አያት አክሲዮን ማኅበር 176.5 ሚሊዮን ብር ቅጣት ተጣለበት

hayat

– 79 ዓመታት እንዲቀጡ የተጠየቀባቸው ከፍተኛ ባለድርሻው 12 ዓመት እስራት ተፈረደባቸው

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዓቃቤ ሕግ ከሦስት ዓመታት በፊት ከመሠረታቸው 23 ክሶች ውስጥ በስምንት ክሶች ጥፋተኛ ተብሎ የነበረው ፈር ቀዳጁ የሪል ስቴት አልሚ ድርጅት አያት አክሲዮን ማኅበር፣ 176.5 ሚሊዮን ብር እንዲቀጣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ስምንተኛ የወንጀል ችሎት ግንቦት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

ፍርድ ቤቱ በዕለቱ ባስተላለፈው የቅጣት ውሳኔ፣ የባለሥልጣኑ ዓቃቤ ሕግ በቅጣት ማክበጃ ሐሳቡ፣ በዘጠኝ ክሶች ጥፋተኛ ተብለው የነበሩትን የ70 ዓመት አዛውንቱንና የአክሲዮን ማኅበሩ ከፍተኛ ባለድርሻና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አያሌው ተሰማን በድምሩ በ79 ዓመታት እንዲቀጡ ጠይቆ የነበረ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ በ12 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡ አቶ አያሌው ተሰማ ከእስራቱ በተጨማሪ ከ3.2 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል፡፡

ከአክሲዮን ማኅበሩ ጋር ክስ የተመሠረተባቸው የማኅበሩ የፋይናንስና ኢንቨስትመንት ዳይሬክተር ዶ/ር መሐሪ መኮንንና የፋይናንስ ክፍል ዋና ኃላፊ አቶ ጌታቸው አጐናፍር ናቸው፡፡

የባለሥልጣኑ ዓቃቤ ሕግ ከመሠረተባቸው ክሶች ውስጥ ዶ/ር መሐሪ በአምስት ክሶች ጥፋተኛ መባላቸውን ተከትሎ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበባቸው የቅጣት ማክበጃ ሐሳብ በ57 ዓመት ከዘጠኝ ወራት እንዲቀጡ መጠየቁ ይታወሳል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግንቦት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. በሰጠው የቅጣት ውሳኔ ደግሞ ዶ/ር መሐሪ በ12 ዓመታት ፅኑ እስራትና 436,969 ብር እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል፡፡ የቅጣት ውሳኔያቸውን ሲከታተሉ የነበሩት የዶ/ር መሐሪ ባለቤት፣ “ባለቤቴ ለ12 ዓመት የተቀጣው ሦስት ዓመታት ብቻ በሠራበትና ምንም በማያውቀው ጉዳይ ነው፤” በማለት ድምፅ እያሰሙ ሲያለቅሱ ተስተውለዋል፡፡

በስድስት ክሶች ጥፋተኛ የተባሉትና የባለሥልጣኑ ዓቃቤ ሕግ በቅጣት ማክበጃ አስተያየቱ በ62 ዓመት ከዘጠኝ ወራት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ጠይቆባቸው የነበሩት አቶ ጌታቸው አጐናፍር፣ በአሥር ዓመት ፅኑ እስራትና 411,969 ብር እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔውን አስተላልፏል፡፡

አያት አክሲዮን ማኅበር ከ176.5 ሚሊዮን ብር በላይ ቅጣት የተጣለበት በድምሩ ሲሆን፣ ጥፋተኛ በተባለባቸው ስምንት ክሶች በድምሩ 55 ዓመታት ከአንድ ወር ፅኑ እሥራት የሚያስቀጣው በመሆኑ ወደ ገንዘብ ተቀይሮ 90,081,270 ብር እንዲቀጣ፣ እንዲሁም ማኅበሩ የባንክና የፋይናንስ ተቋማትን ሥራ ተክቶ ሲሠራ የነበረ በመሆኑ 86,495,726 ብር እንዲወረስ በመደረጉ መሆኑን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አሳውቋል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ስምንተኛ ወንጀል ችሎት፣ አክሲዮን ማኅበሩንና አቶ አያሌው ተሰማን በጋራ ጥፋተኛ ባለባቸው ስምንተኛ ክስ ማለትም ከቀረጥ ነፃ ሆነው ወደ አገር ውስጥ የገቡ ስምንት ተሽከርካሪዎችና ሰባት ማሽነሪዎችን ለሦስተኛ ወገን ለኢትዮጵያ ማሽነሪ ሊዝ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አስተላልፈው መገኘታቸው በሰነድና በማስረጃ መረጋገጡን በመግለጽ ለመንግሥት በውርስ እንዲተላለፉ አዟል፡፡

ፍርድ ቤቱ ከላይ የተገለጹትን ቅጣቶች ሲጥል የባለሥልጣኑ ዓቃቤ ሕግና የተከሳሾች ጠበቆች ያቀረቡትን የቅጣት ማክበጃና ማቅለያ ሐሳቦችን ከሕጉ ጋር በማገናዘብ መመርመሩን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ ካቀረባቸው በርካታ የቅጣት ማክበጃ አስተያየቶች ውስጥ፣ አያት አክሲዮን ማኅበርና አቶ አያሌው ተሰማ የወንጀል ድርጊቶቹን የፈጸሙት፣ በሕጋዊ መንገድ ባፈሩት ሀብት ላይ አግባብ ባልሆነ መንገድ ተጨማሪ ሀብት ለማካበት በመሆኑ የሚለውን የማክበጃ ሐሳብ በወንጀል ሕግ ቁጥር 84(1ሀ) መሠረት እንደማክበጃ ከመውሰዱ በስተቀር፣ ሌሎች የማክበጃ ሐሳቦችን ውድቅ ማድረጉን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ አንድ ዕርከን በቅጣቱ ላይ መጨመር መቻሉንም ጠቁሟል፡፡

የተከሳሽ ጠበቆች ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ፣ አቶ ታምሩ ወንድምአገኘሁና አቶ ገብረእግዚአብሔር ተስፋይ ካቀረቧቸው በርካታ የቅጣት ማቅለያዎች ውስጥ፣ ተከሳሾቹ ቀደም ባሉት ጊዜያት የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸው መሆኑን፣ በሪል ስቴት ዘርፍ ፈር ቀዳጅ መሆናቸውን፣ በተለያየ የሥራ ዘርፍ ያደረጉትን አስተዋጽኦ፣ በትምህርት ዘርፍ ያደረጉትን አስተዋጽኦ፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸው፣ የልብ፣ የደም፣ የስኳርና የነርቭ ሕመምተኞች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ በመቅረቡ ለአክሲዮን ማኅበሩ አንድ ማቅለያ፣ ለአቶ አያሌው ሦስት ማቅለያ፣ ለዶ/ር መሐሪ ሁለት ማቅለያና ለአቶ ጌታቸው ሦስት ማቅለያ እንደተያዘላቸው ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አሳውቋል፡፡ በመሆኑም ከእስር ቅጣቱ ላይ እያንዳንዱ ማቅለያ ሦስት ዕርከን እንደሚቀንስ፣ በዚህ መሠረትም አቶ አያሌው ዘጠኝ ዕርከን፣ ዶ/ር መሐሪ ስድስት ዕርከንና አቶ ጌታቸው ዘጠኝ ዕርከን ተቀንሶላቸዋል፡፡ ማኅበሩን ጨምሮ በገንዘብ ቅጣቱ ላይ አንድ ዕርከን ብቻ ተቀንሶ ቅጣቱ መወሰኑን ፍርድ ቤቱ በችሎት በንባብ አሰምቷል፡፡

አያት አክሲዮን ማኅበር፣ ከፍተኛ ባለድርሻው አቶ አያሌውና አመራሮቹ በባለሥልጣኑ ዓቃቢያነ ሕግ ከሦስት ዓመታት በፊት ተመሥርቶባቸው የነበረው ክስ፣ ያልተፈቀደ የባንክ ሥራ መሥራት፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን መተላለፍ፣ የገቢ ግብር አዋጅን መተላለፍ፣ ሕገወጥ በሆነ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አድርጎ (አስመስሎ) መሥራት፣ በቀረጥ ነፃ መብት አላግባብ መጠቀም፣ በአራጣ ላይ የተመሠረተ ጥቅም መቀበልና የጉምሩክ ፎርማሊቲ ያልተሟላበት ዕቃ ይዞ መገኘት የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ፣ በጥቅሉ 23 ክሶችን መመሥረቱንና ሁለቱ ብቻ ውድቅ ተደርገው ተከሳሾቹ በ21 ክሶች ጥፋተኛ መባላቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Ethiopian Reporter

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: