ሁለት የአረና ለትግራይ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ከፓርቲው ለቀቁ

asreat-abrham

አቶ ግዑሽና አቶ አስራት

ለረዥም ጊዜ መድረክ ወደ ውህደት እንዲመጣ ሲለፉና ሲታገሉ የነበሩት ሁለት ለአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉአላዊነት ሥራ አስፈጻሚ አባላት ከፓርቲው ራሳቸውን ማግለላቸውን ለድርጅቱ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ አስታወቁ። አስራት አብርሃም የተባሉ የዓረና የስራ አስፈፃሚ አባልና የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ እንዲሁም፤ ጉዕሽ ገብረፃዲቅ የዓረና የስራ አስፈፃሚ አባልና የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ የሆኑት እነዚህ ሁለት የድርጅቱ አመራር አባላት ከድርጅቱ ለመልቀቅ ለምን እንደወሰኑ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ላይ “እኛ ፓርቲውን ለመመስረት ከታሰበበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች እስካሁን እየሰራን መቆየታችን የሚታወቅ ነው። ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመድረክ ውስጥ እየተከሰተ ባለው ፖለቲካዊ ድባብና በሌሎች ከዚህ ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ፓርቲው ሁኔታውን ገምግሞ፣ “መድረክ ከዚህ በኋላ ወደ ምንፈልገው ግብ ያደርሰናል ወይስ አያደርሰንም? በእኛ በእኩል መድረክ ወደ እሚፈለገው ግብ እንዲደርስ ምን ዓይነት እስትራቴጂና የትግል ስልት እንከተል?” የሚሉ ጉዳዮች በጥልቀት ለማየትና የእስትራቴጂ ማስተካኪያ ለማድረግ ያለው ፍላጎት ዝቅተኛ መሆኑን በመገንዘብ፤ ከዚህም በተጨማሪ በዓረና ውስጥ እየተስተዋሉ ባሉት እንግዳ ሁኔታዎች ምክንያት ፓርቲው እንዲከፋፈልና እንዲዳከም የሚያደርጉ መሆናቸውን በመገንዘብ፤ ይህን ሁኔታ ለማረም ደግሞ በሌሎች የስራ አስፈፃሚ አባላት ዘንድ ዳተኝነት መኖሩ ግልፅ እየሆነ በመምጣቱ፤ የዚህ አካል ላለመሆንና ፓርቲውን ደግሞ የበለጠ እንዳይከፋፈል በማሰብ፣ ይህ ደብዳቤ ከተፃፈበት ዕለት ጀምሮ ፓርቲውን ለመልቀቅ የወሰንን መሆናችንን በአክብሮት ለማሳወቅ እንወዳለን።” ብለዋል።
“ለዓረና/መድረክ አባላትና ደጋፊዎች በሙሉ ስላሳለፍነው ጥሩ የአብሮነት ጊዜ ማመስገን እንፈልጋለን። ብዙ የትግል ልምድ ካለው አመራር ጋር አብሮ መስራት በራሱ እንደ አንድ ትልቅ እድል ነው ምናየው። ለዓላማ የመኖር ፅናት፣ ትዕግስትና ፖለቲካዊ ተሞክሮ አግኝተንበታል። ከዚህ በተጨማሪም ስለአገራችን ፖለቲካ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለመረዳት እድል ፈጥሮልናል። በእዚያ ባሳለፍነው አስቸጋሪ የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ ስብዕናህን የሚፈታተኑ፣ ትግል የምታደርግበትን ምክንያት እስኪጠፋህ ድረስ የሚያደርሱና ፀጉር የሚያቆሙ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች የነበሩበት ቢሆንም፤ የዚያው ያህል ደግሞ ብዙ የተማርንበት፣ አቅምና ክህሎት ያገኘንበት፣ ከአገር ውስጥም ከውጭም ብዙ ለአገርና ለወገን ተቆርቋሪ የሆኑ ዜጎች ለመተዋወቅ ዕድል የፈጠረልን በመሆኑ ሁላችሁም እናመሰግናለን።” ያሉት አቶ አስራት አብርሃም እና ጉ ዕሽ ገብረጻዲቅ “ከሁሉም በላይ ደግሞ ዓረና የፖለቲካ ጥርሳችን የነቀልንበት፣ ስለሀገር፣ ስለሰው ልጅ፣ ስለስልጣን ምንነት፣ ስለሁሉም ነገር በጥልቀት እንድናውቅ ዕድል የሰጠን ፓርቲ በመሆኑ በህይወታችን ሁሉ ስናስታውሰው የሚኖር ነው። ባለፉት ስድስት ዓመታት የተማርነው ነገር ብዙ ነው፤ አገራችን የብዙ ችግሮች ባለቤት መሆኗም ተገንዝበናል። ይህ ሁሉ ችግር ለማቃለልም አሁንም ቢሆን እልህ አስጨራሽ ትግል ማድረግ ግድ የሚል መሆኑን እንረዳለን፤ ከዚሁ ትግል ደግሞ እኛ ወደኋላ እንል ዘንድ ስብዕናችንና ተፈጥሯዊ ባህርያችን የሚፈቅድልን አይደለም።” ብለዋል።
“ዛሬ ከፓርቲው በዚህ ሁኔታ ብንለይም ፓርቲው እስከ አሁን ይዞት የመጣውን ለመርህ የመገዛት፣ በጋራ አመራር የማመንና ተግባብቶ የመስራት ባህሉ መቀጠልና መጠናከር አለበት እንላለን። ውስንነት ቢኖረውም ውስጣዊ ልዩነቶችን አቻችሎ የሚጓዝበት፣ ችግሮች ሲከሰቱ ደግሞ በሰከነ ሁኔታ የሚፈታበት መንገድ ለሌሎችም ትምህርት ሊሆን የሚችል ነው። ይህ ልምድም መጠበቅ አለበት። በአንፃሩ ደግሞ ጎጂ የሆኑ ዝንባሌዎች ማለትም ወግ አጥባቂነትን፣ ቡድናዊነትን፣ ግላዊ ጥቅመኝነትንና ስልጣን ወዳድነትን ሥር እንዳይሰዱ ነቅቶ መጠበቅና መታገል የሚገባ ነገር ነው።” ሲሉ በደብዳቤያቸው ላይ ያተቱት የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚዎች “በተለይ ደግሞ መድረክ አሁን ካለበት የተሻለ አደረጃጀትና አሰራር እንዲኖረው፣ በአባል ፓርቲዎች መሀከል ያሉትን ጥቃቅን ልዩነቶች በማቀራረብና በማመቻመች የተሻለ መተማመንና አብሮ መስራት የሚቻልበት ብሎም ወደ ውህደት የሚመጣበትን መንገድ እንዲፈጠር ጠንክሮ መስራቱ ለሁሉም የሚበጅ ነው የሚሆነው። ዓረና በዚህም በእኩል ከሸምጋይነት ሚናው ወጥቶ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ የሚጠበቅበት ነው። ጠብ እና አለመተማመን በመርህ፣ ብሎም ተቀራርቦ በመስራት ይፈታሉ እንጂ የመርህ ችግር በሽምግልና የሚፈታ አይደለም።” ሲሉ አስረድተዋል።
“መድረክ የአመራር ዳይናሚዝም ለመፍጠር የሚያስችል አሰራር መከተል፣ ብቃት ያላቸው አዳዲስ አመራሮች ማብቃና ወደፊት ማምጣት ይጠበቅበታል። ነባርና ልምድ ያለው አመራር መኖር ለአንድ ፓርቲ እጅግ ጠቃሚ ቢሆንም የተለየ እንቅስቃሴ ማድረግ ግድ ለሚለው የሀገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚመጥን ፖለቲካዊ አመራር መስጠት ባልተቻለበት ሰዓት ግን “የማርያም መንገድ አለኝ” ለሚል አዲስ አመራር ዕድል መስጠት ተገቢ ይሆናል። ደግሞም አመራርነት በብቃትና በአባላቱ ዘንድ በሚኖረው ቅቡልነት ላይ የተመሰረተ መሆን ይገባዋል እንላለን።” በሚል የተነተኑት እነዚህ ሁለት አመራር አባላት “ውድ የዓረና/መድረክ አባላትና ደጋፊዎች፣ እኛ ዜጋ በዜግነቱ የሚከበርባት፣ ፍትሃዊትና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እስክትፈጠር ድረስ ፖለቲካዊ ትግሉን የምናቆም አይደለንም። ከዚህ በኋላም ቢሆን በሀሳብና በተግባር በአጠቃላዩ የሀገራችን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ መኖራችን የሚቀጥል ነው የሚሆነው። እኛ የትግራይ ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ተስማምቶና ተግባብቶ ለመኖር ያለውን መልካም ፍላጎት ከማንፀባረቅና ከማሳየት ውጪ ሌላ ዓላማ የለንም። ከአሁን በኋላም ቢሆን ይህን ጉዳይ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ከመግለፅና ከማሳየት ወደኋላ የምንል አይደለንም። ከሁሉም በላይ ደግሞ በአገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትህ፣ ፖለቲካዊ እኩልነትና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ማንነቱ፣ መብቱና ክብሩ እኩል ተጠብቆለት፣ በአገሪቱ ውስጥ እንደ ዜጋ በሙሉ ነፃነት የመንቀሳቀስ እና ሰርቶ የመኖር መብቱ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ እንዲከበር በምንችለው አቅም ሁሉ ከመታገል ወደኋላ አንልም።” ሲሉ የወደፊቱን የትግል አቅጣጫቸውን አስምረውበታል።
“በአንድ መንገድ ይሁን በሌላ፣ ለሁላችንም የምትስማማ፣ የተሻለች አገር ለመፍጠር መታገላችን እስከቀጠልን ድረስ ተለያየን አንልም። የእኛ እና የሌሎች በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚደረጉ ትግሎች ተደማምሮ ነው ውጤት ሊመጣ የሚችለው።” የሚሉት አቶ አስራት እና አቶ ጉዕሽ “እንግዲህ በዚሁ ስንሰናበት ሀዘናችን በጣም ጥልቅ ነው። ስትለያይ ሀዘን መኖሩ፣ ቅር ማለቱ ያለና የማይቀር ነገር ቢሆንም ሀዘናችን እጅግ በጣም ጥልቅ እንዲሆን የሚያደርገው በዚህ ሁኔታ መለያየታችን ነው። ብፆት ሰላም ኹኑ! ድል ለዴሞክራሲያውያን ታጋዮች! ድል አዲሱ ኢትዮጵያዊ ትውልድ!” በማለት ለድርጅታቸው የጻፉትን ግልጽ ደብዳቤ ቋጭተዋል።
ይህ በ እንዲህ እንዳለ አቶ አስራት አብርሃም እና ጉዕሽ ገብረፃዲቅ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን ይቀላቀላሉ ተብሎ በሰፊው እየተወራ ነው።
ዘ-ሐበሻ

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: