በጅማ ዩኒቨርስቲ የኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች መብት መረገጥ ተባብሷል፤ የትምህርት እና የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴሮች የአምልኮ፣ የአለባበስና የአመጋገብ መመሪያውን ማስከበር ተስኗቸዋል

jimma-universityበአለባበስ እና በአመጋገብ በክርስቲያንና በሙስሊም ተማሪዎች መካከል አድልዎ ይፈጸማል
በተማሪዎች ዲኑ ማንአለብኝነት ተማሪዎች የፍልሰታ ለማርያምን ጾም ለመጾም ተቸግረዋል
የጅማ የማኅበረ ቅዱሳን ማዕከል ምእመኑን በማስተባበር ለተማሪዎቹ ድጋፍ እያደረገ ነው
ቅ/ሲኖዶስ ሃይማኖታዊ መብታቸውን የሚያስከብር አቋም እንዲወስድ ተማሪዎቹ ጠይቀዋል
‹‹ኦርቶዶክሳዊ ሥርዐተ እምነትን በማንአለብኝነት ለይቶ የመጋፋት አካሔዱ፣ አኹን በደረሰበት ደረጃ አሳሳቢ የሃይማኖታዊል ነፃነት መረገጥ እንጂ የመብል ጉዳይና የአንድ ዩኒቨርስቲ ችግር ብቻ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡›› /ተማሪዎቹ/
(ኢትዮ – ምኅዳር፤ ቅፅ ፪ ቁጥር ፷፤ ረቡዕ፣ ነሐሴ ፯ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)

jimma-university-logoበጅማ ዩኒቨርስቲ የተለያዩ ካምፓሶች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ተማሪዎች በሥርዐተ እምነታቸው የተደነገጉ የዐዋጅ አጽማዋትን በመጾም ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን ለመወጣት መቸገራቸውንና የትምህርት ተቋማት የአምልኮ፣ የአለባበስና የአመጋገብ መመሪያውን* በአድሏዊነት በሚያስፈጽሙ ሓላፊዎች ምክንያት በእምነት ነፃነታቸው ላይ የሚደርሰው መረገጥ ተባብሶ መቀጠሉን ለኢትዮ – ምኅዳር ገለጹ፡፡

በጅማ ዩኒቨርስቲ በዋናው ግቢ፣ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እንዲኹም በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ካምፓሶች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ የክረምት፣ የፔዳጎጂና የሕክምና ሳይንስ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ለኢትዮ – ምኅዳር እንደተናገሩት÷ በየዓመቱ ከነሐሴ ፩ – ፲፮ ቀን በሚቆየው የፍልሰታ ለማርያም መታሰቢያ ጾም ‹‹የጾም ምግብ አይዘጋጅም›› በመባሉ በሥርዓተ እምነታቸው ላይ አድልዎና ጫና እየተደረገባቸው እንዳለ ገልጸዋል፡፡

የፍልሰታ ለማርያም ጾም ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሰባት ዓመት ዕድሜ በላይ የሚገኙ ምእመናንዋ እንዲጾሟቸው ካዘዘቻቸው የሕግ/የዐዋጅ/ አጽዋም አንዱ እንደኾነ የሚጠቅሱት ተማሪዎቹ፣ መዋዕለ ጾሙ ከተጀመረበት ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ ከምግብ ቤቱ የሚያገኙት አንድ ዳቦ ብቻ እንደኾነና እርሱም ለኹሉም ጿሚ ተማሪዎች ሳይዳረስ እንደሚያልቅ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በመዋዕለ ጾሙ ተማሪው ወደ ካፊቴሪያው ገብቶ የሚቀርብለት ሥጋ በመኾኑ ሊመገበው አይችልም፤ ዳቦውም አይዳርስም፤ ቶሎ ያልቃል፤›› ብለዋል ተማሪዎቹ፡፡

ቀደም ሲል በአጽዋማት ወቅት የጿሚ ተማሪዎችን ዝርዝር ለተማሪዎች ዲኑ በማሳወቅ በብዛታቸው ልክ ምግቡ ተዘጋጅቶ ይስተናገዱ እንደነበር ተማሪዎቹ አውስተው፣ ጾመ ፍልሰታ ባለፈው ሳምንት ኃሙስ ከመግባቱ አንድ ሳምንት በፊትና ጾሙ በገባበት ዕለት እንደተለመደው ለዲኑ ቢሮ ብናሳውቅም፣ ዲኑ አቶ እውነቱ ኃይሉ፣ ‹‹በዚኽ ጉዳይ እኛ ጋራ እንዳትደርሱ፤ ማመቻቸት አይቻልም›› የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ተናግረዋል፡፡

higher-institutions-rules-and-regulations-on-worshippingየትምህርት ሚኒስቴር ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያወጣው የአምልኮ፣ የአለባበስና የአመጋገብ መመሪያ፣ በጾም ወቅት ለክርስቲያኑ ይኹን ለሙስሊሙ ተማሪ አቅም በፈቀደ መጠን ሃይማኖቱን መሠረት አድርጎ የጾም ይኹን የፍሥክ ምግቦች ሊዘጋጁ እንደሚችሉ ይገልጻል፡፡** በጾም ምግብ ዝግጅት ተማሪው ከተመደበለት በጀት ያነሰውን ቢጠቀም እንጂ ከምግብ ቤቱ አቅም በላይ ሊኾን እንደማይችል ተማሪዎቹ አመልክተዋል፡፡

በዩኒቨርስቲው አራቱም ካምፓሶች ግን፣ ከ፳፻፬ ዓ.ም. ጀምሮ ታላቁን የሑዳዴ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያትንና ጾመ ፍልሰታን ጨምሮ ለኦርቶዶክሳውያን ምእመናን በአጠቃላይ በዐዋጅ የታዘዙ አጽዋማትን በቀኖናው መሠረት እንዳይፈጸሙና በጀታቸውንም በአግባቡ እንዳይጠቀሙ በተለይ በተማሪዎች ዲኑ ውሳኔ ይደረጋል የሚሉት አድልዎና ጫና በየዓመቱ እየከፋ መምጣቱን ነው ተማሪዎቹ ለዝግጅት ክፍሉ ያስረዱት፡፡ በዚኽ ዓመት ሰኔ ወር መግቢያ ላይ በጀመረው ጾመ ሐዋርያት ወቅት፣ የተማሪዎች ኅብረት የጿሚ ተማሪዎችን ጥያቄ በመያዝ ከዲኑ ጋራ ቢወያይም ‹‹የሰኔ ጾም የሚባል የምናውቀው የለም፤ ማንም የፈለገውን ቢል አይዘጋጅም›› በሚለው የዲኑ እብሪትና ጥላቻ የተሞላበት አቋም ምክንያት ጥረታቸው ውጤት እንዳላመጣ ተማሪዎቹ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የፍልሰታ ለማርያም ጾም እና የረመዳን ጾም በአንድ ወቅት በዋለበት በ፳፻፭ ዓ.ም. ክረምት፣ ሙስሊም ጿሚ ተማሪዎች ምግብ ከማውጣት ጀምሮ የካፊቴሪያውን ሙሉ አገልግሎት ሲያገኙ፤ ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ጿሚ ተማሪዎች በአንጻሩ ተገቢ መስተንግዶ አለመዘጋጀቱ፣ የጾም ሰዓታቸውን ጠብቀው ለመመገብ እንዲችሉ ምግብ ቤቱ ክፍት አለመደረጉና የድርሻቸውን እንዳያወጡ መከልከላቸው፣ ይህንንም ተከትሎ ሥርዓተ እምነታቸው በመመሪያው አግባብ እንዲከበር በዩኒቨርስቲው ቅጽር ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ የጠየቁ ተማሪዎች በፖሊስ መደብደባቸው፣ ለእስራት መዳረጋቸውና ከእነርሱም መካከል በአራት ተማሪዎች ላይ ከአንድ እስከ ሦስት ዓመት ከትምህርት ገበታቸው የማገድ ርምጃ መተላለፉ፣ እንደ እውነቱ ኃይሉ ያሉ የዩኒቨርሲቲው ሓላፊዎች ‹‹የተቋሙ ሴኩላር መመሪያና ፕሪንስፕል አይፈቅድም›› በሚል ሰበብ በኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ላይ ይፈጽሙታል ለተባለው ሃይማኖታዊ እና አስተዳደራዊ አድልዎ እና ጫና በአስረጅነት ቀርቧል፡፡

የተማሪው ጥያቄ፣ በነፍስ ወከፍ የተተመነው በጀት በሚፈቅደው መጠን በዩኒቨርስቲው ሲደረግ የቆየው የጾም ወቅት መስተንግዶ ያለአድልዎ ተጠብቆ እንዲቀጥል መኾኑን ያመለከቱት ተማሪዎቹ፣ ሴኩላሪዝምን በማስፈን ስም መንግሥት በፌዴራል ደረጃ ያወጣውንና ክልሎችም ያለመቃረን እንዲፈጽሙት ያስተላለፈውን የአምልኮ፣ የአለባበስና የአመጋገብ መመሪያ የሚፃረር ‹የሴኔት ሕግ፣ ፕሪንስፕልና መመሪያ› ለሙስና በር የሚከፍት፣ ግለሰቦችና ቡድኖች በአካዳሚያዊ ተቋሙ ባላቸው ሥልጣን ተጠቅመው የአንዱን እምነት ከሌላው በመለየት ለሚፈጽሙት አድልዎና ጫና ምቹ ኹኔታ የሚፈጥር በመኾኑ ኹኔታው ወደ ቀውስ*** ከማምራቱ በፊት አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

አሠራሩ፣ ‹‹ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያኑን ሥርዐተ እምነትኽ እንደሚደነግገው አትጹም ብሎ ከመከልከል አይተናነስም፤›› ያሉት ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች፣ የዩኒቨርስቲው የተማሪዎች ዲን በአመጋገብና በአለባበስ ያደርሱብናል ያሉትን አስተዳደራዊና ሃይማኖታዊ በደል በየጊዜው ለጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በመግለጽ በሊቀ ጳጳሱ አማካይነት እልባት ለማግኘት ጥረት ቢደረግም ጥረቱን ከጣልቃ ገብነት በመቁጠርና ‹‹ዐርፈው ይቀመጡ›› በሚል በሊቀ ጳጳሱ ላይ በሚደረገው የባለሥልጣናት ዛቻ መፍትሔ እንዳልተገኘ አስታውቀዋል፡፡

ኦርቶዶክሳዊ ሥርዐተ እምነትን በማንአለብኝነት ለይቶ የመጋፋት አካሔዱ፣ አኹን በደረሰበት ደረጃ አሳሳቢ የሃይማኖታዊ ነፃነት መረገጥ እንጂ የመብል ጉዳይና የአንድ ዩኒቨርስቲ ችግር ብቻ ተደርጎ ሊወሰድ እንደማይገባ ተማሪዎቹ አሳስበው፣ ጉዳዩን የቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳ አድርጎ በመወያየት ሃይማኖታዊ መብታቸውን የሚያስከብር አቋም እንዲወስድ በአጽንዖት ጠይቀዋል፡፡

ኢትዮ – ምኅዳር የዜና ጥቆማው ለዝግጅት ክፍሉ በደረሰበት እሑድ ማምሻውን በስልክ ያነጋገራቸው የጅማ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ዲን አቶ እውነቱ ኃይሉ፣ በጉዳዩ ላይ ዩኒቨርስቲውን ወክለው መልስ ለመስጠት እንደማይችሉ ቢገልጹም ‹‹ወደ ኋላ ደውሉልኝ፤ አኹን ስብሰባ ላይ ነኝ፤›› በማለታቸውና የኅትመት ሰዓታችን በመድረሱ አስተያየታቸውን ለማካተት አልቻልንም፡፡
*******************************************************
* የትምህርት ሚኒስቴር ለትምህርት ተቋማት ባወጣው ‹‹የአምልኮ፣ የአለባበስና የአመጋገብ መመሪያ›› እንደሚገልጸው፣ የመመሪያው ዓላማ፡-

የትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደት የሚከናወንባቸው ማድረግ፤
የትምህርት ተቋማት ወጣቱ ዕውቀት የሚገበይባቸውና በማንኛውንም ኹኔታ አድልዎ የማይፈጽምባቸው ማእከላት መኾናቸውን ማረጋገጥ፤
በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ የሃይማኖት ነጻነትና እኩልነት በማንኛውም ቦታ መረጋገጥ ያለባቸው በመኾኑ በትምህርት ተቋማት ይህንኑ ሕገ መንግሥታዊ መብት ተግባራዊ ማድረግ፤
በትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ መሠረት ትምህርት ከማናቸውም ወገንተኝነት ነፃና ሴኩላር መኾኑን ማረጋገጥ ነው፡፡
በመመሪያው ክፍል ሦስት የተፈጻሚነት ወሰን ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች አንቀጽ ፲ እንደሰፈረው፥ መመሪያው ሃይማኖትን ለማስፋፋት ባልተቋቋሙ በኹሉም የአገሪቱ ተቋማት ተፈጻሚነት ይኾናሉ፤ በመመሪያው የተጠቀሱ ድንጋጌዎች በትምህርት ተቋማት መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ላይም ተፈጻሚነት አላቸው፡፡ በክልሎች የትምህርት ተቋማት ከመመሪያው ጋራ የማይቃረን የአፈጻጸም መመሪያ ማዘጋጀት የሚችሉ ሲኾን በመመሪያው የተገለጹ ድንጋጌዎችን በማንኛውም ኹኔታ የሚጥሱና እንዲጣስ የሚያደርጉ ተማሪ፣ መምህር፣ ሠራተኛና አመራር በዲስፕሊን ተጠያቂ ይኾናሉ፡፡

** በመመሪያው አንቀጽ ፰ አራት ንኡሳን አንቀጾች ስለ አመጋገብ እንደተዘረዘረው፡-

ተማሪዎች በግላቸው የመረጡትን የምግብ ዐይነት መመገብ የሚችሉ ቢኾንም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወይም በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ከሃይማኖት ጋራ የተያያዘ የተለየ የምግብ አዳራሽ/ቦታ/ አይዘጋጅም፡፡
በትምህርት ተቋማት ለተማሪዎች የሚዘጋጁ የጾምም ይኹን የፍሥክ ምግቦች ሃይማኖትን መሠረት አድርገው ሊዘጋጁ ይችላሉ፡፡
በአጽዋማት ወቅት ኾነ በበዓላት ቀናት ለልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ማክበርያ በሚል ለተማሪ የተዘጋጀነው ምግብ ከመመገቢያ አዳራሽ ውጭ ይዞ መውጣት አይቻልም፡፡
በምግብ አዳራሽ በመመገቢያ ሰዓት በግል የኅሊና ጸሎት ማድረግ የሚቻል ሲኾን በቡድን(ከአንድ በላይ) በመሰብሰብ በጋራ መጸለይ አይቻልም፡፡
* * *

*** የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በሚያዝያ ወር ፳፻፮ ዓ.ም. ‹‹አክራሪዎች/ጽንፈኞች በተሳሳተ መንገድ ሃይማኖታዊ ይኹንታን ለማግኘት በሕዝባችን ውስጥ የሚያነሷቸው የማደናገርያ መልእክቶችና ማብራሪያዎቻቸው›› በሚል ርእስ ለብዙኃን መገናኛዎች ሥልጠና የሰጠበት ሰነድ አዘጋጅቷል፡፡ በትምህርት ተቋማት እንዲተገበር የወጣው የአምልኮ፣ የአለባበስና የአመጋገብ መመሪያ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲከናወንና ተቋማቱ የልህቀትና ምርምር ማዕከል እንዲኾኑ ታስቦ የተሠራ ሥራ መኾኑን የሚያትተው ሰነዱ፣ ከአመጋገብ አንጻር ማንኛውም ተማሪ የሌላውን መብት እስካልተጋፋ ድረስ በግሉ ጸልዮ ከመመገብ እንዳልተከለከለ ገልጾ፣ ‹‹እንዲያውም ከዚኽ አንጻር አቅም በፈቀደ መጠን መንግሥት ለሙስሊሙ ኾነ ለክርስቲያን ተማሪዎች በተለየ ምግብ እንዲዘጋጅ ፈቅዷል፤›› ይላል፡፡ ይህም፣ በሰነዱ እንደሰፈረው፣ መንግሥት ‹‹የእምነት ነፃነትን ለማክበር የሔደበት ርቀት ምን ያኽል እንደኾነ የሚያሳይ ነው፡፡››

ሚኒስቴሩ ‹‹አክራሪውና ጽንፈኛው›› በማለት የሚጠራው ኃይል፣ መመሪያው ‹የትምህርት ተቋሙን ማኅበረሰብና ተማሪዎች የሃይማኖትና የእምነት ነፃነት የሚጋፋ ነው› የሚል ‹‹ማደናገርያ›› በማሰራጨት ለርካሽ ጥቅምና ፍጆታ ሲጠቀምበት እንደሚታይ በመግለጽ የትምህርት ተቋማት ማኅበረሰቡ ‹‹የአክራሪዎችንና ጽንፈኞችን ድብቅ ዓላማ በማክሸፍ ራሱን ከማደናገርያ መልእክቶች መጠበቅ እንዳለበት›› ያሳስባል፡፡ (ገጽ ፳ – ፳፫)

ዳሩ ግን ሚኒስቴሩ፣ ‹‹የእምነት ነፃነትን አይገድብም፤ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ተልእኮን ያስፈጽማል›› በማለት ደጋግሞ የሚናገርለትንና ሌላው በአክራሪነትና ጽንፈኝነት የሚከሥበትን መመሪያ ተግባራዊነት ማስከበር እንዳልቻለ ተሰምቷል፡፡ በጅማ ዩኒቨርስቲ በኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ላይ ስለሚፈጸመው በደል ተመሳሳይ ዘገባ በብዙኃን መገናኛ መውጣቱን ተከትሎ የሚኒስቴሩ ሓላፊዎች (በተለይ በሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሙሉጌታ ውለታው በኩል) ለዩኒቨርስቲው ሓላፊዎች የሰጡት ማሳሰቢያ ሰሚ ጆሮ እንዳላገኘ ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡

* * *

‹‹የፀረ አክራሪነት ትግል የወቅቱ ኹኔታና ቀጣይ አቅጣጫዎች›› በሚል ርእስ በመጋቢት ፳፻፭ ዓ.ም. የወጣ ሌላው ሰነድ፣ የመንግሥት መዋቅር ሴኩላር መንግሥት መኾናችንን ዐውቆ የመንግሥትን መዋቅር ተጠቅሞ የራሱን ሃይማኖት መሠረት ያደረገ አገልግሎት ከመስጠት ሙሉ በሙሉ ያልጸዳ መኾኑንና ለዚኽም ገሃድ የወጡ መገለጫዎች እንዳሉ ያሔሳል፡፡ እንዲያውም ከመዋቅር አካል በርታ ሳይባልና ሽፋን ሳይሰጠው የሚንቀሳቀስ ‹‹አክራሪ ኃይል እንደሌለ›› በግልጽ ይቀበላል፤ በዚኽ ደረጃ በተፈረጀው አመራር ላይም ሚናውን የሚለይበት የማስተካከያ ርምጃ መወሰድ እንዳለበት ያሳስባል፡፡

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በፍረጃው ላይ ተመሥርቶ በግንባሩና በመንግሥት መዋቅር እንዲኹም በሕዝቡ ውስጥ ዘርፈ ብዙ ንቅናቄ በመፍጠር ‹‹አክራሪነት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዐተ ግንባታ ማነቆ እንዳይኾን ማድረግ›› የሚል ዓላማ በመያዝ ከተጣሉት ግቦች ውስጥ፡- ‹‹የአምልኮ፣ የአለባበስና የአመጋገብ መመሪያውን ተግባራዊ በማድረግ የትምህርት ተቋሞቻችን ከሃይማኖት፣ ከባህልና ፖሊቲካ ተጽዕኖ የተላቀቁ መኾናቸውን ማረጋገጥ፤›› የሚለው ይገኝበት ነበር፡፡

በሃይማኖት ነክ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መለየትና መፍትሔ መስጠት፣ የመንግሥት መዋቅርና ሲቪል ሰርቪስ የሴኩላር መንግሥት ሚና እንዲወጣ ማስቻልና መልካም አስተዳደር ማስፈን ለታለሙት ግቦች መሳካት በበጀት ዓመቱ እንዲፈጸሙ የተያዙ ተግባራት ሲኾኑ በተግባራቱ ፈጻሚነት ከተዘረዘሩት ተቋማት መካከል የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርና የትምህርት ሚኒስቴር ይገኙበት ነበር፡፡

በአፈጻጸማቸው ላይ ክትትል እንደሚያደርግ የተገለጸው የበላይ አካል ክንውናቸውን የገመገመበትንና በቀጣይ አቅጣጫ ላይ የተግባባበትን ኹኔታ ለማወቅ ባይቻልም፣ እነ እውነቱ ኃይሉ የኦርቶዶክሳውያንን የሃይማኖት ነፃነት በማንአለብኝነት የሚረግጡበት የጅማ ዩኒቨርስቲ ልዩ ኹኔታ ግን፥ ተርታ የአፈጻጸም ድክመት ብቻ ሳይኾን ውሎ አድሮ የከፋ አደጋ የሚጋብዝና ከዲስፕሊን ርምጃ በላይና ባሻገር መቀጣት የሚያስፈልገው‹ኮር ኃይል› በመዋቅሩ እንደመሸገ ለመረዳት አያዳግትም፡፡

haratewahido

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: