፍጠርና በሐሰት ክስ ተመስርቶባቸው በእስር ላይ የሚገኙ የነፃው ፕሬስ ሰዎችና ሌሎች ፖለቲከኞች ሁሉ ከእስር የሚለቀቁበትን ሁኔታ በማመቻቸት ይህን የመከራ ዘመን ቢያሳጥሩልን ለክብሮና ለስምዎ የማይደበዝዝ አሻራ የማያሳርፉበትን ምክንያት የለምና በሙት መንፈስ መምራቶን ትተው ወደ ሕሊናዎ ተመልሰው የተበከለውን የመለስን ራእይ እንደባለ ራእይው አፈር አልብሰው ያልተበከለውን የራሶን የብሩህ ዘመን ተስፋ ገቢራዊ ቢያደርጉት መልካም ነው እላለሁ።
ይህን ለመከወን ከወዲሁ የራስዎን ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ካልተነሱ መጪው ጊዜ ለርሶዎና ለመንግስትዎ እንዲሁም ለሚመሩት ህዝብና ሀገር ላይ አጣብቂኝ ችግር ውስጥ ተያይዘን እንዳንዘፈቅና ያልታሰበ አገራዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ እንዳይከሰት የበኩሌን ስጋት ካለሁበት ላሰማዎ ወደድኩ።

ቸር እንሰንብት ሳሙኤል /ከእስራኤል/

medrekonline

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: