በአራዳ ጊዮርጊስ የኃይሌ ኣብርሃ አስተዳደር ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ልዩነት የታየበት ሕንጻ ግንባታ አግባብነት እንደሌለው ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አረጋገጠ

171-mi-birr-st-george-church-bld-complex* ብክነቱን በአውራነት በማጋለጣቸው የታገዱት ተቆጣጣሪ የከፈሉትን መሥዋዕትነት አድንቋል
*የብር 110 ሚሊዮን ጭማሪ ሲደረግ ሀገረ ስብከቱ አያውቀውም፤ ሊቀ ጳጳሱም አልፈቀዱትም
*የብር 103 ሚ. ጠቅላላ በጀት በሚመደብበት ተቋም በብር 110 ሚ. አለመወሰኑ አነጋጋሪ ነው
*ግለሰቦችን በመጥቀም ራሱን ያበለጸገው አለቃው፣ አድባራትን ባለዕዳ በማድረግ ይታወቃል
* * *

*የደብሩ ዋና ጸሐፊ በሀገረ ስብከቱ በዋና ሥራ አስኪያጅነት ሲሾሙ ከጸሐፊነታቸው አልተነሡም
*ጭማሪውን በማጸደቅ ለመሸፋፈን መሞከራቸው ሹመቱ ለተጠያቂነት ማስቸገሩን አመላክቷል
*ሀ/ስብከቱም የጭማሪው አግባብነት በባለሟያ ተጠንቶ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ እንዲቀርብ ወስኗል
*ለዓመታዊ ሒሳብ ምርመራ በደብሩ የተመደበው ልኡክ እና ሪፖርቱ ጥብቅ ክትትል ይደረግበት!
* * *

*የደብሩ አስተዳደር ከመዋቅራዊ አሠራር ውጭ የሌሎችን የሥራ ሓላፊነት በመጣስ ያልተገባ አመራር ይሰጣል፤ ተገቢው የደረሰኝ ማስረጃ ያልቀረበባቸው፣ የቁጥጥር ክፍሉ ያላመነባቸውና ያልፈረመባቸው ወጭዎች በሕገ ወጥ መንገድ በመደበኛ ወጭ እንዲወራረዱ ያዝዛል፤ ያወራርዳል፤ ያለምንም መመዘኛ እና ውድድር የተቆጣጣሪ መሐንዲስ ቅጥር ፈጽሟል፤ በግንባታ ላይ ለሚገኝ ሕንጻ የማሻሻያ ጥናት በሚል እንዲኹም ለተጨማሪ ሕንጻ ሥራ የጨረታ ሕግን በመጣስ በተጋነነ ዋጋ ውሎች በመፈጸም የደብሩን ገንዘብ አላግባብ አባክኗል፤ ላልተገባ ከፍተኛ የብድር ዕዳም ተዳርጓል፤ ለልማት መዋል የሚገባውን የደብሩን ገንዘብ በብድር ሰጥቷል፤ በአጠቃላይ በደብሩ ተቋማዊ ሳይኾን ግለሰባዊ አሠራር እየተስፋፋ ስለኾነ ችግሩ ተባብሶ ወደ ከፋ ደረጃ ከመድረሱ በፊት አፋጣኝ መፍትሔ ይሰጠው፡፡
/ዋና ተቆጣጣሪው በጥር ፳፻፯ ዓ.ም. ለሚመለከታቸው አካላት በጽሑፍ ከሰጡት ጥቆማ/

*… አቶ እየተባሉ በሚዲያ ይቀርቡ የነበሩት የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ ከቀድሞው ፓትርያርክ ኅልፈት ሦስት ወራት በኋላ በኋላ የብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ዋና ጸሐፊ ተደርገው እንደ አዲስ ተቀጥረዋል፤ በመቀጠልም ወደ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዋና ጸሐፊነት ተዘዋውረዋል፡፡ የመንግሥት ሹመኛ እና ምስጢረኛ ነኝ የሚሉት የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ ሊቀ ማእምራን በሚል የሊቃውንቱ ማዕርግ በሀገረ ስብከቱ በዋና ሥራ አስኪያጅነት ሲመደቡ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና ጸሐፊ የሚኾን ሠራተኛ የሌላት ይመስል በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት አዛዥ – በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ታዛዥ ኾነው ኹለት ቦታ ደመወዝ እንዲከፈላቸው ተደርገው ተሹመዋል፡፡… ጣራ የተመታ ሕንጻ መሠረቱ እንዳልተቀመጠ በማድረግ ከሀገረ ስብከቱ ዕውቅና እና ፈቃድ ውጭ አልተሠራም ለማለት ከኦዲት በፊት ለማጸደቅ አቅርበው ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ እና የፓትርያርኩ እንደራሴ ነኝ፤ በእጄ ናቸው ባዩ አለቃ በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሕንጻ ገንብተናል፤ ልማት አልምተናል ይበሉ እንጂ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ በቀጣይ የተጣለው ዕዳ የፎቁን ቁመት ያኽል ደብሩን ወደ መሬት የቀበረ ነው!!!፡፡
/ጥቅመኝነት እና ጎጠኝነት በመላው የዝውውር አሠራራቸው የተመረሩ ሠራተኞች/

*ኮንትራክተሩ ከደብሩ ለተከራዩት መጋዘን ለአንድ ዓመት ምንም ዐይነት ክፍያ ሳይፈጽሙ መቆየታቸው በደብሩ እና በኮንትራክቱ መካከል የኾነ ስምምነት የነበረ መኾኑን የሚያመላክት በመኾኑ አግባብነት የለውም፡፡ በሕጋዊ መንገድ በጨረታ ሌላ ተቆጣጣሪ መሐንዲስ እንዲቀጠር ከማድረግ ይልቅ በደብሩ ዋና ጸሐፊ ጠቋሚነት ሌላ መሐንዲስ እንዲቀጠሩ ተደርጓል፡፡… በደብሩ በመሠራት ላይ ያለው አዲሱ የሕንጻ ማስፋፊያ ሥራ በአዲሱ ጥናት እና በአዲሱ ተቆጣጣሪ መሐንዲስ መሪነት ከሀገረ ስብከቱ ዕውቅና እና ፈቃድ ውጭ እየተካሔደ ይገኛል፡፡ የሕንጻ ሥራ ማሻሻያው ከብር 61 ሚሊዮን ወደ ብር 171 ሚሊዮን አድጎ እንዲከናወን ሲደረግ በቃለ ዐዋዲው አንቀጽ ፲፪ ቁጥር ፰ መሠረት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ እንዲያውቁትና እንዲፈቅዱት ማድረግ ሲገባ ይህ ሳይደረግ ወደ ሥራ መገባቱ አግባብነት የለውም፡፡
/የመሬት፣ የሕንጻ እና የልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ ተቋማት ኪራይ ተመን ጥናታዊ ሪፖርት/

*በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቁጥጥር ሓላፊነት ሲሠሩ የነበሩት እና በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል በሒሳብ ሹምነት ሲያገለግሉ የነበሩት ሠራተኛ፣ ጥናቱ በተካሔደበት ወቅት ግንባር ቀደም ተሰላፊ እና በሰነድ በተደገፈ አግባብ በደብሩ የሚታዩ የአሠራር ችግሮችን በማጋለጥ መሥዋዕትነት የከፈሉ ከመኾናቸውም በላይ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ ለሚመለከታቸው አካላት ኹሉ አስፈላጊውን መረጃ አቅርበዋል፤ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ፊት ለፊት የተጋፈጡ ቢኾንም ያለሥራ እንዲቀሩ እና ካሉበት ደብር እንዲዘዋወሩ ተደርጓል፡፡ ይህ ኹኔታ የማጣራት ሥራውን ተአማኒነት እና የበላይ አካልን ውሳኔ ሰጪነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ከመኾኑም በላይ ተጨማሪ የማጣራት ሥራ ቢያስፈልግ እንኳ ጉዳዩን የበለጠ ሊያብራራ እና በሰነድ በተደገፈ መልኩ ሊያቀርብ የሚችል ሰው እንዳይኖር ያደርጋል፤ በአጥቢያ የሚታዩ የአሠራር ችግሮችን በፊት ለፊት ማቅረብ እንደ ወንጀል እንዲታይ በማድረግ ችግሮችን ለማጋለጥ የሚንቀሳቀሱ ወገኖችን ቅስም የሚሰብር ስለኾነ ኹለቱ ባለሞያዎች ቀድሞ ወደነበሩበት ቦታና የሥራ ሓላፊነታቸው እንዲመለሱ ሲል የአስተዳደር ጉባኤው በአንድ ድምፅ ወስኗል፡፡
/የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ በጥናታዊ ሪፖርቱ ላይ ካሳለፈው ውሳኔ/

(ሰንደቅ፤ ፲ኛ ዓመት ቁጥር ፭፻፲፰፤ ረቡዕ ነሐሴ ፮ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር በማሠራት ላይ ለሚገኘው ባለአራት ፎቆ የንግድ ማእከል ሕንፃ፣ የዲዛይን ክለሳ በሚል በአስተዳደሩ የተደረገው የ110 ሚሊዮን ብር ጭማሪ ሀገረ ስብከቱ የማያውቀው እና ሊቀ ጳጳሱ ያልፈቀዱበት በመኾኑ አግባብነት እንደሌለው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አረጋገጠ፡፡

ግንባታው ከሀገረ ስብከቱ ዕውቅ እና ፈቃድ ውጭ እየተካሔደ እንደሚገኝ በጥናት ያረጋገጠው የአስተዳደር ጉባኤው፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ንብረቶች አላግባብ ሀብት ያፈሩ የአድባራት ሓላፊዎች ጉዳያቸው በሕግ አግባብ እየታየ ክሥ እንዲመሠረትባቸውም ወስኗል፡፡

ደብሩ ‹‹ዳዊት ወንድሙ›› በተባለ የሥራ ተቋራጭ በሚያሠራው ኹለ ገብ የንግድ ማእከል፣ ‹‹በቀድሞው ዲዛይን ያልተካተቱ እንደ አሳንሰርና የኤሌክትሪክ ሥራዎችን በማሻሻል ሕንፃውን ተመራጭ ለማድረግ›› በሚል ክለሳ አድርጓል፡፡ ይኹንና የግንባታ ወጪው በተያዘለት የብር 61,234,885.02 ውል እንደሚሠራና የማሻሻያ ጥናቱ ሲጠናቀቅም ለሀገረ ስብከቱ በማሳወቅ፣ ሲፈቀድ ወደ ተግባር እንደሚገባ ተገልጾ እንደነበር በጠቅላይ ጽ/ቤቱ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ለአስተዳደር ጉባኤው ባቀረበው ጥናታዊ ሪፖርቱ አስታውሷል፡፡

specification-and-bill-of-quantities00

‹‹የዲዛይን ክለሳና ተያያዥ ሰነዶች ፍተሻ›› በሚል በተካሔደው ጥናት ወጪው ከብር 61 ሚሊዮን ወደ ብር 171 ሚሊዮን መናሩንና ውሉም መቀየሩን የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ የሕንፃ ሥራው በማሻሻያ ጥናቱ በአዲስ ተቆጣጣሪ መሐንዲስ መሪነት ከሀገረ ስብከቱ ዕውቅና እና ፈቃድ ውጭ እየተካሔደ እንደሚገኝ ገልጧል፡፡ በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ አንቀጽ ፲፪ ቁጥር ፰ መሠረት፣ ዝርዝር ጥናቱን የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ እንዲያውቁት እና እንዲፈቅዱት ማድረግ ሲገባ፣ ይህ ሳይፈጸም ወደ ሥራ መገባቱ አግባብነት እንደሌለው ሪፖርቱ አረጋግጧል፡፡

ቀደም ሲል በሕጋዊ መንገድ የተቀጠሩት ተቆጣጣሪ መሐንዲስ በሥራ አፈጻጸም ጥራት መጓደል የተነሣ ድክመታቸው በቴክኒክ ኮሚቴ ተረጋግጦ እንዲሰናበቱ መደረጉን ሪፖርቱ አስታውሶ፣ በአዲሱ ጥናት የሕንፃ ሥራውን በመምራት ላይ የሚገኙት ተቆጣጣሪ መሐንዲስ በዋና ጸሐፊው ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ጠቋሚነት ከሕግ ውጭ ያለጨረታ መቀጠራቸውን አስፍሯል፡፡ ተቆጣጣሪው በብቃት አሠርተዋቸዋል የተባሉ ካቴድራሎች እና ሕንፃዎች እንዲኹም የደመወዝ ቅናሽ ለቅጥሩ አግባብነት በምክንያትነት ቢጠቀሱም ‹‹የሕጋዊ አሠራር አመላካቾች ባለመኾናቸው ተቀባይነት የላቸውም፤›› ብሏል፡፡

specification-and-bill-of-quantities01በደብሩ 49 ሕንፃዎች እና ኹለት ቦታዎች ተከራይተው እንደሚገኙ የዘረዘረው ሪፖርቱ፣ ደብሩ የሚያስገነባውን ሕንፃ የሚሠሩት ኢንጅነር ዳዊት ወንድሙ ለመጋዘን ለተከራዩት የደብሩ ቦታ ለአንድ ዓመት ምንም ዐይነት ክፍያ ሳይፈጽሙ መቆየታቸውን ጠቅሷል፡፡ ኮንትራክተሩ ክፍያውን ባይፈጽሙም በዝምታ እንደታለፉ በአጣሪ ኮሚቴው ተረጋግጦ ሕጋዊ አለመኾኑ በተገለጸ ማግስት ብር 400,000 ገቢ ማድረጋቸው፣ ‹‹በደብሩና በኮንትራክተሩ መካከል የኾነ ስምምነት የነበረ መኾኑን የሚያመላክት በመኾኑ አግባብነት የለውም›› ብሏል፡፡

ሕንፃው የብር 110 ሚሊዮን የግንባታ ወጪ በታየበት ልዩነት የኮንትራት ውል ተፈጽሞ ወደ ሥራ ከመገባቱ በፊት የቁጥጥር ሓላፊው፣ የደብሩ ገንዘብ የጨረታ ሕግን በመጣስ በተጋነነ ዋጋ በሚፈጸሙ የሥራ ውሎች አላግባብ እየባከነ እንዳለ በማስረጃ በማጋለጣቸውና በማጣራቱም ወቅት ግንባር ቀደም ተሰላፊ በመኾናቸው በእነኃይሌ ኣብርሃ እና የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ አስተዳደር ታግደው ላለፉት ስድስት ወራት ያለሥራ እና ያለደመወዝ ቆይተዋል፡፡

የቁጥጥር ሓላፊው፣ የአሠራር ችግሮችን በሰነድ አስደግፈው በማጋለጥ እና ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ ለሚመለከታቸው አካላት በማሳወቅ ፊት ለፊት የተጋፈጡና መሥዋዕትነት የከፈሉ መኾናቸውን በአጽንዖት የጠቀሰው የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የአስተዳደር ጉባኤ፣ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ በአንድ ድምፅ ወስኗል፡፡

በጥናታዊ ሪፖርቱ እንደተረጋገጠው፣ ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ ከደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ያለተጠያቂነት ተዛውሮ በአስተዳዳሪነት የተመደበው ቀንደኛው አማሳኝ መልአከ መንክራት ኃይሌ ኣብርሃ፣ ከሰበካ ጉባኤያት የወሳኝነት ሥልጣንና ከሀገረ ስብከቱ ዕውቅና ውጭ ለግለሰቦች ጥቅም በሚያደሉ የግንባታ እና የኪራይ ውሎች ራሱን አበልጽጓል፤ አድባራቱንም የበርካታ ሚሊዮን ባለዕዳ አድርጓቸዋል፡፡

‹‹ሀገረ ስብከቱ ምን አገባው›› በማለት የሚታወቀው የኃይሌ ኣብርሃ አስተዳደር፣ የብር 171 ሚሊዮኑን ሕገ ወጥ የኮንትራት ውል ለተፈራረመው ተቋራጭ፣ ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ ይጨርሳል የተባለ ተጨማሪ ባለኹለት ፎቅ ሕንጻ ያለጨረታ እንደሰጠውም ታውቋል፡፡ ከባለአራት ፎቅ የንግድ ማእከሉ ጋር ተያያዥ የኾነ ሌላ ሕንጻ በብር 11 ሚሊዮን እንገነባለን በሚል ካመጣቸው ግለሰቦችም ጋር መዋዋሉ ተመልክቷል፡፡ በውሉ፣ ግለሰቦቹ ለሕንጻው ያወጡት ገንዘብ፣ በየወሩ በብር 200,000 እየታሰበ የግንባታ ወጪውን እስኪመልስ ድረስ ደብሩን ጥቅም አልባ እንደሚያደርገው ተገልጧል፡፡

ከአለቃው ኃይሌ ኣብርሃ ጋር በተመሳሳይ ወቅት በደብሩ ዋና ጸሐፊነት የተመደቡት ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ የዋና ጸሐፊነት ሓላፊነታቸውን እንደያዙ ካለፈው የካቲት ወር አጋማሽ ጀምሮ በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅነት በአወዛጋቢ ኹኔታ ተሹመዋል፡፡ አሿሿማቸው ሕገ ወጥ ብቻ ሳይኾን ግራ አጋቢም እንደኾነ የሚገልጹ ወገኖች፣ ዋና ሥራ አስኪያጁ በደብሩ የፈጸሟቸውን ምዝበራዎች ሕጋዊነት ለማላበስ እና ከተጠያቂነት ለማምለጥ እየተጠቁሙበት እንዳሉም ይናገራሉ፡፡

ለዚኽም ከሀገረ ስብከቱ ዕውቅና እና ፈቃድ ውጭ በብር 171 ሚሊዮን የተጋነነ ወጪ በመሠራት ላይ የሚገኘውን ባለአራት ፎቅ ኹለገብ ሕንፃ በአስተዳደር ጉባኤው ለማጸደቅ መሞከራቸውን በአብነት ይጠቅሳሉ፡፡ ጉዳዩ ‹‹ቀደም ሲል ያለጥናት ተሰጥቶ የነበረው የግንባታ ሥራ ውል በባለሞያ ሲፈተሽና ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የብር 92 ሚሊዮን ያመጣ በመኾኑ ጉባኤው ይህንኑ ዐውቆ እንዲያጸድቅና ይኹንታውን እንዲሰጥበት›› በሚል ሰኔ ፳፭ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በምክትል ሥራ አስኪያጁ በተመራ የአስተዳደር ጉባኤው ስብሰባ በአጀንዳነት ቀርቦ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

የአስተዳደር ጉባኤው አባላት በተወዛገቡበት አጀንዳ፣ የሀገረ ስብከቱ ቁጥጥር ዋና ክፍል ሓላፊ ሊቀ ትጉሃን ገብረ መስቀል ድራር ይጸድቅላቸው ሲሉ መሟገታቸው ተሰምቷል፡፡ ጉዳዩ በሞያዊነት ሊታይ እንደሚገባ የተስማሙት የሚበዙት የጉባኤው አባላት፣ ገለልተኛ የግንባታ ባለሞያዎች በይፋዊ ጨረታ ተጋብዘው አጠቃላይ ኹኔታውን በማየትና በመገምገም በማጣራትም ጭምር እንዲያቀርቡና ጥናቱ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በኩል ታይቶ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት መወሰናቸው ታውቋል፡፡haile-and-yemane

ዋና ሥራ አስኪያጁ ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ባላቸው እንደ ደብረ ገሊላ ቅዱስ ዐማኑኤል ካቴድራል፣ ደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል፣ ማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም እና ቦሌ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም አድባራት በዋና ጸሐፊነት ሲሠሩ ልማት ይኹን ተቀማጭ ካፒታል አላስመዘገቡም፡፡ የቦሌ መድኃኔዓለምን ዋና ጸሐፊነት እንደያዙ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ በነበሩበት ወቅት፣ ከፍተኛ ሙስና እና አስተዳደራዊ በደሎች ሲፈጽሙ በመገኘታቸው ከሓላፊነታቸው በአስቸኳይ ተነሥተው በደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን በጸሐፊነት ሥራ ብቻ እንዲሠሩ ተዘዋውረዋል፡፡ ከፍተኛ የወርኅ ገቢ ያለበት ትልቅ ደብር ይሰጠኝ በማለት አኩርፈው ሥራቸውን በፈቃዳቸው ለቅቀው ነበር፡፡

… አቶ እየተባሉ በሚዲያ ይቀርቡ የነበሩት የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ ከቀድሞው ፓትርያርክ ኅልፈት ሦስት ወራት በኋላ በኋላ የብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ዋና ጸሐፊ ተደርገው እንደ አዲስ ተቀጥረዋል፤ በመቀጠልም ወደ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዋና ጸሐፊነት ተዘዋውረዋል፡፡ የመንግሥት ሹመኛ እና ምስጢረኛ ነኝ የሚሉት የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ሊቀ ማእምራን በሚል የሊቃውንቱ ማዕርግ በሀገረ ስብከቱ በዋና ሥራ አስኪያጅነት ሲመደቡ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና ጸሐፊ የሚኾን ሠራተኛ የሌላት ይመስል በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት አዛዥ – በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ታዛዥ ኾነው ኹለት ቦታ ደመወዝ እንዲከፈላቸው ተደርገው ተሹመዋል፡፡

… ጣራ የተመታ ሕንጻ መሠረቱ እንዳልተቀመጠ በማድረግ ከሀገረ ስብከቱ ዕውቅና እና ፈቃድ ውጭ አልተሠራም ለማለት ከኦዲት በፊት ለማጸደቅ አቅርበው ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ እና የፓትርያርኩ እንደራሴ ነኝ፤ በእጄ ናቸው ባዩ አለቃ በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሕንጻ ገንብተናል፤ ልማት አልምተናል ይበሉ እንጂ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ በቀጣይ የተጣለው ዕዳ የፎቁን ቁመት ያኽል ደብሩን ወደ መሬት የቀበረ ነው፡፡

በዘንድሮው[በ፳፻፯] የበጀት ዓመት የደብሩን ሒሳብ የሚመረምረው ማን ይኾን? ለዚኽም ነው የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የደብሩን ዋና ጸሐፊነት አለቅም ያሉት፡፡ እግዚአብሔር ያሳያችኹ፡-

*የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና ጸሐፊ – ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ
*የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ – ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ
*የ፳፻፯ በጀት ዓመት የ169 አድባራት ኦዲተሮች መዳቢ – ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ
ታዲያ በዚኽ አሠራር የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር ሒሳብ ተመረመረ ማለት ይቻላልን? በፍጹም አይቻልም!!! የሀገረ ስብከቱ ኦዲተር የሚያየው በሞዴል ፷፬ ገባ በሞዴል ፮ ወጣ፤ ከወጪ ቀሪ ይኼ ነው ማለት ተመረመረ አያሰኝም!!!

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ የአስተዳደር ጉባኤ፣ ባለፈው ረቡዕ ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባው፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እና ከሀገረ ስብከቱ በተውጣጡ የሥራ ሓላፊዎች ላለፉት ስድስት ወራት በተመረጡ 69 አድባራት የመሬት፣ የሕንጻ እና የልዩ ልዩ የገቢ ማስገኛ ተቋማት የኪራይ ተመን ላይ ሲካሔድ የቆየውን ማጣራት ተከትሎ በቀረበለት ጥናታዊ ሪፖርት ላይ ተወያይቷል፡፡

በቤተ ክርስቲያኒቱ ንብረቶች አላግባብ ሀብት ያፈሩና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ለምዝበራ ያጋለጡ የአድባራት ሓላፊዎች፣ ጥፋታቸው እየተመዘነ ጉዳያቸው በሕግ አግባብ እንዲታይና ክሥ እንዲመሠረትባቸውም በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡ አጥኚ ኮሚቴው፣ በየአድባራቱ የታዩ የአሠራር ጥፋቶችን ባጣራበት ወቅት ከ1500 በላይ ውሎችን፣ ቃለ ጉባኤዎችንና ውሳኔዎችን በማሰባሰብ ጥናታዊ ሪፖርቱን ያጠናቀረ ሲኾን በማስረጃነት እንደያዛቸውም ተገልጧል፡፡

የአስተዳደር ጉባኤው ጥናታዊ ሪፖርቱን በሙሉ ድምፅ የተቀበለው ሲኾን ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ ውሳኔ እንዲያገኝም በማግስቱ ኀሙስ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስን መጠየቁንና አዎንታዊ ምላሽ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን የፀረ ሙስና አቋም ተግባራዊ ለማድረግ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል የተባለው ጥናታዊ ሪፖርቱ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ የገቢ ማስገኛ ተቋማት ዙሪያ የሚታዩ የአፈጻጸም ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት በሕግ፣ በሥርዐት እና በመመሪያ ለማስተዳደር የሚያስችሉ የመፍትሔ ሐሳቦች የቀረቡበት መኾኑ ታውቋል፡፡

* * *

በ58 አድባራት ላይ የመሬት፣ የሕንጻ እና የልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ ተቋማት ኪራይ ተመን የተጠናበት እና በጠቅላይ ጽ/ቤቱ አስተዳደር ጉባኤ በሙሉ ድምፅ ተቀባይነት ያገኘው ጥናታዊ ሪፖርት፣ የኃይሌ ኣብርሃ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ አስተዳደር ከፍተኛ የሙስና እና የብልሹ አሠራር ችግሮች ካለባቸው 15 አድባራት አንዱ መኾኑን ያረጋገጠበት ዘገባ ከዚኽ በታች የሚታየው ነው፡፡

st-george-report

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: