የወንድሞች ከሳሽ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ማሳደዱን ቀጥሏል

(በጽሑፉ የተጠቀሰውን ደብዳቤ ከጽሑፉ መጨረሻ ያገኙታል)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን ቁጥር በ7 ሚሊዮን መቀነሱን ቀደም ብላ በ2002 ዓ.ም ቤተ ክርስቲያኗ በይፋ አምናለች፡፡ “ኤጲስ ቆጶስ ጠባቂ ነውና ይጠብቅ ተብሏል። እንደ ተባለው መንጋው ተጠብቋል ወይስ አልተጠበቀም? መንጋው አልተጠበቀም የሚለው መልስ እንደሚጎላ ግልጽ ነው። ይህንንም የሚያሳየው ያለፈው ዓመት የሕዝብ ቈጠራ ነው። መንጋው በትክክል ከተጠበቀ 7,000,000 (ሰባት ሚሊዮን) ያህል ሕዝበ ክርስቲያን ለምን ቀነሰ? ይህን ያህል መንጋ በመናፍቃን ተሰርቋል ወይም ወደ ሌላ ሃይማኖት ተወስዷል ማለት ነው።” (የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ 17ኛ ዓመት የፓትርያርክነት በዓለ ሲመት 2002 ገጽ 34)።
ቤተክርስቲያን እንዲህ ስትል በአንድ ወገን መንጋው አለመጠበቁንና በዚህ ምክንያት መሰረቁን አምናለች፡፡ በሌላ በኩል ግን ሌሎች ሰረቁኝ ወሰዱብኝ ከማለት ባለፈ ምክንያቱን በሚገባ ያጤነችው አይመስልም፡፡ ሌሎች በውጪ አግኝተው ከወሰዷቸው በላይ እንደማኅበረ ቅዱሳን ያለ የወንድሞች ከሳሽና አክራሪ ቡድን እኔን አልመሰላችሁምና መናፍቃን ሆናችኋል በሚል በህገ ወጥ መንገድ ያሳደዳቸው ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ምናልባት ለቁጥሩ መቀነስ የማቅ እጅም እንዳለበት መታመን አለበት፡፡ ይሁን እንጂ ለወንድሞች ከሳሽ ለማቅ ይህ እንደሃይማኖተኝነት የሚቆጠር ትልቅ ገድል ነው፡፡ ማኅበሩ በዚህ ድርጊቱ ከማፈር ይልቅ “ቤተክርስቲያንን ከመናፍቃን እየጠብቅኩ ነው፡፡ እኔ ባልኖር ይህች ቤተክርስቲያን ትጠፋ ነበር” እያለ በመለፈፉ ብዙዎች ማቅን እንደቤተክርስቲያን ጠበቃ ያዩታል፡፡ ቢያስተውሉት ግን ይህ ቤተክርስቲያንን ሰው አልባ እያደረገበት ያለ የማቅ አጋንንታዊ ስራ ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ 7 ሚሊዮን ምእመናን የጎደሉት ማቅ እኔ እየጠበኳት ነው እያለ አሳዳጅነቱን እንደ ገድል በሚያወራበት ዘመን ላይ መሆኑ ነው፡፡
ታዲያ በማቅ ዘመን ቤተ ክርስቲያን አተረፈች? ወይስ ከሰረች? ሌላው ቢቀር እንኳን 7 ሚሊየን አማኞቿን ያጣችው ማቅ ለቤተክርስቲያን ዘብ ቆሜያለሁ እያለ በሚፎክርበት ዘመን መሆኑ ማቅ ቤተክርስቲያንን እያፈረሰ ለመሆኑ አንዱ ማስረጃ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ማቅ የቤተክርስቲያን ያልሆኑ ትምህርቶችን እያቀረበና ወንጌል እንዳይሰበክ እየተቃወመ ቤተክርስቲያንን የያዘበት ዘዴ ለጊዜው እንጂ ሰውን የሚያሳርፍና በቤተክርስቲያኑ የሚያጸና አይደለም፡፡ ስለዚህ ከአባላቱ ብዙዎቹ እንኳ እየከዱት ይገኛሉ፡፡ እርሱ ግን ቆም ብሎ ራሱን ከመመርመር ይልቅ በወግና በልማድ ተተብትቦ ማሳደዱን ቀጥሏል፡፡
ማቅ በዚህ ማሳሳቻው የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን እየከሰሰና ተጠርተው ሳይጠየቁ በአንድ ወገን ክስ ብቻ ህገ ወጥ ውግዘት ሲያስተላልፍ እንደኖረና አሁንም ሌሎችን ለማስወገዝ እየተራወጠ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ስንት ሊቃውንት እንዳላላፉባትና ትምህርቷ መጽሀፍ ቅዱሳዊ እንዳልነበረ ዛሬ ግን ሰው የሌለባት የምትመስለው ቤተክርስቲያን እውነተኛ ልጇችንና ሊቃውንቷን የምታወግዘው በአብዛኛው የስህተት ትምህርት ተገኝቶባቸው አይደለም፡፡ ቀደም ያሉት ሊቃውንት እንደዋና ትምህርት በማይቆጥሩትና በልማዳዊ ትምህርትነት በፈረጁት ማቅ ግን እንደ ትልቅ ዶክትሪን በተቀበለውና በሚመራበት የአዋልድ መጻህፍት ትምህርት መሰረት መሆኑ ደግሞ ቤተክርስቲያኗ ከትናንት ይልቅ ዛሬ ይዞታዋ እየወረደ መምጣቱንና ከቅዱሳት መጻህፍትና ከአበው ምስክርነት እየራቀች መምጣቷን ያሳያል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ማቅ የሚያቀርበው ክስ በእውቀት ተፈትሾ ሳይሆን በግፊት እንዲያልፍ መደረጉ ማቅ ያቀረበው ሁሉ ትክክለኛ ቤተክርስቲያን የተመሰረተችበት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ደግሞ ስህተት እየተባለና በሲኖዶስ እየተወገዘ መምጣቱ ቤተክርስቲያን መራቆቷን ያሳያል፡፡
ባለፈው ግንቦት የተላለፈው ውግዘት ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ እስካሁን በተከታታይ እያወጣን ያለነው በውግዘቱ ላይ የተመሰረተ ሀተታም ይህንኑ ያሳያል፡፡ ሲኖዶሱም እውነትን አውጋዥ ሐሰትን አንጋሽ መሆኑ ለቤተክርስቲያኗ ትልቅ አደጋ ነው፡፡ ውድቀቷንም ያፋጥነዋል፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያን ቆም ብላ ነገሮችን መመርመር አለባት፡፡
የወንድሞች ከሳሽ ማቅ ለእርሱ ያልተመቹትን ሁሉ መናፍቅ የሚል ስም እየሰጠ በርካቶችን ከእናት ቤተ ክርስቲያናቸው እንዳፈናቀለና አሁንም ለማፈናቀል ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ በ22/5/05 ለጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ ለብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ባቀረበው ክስ በጀርመን አገር በቪዝባደን የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት ቄስ ገዳሙ ደምሳሽ እንዲወገዙለት የጠየቀበትና የአውግዙልኝ እንቅስቃሴ የጀመረበት ደብዳቤ ከእጃችን ገብቷል፡፡
ቄስ ገዳሙን ለመክሰስ ማቅ ያቀረባቸው ሶስት ማስረጃዎች መሆናቸው የክሱ ደብዳቤ ያሳያል፡፡ የመጀመሪያው በቄስ ገዳሙ ደምሳሽ የተጻፉ ሶስት የኑፋቄ መጻህፍት አጭር መግለጫ 9 ገጽ የሚል ነው፡፡ የቄስ ገዳሙን መጻህፍት ገና ከመነሻው የኑፋቄ መጻህፍት ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ ኑፋቄ መሆን አለመሆናቸው በሊቃውንት ጉባኤ መች ተረጋገጠ? ማንኛውንም ጉዳይ ኑፋቄ ማለት የማቅ የተለመደ ክስ ነው፡፡ እስካሁን ከታየው ለማረጋገጥ እንደተቻለው የማቅ ክስ ቅዱሳት መጻህፍት በአዋልድ መጻህፍት መታረም አለባቸው የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ ምን ኑፋቄ አለ? ከማቅ በላይስ መናፍቃዊ ድርጅት የት አለ? ነገር ግን ቤቱ ሰው የሌለበት የተፈታ ቤት ስለሆነ መናፍቃን ይከበሩበታል፤ እውነተኞች ይወገዙበታል፡፡
የቄስ ገዳሙ መጻህፍት ኑፋቄ የተባሉት በምን ሚዛን ነው? ለማቅ አስተምህሮ ስላልተስማሙ ነው ወይስ እንደተባለው ኑፋቄ ስለተገኘባቸው? ይህን የሚያረጋግጠው ማነው? ማቅ ነው ወይስ የሊቃውንት ጉባኤ? የሊቃውንት ጉባኤው ከማቅ ተጽእኖ ነጻ ሆኖና በራሱ በመተማመን ይሰራል ወይ? ከግንቦቱ ሲኖዶስ ልምድ ስንነሳ ግን ማቅ ያቀረበው ክስ በቅዱሳት መጻህፍትና በቤተ ክርስቲያኗም መሰረታዊ አስተምህሮ ሳይመረመር በግልብ ስሜት በመነዳት ነው ውግዘቱ የተላለፈው፡፡ ዛሬም አዲስ ነገር አይኖርም፡፡ ሁሉም እንደተጻፈለት ይኖራል፡፡ ማቅ ቄስ ገዳሙ ትክክለኛና ሕይወት የሚገኝበትን ወንጌል ስላስተማሩ መናቅፍ ይላቸዋል፤ ያሳድዳቸዋል፡፡ ቄስ ገዳሙም ከኦርቶዶክሳዊ ትምህርት ሳይወጡ ለክርስቶስ ወንጌል ዘብ ስለቆሙ መናፍቅ ይባላሉ ይሰደዳሉ። “በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።” (2ጢሞ. 3፡12)፡፡ ክሱ በዚህ መንገድ የመጣና በሌላ ወንጀል ባለመሆኑ ለቄስ ገዳሙ ትልቅ እድል ነው፡፡
ሁለተኛው የክስ ነጥብ “የሦስት መቶ ሰላሳ አምስት ምእመናን ፊርማ የያዘ ማመልከቻ”የሚል ነው፡፡ በቅድሚያ በአድማና በምእመናን ፊርማ አንድ ቄስ መናፍቅ ይባላል ወይ? አድማውን ያስተባበሩትና ፊርማውን ያሰባሰቡት የማቅ ሰዎች ቢሆኑስ? የሃይማኖት ጉዳይ በሃይማኖት ትምህርት እንጂ በምእመናን ፊርማ የሚታየውስ ከመቼ ጀምሮ ነው? በመጀመሪያ አድመኝነት የሥጋ ስራ አይደለም ወይ? ዳሩ ይህ በማቅ ሰፈር መች ይታወቃል!
ሶስተኛው የክስ ማስረጃ ደግሞ፣ “የምእመናንን ቁጣ የሚያሳይ የምስልና የድምጽ ዝግጅት 1 ሲዲ” ነው፡፡ ይህም ከሁለተኛው ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው ከአድማ ጋር የተያያዘ እንጂ ሃይማኖታዊ ይዘት የለውም፡፡ ምናልባት በቪሲዲው ላይ የተባሉት ምእመናን የተቆጡት በሃይማኖት ጉዳይ ነው ቢባል እንኳን አሁንም መንፈሳዊነት የጎደለው ነው፡፡ ቁጣ የሥጋ ስራ ነው፡፡ የሃይማኖት ትምህርት እንጂ ቁጣ ለመናፍቅነት ማስረጃ ሆኖ ሊቀርብ አይችልም፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው ማቅ በቄስ ገዳሙ ላይ የሚያስወገዝ ማስረጃ ሊያገኝላቸው አለመቻሉንና በሌሎች ላይ ሲያደርግ እንደነበረው ፊርማ በማሰባሰብና ቁጣን በማነሳሳት ትክክለኛ የቤተክርስቲያን አባቶችን የማሳደድ ተግባሩን እንደገፋበት ነው፡፡
እንደ ቄስ ገዳሙ ያሉና ሰው ከቤተክርስቲያኑ እንዳይወጣና ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት በእናት ቤተክርስቲያኑ ሆኖ እንዲማርና በሃይማኖቱ እንዲጸና የሚያደርጉትን እውነተኞች በማሳደድ ምእመናንን ከቤተክርስቲያን እንዲሰደዱ ማድረግ ትናንትም ሆነ ዛሬ የማቅ ዋና ሥራ ሆኗል፡፡ ማቅ የቤተክርስቲያን ልጆችን በዚህ መንገድ ባሳደደ ቁጥር እነርሱ እንደሚባዙ ግን አላስተዋለም፤ አላወቀም፡፡ ስደት ያበዛል እንጂ እኮ አያጎድልም፡፡ ማቅና የግብር አባቱ የወንድሞች ከሳሽ ሰይጣን በታሪክ ውስጥ የማይማሩት እውነት ቢኖር ይህ ነው፡፡ ሰይጣን ክርስቶስን በማሳደድና እንዲሞት በማድረግ የክርስቶስን ተልእኮ ያጨናገፈ መስሎት አይሁድን በእርሱ ላይ አነሳስቶ ነበር፡፡ አይሁድም የተሰጣቸውን ተልእኮ ፈጸሙ፡፡ የክርስቶስ ሞት ግን በእግዚአብሔር የተወሰነና ለእኛ ቤዛ የሆነ ሞት ነው፡፡ በክርስቶስ ትንሣኤ የእርሱ ሽንፈት ታወጀ፡፡ በክርስቶስ ላይ ባደረሰውና በውጤቱ መማር ያልቻለው ሰይጣን ሐዋርያትንም ማሳደዱን ቀጠለ፡፡ ነገር ግን ከግዛቱ ብዙዎች ወደ ክርስቶስ መንግስት ፈለሱበት፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ያድግና በየስፍራው ይበዛ የአማኞች ቁጥርም ይጨምር ነበር፡፡ ኧረ እንዲያውም ከካህናት ብዙዎቹ በወንጌል አመኑ ነው የሚለው የሐዋርያት ስራ፡፡ የወንጌል መንገድ ይኸው ነው፤ ዛሬም ከዚህ ውጪ የሚሆን ነገር የለም፡፡ የተጣለውን የወንጌል እሳት ማጥፋት አይቻልም፡፡ ክርስትና እንዲያውም በስደት ውስጥ ይስፋፋል፡፡ ስለዚህ ማቅ ሆይ እባክህን ዛሬ እንኳን ቆም በልና እያደረግክ ያለውን ነገር አስብ፤ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል፡፡
Kes gedamu
kes gedamu2

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: