አባይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መደበቂያ አይሆንም!

በስዊትዘርላንድ የሚገኙ የሲቪክ ተቋማት፣ የፖለቲካ ሃይሎችና፣ የዴሞክራሲና ሰብአዊ መብቶች ግብረ ሃይል የጋራ አቋም መግለጫ

በኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት በስልጣን ላይ ያለው ራሱን ወያኔ /ኢህአዴግ ብሎ የሚጠራው ገዢ አምባገነናዊ ቡድን በነዚህ አመታት የፈጸማቸውን እንዲሁም አሁንም እየፈጸማቸው ላሉት ግፎች መደበቂያ ይሆነው ዘንድ አፍራሽ ቀያሽ በሆነው መሃንዲሱ ሟቹ መለስ ዜናዊ አማካይነት የህዝቡን ቀልብ ይስብልኛል ያለውን የአባይ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ከዛሬ ሁለት ዓመት ቀደም ብሎ በሚያዚያ ወር 2003 ማወጁ ይታወሳል፣ በመሰረቱ ግድቡ ጥልቅ ጥናት ያልተደረገበት፣ ከበስተጀርባው ውስብስብና ያልተፈተሹ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና፣ ዲፕሎማሲያዊ ችግሮችን አግተልትሎ የያዘና ይልቁንም በወቅቱ በቱኒዚያ በግብጽና ሌሎች በዓረቡ አለም አካባቢዎች የተነሳውን ህዝባዊ ቁጣና ማእበል እንዳይዛመት ብሎም የህዝብን ቀልብ ለመስረቅ ተብሎ እንደሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ አስቀድሞ ያውቀዋል። በመሆኑም የተጠቀሱት አንኳር ችግሮች እንደተጠበቁ ሆነው መሰረታዊ የሆኑትን የህዝቦችን ጥያቄ ሳይመልሱ በአባይ ስም ህዝብን እያጭበረበሩ መኖር አይቻልም።

ገዢው ቡድን ስልጣን ላይ ከወጣበት ከመጀመሪያዎቹ አመታት ጀምሮ በዴሞክራሲያዊነት ስም እያጭበረበረ ነገርግን በስውርም በገሃድም ዜጎችን በማሸማቀቅ፣ መብቶቻቸውን በማፈን፣ ያለፍርድ በማሰር፣ ሲከፋም በመግደል ግፈኝነቱን አጠናክሮ የቀጠለበት ሲሆን ለዚህም በአገዛዙ የመጀመሪያ ምእራፍ የተፈጸሙት የአርባ ጉጉ፣ የበደኖ፣ እና አኙዋክ ማህበረሰቦች ጅምላ ጭፍጨፋ በቂ ምስክሮች ናቸው።

በወራሪ ስም ፋይዳው ለማይታወቅ ይልቁንም የሃገሪቱን ግዛት አሳልፎ ለሰጠውና የአገዛዙን እድሜ ለማራዘም በተከፈተው የኢትዮ_ኤርትራ ጦርነት ላይ ቁጥራቸው ከ60, 000 በላይ ወንድሞቻችን በበረሃ ደማቸው ከንቱ ሆኖ ቀርቶአል። ሲቀጥልም የይስሙላ ዴሞክራሲያዊነት ልፈፋውን የልመና ቋት/ከረጢቱን/ የሚሞሉለት ምእራባውያን እንዲሰሙለት በ1997 ዓም ነጻ ምርጫ አካሂዳለሁ በማለት ለፍፎ “በለፈለፉ ባፍ ይጠፉ“ እንዲሉ አምባገነኖቹ ገዢዎች በህዝብ ማእበል ተውጠው ያወሩበት ምላስ ሳይታጠፍ በህዝብ ድምጽ ላያገግሙ ተቀጡ ። ሆኖም ግን ይህን የህዝብ ማእበል ባዘጋጇቸው ቅጥር ነፍሰ ገዳይ አጋኧዚዎች በጥይት አረር አነደዱት። በዚህም ሳቢያ ከ200 በላይ ወገኖቻችን ግንባርና ደረታቸውን በጨካኞች ጥይት ተበስተው በየጎዳናው ወደቁ፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ የሲቪክ ተቋማት መሪዎችና አባላት፣ጋዜጠኞች፣ የሰ/መብት ተሟጋቾች ወጣቶች፣ የ70 እና የ80 ዓመት አዛውንቶች፣ ከ13 እስከ 18 ዓመት ያሉ ታዳጊ ህጻናት ሳይቀሩ የእስር ሰለባ ሆነዋል።

ከዚህ በኋላ ይህ ገዢ ቡድን የወሰዳቸው አረመኔያዊ እርምጃዎች ሃገሪቱን ቁልቁል ወደ ገደል ነዳት ።ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ እንዲሁም ባህላዊ እሴቶቻችን በሙሉ ተንኮታኩተው የህዝቡም ስነ ልቦና ተሰብሮ ሳይጠገን ቆየ። በዚህ /ገዢዎች በደረሰባቸው ሽንፈት/ ሳቢያ ራሳቸው የደነገጉትን ህገ መንግስት ራሳቸው ጣሱት፥ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት፣ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ በነጻነት የመዘዋወር፣ ዜጎች በመረጡት ስፍራ የመኖር፣ የፈለጉትን የማምለክ የመከተልና እምነቱን በነጻነት የማስፋፋት፣ ዜጎች ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ያለመያዝና መኖሪያ ቤታቸው ያለመፈተሽ፣ ሰርቶ የመኖር፣ የንብረት ባለቤት የመሆን መብቶቻቸው በሙሉ በአንድ ጠ/ሚኒስቴር ትእዛዝ ታገዱ።

በተጨማሪም ያለህግ በአንድ ሰው በሟቹ መለስ ዜናዊ ትእዛዝ ከተከለከሉት መብቶች ውጪ “የጸረ ሽብር ህግ“ በሚል ስያሜ የወጣ በራሱ ሰላማዊውን ዜጋ የሚያሸብር ሕግ በማውጣት ጭል ጭል ባለችው ኩራዝና በአንድ አይን በምትታይ ሜዳ ላይ የተሰበሰቡትንና የሚቃወሙትን ኃይሎች ሰብስቦ እስር ቤት አጉሮአል ። “የነፃ ፕሬስ መተዳደሪያ” በሚል ባወጣው ደንብ ደግሞ ጋዜጠኞች፣ ፀሐፊዎችና የኪነ-ጥበብ ሰዎች እንዲሳቀቁና ራሳቸውን ሳንሱር እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ሕግ በማውጣት ሲገፋም እውነትን የሚፅፉ ጋዜጠኞችን እጁ የደረሰባቸውን ለቅሞ ሲያስር ቀሪዎቹ በግፍ ለመሰደዳቸው ምክንያት ሆኖአል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እነዚህን ግፍና በደሎች ሁሉ በትጋት በመፈፀም ላይ እያሉ የህዝቡን የለውጥ ስሜት ለማቀዝቀዝ የኢትዮጵያን ሚሊኒየም እንደ መልካም አጋጣሚ ያዩት ገዥዎች አድርባይ ካድሬዎቻቸው በሚሊኒየሙ ሚሊዮን ብሮችን ያለአግባብ በማፍሰስ የህዝቡን ቀልብ መግዛት ሽተው ነበር፣ ሆኖም ለአንድ ዓመት ሙሉ በየቦታው ሊከበር የታቀደው ሚሊኒየም ከአንድ ሳምንት ጭፈራና የካድሬዎች አስረሽ ምችው ሳያልፍ የህዝቡ ስሜት ተመልሶ ቦታው ገባ ። እንደሚታወቀው ከዚህ ሚሊኒየም በሁዋላ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዳግም በነሱ(በገዢ ቡድኖቹ) አቅም ሊስተካከል በማይችል መልኩ ተንኮታኮተ፣ የኑሮ ውድነቱ ሕዝቡን አማረረ፣ ስደት በየአቅጣጫው በከፋ መልኩ ተበራከተ፣ የአዛውንት እናትና አባቷን በረሃብና በእርዛት መቆራመድ ዘወትር ማየት ያልቻለች ሴት ለአረብ ግርድና ራሷን አሳልፋ ሰጠች፣ ወንዱም ከረሃብና እንግልት በየመንና ቀይ ባህር ሰጥሞ መሞትን የተመኘበት ዘመን መጣ፣ ታላላቅ የትምህርት ተቅዋማት በገዢው ክፉ የፖለቲካ ቅርሻት ተመረዙ፣ ከዚህ አልፈውም ትምህርታቸውን ጨርሰው የሚወጡትም ዕጣቸው የመንገድ ድንጋይ ንጣፍ ማንጠፍ ሆነ።

ገዢው ቡድን እነዚህን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎችን ሳይፈታ በእምነት ተቅዋማት ውስጥ ገብቶ መፈትፈት ጀመረ ።ቤተክርስቲያንን አይታ የማታውቀው የጨለማ ዘመን ውስጥ ጨመራት፣ ገዳማት ቅዱሳት መካናት መታረስ ጀመሩ፣ አብያተ ክርስቲያናት የካድሬና የፌደራል ፖሊስ መፈንጫ ሆኑ፣ ባህታውያንና መናንያን ተደበደቡ ታሰሩ፣ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን “ድምፃችን ይሰማ “እንዳሉ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ይሄው ዓመት አለፈ ከዚህም አልፎ መሪዎቹን አሸባሪ በማለት ሰብስቦ አሰረ ፣ አንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረና አማርኛ ተናጋሪውን ብቻ ኢላማ ያደረገ የዘር ማጥፋት እንዲሁም የዘር ማጥራት አሰቃቂ ወንጀል ፈፀመ፣ ለአመታት ከኖሩበት አካባቢ ሃገራችሁ እዚህ አይደለም በማለት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና፣ ማንነታዊ ቀውስ አስከተለ፣በኢንቨስትመንት ስም ዜጎች ከቀዬአቸው ተፈናቀሉ።

እነዚህንና ሌሎችንም ያልተጠቀሱ ዘግናኝ ወንጀሎችን የፈፀመው ገዢ ቡድን ግፉን ይሸፍንልኛል በማለት ለዘመናት ስለተዘፈነለት የቅኔ ሰዎች ብዙ ስለተቀኙለት አባይ አሰልቺ ዘፈን ያላዝን ገባ፣ መጀመሪያ ላይ ያነሳናቸው ተግዳሮቶች እንደተጠበቁ ሆነው ከሁሉም በፊት አሁንም በፅናት የምንለው መሰረታዊ የህዝቦች መብቶች ይከበሩ፣ ግፍ ይቁም፣ ዘረኝነት ይወገድ፣ የህሊናና የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ ! በመሆኑም በአባይ ስም በሀገር ውስጥ ካለው ምስኪን ሕዝብ ከወር ደመወዙ የሚለቃቅመውና ከዲያስፖራው የሚሰበስበው ገንዘብ መብቶችን ለማፈን የካድሬዎችን ቁጥር ለመጨመርና የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ለማፈን በቀጥታ ስለሚጠቀምበት በሌላ በኩል ደግሞ ገዢው ቡድን መንግስት ነኝ ብሎ ያለሕዝብ ፈቃድ ራሱን የሰየመው ወያኔ/ኢህአዴግ ላይ ፍፁም እምነት ስለሌለን ከግድቡ በፊት ፍትህ ፍትህ ፍትህ እያልን እንጮሃለን፣ ሕዝባዊና የምናምነው መንግስት እንሻለን ።

በዚህም መሰረት በገዢው ቡድን በጁን 1 በስዊትዘርላንድ ጄኔቫ ከተማ ለማካሄድ የታቀደውን የገንዘብ ዘረፋ ዘመቻ ለመቃወም እንዲሁም ለማክሸፍ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ቀን ቆርጠናል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የወያኔ ተልዕኮ አስፈጻሚ ለሆናችሁ በሙሉ ከህሊና ወቀሳ በላይ የታሪክ ተወቃሸነት እንዳለ አውቃችሁ በዚህ የግፍ ድርጊት እንዳትሳተፉ ለማሳሰብ እንወዳለን። ስለዚህም በፍራቻም ሆነ በጥቅማጥቅሞች ተታላችሁ የዚህ ዝግጅት ተባባሪ የሆናችሁ ባለሃብቶች፣ ባለሬስቶራንቶች፣ አርቲስቶች በስዊትዘርላንድም ሆነ በሌላ ሃገር ያሉ ኢትዮጵያውያን እንዲያውቋችሁና አገልግሎቶቻችሁን እንዳይጠቀሙ የምናጋልጥ መሆኑን፣ እንዲሁም የእምነት ተቋማትና ግለሰቦችን ጨምሮ የነጻነት ትግሉ አካል እንድትሆኑ ጥሪያችንን እያስተላለፍን፣ ከአባይ በፊት የእምነት ነጻነት ይከበር፣ ዜጎችን ከቀዬአቸው ማፈናቀል ይቁም፣ “አባይም የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መደበቂያና የአምባገነኖች እድሜ ማራዘሚያ አይሆንም” !!! እንላለን።

ትንሣኤ ለኢትዮጵያ—ድል ለተጨቆኑት!

ECADF

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: