በስዊዘርላድ-ጄኔቭ ኢህአዴግ የጠራው የቦንድ ሽያጭ ስብሰባ “ከ ዓባይ በፊት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይገደብ!” የሚል መፈክር ባነገቡ ኢትዮጵያውያን ብርቱ ተቃውሞ ከሸፈ

esat

ግንቦት ፳፮ (ሀያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ኢህዴግ -በጄኔቭ  ለ ዓባይ ግድብ ቦንድ ሽያጭ ለማካሄድ ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ በምስጢር ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርግ ከቆየ በሁዋላ በቅርቡ ለደጋፊዎቹ ብቻ የዝግጅቱን ዕለት፣ቦታ እና ሰዓት አስመልክቶ ጥሪ ያቀርባል።

ይሁንና ኢህአዴግ  መቼ እና የት ዝግጅቱን ሊያደርግ እንዳሰበ የውስጥ መረጃ የደረሳቸው በጄኔቭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጎን ለጎን የተቃውሞ ዝግጅት ሲያስተባብሩ ይከርማሉ።

ከተቃውሞ ሰልፉ አስተባባሪዎች አንዱ የሆኑት አቶ ጴጥሮስ አሸናፊ እንደገለጹት፤በስፍራው የሚገኙት  የ ኢህአዴግ ካድሬዎች ተቃውሞ እንዳይነሳ በማሰብ ዝግጅቱን ከጄኔቭ ወጣ ብሎ በሚገኝና ለትራንስፖር ፈጽሞ አመች ባልሆነ ጭር ባለ ስፍራ እንዲሆን ቢያደርጉም በ ኢትዮጵያኑ ብርቱ ተቃውሞ ሊሳካላቸው አልቻለም።

እንደ አቶ ጴጥሮስ ገለፃ ከትናንት በስቲያ  ቅዳሜ በ ኢትዮጵያ ሰ ዓት አቆጣጠር ከቀኑ 10 ሰ ዓት ጀምሮ ሊካሄድ የታሰበውን የቦንድ ሽያጭ ለመቃወም ከዙሪክ፣ከበርገን፣ከሎዛን እና ከባዝል-ከተሞች  ከ 200 በላይ ኢትዮጵያውያን  አውቶቡሶችንና ሚኒባሶችን በመከራየትና የግል መኪኖቻቸውን በማሽከርከር በዝግጅቱ ቦታ የተገኙት  አንድ ሰ ዓት በመቅደም ነበር።

የ ኢትዮጵያውያን ማህበር በስዊዘርላንድ፣ ግንቦት 7 ለፍትህ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ፣የ ኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣የቢላል ኢትዮ-ስዊዝ ማህበር፣የዲሞክራሲያዊና የሰብዓዊ መብቶች አስተባባሪ ወጣቶች ግብረ-ሀይልና የስዊዘርላን ድምፃችን ይሰማ ኮሜቴ በጋራ በመሆን ባስተባበሩት በዚህ ሰልፍ ፦”ከዓባይ በፊት ዘረኝነት ይገደብ! በግፍ የታሰሩ ጋዜጠኞች፣የህዝበ-ሙስሉሙ መሪዎችና የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ!” የሚሉት መፈክሮች መስተጋባት የጀመሩት ገና የ ኢህአዴግ ዝግጅት ሳይጀመር ነው።

ተቃውሞው እያየለ በመምጣቱ የ ኢህአዴግ ደጋፊዎች እንደተጠበቀው ወደ አዳራሹ ሊመጡ አለመቻላቸውን የገለጹት አቶ ጴጥሮስ እስከ ምሽቱ አራት ሰ ዓት ድረስ  ራሳቸውን ተሸፋፍነውና አቀርቅረው ወደ አዳራሹ የገቡት ሰዎች ከ 30 እንደማይበልጡ ተናግረዋል።

በተቃውሞው ማየል ፕሮግራሙ ይጀመራል በተባለበት ሰ ዓት ካለመጀመሩም ባሻገር የዝግጅቱ እንግዳ የነበሩት በስዊዝ የ ኢትዮጵያ አምባሳደር እና ሌሎች የ ኢህአዴግ ባለስልጣናት ወደ ስፍራው ዝር ሳይሉ ቀርተዋል።

በስፍራው የሚገኘው የ ኢሳት ወኪል እንዳጠናቀረው ሪፖርትም፤በሰልፈኞቹ ጩኸት የተደናገጡት ጥቂት ተሰብሳቢዎች ወደፖሊስ በመደወል ተጨማሪ ሀይል እንዲመጣላቸው ባቀረቡት ተማጽኖ መሰረት የፖሊስ ሀይል ቢመጣም፣ ዝናቡ ጉሉበቱን ጨምሮ ቢወርድም፣ ኢትዮጵያውያኑ ያለ አንዳች መነቃነቅ በከፍተኛ ወኔ እና አገራዊ ስሜት ተቃውሟቸውን ቀጥለዋል።

የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ከዚህም ባሻገር በዝግጅቱ አዳራሽ ተሰቅሎ የነበረውን ባለ ኮከብ ባንዲራ በማውረድና ፦”ኢትዮጵያውያንን የሚወክለው ባንዲራ ይሄ ነው”በማለት ትክክለኛውን የ ኢትዮጵያ ባንዲራ ሰቅለዋል።

ሰልፈኞቹ በዚህም ሳይወሰኑ   በአዳራሹ ውስጥ የጋዜጠኞችን፣የፖለቲካ እስረኞችንና የታሰሩትን የሙስሊም አመራሮች ፎቶግራፎች ለጥፈዋል።

“በኦሮሞ ነፃነት ግንባር መካከል መለስተኛ ልዩነት የተፈጠረ ቢሆንም፣ በዚህ ሰልፍ ላይ ግን ከሁለቱም ወገኖች ያሉት የግንባሩ አባላት ተገኝተው ከሁላችንም ጋር በአንድ ላይ ድምፃቸውን ማሰማታቸው በጣም ደስ የሚያሰኝና ልዩ ስሜትን የፈጠረብን ክስተት ነበር”ብለዋል-አቶ ጴጥሮስ።

ዕለቱ የሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ የሚካሄድበት ዋዜማ መሆኑም ለሰልፈኞቹ ትልቅ ደስታን የሰጠና ተስፋን የፈነጠቀ ነበርም ብለዋል-አስባባሪው።

በ ኢትዮጵያውያኑ ብርቱ ተቃውሞ ገንዘብ የመሰብሰብ እቅዳቸው የከሸፈባቸው የ ኢህአዴግ ካድሬዎች በስተመጨረሻም ያዘጋጁትን ምግብ ሳይቀር የውጪ ዜጎችን በመጥራት በነፃ እስከመጋበዝ ደርሰዋል።

“የ አባይ መገደብ የሁላችንም ደስታ ነው፤ ዓባይ እንዲገደብ እንሻለን። ሰውን ያለ አግባብ እየገደሉና እያሰሩ በሰው ደም ላይ የሚደረግን ልማት ግን እንቃወማለን!ዓባይም ከልማት አልፎ ለፖለቲካ ንግድ መዋሉን ም ፈጽሞ አንቀበለውም! ቅድሚያ ፍትህ፤ነፃነት፣ዲሞክራሲ በአገራችን ይንገስ! ያኔ ዓባይን በጋራ ክንድ እንገነባዋለን!”ብለዋል-አስተባባሪው ስለተቃውሞ ሰልፉ ዓላማ ሲያብራሩ።

Advertisements

One thought on “በስዊዘርላድ-ጄኔቭ ኢህአዴግ የጠራው የቦንድ ሽያጭ ስብሰባ “ከ ዓባይ በፊት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይገደብ!” የሚል መፈክር ባነገቡ ኢትዮጵያውያን ብርቱ ተቃውሞ ከሸፈ

 1. dagmawitewodros June 5, 2013 at 10:23 pm Reply

  የዜና እርማት

  ግንቦት ፳፰ (ሀያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

  ኢሳት ዜና:-ተመልካቾቻችን እና አድማጮቻችን፣
  ከትናንት በስቲያ ሰኞ ዕለት በስዊዘርላንድ-ጄኔቫ ስለተካሄደው የአባይ ቦንድ ሽያጭ ባስተላለፍነው ዜና ላይ፤ ተቃውሞ ባሰሙት ኢትዮጵያውያን ሳቢያ ዝግጅቱ እንደከሸፈ መዘገባችን ይታወሳል። ይሁንና ዜናው ስህተት እንዳለበት የደረሰንን ጥቆማ መሰረት በማድረግ ባደረግነው ማጣራት መሰረት የኢትዮጵያውያኑ ተቃውሞ እስከ ምሽቱ 6፡00፣ ዝግጅቱ ደግሞ ከሌሊቱ 6፡00 ጀምሮ እንደተካሄደ ተገንዝበናል። በመሆኑም በስዊዘርላንድ-ጄኔቭ የተካሄደውን የዓባይ ቦንድ ሽያጭ አስመልክቶ ባስተላለፍነው ዘገባ ለተፈጠረው ስህተት አድማጮቻችንን እና ተመልካቾቻችንን ከፍ ያለ ይቅርታ እንጠይቃለን!

  Like

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: