ሰበር ዜና – የአ/አ አህጉረ ስብከት በአንድ ረዳት ሊቀ ጳጳስና በአራት ሥራ አስኪያጆች ይመራል

205565_434229273308766_1499595463_n
በአህጉረ ስብከቱ መስፈርት ወጥቶለት ጥናት ተደርጎለት የተደረገ ምደባ የለም
የወረዳ ቤተ ክህነት መዋቅር በተሰጠው ሥልጣን ሥራውን አለመሥራቱ ችግሩን አግዝፎታል
የአዲስ አበባ አራት አህጉረ ስብከትን የፓትርያሪኩ ረዳት የሚኾን አንድ ረዳት ሊቀ ጳጳስ በመመደብና ሊቀ ጳጳሱን የሚረዱ አራት ሥራ አስኪያጆች በመሠየም፣ ተጠያቂነትና ሓላፊነት ያለው ግልጽ የኾነ ጠንካራ የአስተዳደር ሥርዐት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አስታወቁ፡፡

ዛሬ ጥዋት የተጀመረውን የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ አስመልክቶ ቅዱስነታቸው በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፣ በጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት በሁለት ሊቃነ ጳጳሳትና በሁለት ሥራ አስኪያጆች እንዲመራ የተደረገበት አደረጃጀት ችግር ፈቺ ኾኖ አልተገኘም፡፡

በቅዱስነታቸው መልእክት እንደተመለከተው ለአደረጃጀቱ ድክመት በምክንያትነት የተጠቀሱት÷ የሥራ አስኪያጅነት ምደባው ጥናት ተደርጎለትና መስፈርት ወጥቶለት በውድድር የተደረገ አለመኾኑ፣ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ድንጋጌ መሠረት የወረዳ ቤተ ክህነት መዋቅሩ ሥልጣን ተከፍሎ ያልተሰጠውና ሥራውን የማይሠራ መኾኑ የሚሉት ናቸው፡፡ በእኒህ ሁለት አስተዳደራዊ ውስንነቶች ሳቢያ ችግሩ እየገዘፈና እየተመሰቃቀለ ለመልካም አስተዳደር ዕጦት መንሥኤ በመኾኑ አደረጃጀቱን መቀየር አስፈላጊ ኾኖ መገኘቱን ቅዱስነታቸው በስብሰባ መክፈቻ መልእክታቸው ገልጸዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን የሚታዩትን የአሠራር ክፍተቶች በፍጥነት ማስተካከል እንደሚገባ ያሳሰቡት ቅዱስነታቸው፣ ‹‹ክፍተቶቹን በፍጥነት ማስተካከል ካልቻልን በቅድሚያ እኛ ላይ የሚፈርደው የገዛ ራሳችን ኅሊና ነው፤ በይቀጥላልም እግዚአብሔርም ሌላውም ይፈርድብናል፤›› በማለት ነባሩና ሰሞናዊው የአህጉረ ስብከቱ የሙስናና የጎጠኝነት ችግሮች የፈጠሩትን ጫናና የሚሹትን አስቸኳይ መፍትሔ አስገንዝበዋል፡፡

ለቅዱስ ሲኖዶሱ ተሰብሳቢ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በይፋ ባቀረቡት ተማኅፅኖም፣ ‹‹እኔ ወንድማችኹንም በዚህች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዳገለግልና እንድላላክ መርጣችኹ በዚህ ትልቅ የሓላፊነት ወንበር ላይ ስታስቀምጡኝ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ፣ የምእመናንን የልብ ትርታ እያዳመጥኹ ለእናንተ ለብፁዓን አባቶች ሳቀርብ ይኹንታንና እገዛውን እየለገሳችኹኝ የጋራ ሓላፊነታችንን እንድንወጣ መኾን አለበት፤›› በማለት የምልአተ ጉባኤውን ድጋፍ በይፋ ጠይቀዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ በሙስናና ብልሹ አሠራር ሀብቱ ያለርኅራኄ ሲመዘበር ለኖረው የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት አስተዳደራዊ ችግር አስቸኳይ መፍትሔ ያሳዩት ዝግጁነት የሚመሰገን፣ ሊደገፍና ሊበረታታም የሚገባው ነው፡፡ ለመፍትሔ ያቀረቡት ሐሳብና የጠየቁት ይኹንታም በአጀንዳ ተይዞ፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን፣ የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌና ወቅታዊውን የችግሩን ስበት ባገናዘበ አኳኋን በምልአተ ጉባኤው ስፋትና ጥልቀት ባለው አኳኋን ውይይት ተደርጎበት እንደሚጸድቅም ተስፋ ይደረጋል፡፡

እግረ መንገድ፡-

በአ/አ አህጉረ ስብከት የሚመደበው ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ፓትርያሪኩ ረዳት የተባለው አዲስ አበባ የፓትርያሪኩ ሀ/ስብከት ስለኾነ ነው ተብሏል፡፡ በጉዳዩ ላይ የሚተቹ አስተያየት ሰጭዎች በሕገ ቤተ ክርስቲያን አዲስ አበባ የሁሉም አህጉረ ስብከት ማእከል በመኾኑ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚሠይመው ዐቢይ ኮሚቴና ዐቢይ ኮሚቴውን በሚመራው ሊቀ ጳጳስ እንደሚመራ ከመገለጹ በቀር ከቀድሞ ጀምሮ ሲወራረድ እንደመጣው ሊቀ ጳጳሱ የፓትርያሪኩ ረዳት ይኾናል አለማለቱ እንዲጤንና እንዲገናዘብ ይሻሉ፡፡

የአራቱ ሥራ አስኪያጆች ምደባ ‹‹በሥራ ችሎታቸው ብቁና ጠንካራ›› መኾናቸው ታይቶ እንደኾነ ተገልጧል፡፡ የአስተያየት ሰጭዎቹ ጥያቄ÷ የሥራ አስኪያጅነት ብቃትና ጥንካሬ በተጨባጭ የሚለካበት የምደባና ቅጥር መስፈርት አለን ወይ? የሚል ነው፡፡

እንደ ቅዱስነታቸው መልእክት፣ በአጭር ጊዜ የተፈለገውን ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡ የለውጡን መሠረት ግን በአስቸኳይ ማስቀመጥና አቅጣጫውን መቀየስ ያስፈልጋል፡፡ እውነት ነው! ትክክል ነው! ጥያቄው ግን የለውጡ መሠረት የሚጣለውና የለውጡ አቅጣጫ የሚቀየሰው ‹‹በአስተዳደር ችሎታው ጠንካራ ረዳት የኾነ ሊቀ ጳጳስ በመመደብ››፣ ‹‹ብቁና ጠንካራ ሥራ አስኪያጅ በመሠየም›› ብቻ ነው ወይ? ከዚህ በላይና ከዚህ በፊት ጠንካራው ሊቀ ጳጳስ፣ ብቁው ሥራ አስኪያጅ የሚሠራበት፣ የቤተ ክርስቲያንን ዘርፈ ብዙ ሀብቶች በሚገባ ለይቶና ዐውቆ የሚያሰማራበት፣ የሚከታተልበትና የሚቆጣጠርበት የሥራ አስተሳሰብ፣ የሥራ መዋቅርና የሥራ ዕቅድስ?

haratewahido

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: