ይድረስ ለኢትዮጵያ ህዝብ – ልጆቼ እስር ቤት ግፍ እየተፈጸመባቸው ነው

0

ከኣስገደ ገ/ስላሴ

መቀሌ

ህገ-መንግስቱ የሰጠኝን መብት ተጠቅሜ በስልጣን ላይ ያለውን ገዢ ፓርቲና መንግስት በተለያዩ ጽሁፎች ስቃወም፣ የዓረና/መድረክ ተቃዋሚ ፓርቲም አባል ሆኜም ስንቀሳቀስ መቆየቴ ለህዝብ ግልጽ ነው። የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣናት ስም አጉድፈሀል በሚል ሰበብም ስታሰርና ስፈታ ቆይቿለሁ። ይህ አልበቃ ብሏቸው በልጆቼ መጡብኝ። አሕፈሮም እና የማነ አስገደ የተባሉ ሁለት ልጆቼ በአሁኑ ሰአት በተለያዩ አስርቤቶች ታስረው ሰቆቃ እየተፈጸመባቸው ይገኛሉ። ህዝብ እንዲያውቅልኝ ያክል የሚገኙበት ሁኔታ ይህን ይመስላል።

የአሕፈሮም አስገደ መታሰር

አሕፈሮም  እና የማነ አስገደ

በ 16/8/2005 ዓ.ም ቀበሌ 16 ኣካባቢ በኣንድ ሻሂ ቤት ቡና እየጠጣ ሳለ ከቀኑ ኣራት ተኩል በፖሊሶች ተይዞ በቀዳማይ ወያኔ ጣብያ ገባ:: ቤተሰቡ በጋደኞቹ ተነግሮን ሄደን ስንጠይቅ የለም ኣሉን፤ ውለን ኣደርን። ከ48 ሰኣት በኋላ እነሱ ጋር ታስሮ እንዳለ ኣመኑልን። መርማሪ የመቶ አለቃ ኣለም ከልጃችን ጋር ኣገናነኘን ስንለው ወንጀሉ ከባድ ስለሆነ ኣይፈቀድም ኣለን። ቀጥለን የጣብያው ኣዛዠ ኮሎኔል ኣንድነት ሊያገናኘን ጠየቅነው፤ ኣይቻልም ኣለ። ታድያ ለማን ኣቤት ይባል? ጨነቀን። በህገ መንግስት ድንጋጌ መሰረት ኣንድ ተጠርጣሪ በ 48 ሰኣት ግዴታ ፍርድ ቤት መቅረብ ኣለበት ግን ፍርድ ቤት ሳይቀርብ 55 ሰኣት ሆነ፡፡ ኣርብ ምሽት እኛ የሚቀርበው ሰኞ ነው ብለን ቤታችን ስንሄድ ሆን ብለው እኛ እንዳናየው ቅዳሜ በ 72 ፍርድ ቤት ኣቀረቡት። ለ30/8/2005ዓ.ም እንደተቀጠረ በወሬ ሰማን ልጃችን ለማየት ተነፈግን ብለን ስናዝን ይባስ ብሎ ኣስደንጋጭ መረጃ ሰማን ልጃችን በፖሊስ መኪና ሰዎች ታስረው የሚመረመሩበት የሚገረፉበት ጨለማ ቦታ 06 የህውሓት እስር ቤት ተወሰደ ኣሉን በመኪና ታፍኖ ሲሄድ ያዩ ወጣቶች ነገሩን፡፡

እኛም ወደ ቀዳማይ ወያኔ ፖሊስ ጣብያ ሄደን ለኮማንደር ኣንድነት ልጃችን የት ኣለ ብለን ጠየቅነው። ኮማንደሩ መጀመሪያ ሊደብቅ ሞከረ ጠንከር ብለን ስንጠይቀው ልጁ ወንጀሉ ከባድ ስለሆነ 06 ወስደነዋል ብሎ ኣስረዳን። የት ነው 06 በበረሃ የነበረ እስር ቤት ነው ስንለው ኣስገደ ለራስህ ተበከለህ እየጨሆክ እዚህ ያለውን ሰው እየበከልክብን ነህ በማለት ሰደበኝ ። መጨረሻው ከፈለግክ ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጠይቅ እኛ ኣናውቅም ኣለኝ ኣሁንም ቤተሰብ ተጨንቀን ልጃችን በዚያች የትግራይ ጋንታናሞ ሊገርፉት ነው ፡፡

06 የሚባል እስር ቤት በትግሉ ወቅት በበረሃ የነበረ እስር ቤት ነው። የታሰሩ ዜጎች ታጋዮች እና ሲቭል ህዝቦች የሚመረመሩበት የሚፈረዱበት የሚቀጡበት ነበር፡፡ ይህ እስር ቤት በ 1983ዓ.ም ጀመሮ ኣልፎ ኣልፎ ግን ህጋዊ ያልሆኑ ድብቅ እስርቤቶች በመቀሌ ባሎኒ ጫካ የበዛበት ጎድጓዳ ሸሎቆ ቦታ ዙሩያው በተራራ የተከበበ ወደ ሰማይ ካልሆነ ወደ መሬት ኣሻግረህ የማይታይበት ኣስጨናቂ ቦታ ለ 23 ኣመት 06 የተባለ ህቡእ እስር ቤት ከመላው የትግራይ ዞኖች ወረዳዎችና ሌሎች ቦታዎች እየመጡ የሚታሰሩበት እስርቤት መሆኑን ፍርድቤቶቸ ኣያውቁም ነበር። ኋላ ግን የክልሉ የፍትህ ፅህፈት ቤት ሃላፊ የነበሩ ኣቶ ጌታሁን ካሳ ጉዳዩ ስላሳሰባቸው ከሌሎች የሰራ ባልደረቦቻቸው ሆነው ህቡእ እስር ቤቱን ኣይተው ድርጊቱ በመቃወም በትግራይ ክልል መሪዎች ህጋዊ እስር ቤት ስላልሆነ ይዘጋ ብለው ኣስታየት ቢሰጡም በክልል መሪዎች ተቀባይነት ኣላገኙም። ይህ ድብቅ እስር ቤት ከ23 ኣመት በላይ በዋናነት በቀጥታ የሚያዙት ኣቶ ዘአማኑኤል ለገሰ /ወዲ ሻምበል/ በበረሃም የ 06 ሃለፊ ነበሩ በዚህ እስር ቤት 15-20 የሚሆኑ ነባር የ 06 ታጋይ የነበሩ ኣባላት ይገኛሉ መርማሪዎች እነሱ ጠባቂዎች እነሱ ናቸው። ወደ እዚህ እስርቤት ይቅርና ስቭል ህዝብ ከእነዛ የተመደቡ ፖሊሶች ውጭ ማንም ፖሊስ ኣይገባም። በተጨማሪ ይህ እስር ቤት በፍትህ ኣካላትም ኣይፈተሽም። ህጋዊ እስርቤት ስላልሆነ ሌሎች በመቀሌ ያሉ 7 እስር ቤቶች በፍትህ ኣካላት ይፈተሻሉ። የኔ ልጅም ወደ ዛ ጨለማ ቤት ነው ያስገቡት። ያ እስር ቤት በተራራ የተከበበ ስለሆነ ከ ጥዋት እስከ 7 ሰኣት ኣካባቢ የፀሃይ ብርሃን ኣይገባበትም። ከከተማ ራቅ ብሎ የተሰወረ ነው ወደእዛ ኣከባቢ ሰውም ሆነ እንስሳ ኣይዞርም።

እኛም ጥያቂያችን በመቀጠል ለቀዳማይ ወያኔ ፍትህ ፅህፈት ቤት ኣቃቢ ህግ ታጋይና ፖሊስ የነበረ ኣቶ ሙዑሾ ለወረዳው ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ ኣቶ መሓሪ ካሕሳይ ለወረዳው ዳኞች ፕሬዝደንት ወ/ሮ ሰብለ ኣለሙ በፅሑፍና በቃል ኣቤቱታ ኣቀረቡክ። ኣቃቢ ህግ ማዓሾ ቀርቦ የተደረገ ሁሉ ሊክደን ሞከረ፤ ግን ማስረጃዎች ስላሉን ምንም ለማድረግ ኣልቻለም። በዛ ወቅት የጠየቅናቸው ጥያቄዎች ልጃችን የት እንደታሰረ ሊነግረን ኣማካሪ ጠበቃ ሊያነጋግረው በግልፅ ከልጃችን ጋር ልንገናኝ፤ ልጃችን ያለበት ቦታ ስለማናውቀው ከኣሁን በፊት 06 ወስደው ገርፈው ለማንም እንዳይናገር ኣድርገው ለቀዉት ስለነበር የልጃችን ክብርና መብት ድህንነት የተጠበቀ እንዲሆን ከድብቅ እስር ቤት እንዲወጣ በህጋዊ ፖሊስ ጣብያና በሚመለከተው የ ወረዳ የስልጣን ክልል እንዲታሰር፤ ምግብ ኣስፈላጊ ቁሳቁስ እንድናቀርብበት

የተጠረጠረበት ወንጀል ካለ እንዲነገረን፤ ልጃችን ችግር እንዳለው ወሬ ስላገኘን የፍትህ ኣካላት በየሰብኣዊ መብት ጠባቂዎች ሄደው እንዲፈትሹት ነበር። ሰብሳቢው ዳኛ የጠየቅነውን መብት ሁሉ እንዲፈፀም ለኣቃቢ ህግ መዓሾ ነግረዉት ነበር ነገር ግን ያሁሉ የጠየቅነው ነገር ኣንድ ብቻ ከድብቅ እስር ቤት ሲወጣ በሌላ በኩል ግን በኣደራነት ነው የተረከብነው ከማንም ሰው ጋር እንዳይገናኝ ተብለናል ብሎ እስከ ዛሬ 25/8/2005 ዓ.ም ከልጃችን ልንነጋገር ኣልቻልኩም፤ የህገ ኣማካሪም ለማቅረብ ኣልተቻለም በምን እንደታሰረም ጀሮ ለባለቤቱ በኣድ ነው የሆነብን። ከሁሉም በላይ ደግሞ ለወላጆች በፖሊሶቸ የሚያጋጥመን ያለው የሰብኣዊ መብት ጥሰት ነው፤ ይሰድቡናል፣ ያናኑቁናል።

ሌላ ወደ የክልሉ ሰብኣዊ መብት እና እምባ ጠባቂ ፅህፈት ቤቶች ሄደን ነበር የሰብኣዊ መብት ጠባቂ ሃላፊ የህውሓት ኣባል ነበር ኣቶ ኣባዲ ይባላሉ ግን ኣልነበሩም። የፅህፈት ቤት ሬጅስትራር እና የፅህፈት ቤቱ ምክትል ቀደም ሲል የኣዲግራት ፖሊስ ጣብያ ኣዛዠ የነበሩ ኮማንደር ኣሁን ኣቶ ተብለው ብርሃነ ጼጥሮስ ታጋይ የነበሩ ልጃለም ሃ/ሰላሴ ታጋይ የነበሩ በፅሁፍና በቃል ኣነጋገርኳቸው። ደብዳቤ እንፅፋለን፤ ሄደንም እናነጋግረዋለን ኣሉን። እዚህ ላይ እስረኛው ከድብቅ እስር ቤት ከወጣ በኃላ በኣደራ እስር ቤት ሄደው ኣናግረውታል ያነጋገረው ብርሃነ ጼጥሮስ ነበር ። የእንባ ጠባቂ ሄጄ ኣቶ ኣናጋው ሲሳይ የኣስተዳደር በደል መርማሪ ከፍተኛ ባለሞያ የሚል ፅሁፍ በጠረቤዛቸው ነበር የሰጠኋቸው። ፅሁፉብዙውን ሳያዩ በዚህ በፍርድ ቤትና በፖሊስ የሚታይ የወንጀል ነገር እኛን ኣይመለከተንም ኣሉ። ገረመኝ፣ ኣዘንኩ። ከዚህ በኃላ ለኣቶ ዘአማኑኤል ለገሰ /ወዲ ሻንበል/ የህውሓት ካድሬ እና የትግራይ ክልል ፖሊሰ ኮሚሽነር በሁሉም የፍትህ ኣካላት ፅህፈት ቤት በፀሃይ ስዞር ከዋልኩ በኃላ በመቀሌ ፒያሳ ኮብራ መኪናቸውን ኣቁሞው ኣገኘኃቸው። ላልፋቸው ኣልፈለግኩም፣ ልጄ ካንተው የ06 እስር ቤት ኣውጣልኝ፣ ህጋዊ ኣይደለም። በዚህ መቀሌ ከተማ ያሉ ህጋዊ እስር ቤት 7 ብቻ ናቸው። 06 የሚባለው በበረሃ ጥለነው የመጣን ነው አልካቸው። እኔ ልጁ 06 የገባ መሆኑ የሰማሁት ዛሬ ጥዋት ነው። ኣሁን ኣየዋለው ኣለኝ። ይሀ የሚሆነው ማክሰኞ 22 /8/2005 ነው በዚያን ቀን በ 8 ሰኣት ኣካባቢ እስረኛው ልጄ ወደ የገጠር ወረዳ እንደርታ ወረዳ ንኡስ ፖሊሰ ጣብያ ወሰዱት።

እዚህ ላይ ስለ ልጃችን ስንከራከር ወንጀል ከፈፀመ ህግ ያውጣው ኣንከራከርም። እኛ የጠየቅነው ግን ፍትህ ኣጣን ነው ያልነው። የኣሕፈሮም ጉዳይ ይህ ኣሁንም ሁሉም ኣይነት ህገመንግስታዊ እና ዜግነታዊ መብቱ መጠበቅ ኣለበት፡፡

ይሁኑ ይባስ – የሁለተኛው ልጄ የማነ ኣስገደ መታሰር

የ27 አመቱ ልጄ የማነ አስገደ በሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ ዲግሪ ምሩቅ ነው። ይህ ልጅ በ2004 ዓ.ም ነሃሴ ወር ተመርቆ ለመምህርነት በውቅሮ ከተማ ተመድቦ ከዛም ምክንያቱ ባልታወቀ ወደ ኣጉላዕ ቀየሩት። በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ ቆላ ገርዓልታ ቀየሩት። ይህ ሁሉ በ 10 ቀን ውስጥ የተደረገ ነው ከዛ በኃላ ተበሳጨና ታመመ። እኛም ሄዶ እንዲሰራ ለምነነው ኣልቻልንም። ኣማራጭ ስላጣን ተረጋጋና ዝም ብለን ሲንኖር በማህሉ ታመመ። በህክምና ብዙ ጥረት ኣድርገን ለውጥ ሰላጣን በዚህ በቅርብ ሳምንታት ወደ ተወለደበተ ቦታ ማእከላዊ ዞን በድሮ ኣድዋ ኣውራጃ ወረዳ እምባስነይቲ ዓድ ሓላ ቀበሌ ወደ ሚገኝ ቤተሰቦቹ /የኣያቱ ቤት/ ፀበል እንዲታጠብ እናቱ ሻለቃ ግደይ ወ/ሚካኤል ይዛው ሄዳ እዛው ትታው ወደ መቀሌ ተመለሰች። እዛው ገጠር እያለ የኣካባቢው ህዝብ ያውቀዋል። በዚህ ሁኔታ እያለ ግን በኣከባቢው ኣንደ ኣደጋ ደረሰ። እሱም በኣዲሙናይ የሚባል ሰፈር ከ1-8 ክፍል የሚማሩበት በ21/8/2005ዓ.ም ከለሊቱ ከ8- 9ሰኣት ት/ቤቱ ተቃጥሎ ኣደረ። ላይብሬሪው ፍፁም ወድማል ከዛ በኃላ ማን ኣቃጠለው ሲባል የኣካባቢው የህውሓት ጥቂት ካድሬዎች እና የቀበሌ መሪዎች ፖሊስ ኣዘዠ ኮማንደር ሃ/ስላሴ በምንም የማይገናኝ ለበሽተኛው ልጄ ኣባቱ ኣቶ ኣስገደ የኣረና መድረክ ኣባል ፓርቲ ሆኖ ፀረ ወያኔ ስለሆነ ሆን ተብሎ በኣረና መድረክ ተልኮ ነው ት/ቤቱን ያቃጠለው በማለት የገጠሩ የቀበሌ ህዝብ በሙሉ እንደኣውጫጭኒ/አፍርሳታ/ ሰብስበው ልጄ የማነ ኣስገደ ኣስቁመው ሲመረምሩት ሲጠይቁት ዋሉ የቀበሌ ህዝብ ይህ ልጅ በፍፁም ኣንጠረጥረውም ታሞ ፀበል እየታጠበ የሚውል ከኣያቱ ቤት ወጥቶ ኣያውቅም ውሸታችሁ ነው ከኣባቱ ጋር ምንም የሚያያዘው የለም ኣባቱ ቢሆንም ለዚህ ደህንነት የሚያስብ እንጂ ኣደጋ ኣድርስ ሊለው ኣይችልም ብለው ሲቃወሙ የህዝብ ተቃውሞ ስለበረታ ህዝቡ ከስብሰባ በትኖ ልጄ ቤት ገብቶ ታሞ ተኝቶ እያለ በፖሊሶች እና ምልሻ ኣስረው ወሰዱት። ኣሁን በነበለት ከተማ ፖሊሰ ጣብያ ታስሮ ይገኛል። ነበለት ከመቀሌ በግምት 200ኪ.ሜ ነው ርቃ በስተሰሜን ትገኛለች። ይህ ጉዳይ ሃገርና ህዝብ ወዳድ የሆናችሁ በምንም ወንጀል ያልተገኘ በሽተኛ ልጄ ከተቃዋሚ ፓርት የኣረና መድረክ በማያያዝ ተላላኪ ነህ ብለህ ማሰቃየት

1ኛ ለልጄ በወንጀል ለዘላላም ጠባሳ መተው

2ኛ ለንፁሃን ዜጎች በወንጀል ለሰላማዊ ትግል ኣምነው ለሚታገሉ ፓርቲዎች ስም ማጥፋት

3ኛው በዋናነት ለኣስገደ ፤ ይሀ መወንጀል /ሴራ/ ህውሓት ከጥንት ጀምሮ ይዞት የመጣ ባህሪና ተፈጥሮ ነው። በተጨማሪ ለራሴ በትንሽ የስም ማጥፋት ወንጀል ከሰው እነሆ ከሰኔ 16/10/2003ዓ.ም እስካሁን ድረስ የሚያንገላቱኝ ያሉ ሆን ተብሎ እኔን ለማሰቃየት ብሎም በተፅእኖ እኔን ለአደጋ ማጋለጥ ያለመ ሴራ ነው። ይህ ተግባር በሌሎች ልጆቼም የማፈን ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ ይህ በቤተሰብ ደረጃ የዘርና የቂም በቀል ሴራ ለሃገራችንም ለህውሓትም ኣይጠቅምም። ኣንድ ነገር ግን ላረጋግጥላችሁ ምፈልገው እኔ ተንበርካኪ ኣይደለሁም። ህውሓት ህገ መንግስት የናዱ ኣሸባሪዎች እያለ ዜጎቹን በእስር እንዲማቅቁ እያደረገ ራሱ ግን በወጣት ዜጎች ሽብርተኘነትን እየፈፀመ ነው። ይህ ማሳያ የኣሕፈሮም እና የማየነ ልጆቼ ኣንዱ ማሳያ ነው፡፡ በእኔ ቤትና በሌሎች ዜጎችም ሽብር እየተፈጠረ ነው፡፡

በመጨረሻ ህውሓት ኢህኣደግ የማሳስበው ይቺ ሃገር ለሁላችን እኩል ናት የምትደርሰን። ለምን ይቺ ሃገር እናንተ ልጆቻችሁና ዘር መንዘራችሁ በኣሜሪካ ቻይና ኣውሮፓ በገንዘባችን ስታስተምሩና ስታበለፅጉ ልጆቻችን በእስር ቤት በሽብር ተውጠው ጭንቅላታቸው

ሊበላሽ ፍትሃዊ ኣይደለም። 80 ሚሊዮን ህዝብ ወደ ተሳሳተ መንገድ እንዲጓዝ ታደርጋላችሁ። ውጤቱ ደግሞ ለሃገራችን እና ለህዝባችን ጎጂ ነው፡፡ ህዝብ ነዋሪ ነው ስርኣትና መንግስት ግን ተቀያያሪ ነው። ደርግ ከ2ሚሊዮን በላይ ታጣቂ ነበረው። ህዝባዊ መሰረት ስላልነበረው ወደቀ። ለምን ህውሓት ኢሃደግ ከደርግ አይማርም? መወናጀሉ ቂም በቀል ይብቃ……… ይቺ ኣገር ቁልቁለቱን ተያይዛዋለች፣ ብታስቡበትስ……….

ኢትዮሚድያ

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: