“በሀገሪቱ የተደረገው ምርጫ የቧልትና የቀልድ ምርጫ መሆኑን ለህዝብ አሳውቀናል”

አቶ አስራት ጣሴ

አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ አስራት ጣሴ የዛሬ እንግዳችን ናቸው፡፡ አቶ አስራት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ(አንድነት) ዋና ጸሐፊና የመድረክ አመራር አባል ናቸው፡፡ የ33ቱ ፔቲሽን ፈራሚ ፓርቲዎች ጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴም ሰብሳቢ ናቸው፡፡ በወቅታዊ  የሀገሪቱ  ጉዳይ  ላይ  ከፍኖተ ነፃነት ጋር ቆይታ አድርገዋል  መልካም  ንባብ

ፍኖተ ነፃነት፡- የ33ቱ ፓርቲዎች ስብስብ እስካሁን ምን ምን አከናወኑ?

Asrat-Tassie-976x1024

አቶ አስራት፡- ከተፈራረምን 6 ወር የሆነን ሲሆን ተጨባጭ ሆኑ የስራ እንቅስቃሴዎችን አድርገናል፡፡ ከዚህም መካከል የሚያዚያ 2005 ዓ.ም. ምርጫን አስመልክቶ ለሀገሪቱ ይጠቅማሉ ያልናቸውን 18 ጥያቄዎችን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ለኢፌድሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ፣ ለኢህአዴግ ጽህፈት ቤት በማቅረብ ምርጫውን ነፃ፣ፍትሃዊ፣ ተዓማኒና ሰላማዊ እንዲሆን ትልቅ ትግል አድርገናል፡፡ ነገር ግን ከእነሱ በኩል ምንም ዓይነት ምላሽ ባይገኝም በእኛ በኩል ውጤታማ ስራ ሰርተናል ብለን እናስባለን፡፡ በርግጥ ከ33ቱ ውስጥ 5ቱ ከተፈራረምን በኋላ ወደ ምርጫ ቢገቡም የቀሩት 28ቱ በሙሉ ይህ ምርጫ ፍትሃዊና ተዓማኒ ስለማይሆን አጃቢ መሆን አንፈልግም በሚል ከምርጫው ወጥተናል፡፡
ከምርጫው የወጣነውም ተገደን እንደሆነና ቢያንስ 18ቱም ጥያቄዎች ባይመለሱም እንኳ በመሰረታዊ ሐሳቦች ዙሪያ ውይይት ቢደረግበትና የተወሰኑ ጥያቄዎች እንኳ ቢመለሱና በትንሹ ምርጫው ከፈት ቢል ወደ ምርጫው እንገባ ነበር፡፡ በመሐል ፒቲሽን ፈርሞ ወደ ምርጫው የገባው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ(ሲአን) ተመልሶ ወጥቷል፡፡ ስለዚህ በሀገሪቱ የተደረገው ምርጫ የቧልትና የቀልድ ምርጫ መሆኑን ለኢትዮጵያ ህዝብና ለዓለም አቀፉ ማኀበረሰብም አሳውቀናል፡፡ በዚህ ምርጫ መሳተፍ ለሰብዓዊ መብት መሻሻል፣ ለሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ዕድገት፣ የህግ የበላይነትና ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጥ ምንም ጥቅም እንደሌለው ነው የተረዳነው፡፡ በተፃፃራሪ መልኩ ያየነው እንደሆነ በዚህ ምርጫ መሳተፍ ማለት የሰብዓዊ መብት ጥሰትን፣ የዜጎች መፈናቀልን፣የዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰትን እንዲቀጥል መፍቀድና መቀበል ማለት ነው፡፡ ይህን ደግሞ የማንኛውም ሰው ህሊና የሚቀበለው ተግባር ስላልሆነ የጠቀስኳቸው የመብት ጥሰቶች በሀገሪቱ እንዲቀጥሉ ስለማንፈልግ ከምርጫው መውጣታችን ተገቢ ነው፡፡ ሌላው ትልቁ ውጤታማ ስራ የሆነው ሁሉም ፈራሚ ፓርቲዎች በየፓርቲያችን ከምርጫ ጉዳይ ባለፈ ወደፊት በጋራ ልንሰራቸው ስላሰብናቸው ስራዎች በሰፊው ተወያይተን የካቲት 23 ቀን 2005ዓ.ም በመኢአድ ጽህፈት ቤት በርካታ እንግዶች በተገኙበት የጋራ የስምምነት ሰነድ ተፈራርመናል፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- ወደ ፊት ሊያሰራችሁ የሚችል የመጨረሻ ሰነድ ነው ወይስ ከምርጫ ጉዳይ ውጭ ልትሰሩ አላሰባችሁም?

አቶ አስራት፡- የመጨረሻ የሚባል ሳይሆን በጋራ ለመስራትና ወጥ የሆነ አቋም ለመያዝ እንጂ  ከምርጫ ጉዳይ ባለፈ ወደፊት በተጠናከረ መልኩ በጋራ ሊያሰራ የሚችል ሰፊ ጥናት የተደረገበት ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለየፓርቲዎቹ ተበትኗል፤ ፓርቲዎቹም ተነጋግረው ለሚቀጥለው ስብሰባ ይቀርባል፡፡
ከላይ ከጠቀስኩት ውጭ ሰነዱን የፈረምን ፓርቲዎች በጋራ ህዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ ወስነን ስናበቃ እንቅፋቶች ገጥመውናል፡፡ ከገጠሙን ችግሮች መካከል ጥር 26 ቀን 2005 ዓ.ም. ህዝባዊ ስብሰባውን ለማካሄድ አዳራሾች ፈልገን በመጨረሻ ኢየሩሳሌም ሆቴልን አግኝተን ከተስማማን በኋላ እንደውም እኔው ራሴ 5ሺህ ብር ቀብድ ይዤ ስሄድ በመጨረሻ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ ከዛ በኋላ የወሰድነው እርምጃ አዲስ አበባ ባሉ የፒቲሽን ፈራሚ ፓርቲዎች አዳራሽን በመጠቀም ከህዝብ ጋር መወያየትን እንደ አማራጭ በመውሰድ በመድረክ፣ በአንድነት፣ በመኢአድ እና በሰማያዊ ፓርቲ ጽህፈት ቤቶች ግቢ ውስጥ መጋቢት 29 ቀን 2005 ዓ.ም. በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት የተለያዩ አመራሮች ከህዝቡ ጋር ተወያይተናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዕለቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ በራሪ ወረቀቶችን ለህዝቡ በመበተን የአዲስ አበባ፣ የድሬዳዋ እና የአካባቢ ምርጫ ነፃ፣ተዓማኒ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዳልሆነ በመግለፅ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን ባጭሩ ለማሳወቅ ችለናል፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- ከህዝቡ ያገኛችሁት ግብረ መልስ ምን ነበር?

አቶ አስራት፡- በአራቱ አባል ፓርቲዎች ያደረግነው ህዝባዊ ስብሰባም የተሳካ ነበር፡፡
እንደውም በወቅቱ ከተነሱ በርካታ ገንቢ ሐሳቦች መካከል 33ቱ የሚለው መቼ ነው ወደ አንድ የምትቀየሩት፣ እናንተ እንደዚህ መሰባሰባችሁን እንደግፋለን፤ በርቱና ጠንክራችሁ ስሩ፤ አብረናችሁ ነን የሚሉና እስካሁን የሚጠበቅባችሁን ያህል አልሰራችሁም፤ ፈርታችኋል፤ ደክማችሁብናልም የሚል ወቀሳም መጥቶብናል፤ ለዚህም በርካታ ምክንያቶች ያሉን ቢሆንም ወቀሳውን አምነን ተቀብለናል፤ በዚህ ችግር የለብንም፡፡ ለወቀሳው በእኛ በኩል የተሰጠው መልስ ጠንካራ ፓርቲና አመራር ሊወጣ የሚችለው ከጠንካራ ህዝብ መሐል እንደሆነ እና ለዚህም ህዝቡ ጠንካራ መሆን እንዳለበት ጠቁመናል፡፡ ከዚህ ውጭ አብራችሁ ወደፊት ለመቀጠላችሁ ምን አሳማኝና ተጨባጭ ዋስትና ትሰጡናላችሁ? ሀገሪቱ በአሁን ወቅት ከፍተኛ ችግር ላይ ነችና ከጋዜጣዊ መግለጫ ባለፈ ምን ልትሰሩ አስባችኋል? የሚሉና በርካታ ጥያቄዎችም ተነስተዋል፡፡ ይህም ለእኛ ትልቅ ስኬታማና ውጤታማ ውይይት ነበር፡፡ ከዚህ ውጭ በወቅቱ የታዘብነው ህዝቡ ምን ያህል ብሶት ውስጥ እንዳለ አይተናል፡፡  አመራሩ ጠንክሮ ከወጣና ጥሩ አመራር ካለ ህዝቡ እንከተላለን የሚል ምላሽ ሰጥቶናል፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- አሁን ያለው ጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ መቼ ነው ኃላፊነቱን የሚያስረክበው?

አቶ አስራት፡- የፊታችን ሚያዚያ 20 ቀን 2005 ዓ.ም. ነው፡፡ ያኔ አሁን ሲሰራ የነበረው እኔም ያለሁበት ጊዚያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ በወቅቱ ለሚመረጥ ቋሚ ኮሚቴ ያስረክባል፡፡ አሁን እኔም ያለሁበት ኮሚቴ ጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ነበር፡፡ አሁን ግን ይሄ ሰነድ ከተፈረመ በኋላ ጊዜያዊ አስተባባሪ የሚለው ኮሚቴ ቀርቶ ከየፓርቲዎቹ ሁለት ሁለት ሰዎችን ወክሎ ከዛ ውስጥ በመተዳደሪያ ደንባችን መሰረት በስድስት ወር አንዴ በሚደረግ ምርጫ በቋሚነት ዘጠኙ ተመርጠው አብይ ኮሚቴ በሚል ይተካል፤ ስራውም የተግባር ነው የሚሆነው፡፡ እዚህ ላይ ጉባዔው ከነባሮቹ ተወሰኑትን ሊወስድ ይችላል አሊያም ሙሉ በሙሉ ሊቀይርና ሊወስድም ይችላል፤ ይሄ ያኔ የሚታይ ነው፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- እራሳችሁን ከምርጫው አግልላችኋል፤ የሚያዚያውን ምርጫ እንዴት ታዘባችሁት?

አቶ አስራት፡- ይሄንን በሁለት መልኩ ነው የምናየው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ምርጫ ጣቢያዎቹ እጅግ ቀዝቅዘው ህዝቡ “ምን ተወዳዳሪ አለና ነው የምንመርጠው?” በሚል አብዛኛው ህዝብ እራሱ አለመሳተፉን ሂደቱን ከቃኙ አንዳንድ ጋዜጠኞችና ከህዝቡም ለማወቅ ችለናል፡፡ የነበረው ሂደት የመራጭነት ካርድ ይዘው የነበሩትን በግድ በየቤቱ በመሄድ ካርዱን አምጡ በማለት የማስፈራራት፣ የመቆጣትና የማዋከብ ሂደት እንደነበር የታዘብንበት ሁኔታ እንዳለና አሁንም ድረስ በህዝቡ እየተነገረ መሆኑ ምርጫ ነበረ ለማለት አያስደፍርም፡፡
ምክንያቱም ምርጫ እኮ የራሱ ደረጃ አለው፤ ህዝቡ በፍላጎቱ ሲፈልግ ይመርጣል ሳይፈልግ ይተዋል እንጂ በግድ በየቤቱ እያንኳኩ ምረጡ ማለት ህዝቡ መብቱን አያውቅም ማለትና ህዝቡን የመናቅ ያህል ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ ምርጫው አሳፋሪና አሳዛኝ ነበረ፤ ቀልድም ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ህዝብ ሃብት፣ ንብረት፣ ጊዜና ጉልበት በከንቱ የባከነበት ነው፡፡
ሌላው ምርጫውን የገመገምነው ከ33ቱ ፈራሚ አባል ፓርቲዎች መካከል በአመራርም የነበረው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ(ሲአን) በመርህ ደረጃ ምርጫው ነፃና ፍትሃዊ እንደማይሆን ቀድመን ብናውቅም የሲዳማ ህዝብ 5 ሚሊዮን በላይ የሆነ ብዙ ህዝብ ለምርጫ ወስኖና ቆርጦ በመነሳት ተዘጋጅቻለውና ወደ ምርጫው ግቡ ብሎ ባቀረበለት ጥያቄ መሰረት ወደ ምርጫው ሊገባ መሆኑን ባሳወቀ ጊዜ ፓርቲው የህዝቡ እንደመሆኑ መጠን እኛም ህዝቡ ለምርጫው ከተዘጋጀና ድምፁን ንቁ ሆኖ ለመጠበቅ ከበቃ ለሌሎች ወገኖቻችንም ትልቅ ትምህርትና ተሞክሮ ስለሚሆን ተስማምተን ሲአን ወደ ምርጫው ገብቶ ነበር፡፡ ሁኔታውን በጥብቅ በጋራ እየተከታተልን ሳለን ሲአንም በራሱ አባላትና በእኛም አመራሮችና አባላት ትልቅ ድጋፍ እየተደረገ ለምርጫው ቢዘጋጅም የኢህአዴግ የተለመደው አፈና፣ ግድያ፣ እስርና ስቃይ ተጠናክሮ በመቀጠሉ ምርጫው እሁድ ሊደረግ አርብ ዕለት እራሱን ከምርጫው ማግለሉን ይፋ አድርጓል፡፡
ለዚህም በርካታ ተጨባጭ ማስረጃዎች ከነ ሙሉ ሰነዶች እጃችን ላይ ገብቷል፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- አለ የሚሉትን መረጃ ማግኘት ይቻላል?

አቶ አስራት፡- አዎ፤ በተጨባጭ አለን፡፡ እንደውም እነኚህን ማየት ትችላልህ ( ከላይ የተጠቀሱትን ተፈፀሙ የተባሉ ችግሮችን ሰነድ ማየት ችለናል) የደኢህዴን/ኢህአዴግ አባላት የህዝብ ታዛቢ ሆነው ተመርጠዋል፣ የኢህአዴግ አባላት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ አስፈፃሚ ሆነው ተመድበዋል ይህም አባል የሆኑበትና የከፈሉበት ሰነድ ይኸው እጃችን ላይ ይገኛል፣ ከምርጫ ቀናት በፊት  ምልክት የተደረገባቸው የምርጫ ወረቀቶች ታድለዋል፣ አንድ ለአምስት በሚል ጥርነፋ ኢህአዴግን ለማስመረጥና እንዲመርጡ ለማድረግ ቃል በመግባት የተግባር ስራ የሚሰሩ ከነሙሉ ስም ዝርዝራቸው እና ግዴታቸው ሰነድ ከነ እጅ ፅሑፋቸው አለ፣ ሌላው ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ እንዲመርጡ ተመዝግበዋል፣ አንድ መራጭ ከአንድ በላይ የመራጭነት ካርድ እንዲወስድ ተደርጓል፣ የመራጩ የመኖሪያ ቀበሌ እና የቤት ቁጥርም ሆነ ሌላ አድራሻ የሌላቸው ተመዝግበዋል፡፡  በዚህ ሁኔታ በሀገሪቱ ላይ ምንም ዓይነት ነፃ፣ ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሊኖር አይችልም፡ገዥው ኢህአዴግም ሆነ በስልጣን ላይ ያሉት ቁንጮዎች ድፍረት ያነሳቸው በአዋጅ በሀገሪቱ ላይ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት የለም ብለው ማስነገር ነው እንጂ በተግባር በኢትጵያ የመደበለ ፓርቲ ስርዓት የለም ብዬ አፌን ሞልቼ መናገር እችላልሁ፡ስለዚህ ከላይ የጠቀስኩልህ ጥሩ ማሳያ ስለሆነ ፒቲሽን ፈራሚዎች ከአባላችን ሲአን ጋር በመሆን ያለውን እውነታ ከነሙሉ ማስረጃው አርብ ሚያዚያ 11 ቀን 2005ዓ.ም. የተሰጠውን መግለጫ ማየቱ በቂ ነው፡፡
ሌላው እጃችን ላይ ያለው ሰነድ ኢህአዴግ በድፍረት በየወረዳው ለምሳሌ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት በመንግስት ማህተም በመጠቀም መጋቢት 20 ቀን 2005 ዓ.ም. …ባለሃብቶች፣ ኩባንያዎች፣ ሪልስቴቶችና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በግድ 368 ሺህ ገንዘብ እንዲያዋጡ ደብዳቤ ፅፎላቸዋል፡፡ በደብዳቤው ማጠቃለያ ላይ እራሱ”…. ማሳወቅ ነው “ የሚል አስገዳጅ ነገር ነው የተቀመጠው፡፡
ይሄ ከዚህ በፊት በኢህአዴግና በመንግስት መካከል ልዩነት የለም፤ ሊኖር ግን ይገባል ብለን በተደጋጋሚ መጮሃችን ይታወቃል፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- ከምርጫው እራሳችሁን ማግለላችሁ ትክክል ነው ማለት ነው?

አቶ አስራት፡- አዎ፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዴት ምርጫ ማካሄድ ይቻላል? ስለዚህ ከምርጫ መውጣታችን ተገቢ ነው ብለን እናምናለን፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- ህዝባዊ ውይይቱንስ ከአዲስ አበባ ውጭ አድርጋችኋል?

አቶ አስራት፡- ይሄ የ 33ቱ ፓርቲዎች ጥምረት የገንዘብ አቅም ችግር አለበት፡፡ አሁን የምንንቀሳቀሰው ከራሱ ከየፓርቲዎቹ በሚሰበሰብ አነስተኛ ገንዘብ ነው፡፡ በርግጥ ዕቅዱ ቢኖረንም ካለብን የገንዘብ አቅም እጥረት የተነሳ በቅርቡ በክልሎች ውይይት ማድረግ አስቸጋሪ ቢሆንም ማድረጋችን አይቀርም፡፡ ለምሳሌ ከ33ቱ አባል ፓርቲዎች መካከል የሲዳማ አርነት ንቅናቄ(ሲአን) በቅርቡ በሐዋሳ ከተማ ህዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ ታስቧል፡፡ እዚህ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ የ33ቱም ፓርቲ ተወካዮች ይገኛሉ፡፡
ይሄ ካለቀ በቅርቡ ወደ ሐዋሳ እንሄዳለን ብለን እናስባለን፡፡ በዚህም ህዝቡ እያጋጠመ ያለውን ችግርና በመጨረሻው ሰዓት ለምን ከምርጫው እንዲገለል እንደተደረገና በአጠቃላይ ሀገራዊና አካባቢያዊ ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት እናደርጋለን የሚል እምነት አለን፡፡ ያኔ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት የሚያካትት ሀገር አቀፍ ህዝባዊ ንቅናቄ ለመፍጠር ሰፊ ስራ መስራት ይጠበቅብናል፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- ከዚህ በኋላስ ይሄ የ33ቱ ፓርቲዎች ጥምረት ወዴት ያመራል ብለን እንጠብቅ?

አቶ አስራት፡- በርግጥ ይህን ተንብይ ብባል መገመት ያስቸግረኛል፡፡ ምክንያቱም ገና በበርካት ሀገራዊ ጥያቄዎች ዙሪያ በሰፊው መነጋገር፣ መተማመን እና መግባባት አለብን፡፡ ምክንያቱም አሁን 33ቱ ፓርቲዎች ጠንክረው መውጣታቸውን በማየት ለመከፋፈል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ስለዚህ የአብሮነት ስራችን ተጠናክሮ መቀጠልና ከምርጫ ጉዳይ ባለፈ በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም ላይ በግልፅ በሰፊው መወያየት ያስፈልጋል፡፡
ይህ ማለት ግን በመሐከላችን ጥርጣሬ አለ ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ በአጭሩ ወዴት ያመራል የሚለውን ለመመለስና ወደ ግንባርና ውህደት ለማምራት በእርግጠኝነት ለመናገር ጊዜ ስለሚያስፈልግ ወደፊት አብረን የምናየው ነው የሚሆነው፡፡ በርግጥ በተለያየ ጊዜ በምናደርጋቸው ስብሰባዎች ላይ መቼ ነው 33ቱ፣ 28ቱ መባላችን ቀርቶ በአንድ ማኀተም የምንተዳደረው የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ የህዝቡም ግፊት ይሄው ነው፡፡ ይህንን እኛም የምንደግፈውና የምንቀበለው ጉዳይ ነው፡፡
ስለዚህ በጥንቃቄ ጊዜ ተወስዶ መሰራት አለበት፤ ይህም እንደሚሳካ ጥርጥር የለውም፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- አሁን ካላችሁት 33 ፖለቲካ የፓርቲዎች ውጭ ሌሎች ፓርቲዎችም መምጣት ቢፈልጉ ምንድነው ምታደርጉት? አባል መሆን ይችላሉ?

አቶ አስራት፡- ጥሩና ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡እዚህ ላይ ግልፅ መሆን ያለበት ጉዳይ ቢኖር በምርጫ መሳተፍና ከምርጫ እራስን ማግለል ጋር በተያያዘ ማንም ዘሎ እሚገባበት ቦታ አይደለም፡፡

እኛም የራሳችን መስፈርት ይኖረናል፡፡
ምክንያቱም እኛ የሀገራችን ኢትዮጵያን ጉዳይ ከምርጫ በላይ ነው የምናየው፡፡ ሌለው በግድም ይሁን በተለይየ ምክንያት ወደ ምርጫ የገቡም ቢሆኑ ከእነሱም ጋር መነጋገርና መስራት ይቻላል፤ ችግር የለብንም፡፡
ይህ ማለት ግን ያመለከተና እገባለሁ ያለ ሁሉ አባል ሆኖ ይገባል ማለት አይደለም፤ መስፈርት ይኖረናል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ጥያቄ ያቀረበ አካል ስለሌለ ወደ ዝርዝር መስፈርቱ መግባት አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡
በአጠቃላይ አብሮ መስራት የሚፈልግ አካል ካለ እናበረታታለን፣ እንደግፋለን፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- በመጨረሻ ከምርጫው ጋር በተያያዘ መናገር የሚፈልጉት ካለ ዕድሉን ልስጥዎት፡፡

አቶ አስራት፡- ማለት ያለብኝን ብዙ ብያለሁ፡ነገር ግን በስልጣን ላይ ያለው አካል ምርጫን ከስልጣን ጋር ብቻ ማያያዝና ማየት ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም የዴሞክራሲም ጉዳይ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ጉዳይ ደግሞ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ፣ የእኩልነት፣ የሰላምና መረጋጋት ፣የሰብዓዊ መብትና የሀገር ህልውና ጉዳይ ነው፡፡ስለዚህ ዴሞክራሲንና የህዝብን ጥያቄ አፍኖ በጦር መሳሪያ አስፈራርቶ ሁሉንም ነገር እንደፈለገ አደርጋለሁ ማለት ለማንም ለምንም አይጠቅምም፡፡ ኢህአዴግ እየሄደበት ያለው መንገድ አምባገነናዊ ስርዓትና በጦር መሳሪያ የሚደረግ ስልጣን ኪሳራ እንጂ ጥቅም የለውም፡፡ ስለዚህ ይሄ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከሀገራችን ተወግዶ ስልጣን የህዝብና ለህዝብ መሆን አለበት፡፡ ይሄ ደግሞ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ ባለመሆኑ ሁላችንም ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ ይገባናል እላለሁ፡፡

fnotenetsanet

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: