አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ እንቀበለው

a8e3aff93a8996699786a64a6c13a843_L

በአዲስ ዓመት አዲስ መንፈስ ያስፈልጋል፡፡ እንኳን ከዘመን ወደ ዘመን አሸጋገራችሁ ሲባል የመልካም ምኞት መግለጫው ራሱ የመታደስ ስሜት ይፈጥራል፡፡

አሮጌው ዘመን አልፎ አዲሱ ሲተካ ሁሉም ነገራችን አዲስ የመሆንና የመታደስ ስሜት ይፈልጋል፡፡ አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ እንቀበለው ስንል በዓሉ ከሚፈጥረው ድባብ በላይ ዘለቄታዊው ብሔራዊ ጉዳይ ይቅደም ማለታችን ነው፡፡ ሁሌም አዲስ ዓመት አዲስ መንፈስ ይፈልጋልና፡፡ ስለዚህ አዲሱን ዓመት ስንቀበል የሚከተሉትን አምስት ዋና ዋና ነጥቦች ልብ ልንላቸው ይገባል፡፡

1.የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ይታሰብበት

እንደሚታወቀው የአንድን አገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም ሆነ ዲሞክራሲያዊ ጉዞ ከሚፈታተኑ ችግሮች መካከል የመልካም አስተዳደር እጦት አንደኛው ነው፡፡ መልካም አስተዳደር በሌለበት ልማት የለም፣ ዕድገት የለም፣ ዲሞክራሲ የለም፣ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ አይታሰብም፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት ዜጎችን ለመከራና ለስቃይ ከመዳረጉም በላይ የሕግ የበላይነትን ይጋፋል፡፡ በአዲሱ ዓመት የሕዝባችንን ችግሮች ከሚያባብሱት መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው የመልካም አስተዳደር እጦት ይወገድ ዘንድ መንግሥት በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ መሥራት ይኖርበታል፡፡ የመልካም አስተዳደር ዕጦት የሰላም፣ የልማትና የዲሞክራሲ ፀር በመሆኑ በአዲሱ ዓመት ከፍተኛ ትኩረት ማግኘት አለበት፡፡

ሕዝብ በፍትሕ እጦት፣ በአገልግሎት መስተጓጎልና ጨርሶውኑ አለመገኘት፣ በሕገወጥ ተግባራትና በመሳሰሉት ችግሮች ሲሰቃይ ችላ መባል የለበትም፡፡ የሕግ የበላይነትን የሚጋፉና ዜጎችን ለእንግልት የሚዳርጉ አስከፊ ተግባራት መቆም ይኖርባቸዋል፡፡ ግብር ከፋዩ ሕዝብ የአገልጋይነት መንፈስ ባለው ቢሮክራሲ መስተናገድ አለበት፡፡ የሕዝብን ችግር ከመጤፍ ሳይቆጥሩ በሕዝብ ጫንቃ ላይ ሆነው ያሻቸውን መፈጸም የሚፈልጉ ሕገወጦች ሊታረሙ የግድ ይላል፡፡ በአዲሱ ዓመት በአዲስ መንፈስ ሕዝብን ለማገልገል በብቃትና በቁርጠኝነት የሚመራ አሠራር ተግባራዊ መሆን ይኖርበታል፡፡ የሕዝቡን ችግር ተጠግቶ በማየት መፍትሔ መፈለግ የአዲሱ ዓመት ተግባር መሆን አለበት፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት ሙስና ለሚባለው የአገር ፀር ይዳርጋልና ጠንቀቅ ማለት ይበጃል፡፡ የአገርን ገጽታ የሚያበላሸውና የሙስና መፈልፈያ ዋሻ የሆነው የመልካም አስተዳደር እጦት በቁርጠኝነት ይዘመትበት፡፡

2.ኃላፊነትና ተጠያቂነት ይኑር

የአንድ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገለጫ ከሆኑ ዓበይት ነጥቦች መካከል የኃላፊነትና የተጠያቂነት መኖር ወሳኝ ነው፡፡ አንድ አገር በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ለመኖሯ ማረጋገጫ የሆነው ግልጽነት የሚኖረው ኃላፊነትና ተጠያቂነት ሲሰፍን ነው፡፡ ይህ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ሕዝብ ቢበደል፣ ፍትሕ ቢነፈግ፣ ቢዘረፍና የተለያዩ መከራዎች ቢደርሱበት እንባውን የሚያብስለት አይኖርም፡፡ በሕዝብ ላይ የሚቀልዱ ኃይሎች በኃላፊነትና በተጠያቂነት መርህ እስካልታገደቡ ድረስ ስለዲሞክራሲም ሆነ ስለሰብዓዊ መብት መነጋገር አይቻልም፡፡ አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ ለመቀበል ለዚህ መርህ ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡

ራሳቸውን ከሕግ በላይ በማድረግ ሕዝብ ላይ መፈንጨት የሚፈልጉ ኃይሎች ከሕገወጥ ተግባራቸው የሚገቱት ተጠያቂነት ሲኖርባቸው ነው፡፡ ኃላፊነትና ተጠያቂነት በጠፋ ቁጥር ሕገወጦች ሰላማዊ ዜጎችን ያጠቃሉ፡፡ ንብረታቸውን በጠራራ ፀሐይ ይዘርፋሉ፡፡ የአገር ገጽታ ያበላሻሉ፡፡ የተረጋጋን ማኅበረሰብ ይበጠብጣሉ፡፡ ስለዚህ በአዲሱ ዓመት በአዲስ መንፈስ እነዚህን ወገኖች ከድርጊታችሁ ካልተቆጠባችሁ ቦታ የላችሁም ማለት ያስፈልጋል፡፡ ዲሞክራሲ የሚለመልመው፣ ሰብዓዊ መብት የሚከበረውና የሕግ የበላይነት መኖሩ የሚረጋገጠው ኃላፊነትና ተጠያቂነት ሲኖሩ ብቻ ነው፡፡

3.ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነት ይከበር

ዲሞክራሲ የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት የሚንሸራሸሩበት ገበያ ነው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌም ሆነ እሱን መሠረት አድርጎ በተዘጋጀው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነት ዋስትና አግኝቷል፡፡ ማንም ሰብዓዊ ፍጡር በተፈጥሮ የተቀዳጀው ይህ መብት ተከብሮ ዜጎች ለአገራቸው አስተዋጽኦ ያደርጉ ዘንድ መንግሥት እገዛ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ ዜጎች በመረጡት በማንኛውም መንገድ ሐሳባቸውን በነፃነት እንዲገልጹ፣ ከመንግሥት በተጨማሪ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሚመለከታቸው አካላትም ኃላፊነት አለባቸው፡፡

ማንም ሰው በአመለካከቱ ምክንያት ሊገለል ወይም ችግር ሊደርስበት አይገባም፡፡ በአገራችን በጭፍን ተቃዋሚዎችና ደጋፊዎች ምክንያት የዜጎች መብቶች ሲጣሱ ይታያሉ፡፡ ዲሞክራሲ ተኮትኩቶ የሚያድገው የተለያዩ ሐሳቦች ሲንሸራሸሩ መሆኑ እየታወቀ፣ በአመለካከታቸው ምክንያት ብቻ ከግራም ሆነ ከቀኝ በደል የሚደርስባቸው ወገኖች አሉ፡፡ የተለያዩ አማራጭ ሐሳቦች በቀረቡ ቁጥር ተጠቃሚ የሚሆነው ሕዝብ ነው፡፡ አንድን አመለካከት ብቻ ሕዝብ ላይ ለመጫን የሚደረግ ሙከራ መቆም አለበት፡፡ ጽንፍ የረገጡ ሐሳቦች ብቻ እንዲስተናገዱ የሚፈልጉ ወገኖች ሕዝብን ያክብሩ፡፡ የሥልጣን ባለቤት የሆነው ሕዝብ የተለያዩ አመለካከቶች ቀርበውለት የተሻለውን እንዲመርጥ ካስፈለገ፣ በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ላይ መጠንቀቅ አለባቸው፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነት ቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነውና፡፡ በአዲሱ ዓመት በከፍተኛ ትኩረት ይታሰብበት፡፡

4.ለብሔራዊ መግባባት ልዩ ትኩረት ይሰጥ

በአንድ አገር ውስጥ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ብሔራዊ ጉዳይ ነው፡፡ በብሔራዊ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር ደግሞ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ ማንኛውም ፓርቲ በፖለቲካ አቋሙ ሊለያይ ይችላል፡፡ ከሚከተለው ርዕዮተ ዓለም አንፃር የሚያወጣቸው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ጉዳዮች ፖሊሲዎች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን ከፓርቲም ሆነ ከግለሰብ አመለካከትና ፍላጎት በላይ ብሔራዊ ጉዳይ መቅደም አለበት፡፡ በብሔራዊ ጉዳይ መግባባት ሳይኖር ስለአገር ግንባታ መነጋገር አይቻልም፡፡ ጽንፈኝነትና ጥላቻ ባለበት በብሔራዊ ጉዳይ መግባባት ስለማይቻል፣ ከምንም ነገር በላይ ከራስ ጥቅምና ፍላጎት በላይ የአገር ጉዳይ መቅደም አለበት፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የአገር ጉዳይና የፖለቲካ ፓርቲ አጀንዳ እየተቀላቀሉ ፖለቲከኞቻችን ጽንፍ ይይዛሉ፡፡ በብሔራዊ ጉዳይ ላይ መግባባት የሚቻለው አንዱ ለሌላው አክብሮትና ዕውቅና ሲሰጥ መሆኑ እየተዘነጋ፣ በጠላትነት መተያየት የተለመደ ነው፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ተፎካካሪነቱ እንዳለ ሆኖ በሚያግባባው እየተግባቡ፣ በማያግባባው እየተለያዩ በአገር ጉዳይ ላይ መነጋገር አዳጋች ሆኗል፡፡ ለዓመታት የዘለቀው ይህ የተምታታበት ጉዞ በብሔራዊ መግባባት ካልተተካ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ይገታል፡፡ በአዲሱ ዓመት በአዲስ መንፈስ ከዚህ ዓይነቱ አረንቋ ውስጥ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ ከአገር በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ምንም ነገር የለምና፡፡

5.ሕዝብ የፍትሐዊና ነፃ ምርጫ ተጠቃሚ ይሁን

ምርጫ የአንድ አገር ሕዝብ በገዛ ፈቃዱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያስተዳድረውን መንግሥት የሚመርጥበት መብት ነው፡፡ በዚህ መብት በመጠቀም ሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነቱን የሚያሳይ ሲሆን፣ የመንግሥት ሥልጣን የሚይዘው አካል ደግሞ የሕዝብን ሙሉ ፈቃድ ተግባራዊ የሚያደርግበትን መሣሪያ ምርጫ ነው፡፡ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት በሕዝብ ፈቃድ የሚመሠረትበት ነው ሲባል ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ መሆን አለበት፡፡ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ እንዲሆን ደግሞ መንግሥትን ጨምሮ የሚመለከታቸው ሁሉ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ምርጫ በመጣ ቁጥር ከፍጥጫና ከትንቅንቅ በፊት የሕዝቡን ፍላጎት የመረዳት ኃላፊነት የፓርቲዎች ነው፡፡ ፓርቲዎች ኃላፊነት በጎደለው መንገድ ሲንቀሳቀሱ ሁሌም ችግር አለ፡፡

በአገራችን ዘንድሮ ለአምስተኛ ጊዜ የሚካሄደው ብሔራዊ ምርጫ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ማበብ መሠረት ሊጣልበት ይገባል፡፡ እንደካሁን ቀደሞቹ የዘንድሮ ምርጫ ከዲሞክራሲያዊ ሒደትነት እንዳይወጣና የመራጮችን መብት እንዳይጋፋ በመጀመሪያ ደረጃ መንግሥት፣ ከዚያም ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ ያስፈልጋል፡፡ ምርጫ የዲሞክራሲ መገለጫ አንዱ ምልክት መሆን አለበት ሲባል የይስሙላ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በአዲሱ ዓመት ምርጫ በአዲስ መንፈስ እንዲካሄድ ካሁኑ ሒደቱ ይጀመር፡፡ የሚመለከታቸው ሁሉ በኃላፊነት ስሜት ለተግባራዊነቱ ይረባረቡ፡፡

በአጠቃላይ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የብልፅግናና የደስታ እንዲሆን በአዲስ መንፈስ ስንመኝ፣ በሁሉም ዘርፎች ውጤት እንዲመዘገብ ደግሞ ጥረት ማድረግ አለብን፡፡ ለተግባራዊነቱም አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ የበዓሉ ድባብ እንዳለ ሆኖ ለዘለቄታዊው አገራዊ ጉዳይ እንጠበብ፡፡ አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ እንቀበለው!

 

ሪፖርተር

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: