ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ሹማምንቱን አስጠነቀቁ

8451fae78b6a67a12ffed23a03c952ee_L

• የኦብነግና የኦነግ አመለካከትን የተሸከሙ እንዳሉ ጠቁመዋል

• የባቡር ፕሮጀክት ሪፖርታቸው ከትራንስፖርት ሚኒስትሩ ጋር ይጣረሳል
• ነዳጅ ስለመገኘቱ ማረጋገጫ የለም አሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከተገቢው ጊዜ በላይ የዘገየውን የመንግሥታቸውን የሥራ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ዕለት አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ የተወሰኑ ኃላፊዎች ባህሪ ያስደሰታቸው አይመስሉም፡፡ በየደረጃው ያሉ ባለሥልጣናትንም አስጠንቅቀዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱና በፓርላማው ደንብ መሠረት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሥራ አፈጻጸሙን በዓመቱ አጋማሽና ማጠናቀቂያ ላይ ማቅረብ የሚጠበቅበት ቢሆንም፣ ከተሾሙ የሰባት ወራት ዕድሜ ያስቆጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ግን ከተገቢው ጊዜ ለሦስት ወራት በመዘግየት የስምንት ወራት የመንግሥት ሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን አቅርበዋል፡፡

ያቀረቡት ሪፖርት በርካታ አሳሳቢ ጉዳዮችን ለስለስ አድርጐ ያቀረበ አንዳንዶቹን ደግሞ የዘለለ ነበር፡፡ ነገር ግን ሪፖርታቸውን ካቀረቡ በኋላ ከምክር ቤቱ አባላት ጠጠር ባሉ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁ ሲሆን፣ ይህም በሪፖርታቸው ያልተነሱ ነጥቦችን እንዲዳስሱ አስችሏል፡፡

ከምክር ቤቱ አባላት የተነሱ የተወሰኑ ጥያቄዎች በመንግሥታቸው መዋቅር ውስጥ ያሉ አመራሮች ባህሪን እንዲናገሩ፣ ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክቶችንም እንዲያስተላልፉ ያስገደደ ነበር፡፡

ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በቅርቡ ተፈናቅለው ስለነበሩ ሦስት ሺሕ የሚሆኑ የአማራ ክልል ተወላጆች ጉዳይ፣ እንዲሁም በሐረርጌ ዞኖችና በሶማሌ ክልል መካከል የዜጐችን ሕይወት በቀጠፈው ግጭት ላይ የቀረቡላቸው ጥያቄዎች ዋነኞቹ ናቸው፡፡

በምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች ነዋሪዎችና በሶማሌ ክልል የሽንሌ ነዋሪዎች መካከል ተከስቶ ስለበረው ደም ያፋሰሰና የዜጐችን ሕይወት የቀጠፈ ግጭት ያነሱት አንድ የምክር ቤቱ አባል፣ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል፡፡

ጥያቄውን ያቀረቡት የምክር ቤት አባል በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረው ደም አፋሳሽ ግጭት በአሁኑ ወቅት የተረጋጋ ቢሆንም፣ ጥሎት ያለፈው ጠባሳ ቀላል አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ግጭቱን የቀሰቀሱት በክልሎቹ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ኃላፊዎች መሆኑን በመጠቆም መንግሥት በዚህ ዙሪያ የወሰደውን ዕርምጃ ጠይቀዋል፡፡

የችግሩ መንስዔ ከሕዝብ የመነጨ አለመሆኑን በማንሳት ምላሽ መስጠት የጀመሩት አቶ ኃይለ ማርያም፣ በአካባቢው የሚገኙ የታጠቁ ተቃዋሚዎችንና (መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጃቸው ድርጅቶች) በክልሉ መንግሥት ኃላፊዎች ላይ ጣታቸውን ቀስረዋል፡፡

‹‹ይህ ችግር የሁለት አካላት ችግር ነው፡፡ አንደኛው ይህንን መንግሥት እፋለማለሁ ብለው የሚንቀሳቀሱት ኦነግና ኦብነግ የእርስ በርስ ግጭት ነው፡፡ ሁለተኛው በእኛው መዋቅር ውስጥ ያሉ የኦብነግና የኦነግ አመለካከትን የሚሸከሙ ሰዎች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ ችግሩ የሚከሰትበት ወቅትና ጊዜ እንዳለው የጠቆሙት አቶ ኃይለ ማርያም፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው በአሸባሪነት የተፈረጁ ድርጅቶችን አመለካከት መሸከም ወንጀል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በኋላ አንዲት ነፍስ በዚህ አካባቢ ብትወድቅ በቀጥታ ወደሚፈለገው የሕግ ዕርምጃ እንደሚኬድ በመንግሥት በኩል በፅኑ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ ድርጊት በኬንያ ድንበር ሞያሌ አካባቢ ግጭት የፈጠሩ በሙሉ እስር ቤት መሆናቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሶማሌና በሐረርጌ ግጭት የተሳተፉ የክልሉ አመራሮችና ተጠርጣሪዎች ጉዳይ በምርመራ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹የፌደራል መንግሥት የትኛውም ክልል ገብቶ ሰብዓዊ መብት የማስከበር ግዴታ አለበት፤›› በማለት ማንኛውም አመራር ይህንን እንዲገነዘብ ከክልሎቹ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር መመርያው እንደተሰጣቸው አብራርተዋል፡፡ ‹‹ይህ በክልሎች ጣልቃ የመግባት ጉዳይ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም ክልል ተዘዋውሮ የመሥራት መብት እንዳለው በመግለጽ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሌላ ክልል ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎችን ከክልሉ እንዲፈናቀሉ መደረጉን ኮንነዋል፡፡ ከክልሉ እንዲፈናቀሉ የተደረጉት የአማራ ብሔር ተወላጆች ብቻ ሳይሆኑ፣ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችም መፈናቀላቸውን ጠቁመዋል፡፡ ድርጊቱን በፈጸሙ የክልሉ አመራሮች ላይም ሕጋዊ ዕርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡ ‹‹አፈናቃይ ተብዬዎቹ አመራሮች በሌብነት የተጨማለቁ ናቸው፤›› ያሉት አቶ ኃይለ ማርያም፣ አመራሮቹ መሬት በመቸብቸብ ተግባር ላይ የተሰማሩ እንደሆኑና ከዚህ ጥቅም ጋር የተሳሰሩ አማሮችም ሆኑ ኦሮሞዎች ጉዳት እንዳልደረሰባቸው አብራርተዋል፡፡

ይህ ተግባር አገርን የሚያጠፋ እንደሆነና ማንኛውም አመራር የዜጐችን መብት የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት አለበት ብለዋል፡፡ ይህንን በማይተገብሩ በየትኛውም ደረጃ ባሉ አመራሮች ላይ ደግሞ ጠበቅ ያለ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህን መልዕክት በየትኛውም ክልል ያለ የአመራር አካል ሊገነዘበው ይገባል፤›› በማለት አስጠንቅቀዋል፡፡

ሌላው አስገራሚ የሆነው ንግግራቸው የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ከወር በፊት ለፓርላማው ካቀረቡት ሪፖርት ጋር የሚጋጭ መሆኑ ነው፡፡ ሚኒስትሩ አቶ ዲሪባ ኩማ በትራንስፖርት ዘርፍ የመሥርያ ቤታቸውን የስምንት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት በአምስት ዓመቱ ዕቅድ ከተያዙት የባቡር ፕሮጀክቶች ውስጥ በተያዘላቸው ዕቅድ እየተከናወኑ ያሉት የአዲስ አበባ ጂቡቲ መስመርና የአዲስ አበባው ቀላል የባቡር ትራንስፖርት መሆናቸውን ጠቁመው ነበር፡፡ የተቀሩት የባቡር ፕሮጀክቶች በተለያዩ ችግሮች በዋናነት ደግሞ በከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ከተያዘላቸው ጊዜ በእጅጉ እንደዘገዩ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ከአምስት አበዳሪ አገሮች ጋር የብድር ድርድር እየተደረገ መሆኑን ለምክር ቤቱ አስረድተው ነበር፡፡ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት ሪፖርት በእጅጉ ከዚህ የተቃረነ ነው፡፡ ‹‹የገንዘብ ችግር የለብንም፤›› ያሉት አቶ ኃይለ ማርያም፣ በባቡር ፕሮጀክቶቹ ላይ የተስተዋለው መዘግየት በዋነኛነት በማስፈጸም ችግር የተነሳ ነው ብለዋል፡፡

የቻይና መንግሥት ለማበደር ዝግጁ መሆኑን የተናገሩት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ብድር ለመጠየቅ የሚያስችል ጥናት ባለመሠራቱ ነው ፕሮጀክቶቹ የዘገዩት፡፡ ይህ ደግሞ በዘርፉ ላይ የሚስተዋል የማስፈጸም፣ የዕውቀት ማነስና የልምድ ችግር ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በደቡብ ኦሞ በነዳጅ ፍለጋ ላይ የተሰማራው የሦስት ኩባንያዎች ጥምረት ነዳጅ ስለማግኘቱ የሚያሳዩ ፍንጮችን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ማስነገሩን የተቹ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን በዚህ ጉዳይ ተረጋግተው መቀመጥ እንዳለባቸው መክረዋል፡፡ በነዳጅ ፍለጋ የተሰማሩ ኩባንያዎች ብድር ለማግኘት ሲሉ እንደዚህ ዓይነት ተግባር እንደሚፈጽሙ በመጠቆም፣ በደቡብ ኦሞ ነዳጅ ፍለጋ የተሰማሩት ኩባንያዎች ጉዳይም ከዚህ የተለየ አይደለም ብለዋል፡፡ ኩባንያው ገና ቁፋሮውን አለማጠናቀቁንና በዚህ ደረጃ የተገኙ ፍንጮች ነዳጅ አለ ለማለት እንደማያስችሉ ተናግረዋል፡፡

Ethiopian Reporter

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: