ከ“ሙስና”ው ክስ በስተጀርባ

394711_184013551696255_1365830121_n

(ተመስገን ደሳለኝ)

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለትንተና አዳጋች መሆኑን የሚናገሩ ምሁራን መከራከሪያቸው ፖለቲከኞቹ ከርዕዮተ-ዓለም ይልቅ ‹‹ሴራ››ን ማስቀደማቸውን በመጥቀስ ነው፡፡ በርግጥም አብዛኛው የፓርቲዎቹ የአመራር አባላት ከክህሎት እና ርዕዮተ-ዓለም መራቀቅ ይልቅ በዘልማዱ ፖሊቲካ የተካኑ ናቸው፡፡ በተለይም የ1966ቱ ‹‹አብዮት›› ያሰረፀው የ‹‹ፓርቲ ፖለቲካ›› የተደራ  ‹‹ሴራ›› ምን ያህል ኩነትንም ታሪክንም መቀየር እንደሚችል አሳይቷል፡፡
የሁሉንም ፓርቲ የአመራር አባላት አመዳደብ መስፈርት ከምር ከፈተሽነው ከፊት መስመር ከምናገኛቸው አብዛኞቹ በዚህ አይነቱ የጨዋታ ህግ የተሻሉ ሆነው ስለተገኙ መሆኑን ለመረዳት አያዳግትም (ሻዕቢያ፣ ኦነግ፣ ደርግ፣ ኢህአፓ-እነጌታቸው ማሩንና ብርሃነመስቀል ረዳን፣ ህወሓት-እነስሁል፣ እነአረጋዊ፣ እነስዬ፣ ብአዴን-እነያሬድ ጥበቡንና ሙሉዓለም አበበን፣ ኢህአዴግ፣ መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ ቅንጅት፣ አንድነት… የመርህና የህግ ተገዥ የሆኑ አመራሮቻቸውን ደግመው ደጋግመው በሴራ ፖለቲካ በጓሮ በር ሸኝተዋል) የዚህ ፅሁፍ ዓላማ አውራው ኢህአዴግ፣ በተለይም ከድህረ ትጥቅ ትግሉ ወዲህ ባለተፃፈ ህጉ በመሪዎቹ ላይ የፈፀማቸውን የሴራ ፖለቲካ ለመቃኘት መሞከር ነው፡፡ እንደ ሚታወቀው ስርዓቱ ወደስልጣን ከመጣ በኋላ ተአማኒነትን ያላገኙ ግዙፍ የፖለቲካ እርምጃዎችን በጉምቱ መሪዎቹ ላይ በተደጋጋሚ ሲወስድ አይተናል (በተጠመደ ፈንጅ ህይወቱ ያለፈውን የብአዴን መሪ ሙሉዓለም አበበንና የጄኔራል  የሎም ግድያን ሳንጨምር)
ታምራት ላይኔ
ኢህአዴግ እንደመንግስት ከተሰየመ በኋላ ‹‹በህገወጥ ብልፅግና›› ስም የመ መሪያው ትልቁ ሰለባ ያደረገው ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ታምራት ላይኔን ነበር፡፡ በወቅቱ የታምራት መከሰስ ታምራት በትግሉም ሆነ በመንግስትነት ዘመኑ ከነበረው ከፍተኛ ኃላፊነት አኳያ እና በአንደበቱ ‹‹ተመክሬ፣ ተዘክሬ አልሰማ ብያለሁ›› ከማለቱ አንፃር ግንባሩ ሙስናን ለመዋጋት ቁርጠኝነት ያለው አስመስሎት ነበር፡፡ ነገር ግን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ዘርፏል ከተባለው በእጅጉ የሚልቅ መጠን ያለው የ ገር  ብት ‹‹ሌባ›› ብለው ያሰሩት ጓደኞቹ ሲዘርፉ መመልከታችን፣ እንዲሁም ታምራት ከታሰረ በኋላ በድርጅታዊ ግምገማ ወቅት ሲጠየቁ ‹‹ዘርፌያለሁ›› ብለው ግለ-ሂስ ያወረዱ የኦህዴድ ባለስልጣናት ፍርድ ቤት ሲቀርቡ አለማየታችን ‹‹ወርቁ››ን ከ‹‹ሰሙ›› ለመለየት ብዙ እንዳንጠብቅ አድርጎናል፡፡ ይህ ግን ታምራት ህገ-ወጥ ብልፅግና ውስጥ እጁን አልከተተም ማለት አይደለም፡፡ የዚህ ፅሁፍ ማዕከላዊ ሃሳብም የየትኛውንም የኢህአዴግ ባለሥልጣናትን ‹‹ንፅህና›› መስበክ አይደለም፡፡ ፍላጎቴ ለኢህአዴግ ‹‹አላግባብ ብልፅግና›› ተቀናቃኝን መምቻ ነውን? ወይስ የ ገር ሃብት ዘረፋን ለመከላከል ቆርጦ ስለተነሳ ነው? በሚሉት ጥያቄዎች ላይ የግል ምልከታን ማስቀመጥ ነው፡፡
ስዬ አብርሃ
ስርዓቱ የሙስና ሰለባ ያደረገው ሌላኛው ባለስልጣን ስዬ አብርሃ (ለታምራት ላይኔ ሳይቀር ወታደራዊ ስልጠና የሰጠው) እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እዚህም ጋ ስዬን ‹‹ጲላጦስ›› የማድረግ ፍላጎት የለኝም፤ ነገር ግን ስዬ በ‹‹ሙስና›› ተወንጅሎ ለአመታት እስር ቤት የተወረወረው ከቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ጋር በኤርትራና በመሰል አንዳንድ ጉዳዮች ላይ መለያየታቸውን (አለመስማማታቸውን) ተከትሎ መሆኑ ጉዳዩ ‹‹ሙስና› ብቻ እንዳልሆነ ያመላክታል፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ የሃሳብ ልዩነቱ ከመለስ ጋር አኳርፏቸው ከድርጅቱ የታገዱት ከፍተኛ የአመራር አባላት ከሰባት በላይ ሲሆኑ፣ የታሰረው ግን ስዬና ቤተሰቦቹ ብቻ ነበሩ፡፡ ይህ ሁኔታም ‹‹ስዬ ከሰራዊቱ ጋር ያለው ቁርኝት ለመለስ ስልጣን አስጊ ስለሆነ ነው ከአቻዎቹ ተነጥሎ ለእስር የተዳረገው›› ወደሚል ጠርዝ የገፉኝን ጥቂት ምክንያቶች እጠቅሳለሁ፡፡

ስዬ በህገወጥ-ብልፅግና ላይ መሳተፉ ከተረጋገጠ፣ በህግ ለመጠየቅ የግድ ህወሓት ለሁለት ተከፍሎ፣ ስዬም የመንግስት ስልጣን ከያዘው ኃይል በተቃራኒው እስኪሰለፍና ከድርጅቱ እስኪባረር መጠበቁ አንዱ ነው፡፡ እህትና ወንድሞቹም በተመሳሳይ መንገድ ለእስር መዳረጋቸው ጉዳዩን ህግ ከማስከበር ይልቅ ወደበቀል ያመዘነ አስመስሎታል (በነገራችን ላይ ከነመላኩ ፈንታ ጋር የታሰረው ምረህትአብ አብርሃ የስዬ ታናሽ ወንድም ሲሆን፣ በ93ም ከስዬ ጋር አብሮ ለወራት ታስሯል)

ስዬ ፍርድ ቤት ቀርቦ በዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ በዋስ ከተፈታ በኋላ ገና ከፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ብዙም ሳይርቅ የፍርድ ቤቱ ስልጣን ተሽሮ፣ እስከ አፍንጫቸው በታጠቁ ፖሊሶች በኃይል ወደማዕከላዊ እስር ቤት መመለሱ፤ እንዲሁም በሙስና የተጠረጠሩ ግለሰቦች የዋስትና መብት የሚከለክል ህግ በይድረስ ይድረስ መረቀቁ (መቼም ስዬ የታሰረው በሙስና ከሆነ ‹‹ከፍርድ ቤት በላይ ጠመንጃ ህግ አስከባሪ ሊሆን ይችላል›› የሚል አመክኖ ሊኖር አይችልም)

እስር ቤት ውስጥ የተለያዩ ጫናዎች ይደረጉበት የነበረውም ‹‹የ ገር ሃብት ዘርፈ ል›› ከሚል ተቆርቋሪነት አይመስለኝም፤ ከፖለቲካ ውጪ ያሉ የሙስና ተከሳሾች በስዬ ላይ የተደረገው አይነት አሰቃቂ በደል ሲፈፀምባቸው ብዙም አልታይም፡፡ ይህንን ለማስረዳት አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፤ በአንድ ወቅት ስዬ ከደርግ ባለስልጣናት ጋር እንዲታሰር በመደረጉ ከመቼውም በላይ ተበሳጭቶ ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርቦ እንደነበረ አስታውሳለሁ፤ ለብስጭቱ ሁለት ምክንያት ማስቀመጥ የሚቻል ይመስለኛል፤ የመ መሪያው ‹‹በጠመንጃ ተፋልሚ ከስልጣን ካስወገድኳቸው ደመኞቼ ጋር መታሰሬ ለደህንነቴ ያሰጋኛል›› የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሞራሉን ለመንካት ሆን ተብሎ የተደረገ ይሆናል፤ በአናቱም ስዬ የመከላከያ ሚንስትር በነበረበት ከለታት አንድ ቀን ወደ ከርቸሌ የተወረወሩ የቀድሞ ባለስልጣናትን ሄዶ ከጎበኘ በኋላ ‹‹ለእናንተ ማንም ጥይት አያባክንም፤ በስኳርና ደም ግፊት እዚሁ ታልቃላችሁ!›› ብሎ ተናግሮአቸው ነበር ከሚባለው ጋር የሚያያዝ ነው፤ በእርግጥም ይህንን አምነን እንድንቀበል የሚያስገድደን በ‹‹ሙስና›› ከታሰረበት ክፍል አስወጥተው የደርግ ባለስልጣነት ወደአሉበት ዞን ከአስገቡት በኋላ በዚህ ንግግሩ ያቄሙ አንዳንድ የቀድሞ ባለስልጣናት የስፖርት ልብስ ለብሰው እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ወቅት ስዬን ባዩት ቁጥር ድምፃቸው እንዲሰማ ከፍ አድርገው፡- ‹‹ስኳር አልገደለንም!››፣ ‹‹ደም ብዛት አልገደለንም›› እያሉ ያበሽቁት እንደነበር መስማታችን ነው (መ መሪያውንም ከነበረበት ክፍል ወደእዚህ የቀየሩት ከደርግ ባለስልጣናት መካከል ለተባባሪዎቻቸው ትዕዛዝ አስተላልፈው ሊሆን?)

ጨለማ ቤት በቆየባቸው የተለያየ ጊዜያት ውስጥ ያለአንዳች ጥፋት ሁለቱም እጆቹ በካቴና መታሰሩም ክሱን አምንን እንዳንቀበል ያደረገናል፡፡
እነዚህ ኩነቶች የሚያሳዩት ህግ የማስከበር ሂደትን ሳይሆን፣ ሰውየውን ማሰቃየት፣ ማበሳጨትና ሞራሉን ማንኮታኮት የሚፈልግ ጉልበታም ቡድን ወይም ግለሰብ መኖሩን ነበር፡፡
በጥቅሉም ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩም ሆነ መከላከያ ሚንስትሩ ወደእስር ቤት ከተወረወሩ በኋላ የ ገር ሃብት ዘረፋ በብዙ እጥፍ እየጨመረ ሲሄድ፣ ስርዓቱ አይቶ እንዳላየ ማለፉ ‹‹ህገ-ወጥ ብልፅግና››ን የፖለቲካው መሸፈኛ (ማስቀየሻ) እያደረገው እንደሆነ አስረጂ ነው፡፡ እኔም በግሌ ኢህአዴግ ‹‹መዝረፍ ወን ል ነው›› ብሎ አገር ይያዝልኝ ሲል ሰምቼ አላውቅም፤ ይህ አይነቱ ድርጊት ወን ል የሚሆነው ‹‹ለህወሓት አለመታዘዝ›› ሲጨመርበት ብቻ ነውና፡፡
በተጨማሪም ኃ/ማርያም ደሳለኝ ይህ ሁሉ ሚንስትር፣ ጄነራል፣ እና የተለያዩ ኃላፊዎች በተቀናጣ ህይወት ሲንደላቀቁ፣ ልጆቻቸው እጅግ ውድ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሲማሩ፣ ለራስ ምታትና ጉንፋን ሳይቀር ታይላንድ ሲመላለሱ እያየ ‹‹መንግስት በሚከፍላቸው ደሞዝ ነው›› ሊለን እንደማይችል ግልፅ ነው፡፡
በኢህአዴግ ውስጥ የ ገር ሃብትን መዝረፍ እና አድሎአዊ አሰራር ጥቂት የአመራር አባላትን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ በተለያየ ጊዜም የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ በርካታ አለም አቀፍ ተቋማት ከኢትዮጵያ እጅግ ብዙ ገንዘብ በህገወጥ-መንገድ ወደተለያዩ  ገራት ተልኮ በሚስጥር ጠባቂ ባንኮች መከማቸቱን በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፤ ተ.መ.ድ በ2003 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ‹‹ከ1983-2002 ዓ.ም በአንድ ደሴት  ገር ብቻ በሚገኝ ባንክ 8.4 ቢሊዮን ዶላር በህገወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ወጥቶ ተቀምጧል›› ሲል ያቀረበው ሪፖርትም ሁናቴዎችን ያመላክታል፡፡ በየጊዜው ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጥቃቅን ትችት ሳይቀር ምላሽ የሚሰጠው የመለስ መንግስት በዚህ ሪፖርት ላይ ግን አንዳች ያለው ነገር የለም፤ ለዚህም ይመስለኛል የኃይለማርያም መንግስት ‹‹በፀረ-ሙስና ትግል ላይ ነኝ›› የሚለው ጩኸት፣ የገራፊውን ጅራፍ ጩኸት የመሰለው፡፡ መቼም ባለስልጣናቱ ይህንን ሁሉ ገንዘብ መላኩ ፈንቴና ገብረዋህድ ብቻ የዘረፉት ነው ሊሉን አይችሉም፡፡ እንዲሁም እነዚህ ሰዎች በሙስና መከሰሳቸው ይህን ያህል ጮቤ የሚያስረግጥ አለመሆኑን እነበረከት ስምዖን አይሳታቸውም፡፡ የ ገሬ ሚዲያዎችስ ቢሆኑ መንግስት በቀደደው ቦይ ብቻ መፍሰስ ነበረባቸውን? ጉዳዩን ከስርዓቱ ነባር ልማድና ዛሬም በ ላፊነት ላይ ካሉ ቱጃር ሚሊየነር ባለስልጣናት አኳያ ለማየትና ለመተንተንስ ስለምን ሰነፉ? (የሆነ ሆኖ በግሌ ከ‹‹ክሱ››  ርባ አሉ ብዬ የማስባቸውን የፖለቲካ አንጓ እጠቅሳለሁ)
የስልጣን ሽኩቻ
የክሱ ዋነኛ ምክንያት የመለስን ህልፈት ተከትሎ ግንባሩ ውስጥ የተፈጠረው የስልጣን ሽኩቻ ወደ ኃይል ትንቅንቅ ማደጉ ነው ብዬ አስባለሁ፤ ይህንንም መከራከሪያ በመረጃ ለመደገፍ የህወሓት ሊቀ-መንበርና የኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ አባል የነበሩት አቦይ ስብሃት ነጋ ሰኔ 19 ቀን 2005 ዓ.ም ከታተመው ‹‹ሰንደቅ ጋዜጣ›› ጋር ያደረጉትን ቃለ-መጠይቅ ማየት በቂ ነው፡፡ አቦይ ኢህአዴግን ለመንግስትነት በማብቃቱም ሆነ ለሁለት አስርተ ዓመታት ስልጣኑ እንዲረጋ ታላቅ ተጋድሎ ካደረጉ ጥቂት የስርዓቱ ፍልስፍና ‹‹ኤጲስ ቆጶሳት›› ዋነኛው መሆናቸው አይሳትም፡፡ በእርግጥ ከ2003 ዓ.ም  ምሮ አቦይ ከፓርቲው የአመራር አባልነት በመልቀቃቸው ‹‹ስለድርጅቱ ሚስጥር የሚናገሩትን እንዴት ማመን ይቻላል?›› የሚል ጥያቄ የሚነሳ ከሆነም፣ ህወሓትን በሚገባ ካለማወቅ ጋር መላተም አይቀሬ መሆኑን በሶስት አንፃር ልናየው እንችላለን፡፡
የመ መሪያው ኢህአዴግን የፈጠረው ህወሓት የ ገሪቱን ቁልፍ የስልጣን ቦታዎች ጠቅልሎ እንዲይዝ ቀመሩን ካዘጋጁት ውስጥ አንዱ አቦይ በመሆናቸው በቀላሉ ከመረጃ መረብ ውጪ ማድረግ ከባድ መሆኑ፤ ሁለተኛው ደግሞ እሳቸውና ጓደኞቻቸው ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያ ያለው የአስተዳደር ዘይቤ በጎሳ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ አራቱ ድርጅቶች ከመሰረቱት ግንባር ይልቅ የተናጠል ጥቅም ላይ በማተኮራቸው አባላቱ በተለያየ ምክንያት ከአመራር ለተነሱ መሪዎቻቸው ታማኝ ሆነው የሚቆዩበት አካባቢያዊ (ክልላዊ) ትስስር በነበረበት ስለሚቀጥል፤ ሶስተኛው ከአብዛኛው የህወሓት አመራሮች፣ የደህንነት  ላፊዎች እና ጄነራሎች ጋር የስጋ ዝምድና እና የጋብቻ ትስስር መፍጠራቸው ቢያንስ የቀጥታ የፖለቲካ ጉልበት ባያስገኝላቸውም በኢ-መደበኛ ግንኙነት የፓርቲውን ሚስጥሮች ለማወቅ እንዳይቸገሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ከዚህ በታች የምጠቅሰውን የአቦይ ስብሃትን መረጃ የውስጥ አወቅ አድርገን እንድንወስድ ስለሚያስችለን ወደ ቃለ-መጠየቁ እንለፍ፡፡
ደህና! በአሁኑ ወቅት በ ገሪቱ ያለውን አደጋ እንዴት ያዩታል ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት መልስ እንዲህ ይላል፡-
‹‹…ህገ-መንግስት በመጣስ የላይኛው የታችኛውን ኃላፊ እያዘዘ ለዚህ አድርግለት፣ ለዚያኛው ቅጣው፣ እሰረው የሚል አለ፡፡ ስልጣን የሚቀማው ለኢኮኖሚ (ሙስና) ጥቅም ነው፡፡ ስልጣን እየተቀማ ያለውም በዚያች ወንበር ተቀምጦ ለመቆየትና ትርፍራፊ አገኛለሁ ብሎ በወንበሩ ላይ እስካለ ድረስ ጥቅም ያገኛል››
በእርግጥም በድርጅቱ ውስጥ የስልጣን መነጣጠቅ (ሽኩቻ) ስለመኖሩ ከዚህ የበለጠ ፍንጭ የሚገኝበት ቀዳዳ የለም፤ አቦይ ለጥያቄው የሰጡትን መልስ ሲደመድሙ፡-
‹‹…ጠቅለል አድርገን ስናየው አሁን ያለው የአንዳንድ የመንግስት፣ የፓርቲና የግል ባለ ብቶች ከኢህአዴግ መንግስት ስርዓት ፈፅሞ የማይሄድ ፀረ-ልማት፣ ፀረ-ዲሞክራሲና ፀረ-ሰላም እየሆኑ በመጓዝ ላይ ነው ያሉት›› ማለታቸው ክፍፍል መኖሩን ያስረግጥልናል፡፡ መቼም እርሳቸው ‹‹ፀረ-ዲሞክራሲ…›› ሲሉ ድርጅታቸውን የኮነኑት ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ከ ያ ዓመታት በላይ ‹‹ኢህአዴግ አምባገነን ነው›› ሲል መሰንበቱን አምነው አይመስለኝም፡፡
የኃይል አሰላለፉ
የኃይል አሰላለፉ በዋናነት በሁለት የቡድን አባቶች ስር የሚጠቃለል ነው፤ በአባይ ወልዱና አዜብ መስፍን የሚመራው የህወሓት አንድ ኃይል ከብአዴን ጋር የፈጠረው ግንባር እና አንጋፋ የህወሓት ታጋዮች ያሉበት የእነ ደ/ፅዮን ገ/ሚካኤል/አቦይ ስብሃት ቡድን እንደሆነ ይነገራል (በነገራችን ላይ ህወሓት ውስጥ ያለው ክፍፍል በእነስዬ ጊዜ እንደነበረው የተደራ ና መስመር የያዘ አይደለም፤ የአሁኑ ልዩነት ምናልባት ያሸነፈውን ቡድን የተሻለ ጠንካራ ሊያደርገው ይችል ይሆናል እንጂ ተሸናፊዎቹን እንደ 93ቱ ከድርጅቱ እስከመታገድ የሚያደርስ አይመስለኝም)፡፡
መላኩ ፈንቴ ከመታሰሩ ሁለት ቀን ቀደም ብሎ፣ ብርሃነ ኃይሉ ከስልጣኑ መሻሩን የሚገልፅ ደብዳቤ ደርሶታል (ሁለቱም የብአዴን ስራ አስፈፃሚ አባል ናቸው)፡፡ እናም የእነዚህ ባለስልጣናትን እግድና እስር ከክሱ ለይተን ካየነው የብአዴንን መዘውር በጣምራ ለጨበጡት (አዲሱ ለገሰ እና በረከት ስሞዖን) በዘወርዋራ የተላለፈ ማስጠንቀቂያ ይመስለኛል፤ ምክንያቱም አቦይ ስብሃት የሙስና ዘመቻው በተወሰኑ ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ ነው ስለመባሉ ከጠቀስኩት ጋዜጣ ተጠይቀው ‹‹ሌባና ሌባ፣ የሁሉም ብሔሮች ሌቦች በአንድነት እየተደራጁም በተናጠልም የዚህ ብሔር ተጠቃ፣ የዚያኛው ብሔር ያለጥፋቱ ታሰረ ማለታቸው አይቀርም›› ሲሉ የሰጡት መልስ መላምቱን ይደግፈዋል፡፡
ከዚህ አንፃርም የማሸናፊያ ካርታ ሊደረግ የተሞከረው የሙስናው ክስ አቦይ ለሚደግፉት ቡድን የ ይል ሚዛኑን እንዲያስመልስ የአስቻለ የሚመስልባቸውን ምክንያቶች እጠቅሳለሁ፡፡
ሹም-ሽሩ
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የአስራ ሁለት ሚንስትሮችና የአንድ ዳይሬክተር ሹመት መፅደቁ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ውስጥ በተለይም የአቶ በረከት ስምዖን እና የአቶ ሽፈራው ሽጉጤ ‹‹ሹመት›› አንዳች ቋጠሮ አይጠፋውም፡፡ እንደሚታወቀው ከመለስ ህልፈት በኋላ በረከት ስምዖን ራሱን የ ገሪቱ ቁልፍ ሰው የማድረግ አዝማሚያ ነበረው፡፡ ሆኖም በባህርዳሩ ጉባኤ ላይ «ብአዴን ለትግሉ ካበረከተው አስተዋፅኦ አንፃር የሚገባውን ስልጣን ማግኘት አልቻለም። ሁሌም ሕወሓት ነው በበላይነት ስልጣኑን የሚቆጣጠረው፤» አለ መባሉ በህወሓቶች ዘንድ እንዳልተወደደለት ተነግሯል፡፡ አሁን ደግሞ ወደ አማካሪነት ዝቅ ብሏል፤ በእርግጥ የተመደበበት ቦታ አዲስ መሆኑና ከሌሎች አማካሪዎች በተለየ መልኩ ኩማ ደመቅሳም ምክትሉ ሆኖ መሾሙ በድፍረት ከቀድሞ ያነሰ ቦታ ነው የተሰጠው ለማለት ጊዜው ገና ቢሆንም፣ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚንስቴር ወንበር ከወሳኝ የስልጣን ቦታዎች አንዱ ከመሆኑም በላይ ሁሉንም የመንግስት ሚዲያ ለመቆጣጠር ስለሚያስችል የሚፈጥረው የፖለቲካ ጉልበት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡
ሽፈራው ሽጉጤም ከደቡብ ክልል አስተዳዳሪነቱ ተነስቶ ‹‹የትምህርት ሚኒስትር›› መደረጉ የስልጣን ሽረት መሆኑ አያከራክርም (መቼም የሰውየው የትምህርት ዝግጅትም ሆነ ልምድ በፍፁም ትምህርት ሚኒስትር ላይ እንዲመደብ ሊያደርገው እንደማይችል ግልፅ ነው)፡፡ ይህም ሹም-ሽሩ በድርድር የተደረገ የፖለቲካ ውሳኔ መሆኑን ያሳየናል፡፡ ምክንያቱም ሽፈራው ሽጉጤ ከሙስና ጋር በተያያዘ ስሙ በስፋት ሲነሳ ከመቆየቱ አንፃር ከነበረበት ዝቅ አለ እንጂ እንደ እነመላኩ ፈንቴ የመከሰስ እጣ ፈንታ አልገጠመውም፡፡
የአዜብ መስፍን ዕድል ፈንታ
የአዲስ አበባ ከተማ የከንቲባ ወንበርም ከአዜብ መስፍን ጋር ተያይዞ ይነሳ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ባልተለመደ መልኩ አንድ ከንቲባና ሶስት ምክትሎች ሲመረጡ ወ/ሮ አዜብ መስፍን ምርጫው ውስጥ አልተካተተችም፡፡ ለምን? እንደሚመስለኝ ፍላጎቱ ስለሌላት ሳይሆን፣ ከላይ በጠቀስነው ቡድን አስገዳጅ ድርድር አፈግፍጋ ሊሆን ይችላል፤ ይኽንን መላምት ለማብራራት በዘጠነኛው ጉባኤ ላይ የታዩ ክስተቶችን ወደ ኋላ ተመልስን ማስታወስ ይኖርብናል፡፡ እንደሚታወቀው አዜብ መስፍን ከሙስና ጋር ስሟ በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል፤ እናም ይህንን የሚያውቁት አቦይ ስብሃት ነጋ በስብሰባው ላይ እንዲህ አሉ፡- ‹‹ሙስና የተወራበት ቦታ ካለ የሚመለከታቸው አካላት ለደቂቃዎችም ሳይዘገዩ ማጣራት ግዴታቸው ነው!››፤ ለዚህ የአቦይ ክስ አዜብ በዘወርዋራ መልስ ሰጠች፡- ‹‹ከ ገር መሪዎች በፔሮል በሚከፈለው ደሞዝ የሚኖረው መለስ ብቻ ነው፤ … ከደሞዙ ላይ ለኢህአዴግ መዋጮም ስለሚቆረጥ ብዙ ጊዜ እንቸገራለን››፤ ይህ መወነጃ ልም ወደ ስልጣን ድርድሩ እንድትገፋ አስገድዷታል ወደ ሚል ጠርዝ ይወስደናል፡፡
(በነገራችን ላይ በአሁኑ ወቅት ‹‹ለያዥ-ለገናዥ›› አስቸግሮ የነበረው የሙስና ዘመቻ የቤት ስራውን አጠናቆ የተደመደመ መስሏል፤ ይህም የሚያሳየን ጉዳዩ ሄዶ ሄዶ በቀላሉ ሊደፈሩ የማይችሉ ሰዎች ላይ በመድረሱ ወደ ድርድር መቀየሩን ነው፤ ዓላማውም ይህ ነው፣ ሌላ አይደለም፤)
ከዚህ ሁኔታ ተነስተን ይህንን እርምጃ በማቀነባበር ልዩነቱ በተፈጠረበት ሰሞን የበላይነቱ ተነጥቆ የነበረው አብላጫውን የህወሓት አመራር የያዘውን ቡድን መጠርጠር ይችላል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የዚህ ቡድን አባላት አባይ ፀ ዬ፣ ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል፣ አርከበ ዕቁባይ፣ ፀጋዬ በርሄና የመሳሰሉት መሆናቸው ነው፡፡ ከእነዚህ ሰዎች  ርባ ደግሞ በጋብቻ ከአርከበና ፀጋዬ ጋር የተሳሰሩት አቦይ ስብሃት ነጋ ማድፈጣቸው ግልፅ ነው፡፡ ፀጋዬ በርሄ በሚንስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚንስትሩ የደህንነት አማካሪ በመሆኑ የሁሉንም ‹‹ጓዳ-ጎድጓዳ›› የመዳፉ ያህል ጠንቅቆ የሚያውቀው የደህንነት መስሪያ ቤት በስሩ ያደረ ነው፡፡ እናም በመላኩ እና በገብረሃዋድ (ገ/ሃዋድ የመለስ ታማኝና የትውልድ መንደሩ ሰው ከመሆኑ አኳያ፣ እንዲሁም ባለቤቱ ከአዜብ ጋር ባላት የ‹‹ስራ›› ግንኙነት ከእነአባይ ወልዱና በረከት ስምዖን ጋር የተሰለፈ ሊሆን ይችላል፡፡ የገብረሃዋድ ባለቤት ኮሎኔል ሐይማኖት ከመከላከያ ለቃ የአዜብ ቀኝ እጅ ከሆነች ቆይታለች፡፡ ከሴቶችና ኤች.አይ.ቪ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ጠቀም ባለ ድርሻ ታስተዳድርላታለች) ላይ ለ‹‹ክፉ ቀን…›› ተብለው በደህንነት ቢሮ የተቀመጡ መዝገቦች እንዲገለጡባቸው ተደርጎ ይሆናል፡፡ ለዚህ አይነቱ ዕቅድ አቦይ በቡድኑ ውስጥ መኖራቸው ጠቀሜታውን ያጎላዋል፡፡
የሆነ ሆኖ ከባህር ዳሩ ጉባኤ አስቀድሞ በመቀሌው የህወሓት ስብሰባ ይህ ልዩነት በተሟላ ምስል ተከስቷል፡፡ ከእነአዜብና በረከት ጋር ያበረው የትግራይ ክልል አስተዳዳሪ አባይ ወልዱ፣ ባለቤቱ ትረፉ ኪዳነማርያምና ቴዎድሮስ  ጎስ በስብሰባው ላይ የተገኙት አስቀድመው የቤት ስራቸውን አጠናቀው መሆኑን የተረዱት አቦይ ስብ ት ‹‹በመለስ አመራር እንቀጥላለን›› ብሎ መላ ካድሬውን ከጎኑ ያሰለፈውን ይህንን ቡድን እንዲህ ሲሉ ተንኮሰውት ነበር፡-
‹‹የመለስ ራዕይ እያለን ህወሓትን እያስገፋን ነው፤ ይህ ስህተት ይመስለኛል፤ የመለስ ራዕይ የሚባል ነገር የለም፤ እኔ አላውቅም! ኢህአዴግን ይዘን ብንንቀሳቀስ ይሻለናል››
ከዚህ በኋላ አዳራሹ በብዙ ታቃውሞ፣ በጥቂት ድጋፍ ተናወፀ፤ የዕለቱ አ ንዳም ‹‹የመለስ ራዕይ አለ ወይስ የለም?›› ወደሚል ተቀየረና ለአንድ ቀን ተኩል ያህል ቢያከራክርም በመጨረሻ ‹‹መጥነው የደቆሱት…›› እነአባይ ወልዱ የበላይነትን ጨበጡ፡፡ የዚህ ቡድን የበላይ መሆን ከአቦይ በተጨማሪ አርከበንና አባይ ፀ ዬን ከሚገባው በላይ አሳስቧቸው ነበር፡፡ የእነርሱ ስጋት እነአባይ ወልዱ የህወሓትን የውስጥ ትግል በአሸናፊነት ለመወጣት፣ ነገ ‹‹አስረክብ›› ቢባል ‹‹አሻፈረኝ ይላል›› ብለው ለሚያስቡት ብአዴን የበዛ ስልጣን እየሰጡት ነው ወይም የወቅቱን ፖለቲካ ከአናት ሆኖ እንዲመራው እያደረጉት ነው ከሚል የመነጨ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል አርከበ በስብሰባው መዝጊያ ላይ ‹‹ናይ መለስ ታሪክ ምውራይ አይኮነን ዝድለ፣ ሕዚ ዝደለ ሓዱሽ ታሪኽ ምስራሕ፣ አመራርሓ ምሃብ ምኽኣል እዩ›› (አሁን የሚፈለግብን የመለስን ታሪክ ማውራት ሳይሆን፣ አዲስ ታሪክ ለመስራት ተገቢውን አመራር መስጠት ነው) ያለው፡፡
እነመላኩ ፈንቴ
ፈንቴና ብርሃነ ኃይሉ በመንግስትም ሆነ በብአዴን ውስጥ የጎላ የፖለቲካ ጉልበት እንዳሌላቸው ይታወቃል፡፡ እነርሱም እንደደመቀ መኮንን አብዛኛውን ጉዳይ ‹‹መ መሪያ አቶ አዲሱን ላማክር፣ አቶ በረከትን ልጠይቀው…›› የሚሉ እንደሆነ ይነገራል፡፡ እንግዲህ በመሬት ያለው ይህ ከሆነ እነዚህ ባለስልጣናት በኃይል ትንቅንቁ ላይ አንዱን ወግነው የሚያዛቡት የኃይል ሚዛን የለም ብለን ለመደምደም እንችላለን፡፡ ስለዚህም ለእስራቸውና መሻራቸው የግድ አንድ ምክንያት ልናገኝ ይገባል ማለት ነው፡፡ ደህና! የሙስና ክሱን እንደ አንድ መላ-ምት እንውሰደው፤ በሁለተኝነት የምናስቀምጠው ደግሞ ከክሱ  ርባ የፖለቲካ ጨዋታ መኖሩን የሚያመላክተን ሁለቱ ባለስልጣናት ድንገት የተባረሩና የታሰሩ አለመሆኑን የሚያሳይ ፍንጭ ማግኘታችን ነው፤ ይኸውም ባለስልጣናቱ ከመሻራቸውና ከመታሰራቸው ከጥቂት ቀናት በፊት ደጋግመው ከ ገር ሽማግሌው ቡድን ጋር በተለያዩ ሆቴሎች ረዘም ያለ ቆይታ (ምክክር) ሲያደርጉ መታየታቸው ነው፤ እናም ይህ ሁናቴ የሚያመላክተን ምናልባትም ፊቱን ካጠቆረባቸው አንድ ጉልበታም ቡድን ጋር እንዲማልዷቸው አየተማፀኑ ይሆን? ለዚህ እና ሌሎች መሰል ጥያቄዎች መጪ ጊዜያት ምላሽ ይኖራቸው ይሆናል፡፡

ኢትዮሚድያ

July 27, 2013

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: