አገራችንን ከተደቀነባት አደጋ መታደግ የሚቻለው የሥርዓት ለውጥ በማምጣት ብቻ ነው። የአርበኞች ግንቦት 7 ርዕስ አንቀጽ

AG7-logo-300x300የአገራችንን ሉአላዊነት እና የህዝባችንን አንድነት ድርና ማግ ሆኖ አቆራኝቶ ለዘመናት ያቆዩትን እሴቶች ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ህወሃት እንደ ድርጅት መሪዎቹም አንደ ቡድን ልዩ ጥቅም እናገኛለን በሚል የፖለቲካ ስሌት ላለፉት 27 አመታት ረጅም ርቀት ተጉዘዋል። በዚህም የተነሳ አብዛኞቹ አመራሮች እና ለአመራሩ ቀረቤታ ያላቸው ካድሬዎች እስከነ ዘመዶቻቸው የአገሪቱን ፖለቲካ ሥልጣን ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚውንም በበላይነት ለመቆጣጠር ዕድል አግኝተዋል። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያቤት ውስጥ የአፍሪካ ጉዳይ ረዳት ሚንስትር እና በተለያዩ አገሮች የአገራቸው አምባሳደር ሆኖ ለረጅም ጊዜ ሲያገለግሉ የኖሩት ሚስተር ሄርማን ኮሄን ሰሞኑን ለሚዲያ በሰጡት ምስክርነት ይህንን ሃቅ በይፋ በማጋለጥ የህወሃት የበላይነት የፈጠረው ችግር የበደሉ ገፈት ቀማሽ ከሆነው ህዝችባን አልፎ በምዕራባውያን ወዳጆቹ ዘንድም እንደሚታወቅ አረጋግጥዋል።

ህወሃት ምዕራባዊያን ወዳጆቹ ጭምር እንዲህ እስኪታዘቡት የመንግሥትን ሥልጣን በበላይነት ተቆጣጥሮ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ ቁጥጥሩ ውስጥ ሲያስገባ የኢትዮጵያ ህዝብ ዝም ብሎ እንዳልተመለከተው ግልጽ ነው። ሥልጣን ላይ ለመደላደል ሲባል ለዘመናት ተቻችሎና ተከባብሮ የኖረውን ህዝብ በቋንቋና በሃይማኖት የመከፋፈል ሴራ የኋላ ኋላ አገሪቱን ከመበታተን ሊያደርስ እንደሚችል ሲጋቱን ያለማቋረጥ ገልጾአል። ከዚያም አልፎ “አድሎአዊ የሃብት ክፍፍል ይቁም! ሥልጣንን መከታ በማድረግ የሚካሄደው የአገርና የህዝብ ሃብት ዘረፋ አደብ ይኑረው! ዜጎች እትብታቸው ከተቀበረበት ቄያቸው በጉልበት መፈናቀላቸው እና ጎዳና ላይ መጣላቸው እድገት ወይም ልማት አያመጣም! የሥልጣን ዕድሜ ለማራዘም ተብሎ የሚፈጸመው አፈናና ጭቆና የኋላ ኋላ አገዛዙን የከፋ ዋጋ ያስከፍለዋል! በፖለቲካ ምክንያት የሚካሄደው ጭፍጨፋ፤ የጅምላ እስር እና ሰቆቃ ያብቃ! ህዝብ ግልጽ፤ ነጻ እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ መሪዎቹን ይምረጥ! ወዘተ በማለት ድምጹን አሰምቶአል ፤ ተደራጅቶም ታግሎአል።

ነገር ግን ህወሃት ለዚህ የህዝብ ጥያቄ የሰጠው ምላሽ በጠመንጃ ትግል በተገኘው ድል ልቡን አሳብጦና ጡንቻውን አፈርጥሞ “አርፋችሁ ተገዙ ፤ እምቢ ካላችሁ አሳያችኋለሁ” የሚል ጀብደኝነትና በማን አለብኝነት ተቃዋሚዎችን እያሳደደ ማሰር፤ መግረፍ ፤ መግደል እና ከአገር ማሰደድ ሆኖ ዘለቋአል። በዚህ እርምጃ ውድ ህይወታቸውን ካጡ አስር ሺዎች በተጨማሪ በየእስር ቤቱ ከታጎሩ ቦኋላ በዘር ማንነታቸው እየተንቋሸሹና እየተሰደቡ ሰቆቃ የተፈጸመባቸው ወገኖች ቁጥር ስፍር የለውም። ደም አፋሳሽ ወደ ሆነ የርስ በርስ ግጭት ሳይገባ እና ለትውልድ ወደ ሚተላለፍ ቂም በቀል ሳይኬድ መብታችንን በሰላማዊ መንገድ ለማከበር የተደረጉ ጥረቶች እንደፍርሃት እና ጀግንነት ማጣት ተቆጥረው “በመስዋዕትነት ያገኘሁትን ድል ለማንም አላስረክብም ከፈለጋችሁ እንደ እኔ ተዋግታችሁ ለመምጣት መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ” እስከመባል ተደርሶአል።

ላለፉት 3 አመታት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የመጣውን ህዝባዊ ተቃውሞ የቀሰቀሰው ይህ ለአመታት የተጠራቀመው የወያኔ እብሪትና ጥጋብ የፈጠረው ብሶት ነው። ይህ ብሶት ደግሞ በጠመንጃ ሃይል ባይታገዝም እንኳ ብቻውን የወያኔን እብሪት ማስተንፈስ እና የሚመካበትን ትጥቅ ለማስፈታት አቅም እንዳለው በተግባር እያረጋገጠ ነው። በእብሪት እና በጥጋብ የተወጠረው ህወሃት ግን ዛሬም ቢሆን ይህንን እውነታ ለመረዳት እና ለህዝቡ ብሶት ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ የሆነ ድርጅት እየሆነ አይደለም። ለዚህ ምስክሩ ከየአቅጣጫው የተሰነዘረበትን ህዝባዊ ተቃውሞ እንደ ለመደው በጉልበት ካልሆነ ደግሞ በብልጣ ብልጥነት አክሽፋለሁ ብሎ በአገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቁ ረጃጅም ስብሰባዎች ተጥዶ መገኘቱ ነው።

አንድ ወር ከአምስት ቀናት ከፈጀው የመቀሌው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብስበባ ማግስት ቦኋላ አዲስ አበባ ላይ ለ18 ቀናት በዝግ ሲካሄድ የቆየው የኢህአደግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ በየትኛዎቹ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ እንደመከረ ይፋ ሳያደርግ መጠናቀቁን ይፋ አድርጎአል። ስብሰባው በተጠናቀቀበት ዕለት በምን ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን እንዳስተላለፈ ለህዝብ መግለጽ አለመቻሉ በራሱ የሚናገረው ነገር እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው። በህወሃት ታሪክ ሁለተኛው ረጅም ስብሰባ ከሆነው ከዚህ የአዲስ አበባው የህወሃት ስብሰባ አፈትልኮ የወጡት መረጃዎች እንዳመለከቱት ህወሃት እንደ ድርጅት እስካዛሬ ይዞት የቆየውን የፖለቲካ የበላይነት አስጠብቆ ለመዝለቅም ሆነ መሪዎቹ አይነኬነታቸውን አስከብረው ለመቀጠል ከሚችሉበት ተክለ ሰውነት ላይ አለመሆናቸው ታውቆአል። በዚህና አገሪቱ ውስጥ ተቀጣጥሎ በቀጠለው ህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት ህወሃት ከአሁን ቦኋላ እራሱንና አገሪቱን ከከተቱበት የፖለቲካ ቅርቃር ውስጥ ለማውጣት ይቀለዋል ተብሎ አይጠበቅም።

በሌላ በኩል ህዝባችን በአገዛዙ ላይ ባለው የመረረ ጥላቻ የሚከፈለውን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍሎ ከባርነት ቀንበር ነጻ ለመውጣት የጀመረውን ትግል አጠናክሮ ቀጥሎበታል። ከዚህ ቀደም በአገራቸውና በህዝባቸው መከራና ስቃይ የህወሃት የህይወት እስትንፋስ ሆነው የቆዩት ኦህዴድ እና ብአዴን ውስጥ የበቀሉ አዳድሶቹ ወጣት አመራሮችም እንደ ቀድምቶቹ በጥቅም የሚደለሉ ወይም በባለውለታነት ተተብትበው አገልጋይ ሆነው ለመቀጠል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን በተግባር እያስመሰከሩ ነው።

አርበኞች ግንቦት 7 አዳዲሶቹ የኦህዴድ እና የብአዴን አመራሮች እራሳቸውን ከህወሃት የበላይነት ለማላቀቅ እና ከህዝባቸው ጎን ለመቆም የጀመሩትን የውስጥ ትግል በቅርበት ይከታተላል፤ ያደንቃልም። በተለይ የኦሮሚያ ምክር ቤት በቅርቡ በወሰደው እርምጃ ለዜጎች በሚሰጠው መታወቂያ ወረቀት ላይ የብሄር ማንነታቸው እንዳይገለጽ መከልከሉ ህወሃት በሚቀሰቅሰው የብሄር ግጭት ወይም አድልኦዊ አሠራር ሰለባ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ዜጎችን ህይወት የሚታደግ በጎ እርምጃ በመሆኑ ሌሎች ክልሎችም አረአያነቱን እንዲከተሉ ወገናዊ ጥሪውን ያቀርባል።

በአርበኞች ግንቦት 7 እምነት ህወሃት ላለፉት 27 አመታት አገራችን ውስጥ ያሰፈነው የከፋፍለህ ግዛ ፖሊስ የወለዳቸው የእርስ በርስ ጥላቻና የድንበር ግጭቶች በአገራችን ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ አደጋና ሥር የሰደዱ ፈተናዎችን ደቅነዋል። በቅርቡ በኢትዮጵያ ሱማሌና በኦሮሚያ መካከል ህወሃት ሆን ብሎ በቀሰቀሰው ግጭት ውድ ህይወታቸውን ካጡ በርካታ ዜጎች በተጨማሪ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በየመጠለያ ካምፖች ወድቀው የሚገኙ ቁጥራቸው ወደ ሚሊዮን የሚጠጉ ወገኖቻችን ጉዳይ የሚያሳየው የገባንበትን ችግር ጥልቀትና ከፊት ለፊታችን የተደቀነውን አደጋ መጠን ነው።

በዚህ ሥርዓት ዘመን ተወልደው ያደጉ ወጣቶች በቅርቡ ዩኒቨርሲትዎች ውስጥ ባካሄዱት ተቃውሞ አገዛዙ በወገኖቻቸው ላይ ሲፈጽም የኖረውን አፈናና ግዲያ ለማስቆም በጋራ ከመቆም ይልቅ እርስ በርስ ተቧድነው ከምን ደረጃ እንደተደራራሱ ልብ ብሎ ላስተዋለ ህወሃት አገራችን ውስጥ የፈጠረው ቅራኔ በብልሃት እና በጥበብ ካልተያዘ በቀር ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ፍንጭ የፈነጠቀ ሆኖአል።

ይህንን ሁሉ ችግሮች በማጤንና አገራችን ላይ ያንዣበበውን አደጋ ለመቀልበስ እንዲቻል ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 ሃላፊነት የተሞላበትን ግዳጁን ይወጣ ዘንድ ሁሉንም የፖለቲካ ሃይሎች እና ባለድርሻ አካላቶች ያሳተፈ ፖለቲካዊ መፍትሄ በአስቸኳይ እንዲጀመር የአገዛዙን መሪዎች ማሳሰብን እንደ አንድ አማራጭ ወስዶአል። አለም በሠለጠነቺበት 21ኛው ክፍለዘመን የአንድ አናሳ ቡድን የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት የኢትዮጵያ ህዝብ እስከመጨረሻው ተሸክሞ ይዘልቃል ብሎ ማሰብ እና አገሪቱን ለጥፋት መዳረግ ታሪካ ይቅር ሊለው የማይችል ወንጀል መሆኑን ህወሃቶች ልብ ሊሉት ይገባል።

ስለዚህ በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ እንደ ድርጅት ለመቀጠልም ሆነ እንደ ግለሰብ የዚያች አገር ዜጋ ሆኖ በነጻነት ለመኖር ህወሃቶች እስከዛሬ የሚመሩበትን እብሪትና ጥጋብ ገታ አድርገው በተለያዩ እስር ቤቶች ያጎሩዋቸውን የሂሊና እስረኞች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ፤ የአገሪቱን መከላኪያ፤ ፖሊስ ፤ ደህንነት እና ፍርድ ቤቶችን የአፈናና የጭቆና ተቋማት አድርገው ከመጠቀም እንዲታቀቡ፤ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ መገናኛ ብዙሃንን ለጠባብ ዓላማቸው መጠቀማቸውን እንዲያቆሙ እና ሁሉንም ያካተተ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ስለሚቻልበት ሁኔታ ለመነጋገር በዚህ የመጨረሻው ሥልጣን ዘመናቸው በእጃቸው ላይ በቀረው የመጨረሻ እድል እንዲጠቀሙ እና እራሳቸውንና አገራቸውን ከጥፋት ለማዳን እንዲችሉ ይመክራል።

በዚህ ዕድል ባለመጠቀም አገራችንን ላይ ሊደርስ ለሚችለው የከፋ ችግር ህወሃት በህግም ሆነ በታሪክ ፊት ብቸኛ ተጠያቂ እንደሆነ ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 አጥብቆ ያሳስባል። ለህወሃት የቀረበው ይህ የመጨረሻ ዕድል ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7ን ጨምሮ ሌሎች 4 ድርጅቶችን ያቀፈው የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ በቅርቡ አውሮጳ ፓርላማ ላይ ይፋ ያደረገው የሽግግር መንግሥት ምስረታ ፍኖተ ካርታ አካል እንደሆነ ተረድቶ ይህ ዕድል እንዳያመልጠው የህወሃት አባላትና ደጋፊዎች ጫና ሊያደርጉበት ይገባል።

ለነጻነቱና ለክብሩ ከህወሃት ጋር በመፋለም ላይ የሚገኘውም ህዝባችን የኢህአደግ አባል ድርጅቶች ውስጥ በተጀመረው ትግል ሳይዘናጋና በምንም አይነት ጥገናዊ ለውጥ ሳይደለል አገራችን ውስጥ የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት የጀመረውን ሁለገብ ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 ወገናዊ ጥሪውን ያቀርባል።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: