ኢትዮጵያ የሁላችንም እንጂ የጥቂቶች ብቻ አይደለችም

IMG_3839ቴዎድሮስ ገዛኸኝ

በሰለጠነው ዓለም ዜጎች የተሰማውን ለመናገር የመንግስትን ፈቃድ አይጠይቁም፡፡ በኢትዮጵያ ግን ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት መንግስት ካልፈቀደ አይቻልም በመፅሔቶች ላይ ፅሁፍ ማውጣት ቢፈቀድም መንግስት የሚቃወም ሆኖ ከተገኘ መፅሄቱ ከማተሚያ ቤት ሳይወጣ ታፍኖ እንዲቀር ይደረጋል፡፡ በዚህም የአሳታሚውንና የአታሚውን ኢኮኖሚውን ኪሳራ ማንም አይክሰውም፡፡ የፅሁፉ ባለቤት ሰብአዊ መብቶች መረገጣቸው ይጀምራል፡፡በመጀመሪያ ደረጃ የወያኔ ደላላዎች እንደጥሩ ነገር አድርገው መሸጥ ያለባቸው ሀስትን፣ ገዳይነትን፣ ሀገር አጥፊነትን፣ መስሪንትን፣ ንፁሀንን ማሰርንና መግደልን፣ ጠባብ ጎጠኝነትን፣ በነፃነት ሀሳበ መግለፅ ማገድን፣ በምርጫ ያሸንፉትን አስሮ ለተሸናፊዎች የምክር ቤት ወንበሮችን በጉልበት መስጠትን፣ ፍትህ ማዛባትን፣ የመሳሰሉ አስክፊ የወያኔን ተግባራትን ነው። በአንፃሩ ደግሞ እኛ የምንጠይቀው የሚደርስብንን በደል ተመልከቱልን፣ በሀገራችን በሰላም የመኖር መብታችንን ተነፍገን ለመስደድ ተገደድን እዛው ያሉት ደግሞ ያለፍርድ መታሰርና መገደል ሆነ። አንድ ሰው የሚመስለውን ሀሳብ በፈለገው መንገድ መግለፅ መንግስትን የመተቸት በራስ ፈቃድ የመናገረ እና ያለመናገር በዓልንና ሀይማኖትን መከተልና ማስፋፋት እንዲሁም ህግ ለሁሉም የሚሰራስ ለመሆኑ መረጋገጥ እና የመሳሰሉት ሁሉ ተግባራዊ የሚሆነው ተአቅቦ ያልተደረገበት የመናገር የመረጃ መብት ልውውጥ ተግባራዊ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ሰው በመናገሩና በመፃፉ ብቻ ለእስር እና ለስደት የሚዳረግበት ሀገር በዋነኝነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷናት

ወያኔዎች፣ የአገራችንን ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ ዘርፈው ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ እንዲሁ የሕዝባችንን ሕልውና ተቆጣጥረውታል። ኑሮውን፣ ውሎውን አዳሩን ሙሉ በሙሉ አንቀው ይዘውታል። ድምጽ እንዳያሰማ ጎሮሮውን አንቀውታል። እንዳይሰማ ጆሮውን ድፍነውበታል። አንድ ሰሞን ሬዲዮአቸውን የሚያዳምጥ አልነበረም። በኢትዮጵያ ውስጥ ነጻ ሬዲዮ ድሮም አልተፈጠርም ! ነጻ ቴሌቪዢንማ ከቶ ማን አስቦት! ነጻ ጋዜጣን ድራሹን አጥፍተውታል! የተመጣጠነ ዕውነተኛ መረጃ ከውጭ ለሕዝባችን እንዳይደርሰው፣ ቪኦኤ (የአሜሪካን ድምጽ ሬዲዮ) ዛሬ የለ! ጀርመን ድምጽ ዛሬ የለ! ኢሳት ቴሌቪዥንማ፣ ሳተላየት እንዴት ማፈን እንደሚቻል የአፋኝ ተክኖሎጂ መለማመጃ ሁኗል። “የቻይናን” የፍቅር ዕድሜ ያሳጥርልንና በአጭሩ ተሰምቶ በማይታወቅ ቴክኖሎጂ ከአየር ላይ ቀልበውታል። ይኸ ማለት ሕዝባችን መጮህ ቀርቶ ከውጭ የምንጮለትን እንኳን እንዳይሰማ ምንም ዓይነት መረጃ እንዳይደርሰው ቀፍድደው ይዘውታል። እንዳይዘዋውር፣ እግሮችን ጠፍረው አስረውታል። በአገሩ እንደድሮው ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ አርሶ አምርቶ፣ ነግዶ አትርፎ እንዳይበላ ከልክለውታል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን ሁኔታ ለመለወጥና በምትኩም ሁገራዊ አንድነቱን ጠብቆ በፍትሕ በዲሞክራሲና እኩልነት ተቃቅፎና ተፋቅሮ ለመኖር ትግል እያደረገ መሆኑም አይታበልም።ለዚሁ የተቀደሰ ዓላማ ህይወታቸውን የሰጡ፤ አካላቸው የጎደለባቸው፤ የታሰሩ፤ የተገረፉና ፤የተሠቃዩ፤ የተሰደዱ አሁንም በትግል ላይ የሚገኙ ጀግኖች መኖራቸውም የማይካድ ሐቅ ነው። ያሁን እንጂ እስከዛሬ ድረስ የሕዝቡ ትግልና ዓመፅ የተፈለገውን ያህል ውጤት ሊያስመዘግብ አልቻለም። የትግላችን ድክመት በዝርዝርና በጥልቀት መጠናት ያለበት ቢሆንም አሁን ለሁሉም ግልፅ ሆኖ የሚታየው ግን ታጋዩ ሀይል ለሁኔታው የሚስማማ የጋራ የትግል ዓላማና ስትራተጂ በማውጣት በጋራ የተቀናጀ ትግል ለማካሄድ አለመቻሉ ነው።

ትግሉ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ባሉ የተቀዋሚ ፖለቲካ ሀይሎች የሚመራ ሲሆን የሀገር ውስጥ ሀይሎች የሚደርስባቸውን ወከባ እንግልትና እስር ተቋቁመው መራር ትግል ሲያደርጉ በሌላ በኩል በውጭ የሚገኙት ሀይሎች የወያኔን አምባገነን ስርዓት ለመጣል ከሚያደርጉት የትግል ስልቶች አንዱ የወያኔን ስርጫት ኢ-ሰባዓዊነት እና ስርዓቱ ህዝቡ ላይ የሚፈፅመውን በደል ለውጪው ዓለም በማሳወቅ ዲፕሎማሳዊ ጫና ከመፍጠር ባለፈ የትጥቅ ትግልን እንደ አማራጭ በመጠቀም እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ የሚታወቅ ነው፡፡

ይህንን ትግል ለማኮላሸት ወያኔ በሀገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ሆነ የሲቪክ ማህበር አባላትን አንዴ ስልጣንን በሃይል ለመናድ በሻብያ ተላላኪነት ፣ በሌላ ጊዜ በአሸባሪነት በመክሰስ በየጊዜው ወደ እስር ቤት የሚወረውራቸው ዜጎች ቁጥር በእጅጉ አሻቅቧል፡፡

የደርግ አምባገነናዊ ስርዓት ወጣቶችን በጅምላ በማሰርና በማሰቃየት የታወቀ ቢሆንም በዚህ ስልቱ ስልጣኑን ማቆየት ግን አልቻለም፡፡ የደርግ የጅምላ እስር ሌሎች ወጣቶችም በደርግ ላይ ልባቸው እንዲሸፍት አደረገው እንጂ በስልጣን ለመቆየት መፍትሄ ሊሆነው እንዳልቻለ ታይቷል፡፡ ደርግ ተሸንፎ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን በመጣበት ወቅት ዲሞክራሲ በአለም አቀፍ ደረጃ ከመተግበሩም ጋር ተያይዞ ኢትዮጰያውያን በግፍ መታሰር ይቆማል የሚል ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡ ሆኖም ግን ኢህአዴግ የደርግ የጅምላ እስራት እያወገዘም ቢሆን ስልጣኑን ማስጠበቅ የወሰነው ልክ እንደ ደርግ ተቀናቃኞቹን በማሰርና በመግደል ሆኖት አረፈ፡፡

በዲሞክራሲ በበለፀገው ዓለም የአገር መሪዎች በሚፈጽሙት ያመራር ድክመት ብቻ ሳይሆን በግል ሒይወታቸው ውሰጥ አንኳ በሚያሳዩት የሥነምግባር ብልሹነት ጭምር እየተብጠለጠሉ በአደባባይ በዜና ማሠራጫዎች ይቅርታ እስኪጠይቁ ድረስ በቅሌት ስለሚከሰሱ ለአገራቸው ጥሩ ሥራ ለመሥራትና ጥሩ ሥነምግባር ለማሳየት እኔ እበልጥ አኔ አበልጥ በሚሌ የሚፈጽሙት ፉክክር ለድርጅታቸው ጥራትና ለአገራቸው ዲሞክራሲያዊ ግንባታ ተጨማሪ አስተዋፅዖ አደረገላቸው እንጂ አልጎዳቸውም፤ ስለሆነም ለድርጅታቸውና ለአገራቸው አንድነትና የጋራ ጥቅም የሚሰጧቸውን ቅድሚያ ይመለከቷል።

እንዲመሩንም ኃላፊነት የጣልንባቸው ዕጩ መሪዎቻችን የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄዎች አዳምጠው ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት ፋንታ የሚወክለትን ሕዝብ በመናቅ ወይም እንደደንቆሮ ቆጥረው ራሳቸውን ፍጹም በማድረግ እኛ እናውቅላችኃለን፤ እኛ አናቅድላችኃለን በማለት ገና በድርጅት ሥራ ተሞክሯቸው የራሳቸውን ድርጅት እንኳን በሥርዓት በመምራት ከአቻ ድርጅቶች ጋር የሰመረ ግንኙነት ማድረግ አቅቷቸው ጠዋት የገነቡትን ማታ አፍርሰውት የሰበሰቡትን በትነው ያድራሉ። ይህ የሚከሰተው በዓላማ ፅናት ማነስ፣ ለድርጅት ዓላማ ራስን አለማዝገዛት፣ ከባልደረቦቻቸው ጋር መቻቻልን ባለመተግበር፣ እንዱሁም የማያስፈልግ ግትርነትን በመከተል በአጠቃላይ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ራሳቸውን ባለማስገዛት የተፈጠረ ችግር ነው። ስለዚህ እነዚህን ክስተቶች በግልባጭ ስናስቀምጣቸው በዲሞክራሲ ባህል መመራትን ይመለከቷል።

ሕዝባችን ለለውጥ ዝግጁ ነው፤ አንድነትን ይፈልጋሉ፤ ይዋደዳሉ፤ አንዱ የሌላውን አኗኗር ያደንቃል፤ይጋራዋል። በባህል፤ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ኑሮ የተሣሠረ ስለሆነ መለያየት አይፈልግም፤ የአገሩን ነፃነትና አንድነት ይፈልጋሉ። የተሻለ ገቢ፣ የተሻለ ጤና፣ የተሻለ ትምህርት፣ በሰላምና ብልፅግና፣ ወጉ ተከብሮለት መኖርን ይፈልጋሉ፤ በራሱ የውስጥ ጉዳይ ራሱ በመወሰን ፍትህን ማስከበር ይፈልጋሉ። ሆኖም ከመሀከል የሚወጡ አንዳንድ የሥልጣን ጥመኛ ጀብደኞች ቋንቋን፣ ዘርን፣ ሃይማኖት መነሻ በማድረግ ሕዝቡን የፖለቲካ ምርኮኛቸው ለማድረግ ያላደረጉት ጥረት የለም። እስከ ዛሬ የሕዝቦቻችን መሠረታዊ መብቶች በየትኛውም ክፍል በአስተማማኝ እንዲከበሩ ጠንካራ የሕዝብ ኃይል በመፍጠርና ለጋራ ትግል በመሰለፍ ፋንታ ጀብደኞች የሕዝብ ጥያቄዎችን በማንገብ የመከፋፈያ ስልቶችን ከጠላቶቻቸው በመውረስ ወገኖቻችንን ወደ አፀያፊ የእርስበርስ ግጭት ለመምራት ብዙ ጥረቶች ያደረጉ ቢሆንም ሕዝቡ እሺ አላለም ።

አንድ ነፃ ሰው ነፃነቱን የሚያከብርለት ስርዓት ለማህበረሰቡ ያለውን ግዴታ ይወጣል፡፡ ነፃ ሰው ነፃነቱን የሚያከብርለት ስርአት ይንከባከባል በአንፃሩ ደግሞ ነፃነቱን የማያከብርለትን ስርአት ይታገላል ታግሎም ይለውጣል፡፡ለሰው ልጆች የተፈጥሮ መብቶቻችን ሰው የመሆናችን ፀጋዎች ናቸው፡፡ ወያኔን የምታገለው ነፃነታችንን እንዲሰጠን አይደለም፡፡ ትግላችን በተፈጥሮ የተቸርናቸው መብቶች እንዲከበሩ ነው፡፡ ነፃነታችን ዘላለማዊ ከወያኔ ዕድሜ ቀድሞ የኖረና ከወያኔም ሞት በሗላ የሚኖር ነው ሆኖም ግን ነፃነታችንን ማስከበር ካልቻልን ከሰውነት ደረጃ ወርደን ባርነትን መቀበል አይቀሬ ነው፡፡

መፍትሔው ስለደፈረሰው ፖለቲካ እያወሩ ፈጣሪ ባመጣው ይመልሰው ማለት አይደለም፡፡ መፍትሔው እርስ በእርሳችን ስንወጋገዝ መኖርም አይደለም፡፡ መፍትሔው ወያኔዎችን አረመኔነት ሲያወሱ መኖር አይደለም፡፡ መፍትሔው ልዩነቶቻችን በማጥበብ፤ ጠብታዎች ባህር እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ መፍትሔው እጅን አጣምሮ ጥቂቶች ታምር እንዲሰሩ መጠበቅም አይደለም፡፡ መፍትሔው ከያንዳንዳችን የሚጠበቀውን ሌላውን ሳንጠበቅ መወጣት ነው፡፡

ቸር እንሰንብት

እግዚያብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!!!

ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኑር!!!

 

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: