በፌዴራል ዋና ኦዲተር የ2004 ዓ.ም. ኦዲት ሪፖርት

– 1.4 ቢሊዮን ብር ያልተወራረደ ሒሳብ አለ

– 313.6 ሚሊዮን ብር ዕዳ ሳይመልሱ የተሸጡ ድርጅቶች አሉ
– 897.5 ሚሊዮን ብር ሕጋዊ ያልሆነ ክፍያና ወጪ ተደርጓል
– ከግብር ከፋዮች በስህተት የተሰበሰበ 2.4 ሚሊዮን ብር ይታያል

የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር በ124 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የ2004 ዓ.ም. ሒሳብን ኦዲት በማድረግ ማክሰኞ ዕለት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርብ፣ መንግሥት ሊያገኘው የሚገባ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ አለመታወቁንና በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ደግሞ መንግሥት ማጣቱን አስታውቋል፡፡

የኦዲት ሪፖርቱ ከመቅረቡ በፊት ከሚመለከታቸው ኦዲት ተደራጊ መሥሪያ ቤቶች ጋር በኦዲት ግኝቱና መደረግ በሚገቡ የወደፊት ኃላፊነቶች ዙሪያ ውይይት ከመደረጉም በተጨማሪ፣ ኦዲት ሪፖርቱ ተልኮላቸው የሰጡትን ምላሽ ያገናዘበ ስለሆነ የመረጃዎቹ ተዓማኒነት በሁሉም ወገን ተቀባይነት ያለውመሆኑን ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ ለምክር ቤቱ በማስረዳት ሪፖርቱን አቅርበዋል፡፡

በዚህም መሠረት በፋይናንስ አስተዳደር ደንብ በተደነገገው መሠረት ተሰብሳቢ ሒሳብ በወቅቱ መወራረዱ ሲጣራ በ57 መሥሪያ ቤቶች በድምሩ 1.4 ቢሊዮን ብር ውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳብ ሳይወራረድ ተገኝቷል፡፡

ከዚህ ውስጥ ትምህርት ሚኒስቴር 401.757 ሚሊዮን ብር የሚሆነውን ከፍተኛ ድርሻ የያዘ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 173.756 ሚሊዮን ብር፣ የግብርና ቴክኒክ ሙያና ትምህርት ሥልጠና ፕሮጀክት ማስተባበሪያ 155.597 ሚሊዮን ብር የታየባቸው ተጠቃሽ መሥሪያ ቤቶች ናቸው፡፡

ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶች የመንግሥት ገቢን በወቅቱና በአግባቡ መሰብሰባቸውን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከውዝፍ ግብር፣ ከወለድና ከቅጣት መሰብሰብ የሚገባው ብር 853.920 ሚሊዮን ብር የተገኘ ሲሆን፣ በሌሎች ስድስት መሥሪያ ቤቶች ደግሞ 12.250 ሚሊዮን ብር በድምሩ 866.171 ሚሊዮን ብር መኖሩ ተረጋግጧል፡፡

ሌሎች አምስት መሥሪያ ቤቶች የሰበሰቡት ገቢ ብር 24.606 ሚሊዮን ብር ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት ውስጥ ሳይካተት ተገኝቷል፡፡ በሌላ በኩል 15 መሥሪያ ቤቶች ከልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ ምንጮች ገቢ የሚሰበስቡ ቢሆንም፣ የገቢ ሪፖርት የማያዘጋጁ በመሆኑ ሒሳቡን ኦዲት ማድረግ ካለመቻሉም በተጨማሪ አምስት መሥሪያ ቤቶች የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርን ሳያስፈቅዱ የገቢ ደረሰኝ አሳትመው ገቢ እንደሚሰበስቡ ታውቋል፡፡

በወጪ ለተመዘገቡ ሒሳቦች የተሟላ ማስረጃ መቅረቡን ለማረጋገጥ ኦዲት በተደረጉ 13 ናሙና መሥሪያ ቤቶች የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ 132.364 ሚሊዮን ብር በወጪ ተመዝግቧል ሲል ሪፖርቱ ያትታል፡፡

ተሟልተው ካልቀረቡት ማስረጃዎች መካከል የተከናወነውን ሥራ በሚያሳይ ዝርዝር ማስረጃ ሳይደገፍ በቀረበ ጥያቄ ብቻ የተፈጸመ ክፍያ፣ በባንክ በኩል ገንዘቡ ተልኮ ሥራ ላይ መዋሉን የሚገልጽ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ የተመዘገቡ ሒሳቦች ጐላ ያሉት ናቸው፡፡

በሌላ በኩል 22 መሥሪያ ቤቶች 13.8 ሚሊዮን ብር ማስረጃ የሌለው ወጪ አድርገዋል፡፡ የመንግሥትን የግዥ አዋጅ፣ ደንብና መመርያን በመጣስ 30 መሥሪያ ቤቶች 353.568 ሚሊዮን ብር የሚወጣ ግዥ ፈጽመዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ዋነኞቹ ናቸው፡፡

ግዥዎቹ የተከናወኑት ያለጨረታና ያለፕሮፎርማ ውድድር መሆናቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ በሌላ በኩል 21 መሥሪያ ቤቶች ከደንብና መመርያ ውጭ 137.363 ሚሊዮን ብር ክፍያ እንደፈጸሙ ያስረዳል፡፡

በመቀጠልም በግንባታ ቦታ ላይ ላሉ ዕቃዎች፣ ከሚመለከተው አካል ሳያስፈቅዱ የትርፍ ሰዓት ክፍያ በመፈጸም፣ ሠራተኞች መስክ ላይ ሳይወጡ አበል በመክፈልና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ሳይፈቅድ የኃላፊነት አበል ለዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራሮች በመክፈልና በመሳሰሉት ጅማ ዩኒቨርሲቲ 77.611 ሚሊዮን ብር፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 34.771 ሚሊዮን ብር እና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ 10.825 ሚሊዮን ብር መክፈላቸውን ኦዲት ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

በበጀት ዓመቱ በደንብና በመመርያ በወጪ የተመዘገቡ ሒሳቦችን ለማጣራት በ12 መሥርያ ቤቶች ላይ በተደረገ ኦዲት በተሰብሳቢ መመዝገብ የሚገባው 546.599 ሚሊዮን ብር በወጪ ተመዝግቦ መገኘቱን ይገልጻል፡፡

በግዥ ሒደት ወቅት ያለ በቂ ምክንያት ዝቅተኛ ዋጋ ያቀረቡ እያሉ ከፍተኛ ካቀረቡት ግዥ በመፈጸም፣ ድጋሚ ክፍያ በመፈጸም ወይም ከተገባው ውል ውጪ በመክፈልና ከውሎ አበልና የትርፍ ሰዓት ተመን በላይ በመክፈል 11 መሥርያ ቤቶች 1.4 ሚሊዮን ብር ማባከናቸው ተገልጿል፡፡

የመንግሥት ገንዘብ ወጪ ሆኖ የተገዛ ንብረት ለመሥርያ ቤቱ ገቢ ለመሆኑ የንብረት ደረሰኝ ሳይቆረጥ ስድስት መሥርያ ቤቶች 20.240 ሚሊዮን ብር ክፍያ ፈጽመዋል፡፡ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ከውጭ 832,255 ዶላር ወጪ በማድረግ ተገዝተው ወደ አገር የገቡ ማሽነሪዎች ገቢ ያልተደረጉ መሆኑን የኦዲት ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በተለያየ ምክንያት የተሰበሰበ ቀረጥ ግብር ከፋዩ በስህተት የከፈለ መሆኑ ሲታወቅ ተመላሽ የሚደረግ ቢሆንም፣ በ2004 ዓ.ም. 2.4 ሚሊዮን ብር በስህተት የተሰበሰበ ገቢ ሳይመለስ በወጪ ተመዝግቦ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መቅረቡን፣ እንዲሁም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጉዳዩን እያወቀ እንዲመለስ አለማድረጉን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡

ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ላይ የክንዋኔ ኦዲት የሚያደርግ ሲሆን፣ የቀረጥ ነፃ ንግድ አሠራርና አፈጻጸምን በተመለከተ የኦዲት ሪፖርቱን አቅርቧል፡፡

በዚህም መሠረት በቀረጥ ንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ አካላት ገንዘብ በውጭ ምንዛሪ ለመቀበል የሚያስችል ፈቃድ ማውጣትና በየወቅቱ ማደስ ያለባቸው ቢሆንም፣ በዚህ ሥራ ላይ የተሠማራ አንድ የግል ድርጅት በአዲስ አበባ ኤርፖርት ተርሚናል አንድና ሁለት ውስጥ ላሉ ሁለት ሱቆች በውጭ ምንዛሪ ለመገበያየት ፈቃድ ሳይኖረው ከአሥር ዓመታት በላይ እየሠራ እንደሚገኝ የኦዲት ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ የሚመለከታቸው ተቆጣጠሪ አካላት ጉዳዩን አስመልክቶ ያደረጉት ነገር አለመኖሩንም ጠቅሷል፡፡

የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ በጋራ ልማትና ኢንቨስትመንት ከግል ባለሀብቱ ጋር በሚያስተዳድራቸው ድርጅቶች የኃላፊነትና ተጠያቂነት፣ እንዲሁም ውል ሲያቀርቡ ለመንግሥት ሊከፍሉት የሚገባ 106.481 ሚሊዮን ብርና 760 ሺሕ ዶላር ዕዳ አልገባም፡፡

በተጨማሪም 134.7 ሚሊዮን ብር ብድር ያልመለሱ የመንግሥት ድርጅቶች ስለመኖራቸው፣ የመንግሥት ትርፍ ድርሻ የሆነ 18.549 ሚሊዮን ብር ሳይከፍሉ የተሸጡ ድርጅቶች መኖራቸውንና 44.254 ሚሊዮን ብር ብድር ያለባቸው ድርጅቶች ሲሸጡ የገዛቸው አካል ብድሩን ለመንግሥት መክፈል ቢኖርበትም ይህ አለመሆኑን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

ሪፖርቱን ያዳመጡት የፓርላማ አባላትና የቋሚ ኮሚቴ አባላት ወደ ዕርምጃ ለመግባትና ኃላፊዎችን ለማስቀጣት ተስማምተው በዚህ ጉዳይ ላይ የቤት ሥራቸውን ወስደዋል፡፡

Ethiopian Reporter

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: