በአማራ ክልል የመምህራንና ሰራተኞች ፍልሰት ጨምሯል

esat
ጥቅምት ፲፩(አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በክልሉ በሚገኙ የሰሜን ጎንደር ጠረፋማ ወረዳዎች፣ በአዊ፣ በዋግ ህምራ እና በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች የሚገኙ መምህራን ወደ አጎራባች ክልሎች በመፍለሳቸው በትምህርቱ ጥራት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያደረሰ መሆኑን ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡
ክፍተቱን ለመሸፈን አስረኛ ክፍል ያጠናቀቁ እና በልዩ ልዩ ሙያ የተመረቁ ተማሪዎች እንዲቀጥሩ ለአራቱ ዞኖች ደብዳቤ ስለደረሳቸው ይህንኑም እየተፈጸሙ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የሚቀጠሩ አዲስ መምህራን ለ 15 ቀን ስልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ስራ እንደሚሰማሩ የገለጹት ባለሙያዎች የአስረኛ ክፍል ተማሪዎች የተቀጠሩት በወር 774 ብር ደመወዝ ሲሆን ከአካባቢው በረሃነትና የኑሮ ውድነት ጋር በዚህ ደመዎዝ ስራቸውን በአግባቡ ይወጣሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡
በጃናሞራ፣ብየዳና ጠለምት አካባቢ ያሉ የመንግስት ሰራተኞች በከፍተኛ ሁኔታ እየፈለሱ ወደ ትግራይ ክልል እንደሚገቡ የተናገሩት የወረዳ አመራሮች ባለፈው አመት ብቻ ከ650 በላይ መምህራን እንደፈለሱ ተናግረዋል፡፡
መምህራኑ ከሚያገለግሉበት አካባቢ በአስር ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኘው የትግራይ ክልል የገጠር ከተማ የበርሃ አበል፣መኖሪያ ቤትና የመብራት አገልግሎት ተዘጋጅቶ እየተሰጠ የአማራ ክልል መንግስት ይህንን ባለማድረጉ የተነሳ ወደ ትግራይ ክልል በመሄድ የተሻለ ኑሮ ለመኖር እንደሚገደዱ አመራሮቹ ተናግረዋል፡፡ በአንዲት ሃገርና ሰንደቅ አላማ ስር እየኖሩ እንደ ሁለተኛ ዜጋ መቆጠራቸው እንዳሳዘናቸው ተናግረው የክልሉ መንግስት ችግሩን እንዲስተካክል በተደጋጋሚ ለቀረበለት ጥያቄ መፍትሄ እንዳልሰጠበት ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ያሉ ባለሙያዎች ያለባቸውን ተመሳሳይ ችግር የገለጹ ሲሆን በተመሳሳይ መምህራኑ በመልቀቅ ወደ አዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቤቶች በመፍለስ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡የዚህን ምክንያት የሚገልጹት የትምህርት ባለሙያዎች በኦሮሚያ ክልል የሚሰጠው የመኖሪያ ቤት እና ልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅም ለፍልሰቱ አብይ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባሳለፍነው አመት በደዋጨፋ ወረዳ ብቻ 154 መምህራን የለቀቁ ሲሆን በምትካቸው 35 በዲፐሎማ፣18 በዲግሪ መርሃ ግብር በአካውንቲንግ ና አፕላይድ ሳይንስ የተመረቁ አዲስ ምሩቃን በዲፐሎማ ደመወዝ መቀጠራቸውን ተናግረዋል፡፡የተቀጠሩት መምህራን ምንም አይነት የመማር ማስተማር ትምህርት ኮርስ ያልወሰዱ በመሆናቸው ስራቸውን በአግባቡ ይሰራሉ ተብሎ እንደማይጠበቅ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡ ከነዚህም ውጭ 70 አስረኛ ክፍልን የጠናቀቁ ተማሪዎች ቦታውን ሸፍንው ሲሰሩ መቆየታቸው ታውቋል፡፡
ዲግሪ ይዘው በዲፐሎማ ደመወዝ የተቀጠሩት ስራ በማጣታቸው እንጅ አማራጭ ቢያገኙ ጥለው እንደሚሄዱ ጥርጥር የለውም የሚሉት ባለሙያዎቹ በዚህ አይነት ሂደት የትምህርቱ ጥራት እየወደቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከአጎራባች ክልል ሃላፊዎች ጋር በፍልሰቱ ዙሪያ ኮምቦልቻ ላይ በተካሄደው የሁለትዮሽ ስብሰባ ላይ ቢነጋገርም፣ የኦሮሚያ ክልል አመራሮች ግን ‘ማንኛውም ዜጋ በፈለገበትና በተመቸው አካባቢ ተዘዋውሮ መስራት ስለሚችል ዛሬም ነገም ቢመጡ እቀበላለሁ፡፡እናንተ ጉድለታችሁን በማስተካከል ሰራተኞችን በአግባቡ መያዝ ከናንተ ይጠበቃል’ በማለት እንደመለሱላቸው በስብሰባው ተካፋይ የነበሩት ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ለሚታየው የትምህርት ጥራት ከጊዜ ወደ ጊዜ መውደቅ እንደ መፍትሄ ያቀረቡት በተደጋጋሚ በመምህራንና ሰራተኞች የተጠየቀውን የአጎራባች ክልል ተሞክሮ በመውሰድ የተሻለ ክፍያና ጥቅማ ጥቅም ለሰራተኞች ሊከበር ይገባል በማለት ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: