ዓባይና የአሜሪካ ጨዋታ

576561_4702713808339_449625552_n

መስፍን ወልደ ማርያም

ሰኔ 2005

በአሥራ ዘጠነኛው ምዕተ-ዓመት አስተሳሰብ ከዚህ ቀጥሎ የተጠቀሰው ዓላማ ለአውሮፓ ቄሣራውያን ዋና ግባቸው ሆኖ እስከሃያኛው ምዕተ-ዓመት ዘልቆአል፤ አሀን ፈጽሞ በተለየ ዘመን አሜሪካ ይህንን አስተሳሰብ ይዞ የተነሣ ይመስላል።

ኢትዮጵያን የተቆጣጠረ ዓባይን ይቆጣጠራል፤ ዓባይን የተቆጣጠረ ግብጽን ይቆጣጠራል፤ ግብጽን የተቆጣጠረ ኃይል ቀይ ባሕርን ከመግቢያና መውጫው ጋር ይቆጣጠራል፤ ቀይ ባሕርን ከመግቢያና መውጫው ጋር የተቆጣጠረ ኃይል ዓለምን ይቆጣጠራል።

አሜሪካ በግብጽ ላይ የተከለው ጥፍሩ ሲነቃነቅ መነቀሉ አለመቅረቱን ስላወቀው ሌላ የሚተክልበት አገር ይፈልጋል፤ በአካባቢው የግብጽን ነፍስ የሚነካ ከኢትዮጵያ የተሻለ አገር የለም፤ ለአሜሪካ ዓለም-አቀፍ ዓላማ ኢትዮጵያ ስትመረጥ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም፤ በመሀከለኛው ምሥራቅ የአረቦችን የተባበረ ኃይል ለመቋቋም የተመረጡ ሦስት አረብ ያልሆኑ አገሮች — ቱርክ፣ ኢትዮጵያና ፋርስ (ኢራን) — ነበሩ፤ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የአሜሪካ ዓለም-አቀፍ ኃይል መሰማት በጀመረበት ጊዜ ኢትዮጵያን ከከበቡአት የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ጋር የነበርዋትን የቆዩ ውዝግቦች ለመቋቋም የአሜሪካ ድጋፍ በጣም አስፈላጊ ነበር፤ አሜሪካን ከአውሮፓ አገሮች ጋር እየመዘኑና እያመዛዘኑ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር የተደረገው ዲፕሎማሲ (ዓለም-አቀፍ የሰላም ትግል) የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት በእውነት ከሚያኮሩት ተግባሮች አንዱ ነው፤ ይህንን ትግል አምባሳደር ዘውዴ ረታ ምስጋና ይድረሰውና የኤርትራ ጉዳይ በሚለው መጽሐፉ ግሩም አድርጎ አሳይቶናል።

ምናልባት ገና ያልተጠና ጉዳይ በዘመኑ ኢትዮጵያ የነበራት ታሪካዊ ክብር ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ታሪክና ዝና ጋር ተዳምሮ በአፍሪካ ተደማጭነት ነበራት፤ ይህንን ኢትዮጵያ በአፍሪካ አገሮች ላይ የነበራትን ጫና (የዛሬውን አያርገውና) በመጠቀም አሜሪካ አፍሪካን በሙሉ ለዓላማዋ ለማሰለፍ ኢትዮጵያን መሣሪያዋ ለማድረግ ትሞክር ነበር።

እየቆየ የኢትዮጵያ መንግሥት የነጻነት መንፈስን በማሳየት ለአሽከርነት አልመች በማለቱና ለአሜሪካም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች (የእውቀት ጥበቦች) በመፈጠራቸው ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ዓለም-አቀፍ ዓላማ አስፈላጊነትዋ በመቀነሱ አሜሪካ ኢትዮጵያን ችላ ማለት ጀመረ፤ የ1966 ግርግር ከዚህ ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑን ጠለቅ ብሎ ማጥናት ያስፈልጋል፤ በዚህ መሀልም የሶቭየት ኅብረት ዓለም-አቀፋዊ ጉልበት እየተሰማ በመሄዱ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የነበረውን ዓላማ ቀስ በቀስ እየለወጠ ሄደ፤ ከዚህም ጋር የሶቭየት ኅብረት ተጽእኖ እያደገ ሄደ፤ የአሜሪካ አያያዝ እየላላ ሲሄድ የሶቭየት ኅብረት አያያዝ እየጠበቀ ሄደ፤ 1966 የአሜሪካ መውጫና የሶቭየት መግቢያ ሆነ ለማለት ይቻል ይሆናል፤ ከዚሁ ጋር አብሮ የሚታየው በኢትዮጵያ የባህላዊው ሥርዓት መሰነጣጠቅና የቆየው ትውልድ መዳከም ነው፤ የአሜሪካ መዳከም ሶቭየት ኅብረትን ሲያጠነክር፣ የአሮጌው ትውልድ መዳከም አዲሱን ትውልድ አጠነከረ፤ ይህ ማለት አሮጌው ትውልድ ከአሜሪካ ጋር የተያያዘውን ያህል አዲሱ ትውልድ ከሶቭየት ኅብረት ጋር ተያያዘ፤ የኢትዮጵያ የውስጥ ሁኔታ ብቻውን ለውጥ እንዳላመጣና ዓለም-አቀፍ ሁኔታዎችና የልዕለ ኃያላኑ ተጽእኖም ምን ያህል እንደነበረ አመላካች ነው።

የአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት መውደቅና የአሜሪካ ተጽእኖ መዳከም በአንድ በኩል፣ የደርግ መፈጠርና የእነኢሕአፓና መኢሶን በአጋፋሪነት መውጣት ከሶቭየት ኅብረት ተጽእኖ መጠናከር ጋር በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ሁኔታን ፈጠሩ፤ የአዲሱን ሁኔታ አዲስነት በግልጽና በትክክል መገንዘብ ያስፈልጋል፤ በኢትዮጵያ ለብዙ ሺህ ዓመታት ተከብሮና ታፍሮ የቆየው የዘውድ ሥርዓት ተናደ፤ ተዋረደ፤ በኢትዮጵያ ስር እየሰደዱ የነበሩ መሳፍንትና መኳንንት ከስራቸው ተመነገሉ፤ አዲስ የመሬት አዋጅ ወጣና የመሬት ከበርቴዎችን ሙልጭ አውጥቶ ገበሬውን በሙሉ እኩል ባለመሬት አደረገው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻ ወጣ ባይባልም የኢትዮጵያ መሬት ነጻ ወጣ፤ ወታደር፣ ገዢ ሰላማዊው ሕዝብ ተገዢ ሆነ፤ ትርፍ መሬትና ትርፍ ቤት ሁሉ ተወረሰ፤ ቤትን የሚያከራዩ የኪራይ ቤቶችና ቀበሌዎች ብቻ ሆኑ፤ ደሀዎችንና መሀከለኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች ኑሮ ለማቃለል ከሦስት መቶ ብር በታች የነበረው የቤት ኪራይ ሁሉ ተቀነሰ፤ ደርግ በሁለት ዓመታት ውስጥ የአብዛኛውን ገበሬ ኑሮና የአብዛኛውን የከተማ ነዋሪ ኑሮ የሚነኩ መሠረታዊ ለውጦችን አወጀ፤ እያደር ደርግ አስከፊ እየሆነና እየተጠላ ቢሄድም እነዚህ ሁለት አዋጆች ብዙ ኢትዮጵያውያንን እስከዛሬ ድረስ ለደርግ ባለውለታ አድርገዋል፤ እነዚህ አዋጆች ወያኔ ገና አፍርሶ ያልጨረሳቸው የደርግ ሐውልቶች ናቸው።

በውጭ አመራር ደግሞ የአሜሪካ ተጽእኖ ክፉኛ ተበጠሰ፤ አሜሪካ ማለት ስድብና ውርደት ሆነ፤ አሜሪካ ማለት በዝባዥነትና የቄሣራዊ ተልእኮ አራማጅ ማለት ሆነ፤ የአሜሪካ ማስታወቂያ ቢሮ ተዘጋ፤ ብዙ የአሜሪካ እንደወባ መከላከያ ያሉ የተራድኦ ድርጅቶች ተዘጉ፤ አሜሪካ ለዩኒቨርሲቲዎች ሲያደርግ የነበረውን እርዳታ አቋረጠ፤ በዚህ በተለይም የዓለማያ ዩኒቨርሲቲ በጣም ተጎዳ፤ የወባ ቢምቢም ከ‹‹ኢምፒሪያሊዝም›› ጭቆና ነጻ ወጣችና አዲስ አበባ ደረሰች! ይባስ ብሎም አለማያ ዩኒቨርሲቲ ያፈራቸው አሉ የተባሉት በተለያዩ የእርሻ ሙያዎች የተካኑት አብዛኞች ሙልጭ ብለው ከአገር ወጡ።

አሜሪካ ከደርግ ጋር እየተጋገዘ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ክፉኛ አዳከመው፤ አያይዞም በኢትዮጵያ ዳር ዳር የሚነደውን እሳት አቀጣጠለው፤ በአንድ በኩል የውስጥ ተገንጣይ ቡድኖችን — የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት፣ የኤርትራ ነጻ አውጪ ድርጅት፤ የኦሮሞ ነጻ አውጪ ድርጅት — በሌላ በኩል በድንበርም ሆነ በሌላ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር የሚፋለሙትን አገሮች ሶማልያንና ሱዳንን በግልጽ መርዳት ጀመረ፤ እንዲያውም ከግብጹ ፕሬዚደንት ሳዳት ጋር እየተመካከረ ኢትዮጵያን ለማዳከም ሞከረ፤ ከመሞከርም አልፎ ኤርትራን አስገነጠለ፤ የኢትዮጵያን ዙፋን ለወያኔ አመቻቸ፤ አሜሪካ ኮሚዩኒስት ነኝ የሚለውን ወያኔን በጎሣ ፖሊቲካ አስታጥቆ ቀለቡን እየሰፈረ በኢትዮጵያ ላይ ሠራው፤ ደርግ በሰይፍ ብቻ አንድነትን ለማምጣት መሞከሩና ሕዝቡን ለጦርነት ማነሣሣቱ አሜሪካንን አስደንግጦታል፤ ለአሜሪካ ደርግ የቀሰቀሰው የአንድነት ብሔራዊ ስሜት የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ የሚፈስስ መስሎ ታየው፤ በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያን የአንድነት ብሔራዊ ስሜት የማፈራረስ እቅዱን አወጣ፤ የሚያሳካለትንም ቡድን አገኘ።

 

ጣህሪር አደባባይና ዓባይ

ስንት ሰዎች በካይሮ ያለው አደባባይ ከዓባይ ጋር ግንኙነት አለው ብለው ያምናሉ? እስቲ ጠጋ ብለን እንመርምረው፤ ጣህሪር አደባባይ የግብጽ ሕዝብ የነጻነት ጥሪ ነበር፤ በአሜሪካ አጋዥነት ተጭኖት የነበረውን አገዛዝ ለማውረድ ቆርጦ መነሣቱን የገለጸበት አደባባይ ነው፤ የጣህሪር አደባባይን ማእከል ባደረገ ቆራጥ ትግል አገዛዙን አንኮታኩቶ አወረደው፤ በሰላማዊና ሕጋዊ ምርጫ የግብጽ ሕዝብ አዲስ መንግሥትን መሠረተ፤ የእስልምና ወንድማማቾች የሚባለው ቡድን አሸናፊ ሆኖ መውጣቱን አሜሪካም ሆነ እሥራኤል በጸጋ የተቀበሉት አይመስልም፤ ስጋት አላቸው፤ ለግብጻውያን ከአገዛዙ ጋር የሚወርድ ሌላ ጭነት አለባቸው፤ አሜሪካ ለራስዋም ዓላማ ሆነ ለእሥራኤል ዓላማ በግብጽ ላይ የምታደርገውን ከባድ ጫና ማንሣት ከትግሉ ዓላማዎች አንዱ ነበር፤ አሜሪካንና እሥራኤልን ያሰጋው የለውጡ ዓላማ አገዛዙን መጣሉ ሳይሆን በእነሱ ጥቅም ላይ ያነጣጠረውን ክፍል ነበር፤ በጦር መሣሪያ በኩል ግብጽ የአሜሪካ ጥገኛ ነች፤ ቀደም ሲል የሶቭየት ኅብረት ጥገኛ ነበረች፤ በአሁን በአለው የጊዜው ትርምስ አሜሪካ ግብጽ አንዳታመልጠው ይፈልጋል፤ ስለዚህም ስጋት አለው።

ግብጽን ሰንጎ ለመያዝና ለማስጨነቅ ከዓባይ የበለጠ ኃይል የለም፤ ዓባይን ሰንጎ ግብጽን ለማስጨነቅ ከኢትዮጵያ የበለጠ ምቹ አገር የለም፤ በተጨማሪም ኡጋንዳን፣ ኬንያንና ደቡብ ሱዳንን ከአሰለፈ ለአሜሪካ ሁኔታው ይበልጥ ይመቻቻል፤ ጫናው በግብጽ ላይ የጠነከረ ሊመስል ይችላል፤ አሜሪካ የግብጽን ወዳጅነት ለዘለቄታው ለማጣት ይፈልጋል? ለእኔ አይመስለኝም፤ አሜሪካ የአረቦችን ሁሉ ጠላትነት ይፈልጋል? ለእኔ አይመስለኝም፤ ታዲያ እስከምን ድረስ ነው አሜሪካ ግብጽን ለማስጨነቅ የሚፈልገው? ዋናው ጥያቄ ይህ ነው።

ትልቁ የአስዋን ግድብ ሲሠራ የነበረውን ውዝግብና መካካድ ለማንሣት ይዳዳኛል፤ ግን ሰፊ በመሆኑ አልገባበትም፤ አንዳንድ ሁነቶችን ብቻ ልጥቀስ፡– የምዕራብ ኃይሎች በተለይም አሜሪካና ብሪታንያ ለግድቡ ሥራ አስተዋጽኦ ለማድረግ ቃላቸውን ከሰጡ በኋላ ሀሳባቸውን ለወጡ፤ የሶቭየት ኅብረት አንድ ቢልዮን ተሩብ ያህል ዶላር ለማበደር ዝግጁ ሆነ፤ ግብጽም ብድሩን ለመክፈል እንድትችል በዓለም-አቀፍ ኩባንያ ይተዳደር የነበረውን የስዌዝ ቦይ ብሔራዊ ሀብትዋ አድርጋ አወጀች፤ ይህንን በመቃወም ብሪታንያ፣ ፈረንሳይና እሥራኤል ግብጽን ወረሩ፤ በተባበሩት መንግሥታት ግፊት (አሜሪካና የሶቭየት ኅብረት በተባበሩት መንግሥታት መድረክ ላይ በአንድ ላይ የቆሙበት ብርቅ ሁኔታ ነበር፤) ወረራቸውን አቁመው ከግብጽ ወጡ፤ በኋላ ነገሩ ሁሉ ተገለባብጦ ግብጽ ሶቭየት ኅብረትን ትታ የአሜሪካ ወዳጅ ሆነች!

አሜሪካ የሶርያን ሳይጨርስ፣ የኢራንን ሳይጀምር ከግብጽ ጋር ውዝግብ ቢጀምር ምን ጥቅም ያገኛል? ደግሞስ በዓባይ ጉዳይ በኢትዮጵያና በግብጽ ውዝግብ የሚያሸንፈው አሜሪካ መሆኑ ያጠራጥራል ወይ? አሜሪካ ሲያሸንፍ ግን ከኢትዮጵያና ከግብጽ አንዳቸው ይወድቃሉ፤ ወይም ይቆስላሉ፤ ሁለቱንም እኩል አያቅፋቸውም፤ ደርግ አሜሪካንን በማስቀየሙ በአለፉት ሃያ ዓመታት በኢትዮጵያ መሬትና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያስከተለው መዘዝ እያሰቃየን መሆኑን ልንረሳው አይገባንም።

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያና በግብጽ መሀከል ያለው ጉዳይ አህያ ላህያ ቢራገጥ ዓይነት አይመስለኝም።

መስፍን ወልደ ማርያም

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: