ኢህአዴግ ለግንቦት7 የድርድር ጥያቄ አቀረበ

esat

ህዳር ፳፫(ሃያ ሦስት)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች እንደገለጹት ኢህአዴግ የእንደራደር ጥያቄውን በሁሉት ወር ጊዜ ውስጥ ለ3ኛ ጊዜ ማቅረቡ ነው።

ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ኢሳት ላቀረበው ጥያቄ በሰጠው የጽሁፍ መልስ “የእንደራደር” ጥያቄ እንደቀረበለት አምኖ፣ “ይሁን እንጅ ንቅናቄው በዋናነት  ወያኔ እንደለመደው ድርድርን ለውጥረት ማስተንፈሻነት ለመጠቀም” ያደረገው ነው ብሎአል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመኘውም ሆነ ግንቦት 7 የሚፈልገው ዲሞክራሲያዊ ለውጥ በሰላማዊ መንገድ በሚደረግ ትግልና በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረጉ ዉይይቶች ቢመጣ መሆኑን ጠቅሶ ንቅናቄውን ሁለገብ ትግል ውስጥ እንዲገባ ያስገደደው የወያኔ እምቢተኝነትና እብሪት ብቻ ነው ብሎአል። የድርድር ሂደትን በሚመለከት ሁሌም ለድርድር ክፍት መሆኑን የገለጸው ግንቦት7፣  ይህ የድርድር ሂደት እንዲያው ለለበጣ የሚደረግ ሳይሆን ወደሚፈለገው ነጻነት በአነስተኛ መስዕዋትነት ሊያደርስ ይችል ከሆነ በሩን ላለመዝጋት እንጂ፣ በምንም አይነት ኢትዮጵያን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሀገር ማድረግን፤ የሚቀይር ወይንም ከዚያ ያነሰ ውጤትን ለመቀበል መፍቀድን ፈጽሞ የማያመለክት ነው

ሲል አቋሙን ገልጿል።

የግንቦት 7 ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የእንደራደር መልዕክት እንደደረሰው በጉዳዩ ዙሪያ በሰፊው እንደተወያየመበት በመጥቀስ የኢትዮጵያን ሕዝብ ባጠቃላይ እንጂ ግንቦት 7ን ብቻ የሚመለከት ጉዳይ እንዳልሆነ ከድምዳሜ ላይ መድረሱንም በመግለጫው አመልክቷል።

ንቅናቄው አክሎም ኢህአዴግ የ “እንደራደር” ጥያቄውን ከዚህ በፊት እንዳደረገው ለገባበት የፖለቲካ ውጥረት ማስተንፈሻ፣ ለውሸት ፕሮፓጋንዳው መጠቀሚያ፤ ለጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ መሰብሰቢያ፤ የዴሞክራሲ ታጋዮችን ትጥቅ ማስፈቺያና ወኔ መስለቢያ አድርጎ እንዲጠቀምበት እንደማይፈቅድለት ገልጿል።

ምንም ዓይነት ድርድር ከመደረጉ በፊት መንግስት ጉዳዩን ከምር የወሰደው መሆኑን የሚያሳዩ “የመተማመኛ” እርምጃዎች መውሰድ ተገቢ መሆኑን የገለጸው ድርጅቱ ከእነዚህም መተማመኛዎች መካከል   ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች፤ ጋዜጠኞች፤ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ፣ በግልጽ የሚታወቁ እስረኞችን ብቻ ሳይሆን በድብቅ የተቋቋሙ ማጎሪያና ማሰቃያ ቤቶች ያሉትን ሁሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት ፣  በሕዝብ በተለይ በተቃዎሚ ኃይሎች ላይ በየቀኑ እያካሄደ ያለውን ወከባና እንግልት ባስቸኳይ ማቆም፣ ሰብዓዊና የዜግነት መብታቸውን ማክበር ፣  በፖለቲካ ምክንያት ከዚህ በፊት የተወሰዱ ሁሉም ዓይነት ፍርድ ተብየ ውሳኔዎች እንዲሻሩ ማድረግ፤ በሂደት ላይ ያሉ ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ ምንም አይነት ክሶችን ማቋረጥ ፣ ሕዝብን በፍርሃትና በስጋት ለማቆየት ሆነ ተብለው የወጡ አፋኝ ህጎችን በአስቸኳይ ማንሳት፣  ማንኛውም ድርድር ገለልተኛ የሆኑ ሶስተኛ ወገኖች ባሉበት፤ የድርድሩ ሂደት በምስልና በድምጽ ተቀርጾ በገለልተኛ ወገኖች እጅ ብቻ የሚቀመጥ፣ የድርድሩ ቦታም የተደራዳሪ ወገኖች በጋራ በሚስማሙበት ቦታ መሆኑን መቀበልና ይህንንም በግልጽ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማሳወቅ የሚሉት ተጠቅሰዋል።

” ወያኔ እነዚህን እርምጃዎች ለመውሰድ ቁርጠኝነት ሳይኖረው ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመስረት የሚደረግ ድርድር ላይ ከምር ይሳተፋል ብለን ማመን በፍጹም አንችልም የሚለው ግንቦት7 ፣ እስከዚያው ድረስ ግን ግንቦት 7ም ሆነ ሌሎች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመስረት በቁርጠኝነት የሚታገሉ ኃይሎች፣ ወያኔ እነኝህን የመተማመኛ እርምጃዎች እስኪወስድና ቀደም ብለው በተቀመጡት መርሆች መሠረት በሚደረግ ድርድር በተግባር ሊመነዘር የሚችል ስምምነት፣ አልፎም ለምንም አይነት ማጭበርበርና መንሸራተት እድል የማይሰጥ ጠንካራ መጠበቂያዎች መኖራቸው እስኪረጋገጥ ድረስ፣ የጀመሩትን ትግል አጠንክረው እንዲገፉበት ጠይቋል።

ግንቦት7  የድርድሩ ውጤት የኢትዮጵያን ሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ያረጋገጠ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በአስቸኳይ እውን ማድረግ መሆኑን ገልጾ፣   በሥልጣን ላይ ባለው ኃይል በኩል ወደዚህ ግብ ለመድረስ ቁርጠኝነቱ በሌለበት ሁኔታ በሚደረግ ማንኛውም አይነት ድርድር ውስጥ ግንቦት 7 አይሳተፍም ሲል አቋሙን አንጸባርቋል።

ድርጅቶችን በተናጠል እየለያዩ “እንደራደር” ማለት በራሱ ጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም ስሌትን የያዘ እሳቤ እንጂ፣ በዘላቂነት አገሪቱን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ አገር ለማድረግ መፈለግን አያመለክትም በማለት የሚገልጸው ንቅናቄው፣ ለአንድ ድርጅት ለብቻው የሚመጣ ወይም የሚጠቅም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለመኖሩ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመፍጠር ፍላጎት ያለው ድርድር በአገሪቱ ያሉትን የተለያዩ የፖለቲካም ሆነ የሲቪክ ኃይሎችን ያካተተና ያመኑበት መሆን ይኖርበታል ብሎአል።

“የሚደረገው ድርድር ማን በስልጣን ላይ ይውጣ ወይንም የፖለቲካ ስልጣንን ባሉት ኃይሎች መሀከል እንዴት እናከፋፍለው የሚል የስልጣን ቅርምት ድርድር ሳይሆን፤ ሕጋዊና የሕዝቡን የሥልጣን ሉዓላዊነት ባረጋገጠ ሁኔታ የፖለቲካ ስልጣን እንዴት እንደሚያዝ ፍትሀዊ የሆነ ሂደትን ለማስጀመር የሚደረግ ድርድር መሆን አለበት” ሲል በድርድር ዙሪያ ያለውን መርህ አስቀምጧል።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: